የኢትዮጵያ የእርቅና የሽምግልና ስርዓት ሰዎች በእርስ በርስ ግንኙነት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት ነው። ይሁን እንጂ ከመደበኛው የፍርድና የፍትህ ስርዓት ጎን ለጎን የብሔር ብሔረሰቦች ሀብትና እሴት በሆነው በዚህ ስርዓት የመዳኘትና አለመግባባቶችንና ግጭቶችን የመፍታቱ ልምድ የደበዘዘ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው።
የእርቅ ስርዓቱ ግለሰቦች፣ ድንበር የሚጋሩ ህዝቦች፣ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ቡድኖችና መሰል አካላት በመካከላቸው አለመግባባቶች ሲፈጠሩ፣ ግጭቶቹ ተባብሰው የከፋ ጥፋት እንዳያደርሱ በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከመደበኛ የፍርድ ስርዓት ጎን ለጎን ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነም ይነገራል። ኢትዮጵያም ይህን መሰል ስርዓትን የያዙና በአገር ሽማግሌዎች፣ በባህላዊ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚመሩ ሸንጎዎችና የእርቅ ስርዓቶች ያላት አገር ነች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በዚሁ ስርዓት መፈታት ሲገባቸው በተቃራኒው ጥቃቅን ግጭቶች ተባብሰው በመቀጠል ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደምና ለዝርፊያ ምክንያት እንደሆኑ ተገልጿል። መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በግልም ሆነ በጋራ ይህንን እሴት ለማጎልበት እንዲሁም የመፍትሄ አካል ለማድረግ በተለያየ ጊዜ ጥረት ያደርጋሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምድ ላይ “ባህላዊ የሽምግልና ስርአቶቻችንን በየጊዜው ለሚከሰቱ አለመግባባቶች መፍትሄ እንዲሆኑ ምን መስራት ይኖርብናል?” በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ አተኩሯል። ከሰሞኑም በአፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት ብሔራዊ የባህል መሪዎች ምክር ቤት ለማቋቋም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ፣ ስለተደረገ ምክክር ጥቂት ሃሳቦችን እናነሳለን።
አፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቡሩክ ተመስገን ብሔራዊ የባህል መሪዎች ፎረም የማቋቋም አላማውን በተመለከተ ሲናገሩ፤ ‹‹በአገራችን በልዩ ልዩ አካባቢዎች በርካታ ግጭቶች ይከሰታሉ። ምክር ቤታችን በሰራው ጥናት መሰረትም ‹ግጭቶቹ እየተስፋፉና ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ የመጡት የባህላዊ ስርዓቶቻችንን ወደጎን በመተዋችን ነው› የሚል ሳይንሳዊ ግኝት አለን። ከምንም በላይ ሰዎችን ሊይዛቸውና ሊገዛቸው የሚችለው ባህላቸው ነው። የባህላዊ መሪዎችና ሽማግሌዎች ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ እድሉ ባለመመቻቸቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግጭቶች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጥናታችን ያመለክታል›› ይላሉ።
“ባህላዊ መሪዎችን እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶችን ወደ ቦታቸው ብንመልስ አብዛኛዎቹ አለመግባባቶችና ጥፋት የሚያደርሱ ክስተቶች በቶሎ ጥፋት ሳያደርሱ መፍትሄ ያገኛሉ ብለን እናምናለን” የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ወቅት ይህንን እሴት ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ምክር ቤታቸውም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን የሚመሩ የባህል መሪዎች ይህንን ሚና መጫወት እንዲችሉና በአገሪቱ የተከሰቱት ልዩ ልዩ አለመግባባቶች መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩለን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ ይናገራሉ።
አቶ ቡሩክ ‹‹በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሰራነው ጥናት በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 62 በመቶ፣ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 96 በመቶ ድረስ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት እና ባህላዊ መሪዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው›› ይላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለዚህ መሰል አገር በቀል እሴት ልቡ ክፍት እንደሆነና ተግባራዊ ቢሆን ደስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚገልጹት፣ ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በመተባበር በክልሎች (ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሱማሌ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ) ክልሎች ዋና ከተሞች ላይ በመገኘት ከየክልሉ ለ15፣ በአጠቃላይ ለ150 ባህላዊ መሪዎች የአምስት ቀናት ስልጠና ከግንቦት 2014 እስከ ኅዳር 2015 ድረስ ለ6 ወራት ሰጥተው አጠናቅቀዋል፡፡ ከባህል መሪዎቹ በተነሳ ጥያቄ መሰረት የባህል መሪዎች ምክር ቤት ለማቋቋም ህጋዊ ሂደቶችን ለመጨረስ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በየክልሉ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎችም እርስ በእርስ እንዲገናኙና በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማህበራት እንዲመሰርቱ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል። ከክልል አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስም “ብሔራዊ የባህል መሪዎች ምክር ቤት” ለማቋቋም እየተሰራ ነው።
ዶክተር መልሰው ደጀኔ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት እንዲሁም የልማት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ናቸው። አፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት፣በቱሪዝምና ባህል ሚኒስቴር እንዲሁም በዩኤስ ኤይ ዲ (USAID) ድጋፍ የኢትዮጵያ የባህል መሪዎች ለአገር ግንባታ (ሰላምን ለማስፈን) ያላቸውን ሚና ለማጎልበት ስልጠናዎችን በመስጠትና በማስተባበር ይሰራሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ለባህል መሪዎች ስልጠናዎችን ለመስጠት እንዲሁም የጋራ ምክር ቤት ለመመስረት በተለያዩ ክልሎች በሚዘዋወሩበት ጊዜ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግጭቶች እንዳሉ ተረድተዋል። ይህም እንደ አገር “አዎንታዊ ሰላም” አለመስፈኑን እንዳስገነዘባቸው ይገልፃሉ።
‹‹የእነዚህን ግጭቶች ስረ መሰረታቸውን ስንመረምራቸው ‹አገር በቀል እውቀቶች ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ› የሚለው ዋናው ትኩረት መሆን ይገባዋል፡፡ በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ከምስራቅ ጫፍ እስከ ምእራብ መሄድ ቢቻል አገር በቀል እውቀትና የግጭት አፈታት ስርዓት እውነትና ፍትህ የሚተቃቀፉበት ስርዓት ሆኖ መመልከት እንችላለን›› በማለት ትዝብታቸውን ይናገራሉ።
‹‹አለመግባባትን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ መሄድ ቢቻል ፍትህ አገኘን ማለት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ፍትህ ሁልጊዜ እውነትን ላይዝ ይችላል፡፡ አንድ አካል ባመረተው መረጃና ባቀረበው ሰነድ ልክ በዚያ ተመስርቶ ነው ዳኝነት የሚያገኘው። በአብዛኛው ከደሃ ይልቅ ሃብታም፤ ከተራ ሰው ይልቅ ባለስልጣን አልያም ሰፊ እድል ያለው ሰው መረጃን የማምረት አቅሙ አለው። ወደ ባህላዊው የግጭት አፈታት ስርዓት በምንሄድበት ጊዜ ግን ፍትህ እውነት ማለት ነው፤ ማንኛውም ሰው በየትኛውም የስልጣን፣ የሀብት፣ የዝናና የተፅእኖ ፈጣሪነት ደረጃ ላይ ቢሆንም በባህላዊው ስርዓት ከተራው ሰው እኩል ዳኝነትን ያገኛል፡፡ ባህላዊ መሪዎች እና ሸንጎ ፊት ተይዞ የሚቀርበው እውነትን ያዘለ መረጃ ካልሆነ መርገምን፣ ከማህበረሰብ መገለልንና የመሳሰሉት ቅጣቶችን ይዞ ይመጣል›› ይላሉ።
“በኢትዮጵያ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ቢኖርም የጎለበተ አይደለም” የሚሉት ዶክተር መልሰው፤ ብዙ ውጥንቅጦቻችንን የምንፈታው በዚሁ ባህላዊ በሆነው የግጭት አፈታት ስርዓት ቢሆንም በትኩረት አልሰራንበትም ይላሉ። ይሁን እንጂ ለመንግስት፣ ለፍትህ ስርዓቱና በጥቅሉ ለህግ ያስቸገሩ ጉዳዮች በባህል መሪዎችና ሽማግሌዎች በጥቂት ጊዜ መፍትሄ ሲያገኙ መመልከት ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አለመሆኑንም ያነሳሉ።
“የባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት፣ የጋራ አሸናፊዎች መስተጋብር ነው” የሚሉት ዶክተር መልሰው፤ አጥፊም ሆነ ተጠቂ አሸንፈው የሚወጡበት ስርዓት እንደሆነ ይናገራሉ። ፍርድ ቤት በመሄድ ፍትህ ማግኘት ቢቻልም “የቂም በቀለኝነቱን ሽክርክሪት” የሚሰብር አለመሆኑን በመግለፅም ሙሉ እርቅና ግጭትን ማስወገድ የሚያስችለው በባህል መሪዎች አማካኝነት በሚተገበረው የግጭት አፈታት ስርዓት መሆኑንም ይገለፃሉ።
የአፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት ባመቻቸው እድል የክልሉን ሽማግሌዎች በመወከል የባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓትን በተመለከተ ምክክር ለማድረግና በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የጋራ የባህል መሪዎች ምክር ቤት ለማቋቋም ከአማራ ክልል፣ ጎንደር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ግጭቶችን በሽምግልና መፍታትን በሚመለከት ስልጠና የወሰዱት አቶ አዳነ አዳምሰገድ የመጡበት ክልልም ግጭትና አለመግባባት ሲከሰት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የተለያየ የሽምግልና ስርዓት እንዳለ ይናገራሉ። በዚህ መሰረት ችግሮች ሲቃለሉ መቆየታቸውንም ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ባመቻቸላቸው እድል መሰረት አንድና ወጥነት ያለው፣ ተፅእኖ መፍጠር የሚችል፣ መምከር፣ ማስተማር እንዲሁም ተቆጥቶ ሊያርም የሚችል የሽምግልና ማህበር እንዳቋቋሙ ይናገራሉ።
“በቅማንትና በአማራ አካባቢ የነበሩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት ሽምግልና ትልቅ ሚና ነበረው። አሁንም ድረስ በጎ ተፅእኖ እየፈጠርን እንገኛለን” የሚሉት አቶ አዳነ አዳም ሰገድ፤ ‹‹ወደ አንድነት እንድንመጣ የተሰደዱና ወደ በረሃ የገቡ ወደ ቀያቸው ገብተው ሰላም እንዲፈጥሩ በዚህ በባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው›› ይላሉ።
አቶ ተስፋዬ ደነቀ የአፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት ያመቻቸውን የምክክር መድረክ ለመካፈል ከሲዳማ ክልል ተወክለው የመጡ የአገር ሽማግሌ ባህላዊ መሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ግጭቶች ሲከሰቱ በባህላዊ መሪዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትና ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት እንዲኖር የሚደረገው ጥረት ተገቢ ነው። በዚህ እረገድ አህጉር በቀል አመራር ምክር ቤቱ እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
“በሲዳማ ክልል ባህላዊ የግጭት አፈታት የተመረጠ ሲሆን በግለሰብም ሆነ በቡድን ለሚነሱ አለመግባባቶች በሽምግልናና በልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶች መፍትሄ ይሰጣል” የሚሉት የአገር ሽማግሌው አቶ ተስፋዬ ደነቀ፤ ይህንን ማድረግ የሚችል ባህላዊ አቅምና ስርዓት ማጎልበት እና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ። እርሳቸውን ጨምሮ ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ የአገር ሽማግሌዎችም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በባህላዊ እሴቶች፣ እውቀቶች እና ሀብቶች ለመፍታት እንዲያስችላቸው የጋራ የባህል መሪዎች ምክር ቤት ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ። መንግስትም ይህን መሰል በጎ ሃሳብ እና ምግባር መደገፍ እና ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል እውቅና መስጠት እንደሚገባውም ይገልፃሉ።
እንደ መውጫ
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከራሷ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሰላምን ለማውረድ የሚጠቅሙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንዳሏት ይነገራል። እነዚህን ባህላዊ እሴቶች ከዘመናዊ የህግ ስርአት ጋር በማቀናጀት መስራት እንደሚገባ የተለያዩ ምሁራን እና ተቋማት ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ከእነዚህ መካከል ብሔራዊ የባህል መሪዎች ምክር ቤት ለማቋቋም ላለፉት አንድ ዓመታት እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘውና በእሴቶቹ ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ያለው የአፍሪካ የአህጉር በቀል አመራር ምክር ቤት አንዱ ነው።
አገር በቀል የሽምግልና ባህልን ተጠቅሞ ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት በመንግስት በኩል ቢኖርም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አካቶ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማስኬድ አሁንም ድረስ በበቂ ሁኔታ ተሰርቶበታል ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም የእሴቱ ባለቤት የሆኑ እናቶች እና አባቶች፣ ምሁራን፣ የባህልና ቱሪዝም ተቋማት፣ ህግ አውጪዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት እንዲዳብር መስራት ይኖርባቸዋል የዛሬው መልእክታችን ነው። ይህን ማድረግ ሲቻል እውነትና ፍትህ የሚተሳሰሩበት ጠንካራ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን መዘርጋት እንደሚቻል እናምናለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም