በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት እንደተጀመረ የታሪክ ልሳናት ይጠቅሳሉ። ከዚያን ዘመን ጀምሮ ትውልዶችን በዘመናዊ ትምህርት በማነጽ ሀገርን ወደ ተሻለ የሥልጣን ምዕራፍ ለማሻገር ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። ይብዛም ይነስም የተገኙ ወጤቶች ሀገር ከትናንት ዛሬ የተሻለች እንድትሆን ረድቷል።
በተለይም ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ዘመናዊ ትምህርትን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት፤ ሀገርን የዘመናዊ ስልጣኔ ተቋዳሽ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፤ የተገኘው ውጤትም ከፍያለ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የለፉና የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችም በብዙ መልኩ የሀገር ባለውለታ በመሆን ተጠቃሽ ናቸው።
ደርግ ወደ ሥልጣን እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የነበሩት ጊዜያት ትምህርትን በመላው ሀገሪቱ ለማዳረስ ከፍያሉ ጥረቶች የተደረጉበት፤ አበረታች ውጤቶችም የተመዘገቡባቸው ነበሩ። ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ትምህርትን በስፋት ለመላው ሕዝብ ለማዳረስ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ያስመዘገበውም ውጤትም በትምህርት ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ከመሆኑም ባሻገር ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው መሆኑን አይዘነጋም።
የኢሕአዴግ መንግሥትም ቢሆን በተለይም የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በስፋት የዩኒቨርስቲዎችን ግንባታ በማካሄድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ ዩኒቨርስቲ ገብተው የሚማሩበትን፤ የግል ዩኒቨርሲቲዎችም በስፋት ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉበትን እድል ፈጥሯል። በዚህም ሀገሪቱ ብዛት ያላቸው የዩኒቨርስቲ ምሩቃን እንዲኖራት አስችሏል።
በዚህ ትምህርትን በስፋት የማዳረስ ሂደት ውስጥ ሀገርን ያጋጠማትና በየጊዜው አቅም እየገዛ መጥቶ ዛሬ ላይ ሀገርን በአደባባይ እንደ ሀገር የፈተነው የትምህርት ጥራት ጉዳይ ነው። በየወቅቱ /አንድ የፖለቲካ ሥርዓት መጥቶ በሄደ ቁጥር/ በትምህርት ሥርዓት ላይ የሚደረግ ለውጥ፤ ለውጡ ከትምህርትና ከጥራቱ ይልቅ ፖለቲካን ታሳቢ ማድረጉ በሀገሪቱ በተሻለ መነቃቃትና ተስፋ የተጀመረው ዘመናዊው ትምህርት ጥራቱ ተጠብቆ የሚፈለገውን ያህል ብዙ ርቀት መሄድ ሳይችል ቀርቷል ።
በየወቅቱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተደረጉ ለውጦች ፤ ዘመናዊ ትምህርት እንደ አንድ የለውጥ መሣሪያ ሕዝብና ሀገርን በመለወጥ፤ ለዜጎቿ የተሻለች ሀገር ከመፍጠር ይልቅ ፤ዘመናዊ ትምህርት እራሱ ችግር ውስጥ ወድቆ/በሕይወትና በሞት መካከል ሆኖ/የሚታደገው የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስገድደውታል። ለዚህ ደግሞ የሰሞኑ የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና ትክክለኛ ማሳያ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ ይፋ እንዳደረገው ከ2014 የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት ተፈታኞች ሦስት ነጥብ ሦስት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ መደበኛ ተፈታኞችን ካስፈተኑ 2959 ትምህርት ቤቶች መካከል 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት አንድ ሺህ 798 (60.76 በመቶ) ሲሆኑ፤ አንድ ሺህ 161 (39.24 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ግን በሀገር አቀፍ ፈተናው አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም። ይህ እውነት ችግሩ የቱን ያህል የከፋ እና አስደንጋጭ እንደሆነ በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ ክስተት ነው።
የትምህርት ጥራቱ ችግር እንዳለ ሆኖ ስርቆት እና ኩረጃ አስከፊ ደረጃ በመድረሱ የአሁኑ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ የፈተና አሰጣጡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየና በሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ውጤቱ ግን ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ነው።
ሚኒስቴሩ ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን በኢትዮጵያ ካሉ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 65 በመቶ የሚሆኑት ማንበብ እንደማይችሉ፣ የሚያስተምሩትን ትምህርት ከተፈተኑ መምህራን መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት ብቁ አለመሆናቸውን፣ 99 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን መስፈርት እንደማያሟሉ ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህ ከታች የሚጀምረው ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ችግር ፤አሁን ባለው ሁኔታ በአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ጎልቶ ይውጣ እንጂ በየትምህርት ክፍሉ የሚሠጡ ፈተናዎች በተገቢው ጥንቃቄና ቁጥጥር ተግባራዊ ቢሆኑ ከዚህ የከፋ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል አይጠረጠርም።
ከዚህም ባለፈ በቀጣይም በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የመውጫ ፈተና ለመስጠት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የተያዘው ፕሮግራም ተግባራዊ ሲሆን፤ ምናልባትም ከዚህ የከፋ ነገር ይዞ ስላለመምጣቱ መተማመኛ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ የለም።
ትምህርት የአንድን ሀገር እና ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ከመቀየር አንጻር ካለው ሁለንተናዊ አስተዋጽዖ አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጀመረው የትምህርት ሥርዓቱን የማከም ሥራ ሀገርንም ሆነ ተቋሙን ከፍያለ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው።
ይህንን የገነገነ ፈታኝ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ሚኒስቴሩ የጀመረው ጥረት ፤ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት የሚታይበት ፤ እያስመዘገበም ያለው ውጤትም ተስፋ የሚጣልበት ፤ ሊበረታታና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
ይህ በትምህርቱ ዘርፍ ሀገርን እንደ ሀገር ለመታደግ የተጀመረው ፈታኝ ሥራ የሁሉንም ዜጋ ርብርብ የሚሻ ፤ በአንድ ትምህርት ሚኒስቴር ጥረት ብቻ ከዳር ይደርሳል ፤ የተበላሸው ይቃናል፤ የወደቀው ይነሳል ብሎ ለማሰብ የሚቀል አይደለም! ።
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም