ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጎበዝ ልጅ ሁሌ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርትና በጥናት ነው። እናንተም ጎበዝ ተማሪ ስለሆናችሁ ሳምንቱን ያሳለፋችሁት በትምህርት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ጎበዝ ተማሪ የጊዜን ጥቅም በሚገባ ያውቃል ስለዚህ ያለውን ጊዜ በአግባቡ በመከፋፈል ይጠቀማል፤ ማንበብ ባለበት ሰዓት ያነባል፤ መጫወት ባለበት ሰዓት ይጫወታል፤ መማር ባለበት ሰዓት ደግሞ ይማራል። እናንተም ሰዓታችሁን እንደዚህ በስርዓት ከፋፍላችሁ እንደምትጠቀሙበት አምናለሁ።
ልጆች ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት አንደበተ-ርቱ፣ ቅን እና ቀልጣፋ የሆነውን ተማሪ ኑኤል በረከትን ነው። ኑኤል የስምንት አመት ልጅ ሲሆን በቪዥን የአይነ ስውራን አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤት የኬጂ 1 ተማሪ ነው። በዚህ አመት ከአንድ እስከ ሶስት ለመውጣት አቅዶ ትምህርቱን በትኩረት በመከታተል ላይ ይገኛል። ልጆችዬ ኑኤል ሰዎችን በእጆቹ በመንካት ማን እንደሆኑ መለየት ይችላል። የትምህርት ቤት ጓደኞቹን እና መምህራኖቹን በእጆቹ በመዳበስ ብቻ ይለያቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ ግን ሰዎችን በስማቸው ይለያቸዋል። የሰዎችን ስም አንዴ ከተነገረው ሌላ ጊዜ በቀላሉ ያስታውሳል። ለምሳሌ እናንተ አንድ ቀን ኑኤልን ብታገኙትና ብትተዋወቁት ሌላ ቀን ስትገናኙ ስማችሁን አይረሳም፤ ወዲያው ያስታውሳችኋል።
የኑኤል ልዩ ችሎታ ሰው መርዳት ነው። “ሰው የምረዳው በአቅሜ ነው” የሚለው ህፃን ኑኤል ፤ አብረውት የሚማሩ ልጆች መፀዳጃ ቤት መሄድ ሲፈልጉ መፀዳጃ ቤቱ የት እንደሆነ ያሳያቸዋል፤ ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው መሄድ የፈለጉትንም ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው ያደርሳቸዋል። ልጆች ሰው መርዳት ውስጣዊ ሰላምን የሚሰጥ እጅግ በጣም ጥሩ ስራ ነው። ለተቸገረ መድረስ እና ከችግሩ እንዲወጣ መርዳት በገንዘብ የማይገዛ መንፈሳዊ እርካታን የሚሰጥ የፅድቅ ስራ ነው።
ኑኤልም ሰው በመርዳቱ የሚሰማውን ስሜት ሲገልፅ “ሰው ስረዳ ልዩ ደስታ ይሰማኛል” በማለት ነው። እናንተም ይሄንን የደስታ ስሜት ማጣጣም ከፈለጋችሁ ልክ እንደ ኑኤል ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳትሉ በቻላችሁት ሁሉ ሰዎችን መርዳት አለባችሁ። ህፃን ኑኤልም “ሰው እርዱ ሰው ስተረዱ እናት እና አባታችሁን ስትረዱ ደስታ ታገኛላችሁ” ለእናንተ መልእክቱን እንዳደርስ ነግሮኛል፤ እኔም ይሄው ለእናንተ አድርሻለሁ፤ እናንተ ደግሞ እንደማታሳፈሩኝ እርግጠኛ ነኝ ፤ምክሩን ትተገብራላችሁ ብዬ አምናለሁ።
ኑኤል ቤተሰቦቹ በብዙ ነገር ይደግፉታል፤ እሱም ቤተሰቦቹን የሚችለውን ስራ በመስራት ያግዛቸዋል። ሁሌ ጠዋት ጠዋት ከወላጅ አባቱ ጋር በመሆን አልጋ ያነጥፋሉ፤ ከዚያ በኋላ ቁርሱን በልቶና የመማሪያ ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ ሲጨርስ ወደ ትምህርት ቤት ያደርሱታል፤ ከቦታ ቦታ ሲነቀሳቀሱ የሚሄዱበት ቦታ የት እንደሆነና ስሙ ምን እንደሚባል በመንገር ቦታዎችን እንዲያውቅ ይረዱታል፤ በእግር መንገድ ሲሄዱ እጁን ይዘው እንዳይወድቅ ያግዙታል። እሱም የቤተሰቡን ምክር ስለሚሰማ ሁልጊዜም ውጤታማ ነው። ልጆች እናንተም የቤተሰቦቻችሁን ምክር ብትሰሙ እጅግ ውጤታማ ትሆናላችሁ ምክንያቱም ወላጆች ሁልጊዜ ለልጆቻቸው የሚመኙትም ሆነ የሚያደርጉት በጎ ነገር ነው።
ኑኤል ሲያድግ መሃንዲስ እና ቄስ መሆን ይፈልጋል። ትምህርት ሲጨርስና ትልቅ ሰው ሲሆን ቄስ በመሆን ቤተክርስቲያንን ማገልገል እና መሃንዲስ በመሆን ደግሞ ለሀገሩ የተለያዩ ውብ ህንፃዎችን መስራትና ለቤተክርስቲያንም ህንፃ መስራት ይፈልጋል። ለሀገሩ ስራ መስራት የጎደላትን መሙላት፤ የዕለት ጉርስ አጥተው የተቸገሩ እና ጎዳና የወጡ ወገኖቹን ምግብ ሰርቶ በማቅረብ መመገብ የሁልጊዜ ህልሙ ነው። የተለያዩ ተክሎችን በመትከል ኢትዮጵያን ውብ እና ሁሉም ሊያያት የሚጓጓላት ሀገር ማድረግ እና በታማኝነት ለማንም ሳያዳላ ሀገሩን ማገልገል ወደፊት አድጎ ትልቅ ልጅ ሲሆን ለሀገሩ የሚደርግላት ነገር ነው።
“ልጆች ወደፊት ኢትዮጵያን ማገዝና መርዳት አለባቸው” የሚለው ኑኤል፣ “እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያን ማገዝ እፈልጋለሁ ልጆችም ሀገራቸውን ሊያግዙ ይገባል” በማለት ይመክራል። ውጭ ሀገር ያሉትም ለሀገራቸው ብር እንዲልኩላት እና ኢትዮጵያን በሚችሉት ሁሉ እንዲደግፏት ይፈልጋል።
ልጆች በመጨረሻም ኑኤል ለእናንተ ቆንጆ ምክር አለው፤ ልጆች ትምህርታቸውን በሚገባ በመከታተል ጎበዝ ተማሪ መሆን እንዳለባችሁ፤ እሱ ቤተሰቦቹን በስራ እንደሚያግዘው ሁሉ እናንተም ቤተሰቦቻችሁን ማገዝ እንዳለባችሁ፤ ታላላቆቻችሁና መምህራኖቻችሁ የሚሰጧችሁን ምክር መስማትና ተግባር ላይ ማዋል እንዳለባችሁ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰው የመርዳት ልምዳችሁን እንድታዳብሩ ምክሩን አስተላልፏል። እኔም የኑኤልን ምክር ተግባራዊ እንድታደርጉ መልዕክቴን በማስተላለፍ ለዛሬ እዚህ ላይ ላብቃ። ሳምንት በሌላ ፅሁፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
ልጆችዬ እንደኑኤል ጎበዝ ተማሪ መሆን አለባችሁ፤ ቤተሰባችሁን በስራ ማገዝ አለባችሁ፤ ቤተሰቦቻችሁን መስማት አለባችሁ፤ ትምህርት ቤትም ትምህርታቸውን በደንብ መከታተል አለባችሁ፤ መምህራኖቻችሁ የሚሏችሁን መስማት አለባችሁ፤ ሰው መርዳት አለባችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም