ሙዚቃ ትዝታና ትውስታ ቀስቃሽ ምናባዊ የሕይወት ስዕል ነው። በክስተቶችና በልዩ ልዩ በዓላት መካከል የሚፈጠሩ ሙዚቃዎች የምንወዳቸው አይነት ሆነው ሲገኙ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አድምጠን የማንጨርሳቸው፣ የተዘፈኑበት በዓላት በመጡ ቁጥር ሁሉ አብረን የምናስታውሳቸው ይሆናሉ።
በዓላትና ሙዚቃ፣ ሙዚቃና በዓላት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ለማለት ያስደፍራል። በዓላት ያለ ሙዚቃ ፈጽሞ አይደምቁም፤ በተለይ የጥምቀት በዓል ደግሞ የማይታሰብ ነው። በዓልን ያለሙዚቃ ማክበር ጨው የሌለው ምግብ እንደመመገብ ነውና አይጣፍጥም። ታዲያ ባሳለፍነው የጥምቀት በዓል በእስክስታ ትከሻችንን እየወዘወዝን፣ አንገታችንን እየነቀነቅን ወገባችን እስኪንቀጠቀጥ በብዙ ሙዚቃዎች ተውረግርገናል፣ ጨፍረናል። ነገር ግን ከሙዚቃም ሙዚቃ መርጠን በልዩነት አንድ ሙዚቃ እናስታውሳለን፤ የጥምቀት በዓል አንድ አካል እስከሚመስል ድረስ በየአመቱ እንደ አዲስ እየሰማን እንደ አዲስ ዳንኪራ የምንመታበት፣ ገና ጥምቀት ሲመጣ ሙዚቃው ትዝታና ትውስታ እየሆነ በጆሯችን የሚንቆረቆር አንድ የጥበብ ሰው አለ። መቼም እኔ ገና ዳር ዳሩን ስሄድ ይህንን ሙዚቃና የጥበብ ሰው ማንም ቀድሞ እንደሚገምተው አልጠራጠርም።
አዎ እሱ ነው፤ ‹‹ዘገሊላ›› ይህንን የማያስታውስ ማን ይኖራል? ባለቅኔው ዜመኛ ይሁኔ በላይ ተጨንቆና ተጠቦ ዘመን አይሽሬ የጥምቀት ስጦታ ከ18 አመታት በፊት 1997 ዓ.ም የጥምቀት ዋዜማ ላይ አበርክቷልና በየአመቱ አይሰለችም ሳይሆን ገና አይጠገብም።
‘የዘገሊላ ዕለት፣ የዘገሊላ ዕለት
ነይልኝ በኔ ሞት
ለአስተሰርዮ ማርያም፣ ለአስተርዮ ማርያም
እመጣለሁ እኔም
በዓል ነው፣ በዓል ነው
ኦ በዓል ነው
በዓል ነው፣ ልንገናኝ ነው’ እያለ ውብና ማራኪ በሆነ ድምጹ ይሁኔ ያዜማት ዜማ የጥምቀት በዓል ልዩ መታወቂያ እስከመሆን በቅታለች። እኛም በዛሬው የዝነኞች ገጽ አምዳችን ይህን በይሁኔ በላይ ሌሎች ስራዎችና የሕይወት ገጽታዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን።
የአባይ ወንዝ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሙዚቀኞች መፍለቂያ ከሆነችው ከጎጃሟ ፍኖተ ሰላም ፈልቆ የወጣው ይሁኔ በላይ ከልጅነቱ ጀምሮ በተለያዩ ክበባትና የሙዚቃ ባንዶች የሙዚቃ ክህሎቱን እያሳደገ በውጣውረዶች መሃል ትልቅ ስኬት ላይ መድረስ የቻለ ድምጻዊ ነው። የይሁኔ ሙዚቃዎች አብዛኞቹ ካያቸውና ከሰማቸው እንዲሁም ራሱ ከኖረው ሕይወት የመነጩ በመሆናቸው ቁልጭ ብለው የተቀመጡ የማህበረሰቡ የስሜት ነጸብራቅ ናቸው። ያደገበትን ባህል፣ ወግና ስርዓት በየሙዚቃዎቹ ውስጥ በማሳየትና በየትኛውም ቦታ የማህበረሰቡ የፊት ደጀን ሆኖ በቆራጥነት የሚቆም በመሆኑ ‹‹የጎጃም አምባሳደር›› የሚል ቅጽል ስም ለማግኘት በቅቷል።
እንዲህና እንዲያ እያለ የሰነበተው የጎጃሙ አምባሳደር የሙዚቃ ችሎታውን በማሳደግ የመጀመሪያ ስራው የነበረችውን ‹‹አንቱዬዋ›› የተሰኘውን ሙዚቃ ከሰማኸኝ በለው ጋር በጋራ በመሆን ለመስራት ቻለ። ሙዚቃው በድራማ የተሞላና በግሩም ዝግጅት የቀረበ ስለነበረ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትና ተደማጭነትን አጎናጸፈው። በዚህ ሙዚቃ ውስጥ ይሁኔ ያለውን አቅምና ልዩ ተሰጥኦ በሙሉ ለመጠቀም ሞክሯል። ማራኪ ከሆነው ድምጹ ፊት ለፊት ያለው ሙዚቃዊ እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ባህልን የተላበሰ፣ ከዜማና ግጥሙ ጋር የተሰካካ ስለነበረ ከማህበረሰቡ አልፎ በመላው ኢትዮጵያ ተቀባይነትን አገኘ።
ሙዚቃን በግሉ መስራት ከመጀመሩ በፊት ይሰራበት የነበረበት ግሽ አባይ ባንድ የሙዚቃን ምንነት የተረዳበትና የሙዚቃን ምሉእነት ተገንዝቦ የሕይወቱን የወደፊት የጉዞ ስንቅ የሸከፈበት እንደሆነ ይሁኔ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግሯል። ባንዱ ለብዙ ዘመናት በርካታ የባህል ሙዚቀኞችን ለሕዝብ ያደረሰ፣ በርካታ እውቅ ሙዚቀኞችን ማፍራት የቻለና ለባህል ሙዚቃ እድገት መሰረትን የጣለ መሆኑንም ጭምር ይሁኔ ይናገራል። ‹‹የኔ የሙዚቃ ሕይወት የሚጀምረው ከአካባቢ ነው። በልጅነታችን በግሽ አባይ ውስጥ የምንሰራቸው ሥራዎች የሚገርሙ ነበሩ። እርስ በእርስ የነበረን ተደጋግፎ የመስራት ልምዳችን ከፍተኛ ስለነበረ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የማንሞካክረው ነገር አልነበረም። ከዚያ በፊት ደግሞ ትምህርት ቤት ለጓደኞቼ ስዘፍን አስተማሪዬ አይተው አንተ በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ ዘፋኝ ትሆናለህ ብለው የሰጡኝ ማበረታቻ ለዛሬው መሰረት ሆኖኛል›› በማለት በልጅነትና በባንዱ ውስጥ ያሳለፋቸውን የማይረሱ ጊዜያቶች ያስታውሳቸዋል።
ይሁኔ ከሙዚቃ ባንዱ ወጥቶ የራሱን ጉዞ በመጀመር የመጀመሪያውና የብቻው የሆነውን ‹‹ያገሬ ልጅ ባለጋሜ ትውልዷ ጎጃሜ›› የተሰኘውን አልበም በመስራት ለሕዝብ ጆሮ አበቃ። ይህ አልበሙም በመላው ኢትዮጵያ የተደመጠ ሲሆን በባህል ሙዚቃ ዘርፍ ብዙ ቅጂዎች የተሸጠ፣ የወቅቱ አንደኛና ዝነኛ አልበም ለመሆን ችሎ ነበር። በዚህ ሥራው የማህበረሰቡን ባህል አጉልቶ ያሳየበት መንገድ በትክክልም የጎጃም አምባሳደር መሆኑን ይመሰክርለታል። ስኬት የብዙ ትጋትና ጥረት ውጤት መሆኑን ያሳየበት አልበም ስለነበረ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከመታወቅም አልፎ ለቀጣይ ስራዎቹ በር ከፋች ነበር። ዜማው ለሕዝብ ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ የይሁኔ ሕይወት አንድ በአንድ እየተለወጠ መጣ። በመጀመሪያ አልበሙ የሞራል ብርታትን ያገኘው ይሁኔ በላይ ‹‹አሎ ሉሎ›› የተሰኘ ሁለተኛው የሆነውን አልበም ለሕዝብ ጆሮ አበቃ። በመጀመሪያ ስራው የሙዚቃ መንገዱን በመጥረግ አቅንቶት ነበርና ሁለተኛ አልበሙ እንደወጣ የሕዝብ ጆሮ ለመግባት ጊዜን አልፈጀበትም። ይህን የተመለከቱ ወዳጆቹ እድለኛ መሆኑን ሲነግሩት እሱም ‹‹በእርግጥም እድለኛ ነኝ። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ቶሎ ሕዝብ ጋር ለመድረስ ችያለሁ። ብዙ ነገሮች በሕይወቴ ውስጥ ደርሰውበኛል። ሁሉንም በእግዚአብሔር ኃይል አልፌ ለዚህ በቅቻለሁና ከምንም በላይ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ!›› በማለት ይመልስላቸዋል።
በስራዎቹ ብስለትና ክህሎቱ እያደገ የመጣው ይሁኔ በ3ኛ አልበም ሲመጣ ያለውን ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ለዛ በጠበቀ መልኩ ከባህል የሙዚቃ ስልት ወጣ ብሎም የአፍሪካ የሙዚቃ ስልትን በመቀላቀል መስራት ጀመረ። 3ኛው የሆነችው ‹‹ብ..ብ ከፊላው ስር›› አልበሙ የብቃቱን ደረጃና የፈጠራ ችሎታውም ማደጉን ያሳየ ነበር። ከዚህ በኋላ ‹‹ኩኩ መለኮቴ›› የተሰኘውን ሌላ አልበም አወጣ። በዚህ ወቅትም ከባለቤቱ የሺመቤት (ቱቱ) እና ከሁለቱ ወንድና ሴት ልጆቹ ጋር ኑሮው በአሜሪካን ሀገር በአሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ አድርጎ ነበረ። የነበረ በዚህ ጊዜም አንድ የማይረሳው አጋጣሚ ነበረው። ይሄውም የአሜሪካ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት የቢል ክሊንተን ባለቤት ሚስ ሂላሪ ክሊንተን ጋር በመገናኘት 3ኛውን ካሴቱን በስጦታ ያበረከተበት አጋጣሚ።
ይሁኔና ቤተሰቡ ኑሯቸው በአሜሪካ ይሁን እንጂ ልጆቹ ባህላቸውን እንዳይረሱ ሁሌም እንደሚያስተምራቸው፣ እንዲሁም ወንድ ልጁን የጎጃም ሕጻናት የሚለብሱትን የባህል ካኪ ልብስ እንደሚያለብሰው የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ።
ይሁኔ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን መስራት የቻለ ሲሆን ናፍቀሽኛል፣ ልሳምሽ፣ ምስጋናው ደግ ነው፣ እንዳንቺ የሚያምር፣ ጉዛራ፣ ቤታችን፣ ሀይ መሎ፣ መሸለም እና ሲያምር ጨዋታው የተሰኙ አልበሞችን እና ነጠላ ዜማዎችን ከብዙ በጥቂቱ ለምሳሌነት ያህል ማንሳት ይቻላል።
ሙዚቃ ከሙዚቃነቱ ባሻገር የብዙሃን አንደበትና የውስጥ ስሜት ነው። ብዙዎች በፖለቲካና መሰል ካቴናዎች ተጠፍረው ብዕራቸው መጻፍ፣ አንደበታቸውም ማዜም በተሳነው ወቅት ይሁኔ ግን ደፈር ብሎ በትንንሽ የሙዚቃ ስንኞች ውስጥ ሀገር የሚያህል ቅኔን መቀኘት ችሏል። በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃዎች ዐውድ በተስረቅራቂ ድምፁ ባህሉን ባከበሩ ዜማና ግጥሞች አስፍሯቸዋል። ከእነዚህ መካከልም አንዳንዶቹን ስንቃኝ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ አምስተኛ አገራዊ ምርጫ አድርጎ፣ መቶ በመቶም አሸነፍኩ ባለበት ወቅት ይሁኔ እንዲህ ሲል በውስጠ ወይራ ተቀኘ፡፡ በእርግጥ ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር ሊሆን ይችላል ፖለቲካዊ ትርጓሜ የተሰጠው፡፡
“ላንቺ ይብላኝ እንጂ ምስጋናውን ላጣሽ፣
እኔማ ጠገብኩሽ በህልሜ እየመጣሽ፣
ምስጋናው ደግ ነው፤ ለእልፍኝ የሚበጅ፣
እርጅና በፈረስ ደረሰበት እንጅ”
ሀገር በሰላም እጦት ውስጥ ገብታ ሳለ ባዕዳኑ በቁስሏ ላይ እንጨት ሲሰዱ ከያኒው የዛኔም ዝም አላለም።
“አትዘባበቱ ፤ቀን ጣለው ብላችሁ
ከፊታችሁ ቆሞ፤ታገኙታላችሁ” በሚል ትንቢታዊና ፍካሬያዊ ቅኔ ቅሉ ቢገባቸውም ባይገባቸውም እርሱ ግን ደህና አድርጎ ነግሯቸዋል።
ሌላው የሚኖርባትን አሜሪካ ነገረ ስራዋን ትኩር ብሎ ካጤናት በኋላ ‹‹ምስጋናው ደግ ነው›› በሚለውና ከአምስት ደቂቃዎች ብዙም በማይዘለው አሸወይና ሙዚቃው ውስጥ በመጨረሻዎቹ ስንኞች
“ይሄን ጥሩ ሙያ፤ ከቶ የት ተማርሽው፣
ስንቱን ጎበዝ ጀግና፤ወዶ ገብ አረግሽው” በማለት ጎንተል አድርጓታል።
ሀገሩ ኢትዮጵያ ጥንቱን በሀያልነትዋ ብዙ ታምራትን ሰርታ አሁን ግን በትካዜ ተፋዛ ስትቦዝን፣ ታላቅነቷን ዘንግታ መስራት ያለባትን ሳትሰራ፣ መሆን ያለባትን መሆን ሳትችል ስትቀር ይሁኔ በማራኪ ድምጹ በሚነሽጥ ዜማው እያብላላ እንዲህ አዜመላት
“እኔ እየረሳሁት ፤እሱ እያስታወሰኝ
ቸርነቱ እንዲህ ነው፤እዚህ ያደረሰኝ
መምህር መቼ ጠፋ፤ ቀሲስና አቡን
እየሳትነው እንጂ ፤ቀን ቆጠራውን”
ማን ይጎዳ ብለሽ፤ በእኔ ወድቆ መቅረት
የምድርን አይቶ ነው፤ የላይ ቤቱ ምህ ረት”
ጥንቱን የረታናቸው ጠላቶቻችን መልሰው ዛሬ እያባረሩን ክብራችንን እንዳይነጥቁን እያስጠነቀቀ ደግሞ
“ያደናቀፈኝ ድንጋይ፤ መልሶ ከመታኝ፣
ሳይጥል አይተወኝም፤ ሱሪ ሳያስፈታኝ” እያለ የኋላ ቀርነትና ድኅነት ምሳሌ ሆነን በንቀት መታየታችን እንደሚያንገበግበው ይገልጻል።
‹‹አንዳንድ ቀን ዘራፍ፤ ልበል እንጅ እንደ ወንድ ወተት ብቻ እኮ ነው መገፋት የሚወድ›› የሚሉት ስንኞች በአጭሩ የይሁኔን ስራዎችና ቆራጥነቱን ይገልጹታል። እሱ ላመነበትና ለሚኖርለት አላማ ወደኋላ ብሎ ነገር አያውቅምና እያቀነቀነ የሚያነቃቃ፣ እየጀገነ የሚያጀግን የጥበብ ሰው ነው።
ይሁኔ በላይ በአሁኑ ወቅት ኑሮው በአሜሪካ ሀገር ሲሆን ከባለቤቱ ጋር በመተባበር ‹‹ባውዛ›› የተሰኘ መጽሔት ያዘጋጃል። ከድምጻዊነቱ ባሻገርም የንግድ ሰው እንደሆነም ይነገርለታል። እኛም ለዚህ ከያኒ ረዥም እድሜን ከጤና ጋር ተመኘን!
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም