
የሀገር ሽማግሌ ናቸው፤ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት ሙያ አገልግለዋል። በተወለዱበት አካባቢ ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅመው የውሃ፣ መብራት፣ መንገድ መሠረተ ልማት እንዲገነባ ማህበረሰባቸውን ወክለው በርካታ ተምሳሌት የሚሆን ተግባር አከናውነዋል። ብዙዎች በጡረታ ዘመናቸው የማይደፍሩትን የጥብቅና ሙያ ተምረው ፍቃድ በማውጣት ይሠራሉ። ከገበሬና ነጋዴ ቤተሰብ ቢወጡም እርሳቸው ግን ወደ ትምህርቱ አዘንብለዋል። የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን የዳውሮ ዞን ተወላጅ እና የሀገር ሽማግሌ አቶ በለጠ ባሹ ናቸው። የዛሬው የ«ሕይወት ገጽታ» አምድ እንግዳችን ከሕይወት ምዕራፎቻቸው አስተማሪና አዝናኝ ያሉትን አጫውተውናል። መልካም ቆይታ!!
ትውልድና አድገት
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ እነክሪ በምትባል ቀበሌ በተምሳሌትነታቸው ብዙዎች የሚያውቋቸው፣ በእርቅ በልማት እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፊት ከሚሰለፉ ብርቱዎች መካከል የሆኑት አቶ በለጠ ባሹ ተወለዱ። እናታቸው ወይዘሮ ዳኢሜ ደነፎ የአባታቸው አቶ ባሹ አራት ሚስቶች መካከል አንደኛዋ ነበሩ። አቶ በለጠ የአባታቸው የእናታቸውም የበኩር ልጅ ናቸው። ስማቸው በዚሁ ምክንያት እንደወጣላቸው ይናገራሉ።
‹‹አባቴ በ2010 ዓ.ም በ117 ዓመቱ ነው የሞተው። በጊዜው ሲቆጠር ከልጅ ልጆች ጋር ተደምሮ 170 እንደርስ ነበር›› ይላሉ አቶ በለጠ ቤተሰባቸው ሰፊ መሆኑን እየተናገሩ። አባት በጊዜው በንግድ እና በግብርና ሥራ ላይ ተሠማርተው ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ እንደነበርም ይናገራሉ። ከዳውሮ ቅቤ ወደ ከፋ ጨና ወደሚባል አካባቢ በመውሰድ ከዚያ ደግሞ ቡና በማምጣት ከግብርናው ጎን ለጎን ንግዱን ያቀላጥፉ እንደነበር ያስረዳሉ። በተጨማሪ ፈረስና በቅሎዎችን ይነግዱ ነበር። በዚህም ሥራቸው እስከ አዲስ አበባ ይመላለሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አባታቸው ለትምህርት ልዩ ቦታ ነበራቸው። በንግድ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ከተለያዩ ሰዎች ጋር ይገናኙ ስለነበር ግንዛቤ ነበራቸው። በዚህ ምክንያት የበኩር ልጃቸው የሆኑት አቶ በለጠ ተማሪ ቤት እንዲሄዱ ልዩ ፍላጎት ነበራቸው። ይህንን ተከትሎ ፊደል እንዲቆጥሩ ግፊት በማድረግ መንገዳቸው ከንግድና ከግብርና የተለየ እንዲሆን አስተዋፅኦ አድርገዋል። መደበኛ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት በቄስ ትምህርት ቤት ደብራቸው በሚያስተምሩ መምህር ፊደል ቆጥረዋል።
አዲስ አበባና ትምህርት
አቶ በለጠ ገና ታዳጊ እያሉ (በ7 ዓመታቸው) ነበር የአባታቸው ወንድም ይኖርበት ወደነበረው አዲስ አበባ የመጡት። ምክንያቱ ደግሞ በጊዜው በጠና በመታመማቸው የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ነበር። በዚያው በዳውሮ በሚሲዮናውያን ህክምና ማእከል ለማሳከም ቢሞክሩም ባለመሳካቱ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተወሰነ። እግረ መንገድ አባታቸው ትምህርትን በተሻለ መልኩ ለመማር እንዲችሉም በማሰብ በከአጎታቸው ጋር ተስማምተው ነበር። ዳውሮ በ1947 የትራንስፖርት አማራጭ የነበረው በአውሮፕላን ነበር። እርሳቸውም ወደ መዲናዋ የመጡት በቀላሉ ሜዳማ ቦታ ላይ ታርፍ በነበረው ዳኮታ አውሮፕላን ነበር። አዲስ አበባ እንደገቡ ህክምናውን አደርገው እዚሁ አጎታቸው ጋር ቆዩ።
ይሁን እንጂ የአማርኛ ቋንቋን ለመማር እድል ከማግኘታቸው ውጪ የእርሳቸውም ሆነ የአባታቸው የመማር ፍላጎት አልተሳካም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በአጎታቸው ሚስት ፍላጎታቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነበር። የልጅነት ትውስታቸውን መለስ ብለው እየቃኙ ሲናገሩ ‹‹በጊዜው በቤት ውስጥ ለአጎቴ ሚስት እላላክ ነበር። ትምህርት ቤት እንደ ልጆቻቸው ብገባም መላላኩ እንደሚቀር ስላወቁ ፍላጎት አልነበራቸውም›› በማለት የአዲስ አበባ ቆይታቸው እምብዛም የተሳካ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።
በጊዜው አቶ በለጠ ትምህርቱ ባለመሳካቱ እልህ ውስጥ ገቡ። ካልተማሩ በአዲስ አበባ መቆየት እንደማይሹ ወስነው ወደ ትውልድ መንደራቸው ለመመለስ ቆረጡ። የአባታቸውን መታመም እንደ ሰበብ አድርገው ወደ ዳውሮ ተመለሱ። ዳውሮ እንደገቡ ለአባታቸው የሆኑትን አስረዱ እርሳቸውም ‹‹እንኳን ተመለስክ›› በማለት ልጃቸውን ወደ መደበኛ ትምህርት በመውሰድ አስመዘገቧቸው።
አቶ በለጠ መደበኛ ትምህርት የጀመሩት ከሁለተኛ ክፍል ነበር። ምክንያቱ ደግሞ አቀባበላቸው ፈጣን ስለነበር በቀጥታ ወደ ሁለት እንዲገቡ በጊዜው የዋካ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ጥላሁን ወንድሙ የተባሉ ሰው የሰጧቸውን ፈተና በማለፋቸው ነበር። ጉብዝናቸው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ብቻ አልነበረም የዘለቀው በተከታታይ ደብል እየመቱ (ከሁለት ወደ አራት ከአራት ወደ ስድስት) እያሉ እስከ ስምንተኛ ክፍል ዘልቀዋል። የትምህርት አቀባበላቸው በመምህራኖቻቸው እንዲወደዱና ፈጣን ለውጥ እንዲያሳዩ አድርጓቸዋል።
በዳውሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ነበር ትምህርት ቤት የነበረው። በዚህ ምክንያት አባታቸው ወደ ጅማ ልከዋቸው ዘጠኝ እና አስረኛ ክፍልን ጨርሰዋል። በዚህ ወቅት ላይ ነበር ለመምህርነት ታጭተው ከአስረኛ ክፍል ወደ ማሠልጠኛ በመሄድ የሕይወታቸውን ሌላኛውን ምእራፍ የጀመሩት።
መምህርነትና የፖለቲካ አለመረጋጋት
በጊዜው መምህራንን የሚያሠለጥኑ አምስት ማሠልጠኛዎች ነበሩ። እርሳቸው እንደ አድል ሆኖ ‹‹ካልተማርኩ እዚህ አልኖርም›› ብለው ጥለዋት ወደ ትውልድ መንደራቸው የተመለሱባት አዲስ አበባ ነበረች በእጣ የደረሰቻቸው።
አቶ በለጠ በ1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የያኔው ኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመደቡ። ወቅቱ ተማሪዎች በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቃውሞ ያነሱበት ከፍተኛ ንቅናቄ እና ተቃውሞ የነበረበት ነው። ጊዜውን ሲያስታውሱ የኮሙኒዝም ፍልስፍና በተማሪዎች የሚቀነቀንበትና በተለይ በወሎ በወይዘሮ ስህን እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚያዚያ 27ና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍቶ የነበረበት (የጉምጉምታ) ጊዜ አንደነበር ይናገራሉ።
ንቅናቄው ለአቶ በለጠ ሥልጠናውን ተረጋግተው እንዳይማሩ እንቅፋት ሆነባቸው። በንጉሡ ትእዛዝ ከማሠልጠኛው ለጊዜው (ለዓመት) ተቃውሞውን ለመቀልበስ በሚል ወደመጡበት እንዲመለሱ የግድ ሆነ። በአመቱ ደግሞ ዳግም ምደባ ተደርጎ 750 የሚሆኑ የኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ሥልጠናውን እንዲቀጥሉ ሲደረግ በአጋጣሚ እርሳቸው ጅማ ደረሳቸው። ለሁለት ዓመት በጅማ መምህርነት ሠልጥነው በ1966 ዓ.ም በንጉሡ የተፈረመበት ዲፕሎማ ተቀበሉ። በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር እጣ ሲወጣ በመምህርነት ተመድበው እንዲያስተምሩ ጋሞ ጎፋ ተመደቡ።
በጋሞ ጎፋ ጋርዱላ አውራጃ ኬንያ ድንበር ላይ በሚገኝ ትምህርት ቤት ለጥቂት ጊዜ ሲያስተምሩ ቆዩ። ጊዜው ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት የነበረበት ወቅት ነበር። በተለይ በ1966 ዓ.ም ንጉሡን ከዙፋናቸው ያነሳ አብዮት የተቀጣጠለበት ነበር። እርሳቸውን ከአዲስ አበባ ኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ አንስቶ ወደ ጅማ የወሰደ አለመረጋጋት ተጋጋመ፤ ተጋግሞ ብቻ አልቀረም ያበጠው ሁሉ ፈንድቶ አብዮት እየታወጀ የነበረበት ወቅት ነበር። በተለይ እርሳቸው አባል የሆኑበት የመምህራን ማህበር በ1967 አዲስ ዓመት መባቻ ላይ የንጉሡን ዘውዳዊ መንግሥት እንደማይቀበል የሚገልፅ መግለጫ እስከመነበብ ደርሶ ነበር።
አቶ በለጠ ለኮሙኒዝም ቀና አመለካከት ነበራቸው። በተለይ ለሠራተኛው ክፍል መወገኑ፣ ፈትሃዊ የሀብት ክፍፍል ላይ ያተኮረ ርዕዮተ ዓለም ማቀንቀኑ እና ብዙሃኑን የሚያቅፍ የወቅቱ የፖለቲካ መመሪያ ተመችቷቸው ነበር። ይህንን እሳቤ ይዘው በሚሠሩበት አካባቢ አብዮቱን በመቀላቀል አመፅ እስከመምራት ደርሰው ነበር። ነገር ግን ወታደሩ ንጉሡን አውርደው ሥልጣን መያዛቸው በድጋሚ በመምህራኖች ተቀባይነት ባለማግኘቱ በአብዮቱ ቀስቃሾች (ደርጉ) ምክንያት ለእስር ከተዳረጉ ጥቂት ጓዶቻቸው ጋር ወህኒ ቤት ወርደዋል።
ዳግም ወደ ጅማ
ጊዜው 1969 ዓ.ም ነው፤ አቶ በለጠ ከጋሞ ጎፋ ተመልሰው ወደ ትውልድ መንደራቸው አካባቢ ለመቅረብ የወሰኑበት ጊዜ። በወቅቱ መምህራኑ የደርግን ሥልጣን መያዝ በመቃወም እንቅስቃሴ ያደርግ ስለነበር እርሳቸውም በዚሁ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር በአጋሮ በመምህርነት መሥራታቸውን የቀጠሉት። በወቅቱ ወታደራዊው መንግሥት እና ተቃዋሚዎች በሚያደርጉት ግብ ግብ ነጭ ሽብር/ ቀይ ሽብር በሚል ግድያ እና እስር የነበረበት አስከፊ ወቅት ነበር። ኢህአፓም የተማረውን ሃይል ይዞ ወታደራዊውን መንግሥት ሥልጣን እንዲያስረክብ የከተማ ውስጥ ትግል የሚያደርግበት ጊዜ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አቶ በለጠ ራሳቸውን እየጠበቁ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እውቀት እያስጨበጡ የሕይወት ምእራፋቸው ቀጠለ። በጊዜው ባገኙት የማስተማር ዲፕሎማ ሁሉንም የትምህርት አይነት የማስተማር ፍቃድ ቢኖራቸውም የእርሳቸው ምርጫ ግን የሳይንስ ትምህርቶች ነበሩ። ከፖለቲካው ውጥንቅጥ እና ከዘመኑ የኮሙኒዝም ፍልስፍና ባሻገር ትውልድን በትምህርት የማንቃት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡም ቀጥለዋል። በዚህ ወቅት ነበር የከፋ ክፍለ አገር መምህራን ማህበር ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት።
በሊቀመንበርነታቸው ጊዜ የደርግ መንግሥት ሲቪሎችን በፖለቲካ ውስጥ ማሳተፍና መንበረ ሥልጣኑም በተወሰነ መልኩ መረጋጋት የታየበት ነበር። እርሳቸውም ሙሉ ትኩረታቸውን በመምህራን እና በተማሪዎቻቸው ላይ በማድረግ በጊዜው አስተማሪዎች ተነፍገው የነበረውን መብቶች ለማስከበር ይታገሉ ጀመር። በተለይ ደርግ የወረሳቸው ቤቶች እና የቀበሌ ቤቶች ለመምህራን ጥቅም እንዲውል፤ ተገቢውን ክብር እንዲያገኙ እና አስተማሪዎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች ዝውውር አድርገው ሲሄዱ፣ ሲሞቱ አሊያም ሕግን የተላለፈ በደል ሲደርስባቸው መሞገትና ጥቅሞቻቸውን ማስከበር ላይ በማተኮር በሥልጣን ቆይታቸው ሲሠሩ ነበር።
መሠረተ ትምህርት ዘመቻ
አቶ በለጠ ባሹ በአባታቸው ብልሃትና አርቆ አሳቢነት ወደ ቀለም ትምህርት እንዲያዘነብሉ ተቀርፀዋል። ሞፈርና ቀንበርን የሚያዋድድ ገበሬ አሊያም የአባቱን ፈለግ የሚከተል ነጋዴ አልሆኑም። ይልቁኑ የገበሬውንም የነጋዴውንም ሥራ የሚያዘምን፤ ሳይንሳዊ ምርምርና ዘመናዊነትን በእውቀት ከሽኖ ትውልድ የሚቀርፅ መምህር የእጣ ክፍላቸው ሆነ። በዚህ ልዩ አጋጣሚ ውስጥ ሕይወታቸውን ሲመሩ ደርግ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻን አወጀ።
ደርግ በጊዜው ብሄራዊ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር። እርሳቸው ደግሞ የከፋ አውራጃ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር ነበሩ። በዚህ ምክንያት ከአውራጃው አስተዳዳሪ ጋር በመሆን ዘመቻውን በማስተባበር መምራት ጀመሩ። ጊዜውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ‹‹ደርግ ከሠራቸው መልካም ሥራዎች መካከል የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ተጠቃሽ ነው። በእግራችን በወረዳ ቀበሌ እየሄድን በፈረስ በበቅሎ የሚደረስባቸው ቦታዎች ጭምር ወርደን ዘመቻውን እንገመግም ነበር›› ይላሉ። በጊዜው የነበሩ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ጣቢያዎች አሁን ጥናት ቢደረግባቸው በብዛት ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሆኑና ውጤታማ ዘመቻ እንደነበር ይናገራሉ። እርሳቸው ከሚኮሩባቸው ጊዜዎች መካከልም ይህንን ዘመቻ የመሩበት መሆኑን አልሸሸጉንም። በጊዜው በውጤታማነታቸው የተመሰከረላቸው ዘመቻውን በመምራት ውጤታማ ከሆኑና በብዙዎች ከሚመሰገኑ የመምህራን አመራር መካከል አቶ በለጠ ተጠቃሽ ናቸው።
ማጂ- ሌላ ሃላፊነት
አቶ በለጠ በመምህራን ማህበር ሊቀመንበርነትና በአስተማሪነት በነበራቸው አስተዋፅኦ ራሺያ (የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት) የትምህርት እድል ካገኙ ትጉዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በዚያ በነበራቸው ቆይታ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን እና ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ትምህርት ለሁለት አመት ተከታትለው ተመልሰዋል።
ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ የከፋ ጠቅላይ ግዛት በማጂ አውራጃ የትምህርት ፅህፈት ቤት ሥራ አስኪያጁ በመሆን በጊዜው በነበሩ ስድስቱም ወረዳዎች የምህርት ሥርዓቱን ለመምራት ተመድበዋል። በጊዜው የፖለቲካ ጉሸማና ትንኮሳ ከኢሰፓ አባላቶች የሚደርስባቸው ቢሆንም በሙያቸው ማገልገልና ለእውነት መቆምን አሻፈረኝ አላሉም ነበር። ቆየት ብለውም እውነትን ከውስጥ ሆኖ በሙያ እያገለገሉ መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ በማመናቸው በአባልነት ቀጥለዋል። በሂደቱም ከትምህርት ሥራ አስኪያጅነት እስከ ኩሉ ኮንታ (የትውልድ መንደራቸው) አስተዳዳሪነት የሚደርስ የሥልጣን እርከን ላይ ቆይተዋል።
በአስተዳዳሪነት የቆይታ ዘመናቸው ለትውልድ መንደራቸው የመሠረተ ልማት ግንባታ መሳካት ብዙ ትግል አድርገዋል። በጊዜው ለባለሥልጣናትን የአካባቢውን ሁኔታ በማሳየት በተለይ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ሞግተዋል። በውጤቱም ጥያቄያቸው የደርጉ ሊቀመንበር የነበሩት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሃይለማሪያም ጋር ደርሶ ነበር። በውጤቱም የኩሉ ኮንታን ከወላይታ ጋር የሚያገናኝ መንገድ ለመሥራት ዶዘርና ብር በማሰባሰብ ጥርጊያ መንገድ ሠሩ። በጊዜው የአካባቢውን ሰዎች አስተባብረው አንድ ላንድ ሮቨር በመግዛት ንግድና ትራንስፖርት እንዲጀመር ምክንያትም ሆኑ። ዛሬ በዳውሮ ዞን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴና የትራንስፖርት መናኸሪያ በስፋት ይገኛል። ለዚህ መሠረት የሆነ የልማት ማስተባበር ሥራ እንዲጀመር ካስቻሉ የአካባቢው ተወላጆች ውስጥ አቶ በለጠን በመጥራት የማያመሰግን የለም።
የሥርዓት ለውጥ- ሌላኛው ምእራፍ
በአስተዳዳሪነት ለሁለት ዓመት ነበር የቆዩት። ምክንያቱ ደግሞ የደርግን ሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ ስለነበር ነው። ሥርዓቱ በ1983 ዓ.ም እንደወደቀም እርሳቸውን ጨምሮ የኢሰፓ ዓባላት የነበሩ ለእስር ተዳርገዋል። ጊዜውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ‹‹አሸንፈውን ነበር የገቡት የገደሉትን እየገደሉ ማሰር ያለባቸውንም እያሠሩ ነበር። የእኛም እጣ ፈንታ ያ ነበር›› በማለት በጊዜው ለእስር የተዳረጉትን ሁሉ በትውልድ መንደራቸው (ዳውሮ አዳራሽ) በሚባል ሥፍራ እንደሰበሰቧቸው ይገልፃሉ። ሕዝቡም የአውራጃ አስተዳዳሪ የነበሩትን አቶ በለጠ ለአካባቢው ልማት ባበረከቱት አስተዋፅኦ ምክንያት በኢህአዴግ ወታደተሮች ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው ተከላክሎላቸዋል። ‹‹ኩሉኮንታን ከወላይታ ያገናኘ መንገድ የሠራልን እና ከጨለማ ያወጣን የልማት አርበኛችን ነው። ነፃ ያወጣን አርሱ ነው›› በማለት ክፉ እንዳይደርስባቸው ተከላክሎላቸው ነበር።
አቶ በለጠ ኢህአዴግ እንደገባ ለአራት ዓመት ከሥራ ውጪ ሆነው ቆዩ። ምክንያቱ ደግሞ የደርግ አባል ስለነበሩ ነው። ይሁን እንጂ ከሁለት ቀን የአዳራሽ እስር ውጪ ወህኒ ቤት አልወረዱም ። የዚህ ምክንያት ከላይ እንደገለፅነው በአካባቢው ማህበረሰብ በሠሩት ሥራ ተወዳጅ ስለነበሩ ነው። ጊዜውን እያስታወሱ ‹‹ለአራት ዓመት ሥራ አጥ ደሞዝተኛ ሆኜ ነበር። ሳልሠራ መብላቴ ያሳምመኝ ነበር›› በማለት ያሳለፉትን አስቸጋሪ ወቅት ያስታውሱታል።
አራት ዓመት ሙሉ ያለሥራ የተቀመጡት አቶ በለጠ በመጨረሻም የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦትና ስርጭት የሚባል አዲስ መዋቅር ሲፈጠር በማረቃ ወረዳ ዋካ ከተማ ውስጥ ተመድበው መሥራት ጀመሩ። በነበራቸው የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ዘርፉ ላይ ቢመደቡም እስከ ክልል የትምህርት ቢሮ የደረሰ የካድሬዎች ተቃውሞ አስተናግደው በመጨረሻም ማለፋቸውን ይናገራሉ። በዚህ ዘርፍ ሲሠሩ ቆይተው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በተርጫ ቀበሌ ሲከፈት በዚያ አስተዳዳሪ ሆነው ሠሩ። በወቅቱ የመንግሥትን የትምህርት ፖሊሲ ከማስፈፀም ባሻገር መምህራን የተመቻቸ ሁኔታ እንዲገጥማቸው ትግል ያደርጉ ነበር። በተለይ በአካባቢው ከፍተኛ የውሃ እጥረት ስለነበር ያንን ለመቅረፍና መምህራን በውሃ ሰበብ እንዳይሸሹ ለማድረግ እስከ ጡረታ ዘመናቸው ቆይተዋል።
አቶ በለጠ ባሹ ጠንካራ የሥራ መንፈስ እና ሙያዊ ከህሎት ያላቸው ታታሪ ሰው ናቸው። በተለይ የጡረታ ዘመናቸውን ቁጭ ብለው የማሳለፍ እቅድ አልነበራቸውም። በዚህ ምክንያት ከሥራ በመሰናበቻ ጊዜያቸው አቅራቢያ በሌላ ትምህርት ላይ ለመሰማራት ወሰኑ። ጥሞና አድርገው በጡረታ ዘመን ሊሠሩ ስለሚያስቡት ሙያ ሲያውጠነጥኑ የጥብቅና ሙያ ለእርሳቸው የተመቸ እንደሆነ ተገነዘቡ። በዚህ ወቅት ነበር ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በርቀትና በገፅ ለገፅ ትምህርት በሞጁሎች የታገዘ ትምህርት ወስደው የሕግ ዲፕሎማ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት። ለሶስት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ አቃቤ ሕግ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተውም በ2004 ዓ.ም በጡረታ ተሰናበቱ። ከመንግሥት የሥራ ገበታ እራሳቸውን እንዳገለሉም የጥብቅና ፍቃድ አውጥተው እስካሁን እየሠሩ ይገኛሉ።
ሽምግልና-ሀገርን የማፅናት ትልም
አቶ በለጠ ሲበዛ ሀገር ወዳድ ናቸው። በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ለሕዝቦች አንድነትና ለዳር ድንበራቸው ቀናኢ የሆኑ የሀገር ሽማግሌ። በጡረታ ከመንግሥት ሥራ እንደተሰናበቱ ጥብቅናን ብቻ ሳይሆን ሽምግልና እና የማማከር ሥራንም ደርበው እየሠሩ ይገኛሉ። የትውልድ አካባቢያቸው በልማት ወደኋላ እንዳይቀር መሰሎቻቸውን በማስተባበር ይተጋሉ። በአንድ ወቅት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል እስከመሆን ደርሰዋል። አሁንም ድረስ በዚህ ተግባራቸው እንደቀጠሉ ናቸው።
በሽምግልና እና ማማከር ተግባራቸው ከሚጠቀስላቸው ተግባር መካከል የዳውሮ ዞን የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን የሠሩት ሥራ ነው። በተለይ ሀላላ ኬላ ኢኮ ቱሪዝም እንዲገነባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሽምግልና ከማስተባበር አንስቶ ሌሎች አያሌ የሚያስመሰግኑ ተግባራትን አከናውነዋል። ሎጁ ተመርቆ ሥራ እስኪጀምር ድረስ የሀገሬው ሽማግሌ ሆነው ሠርተዋል። አሁንም መሰል የልማት ሥራዎች በዳውሮ አካባቢ እንዲከናወን ይሞግታሉ። ከዚህ ውስጥ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ይጠቀስላቸዋል።
አቶ በለጠ ተርጫ ከተማ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በሰንበሌጥና ሳር የተሸፈነ የመሠረተ ልማት የማይታይበት መሆኑን ያስታውሳሉ። በተለይ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚባል በአካባቢው የማይታሰብ ነበር። ከተራሮች ከሚፈሱ ምንጮች በስተቀር በየቤቱ በቧንቧ ውሃ የሚገኝ የመጠጥ ውሃ አልነበረም። የማህበረሰቡን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት 17 ኪሎ ሜትር መጓዝ የግድ ነበር። በዚህ ምክንያት ነዋሪው በከፍተኛ ምሬትና የአስተዳደር ብሶት ውስጥ መቆየቱን ይናገራሉ። እርሳቸውም ሌሎች ተወካዮችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በማስተባበር ይህንን መሰል የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲካሄድ ሲሞግቱ ቆይተዋል። በዚህ ጥረትም የፌዴራል መንግሥት 260 ሚሊዮን ብር በጀት እና ባለሙያ መድቦ የውሃ ማከማቻ ታንከሮች እንዲሠሩና የንፁህ የመጠጥ ውሃ ለነዋሪው እንዲቀርብ ማድረጉን ያስረዳሉ።
ዛሬም በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ማህበረሰቡን በመወከል እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እየተጉ ይገኛሉ። በውጤቱም ከግቤ ሶስት በቀጥታ የገባ የመብራት አገልግሎት በለውጡ መንግሥስት መሠራቱን እና የውሃና የመብራት ጥያቄያቸው መመለሱን ያስረዳሉ። በመንገድ በኩልም ወደ ወላይታ፣ ኮንታ እንዲሁም ልዩ ልዩ አጎራባች ከተሞች መተሳሰሩን ያስረዳሉ። የቀደመው የእርሳቸው ጥረት ዳር እየደረሰ ለመሆኑም እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ምስክር ናቸው።
አቶ በለጠ የዳውሮን ማህበረሰብ በመወከል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዞኑ ስለሚገኙ ፀጋዎች በማስረዳት፣ ሥፍራው እንዲለማ ጥያቄ በማቅረብ በሀገር ሽማግሌነት አገልግለዋል፤ በዚህ እርሳቸውና መሰሎቻቸው የተጉለት ጥረት እውን ሆኖ ዛሬ ላይ ዳውሮ በለውጡ መንግሥት ተጠቃሚ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ቀዳሚው ሆኗል። በተለይ የሀላላ ኬላ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዳውሮ ምልክት ሆኖ በብዙዎች ዘንድ እውቅናን ያተረፈ ነው። በዚህ መሰል ፕሮጀከቶች ላይ አቶ በለጠ የሀገር ሽማግሌና አስተባባሪ በመሆን ዐሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ።
የአቶ በለጠ ቤተሰብ
አቶ በለጠ ከባለቤታቸው ወይዘሮ የትናዬት ድንበሩ ጋር ተጋብተው ሶስት ልጆች ወልደዋል። ለቤተሰብ ልዩ ቦታ ያላቸው ልጆቻቸውን አስተምረው፣ ድረው ኩለው የሚኖሩ የሀገር ሽማግሌ ናቸው። ትዳር የመመሥረት ሂደቱ ግን እንዲያው ቀላል አልነበረም። ከባለቤታቸው ዘመዶች ጋር አለመግባባት ውስጥ እስከመግባት ደርሰው ነበር የዛሬው የሕይወት አጋራቸው ከሆኑት ወይዘሮ የትናዬት ጋር ትዳር የመሠረቱት። ‹‹ትዳር አልጋ ባልጋ አይደለም፤ አይደለም ሰው እግርና አግር ይጋጫል›› ይላሉ የእርሳቸውን የቤተሰብ ምሥረታ ሂደት አንስተው ሲያጫውቱን። በዚህ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ትዳራቸውን የሚፈትኑ ነገሮች ገጥመዋቸው የነበረ ቢሆንም ለከፋ ነገር እንዳልዳረጋቸው ያስረዳሉ። በሁለቱ ባለትዳሮች ፅናትም ተወዳጅና ጠንካራ ቤተሰብ መሥርተው እስካሁን ድረስ ለ45 ዓመታት ቆይተዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም