ህፃን ሰሚራ አልሃጂ በቃሊቲ የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት ከእናቷ ጋር ነው የገባችው። የሕግ ታራሚ እናቷ ሣራ ተሰማ እንደምትለው ስትገባ 14 ዓመቷ ነበር። እሷ ኬኒያ ላይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በኢንተርፖል ስትያዝ ሰሚራም በትውልድ ኢትዮጵያዊ በመሆኗ ከእናቷ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጣች። ባልሰራችው ወንጀልም ማረሚያ ቤት ወረደች።
በማረሚያ ቤት ውስጥ ሰሚራ እናቷ ያየችውን መከራና ስቃይ በሙሉ አይታለች። እናቷ ባጠፋችው ጥፋት በግርፊያ ስትቀጣ የልጅ ነገር ሆኖባት ለምን እናቴን ትገርፏታላችሁ ብላ በማልቀሷ ከእናቷ የማይተናነስ ግርፊያ ቀምሳለች። በማዕከላዊ እሷም እንደ እናቷ ባላጠፋችው ጥፋትና ባልሰራችው ወንጀል ከሰውነት ተራ እስክትወጣ ድረስ ለስምንት ወራት በእስር ስትሰቃይ ቆይታለች። ህፃኗ ከእናቷ ጋር ያየችውን ስቃይ በወቅቱ ከእናቷ ጋር ተነስታ የነበረው ፎቶ ይመሰክራል።
የሰሚራ እናት ወ/ሮ ሳራ ማዕከላዊ የነበረውን ስቃይና መከራ ማስታወስ አትፈልግም። በተለይም ምንም ወንጀል ሳትሰራ ልጇ ሰሚራ ያየችውን ስቃይና መከራ ስታስታውስ ያንገፈግፋታል። ሣራ ወንጀለኝነቷ ተረጋግጦ ከማዕከላዊ ወደ ቃሊቲ ከወረደች በኋላ የልጇ ስቃይና መከራ ቢያከትምም እስር ቤት ለልጅ ቀርቶ ለአዋቂም አስከፊ እንደሆነ ትናገራለች።
በ14 አመቷ ቃሊቲ የገባቸው ሰሚራ አሁን ላይ የ22 ዓመት ወጣት ሆናለች። ሆኖም እናቷ ወንጀል በመስራቷ ምክንያት ሕይወቷ ተሰርቋል። ትምህርት አልተማረች፤ እንደ ሌሎቹ የዕድሜ እኩዮቿ በነፃነት እየቦረቀች ተጫውታ አላደገችም። ሰሚራ ብቻ ሳትሆን ሁሉም የሴት ታራሚ ልጆች ከረሜላ እንኳን ብርቅ ሆኖባቸው ነው ያደጉት። አንዲት ታራሚ እናት ለልጇ አንድ ከረሜላ ብትገዛ ይሄን ከረሜላ የመግዛት አቅሙ የሌላቸው ሌሎች ታራሚዎች ሁኔታውን በበጎ አያዩትም። ብዙዎቹ ሴት ታራሚዎች የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው የልጆቻቸውን ጥያቄ መመለስ አይችሉም። የታራሚ ልጆች ይሄን የሚረዱት ከፍ እያሉ ሲመጡ ነው። ጥያቂያቸው ባለመመለሱ ደስተኛ አይሆኑም። በውስጣቸው ጥያቄ እየተፈጠረባቸውና ቅር እየተሰኙም ይመጣሉ። ነጻነታቸውንም ጥያቄ ውስ ጥ ማስገባት ይጀምራሉ።
ነፍስ እያወቁ ሲመጡና ያሉበት እስር ቤት መሆኑን ሲያውቁ ለምን እዛ እንደገቡና ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ መልኩ በዚህ ሁኔታ እንደሚኖሩ እናቶቻቸውን በጥያቄ ያጣድፋሉ። በርግጥ እንደ ነጭ ወረቀት የነፃው አእምሯቸው እናቶቻቸው ቃሊቲ የገቡት ሰርቀው ወይ ነፍስ ገድለው መሆኑን ገና ጡት ሳይጥሉ ከነሱው አንደበት በእርስ በእርስ ንግግራቸው እየሰሙም እንደሚያድጉ ሣራ ትናገራለች።
ሌላ ነገር ስለማያውቁም ጨዋታቸውም ሌባና ፖሊስ ጨምሮ ነው። ሣራ እንደነገረችን ታራሚ እናቶች ይሄ በነሱ ጦስ በልጆቻቸው የመጣ ፈተና አብዝቶ ያስጨንቃቸዋል። በተለይ ያለ ትምህርት ዕድሜያቸው መግፋቱ ይስማቸዋል። ምክንያቱ እነሱ መሆናቸው ከማሳፈርና ማሳቀቅ አልፎ በልጆቻቸው ላይ መብት እንዳላቸው እንዳያስቡ አድርጓቸዋል። ለሰሚራም በወንጀል ከተፈረደባት እናት ጋር ስምንት ዓመታት ያለ ትምህርት ማሳለፍ ቀላል አይደለም።
የሰሚራ እኩዮች አሁን ላይ ትምህርት ጨርሰው ጥሩ ደረጃ ሲደርሱ ሰሚራ ባልሰራችው ወንጀል ማረሚያ ቤት ትገኛለች። እናት ሁኔታውን ስታስበው ትሸማቀቃለች። “በጭራሽ እናትና ልጅ አንመስልም። ልጄን በጣም ነው የምፈራት” ትላለች። በጣም ተሳቃ እንደምትኖርና ለቀጣዮቹም አመታት በዚሁ ሁኔታ መቀጠላቸው እንደሚያስጨንቃት ትናገራለች።
ሣራ እንደምትለው ሰሚራን ጨምሮ አራት ልጆች ናቸው ያሏት። ታስራ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ሰሚራንና ትንሿን ልጇን ይዛ ነው። ትንሿን ልጇን የአባቷ ዘመዶች ሊያሳድጓት ተረከቧት። ሣራ የሰሚራን ጨምሮ አባቷ ዘመዶች ጋር ያለችውና አሜሪካና ለንደን ለማደጎ የተሰጡ ልጆቿ አስተዳደግ ያሳስባታል። ማታ ማታም እንቅልፍ ነስቷታል። ምክንያቱም ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጡ የሚያሳድጉት ልጅ እኩል አይደለም። እስር ልጅ አለማስተማሩንና ማደንዘዙን በሰሚራ ተረድታዋለች። እንዲህ ጫናው በከበደ መከራ ተፈትኖና ከስህተት ተምሮ በይቅርታ ከሥር ቤት መውጣቱን እሷ ብቻ ሳትሆን በእናቷ ጦስ የ16 ዓመት የማረሚያ ቤቱ ፍርደኛ ሆና ለመኖር የተገደደችው የያኔዋ ህፃን የአሁኗ ወጣት ሰሚራም በየዓመቱ ስትናፍቀውና በጉጉት ስትጠብቀው ኖራለች። ሆኖም ሕይወት አሁንም አስከፊ በሆነ መልኩ እየቀጠለ ነው።
የሌላኛዋ ታራሚ አስናቀች ሞገሴ ሕይወትም ከእነሰሚራ የተለየ አይደለም። ‹‹ልጄ እማ ግን ምን አድርገን ነው እሥር ቤት የገባነው?›› ሲል ዘወትር ይጠይቀኛል የምትለው የሕግ ታራሚ አስናቀች ሞገሴ ልጇ በማረሚያ ቤቱ የእሷን ፍርድ ጽዋ ለመቅመስ መገደዱን ታወሳለች። እንባ ባቆረዘዙ ዓይኖቿ ቃለ አብ ተስፋም እንደ እሷ የአራት ዓመት ከአምስት ወር ፍርደኛ ለመሆን መገደዱን ትናገራለች። እናቱ ህፃኑን ወደ ማረሚያ ቤቱ ይዛው የገባችው ከአንድ ባልደረባዋ ጋር የሚሰሩበት የመድሃኒት ስቶር ተዘርፎ ቁልፉ በእጃቸው ስለነበር በከባድ ዕምነት ማጉደል ሲፈረድባት ነበር። ህፃኑ ያኔ ሦስት ዓመቱ ሲሆን አሁን ደግሞ በማረሚያ ቤቱ የአምስት ዓመት ልደቱን አክብሯል።
አስናቀች እዚህ ልጅ መንከባከብና ማሳደግ እጅግ ከባድ መሆኑንም ታወሳለች። ቢሆንም ልጇን አብስላ እንድትመግብ ማረሚያ ቤቱ ስለፈቀደላት ደስተኛ መሆኗን የምትናገረው አስናቀች በወር የሚሰጣት ሁለት ሳሙና የእሷንና የልጇን ልብስ ለማጠብ አይበቃትም። ዳይፐር ያስፈልገዋል። ከቅርብ ዓመት ወዲህ ኑሮ በመወደዱ በየቀኑ ለእሷም ሆነ ለእሱ የሚመደበው የቁርስ፤ ምሳና ራት 22 ብር አንዳንዴ በ15 ቀን አንዳንዴ ደግሞ በስምንት ቀኑ ያልቅና ቆርሳ የምትሰጠው በማጣት በእጅጉ ትቸገራለች።
ልጇ ‹‹ግን ምን አድርገን ነው እሥር ቤት የገባነው?››የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ የሚያነሳውም ለዚህ ነው። ደግነቱ የማረሚያ ቤቱ አመራሮችም ሆኑ አባላቱ ይሄን በህፃናት የሚደርስ ለወላጆች አስቸጋሪ የሆነ ሰቆቃ ላፍታም በዝምታ የሚያልፍ አንጀት የላቸውም። ፈጥኖ ስለሚገባቸውና አሳምረው ስለሚረዱት ሁሉም ህፃናቱ ከመራባቸው በፊት መፍትሄ የሚሰጡ እንስፍስፎች ናቸው። አንዳንዶቹ ዘላቂ መፍትሄ እስኪፈለግ አባላቱ በየፊናቸው በማህበር በመደራጀት በማረሚያ ቤቱ ከከፈቱት ቦቦሊኖ፤ ቺፕስ፤ ዳቦ እንዲሁም ምሳና እራት ከየኪሳቸው በማውጣት እየገዙ በመመገብ እናቶችን ከጭንቀት ይገላግሏቸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከታራሚው ጋር በመቀናጀት ከውጭ ድጋፍ በማፈላለግ እነአስናቀችን እየደጎሟቸው ይገኛሉ።
ህፃናት ባላጠፉት ጥፋት በፍርድ ቤት ከእናት ጋር መቀጣታቸውን አጥብቄም እቃወማለሁ የምትለው አስናቀች መንግስት ለምን የነገ አገር ተረካቢ ህፃናትን በዚህ መልክ እንዲኖሩ ፈቀደ፤ ለምንስ ዳኞች ህፃናትን ወደዚህ ይልካሉ ስትልም በአግራሞት ትጠይቃለች። ምክንያቱም ነፍስ እያወቁ ሲመጡ በአእምሯቸው በርካታ ጥያቄዎች ሲያጭርባቸው፤ አስቀያሜ ስሜትም ሲፈጥርባቸው ይታያል ስትል የታዘበችውን ትናገራለች።
አንዲቱ ልጅ ‹‹አስኒ ግን እናቴ ምን ሆና ነው የታሰረችው?›› ብላ የጠየቀቻትን በምሳሌነት ታነሳለች። እንዳከለችው እዚህ የተወለዱ ልጆች አራትና አምስት ዓመት ሆኗቸው ሲወጡ ለእናቶች ብቻ ሳይሆን ለህፃናቱም የወደፊት ሕይወት በእጅጉ ይከብዳል።
በማረሚያ ቤቱ አድጋ ወደ ሰላም ህፃናት መንደር ማሳደጊያ የተላከች አንዲት ልጅ እናትየዋ ከማረሚያ ቤት ወጥታ ልታያት ስትል ሳታናግራት ጥላት መሄዷንም ለክብደቱ ማሳያ አድርጋ ታነሳለች። ይህች ልጅ በእናቷ ጦስ የተፈረደባትን የ10 ዓመት ፍርድ ጨርሳ ውሻና በግ ሳትለይ በማረሚያ ቤት ውስጥ በማደግ ዘንድሮ መውጣቷን ትናገራለች። እስር ቤት ለህፃናት አስቸጋሪ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ላይ በእናቶች ውሳኔ ሲወሰን ከልጅ ውጭ ቢወሰን ጥሩ ነው የሚል ምክር ትሰጣለች። ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤት ውሳኔን አልቀበልም ማለት ስለማይችል የሚቀበል መሆኑንም ታወሳለች። አንዳንድ ጊዜም ፍቃደኛ ከሆኑ እናቶች ጋር እየተደራደረም ለህፃናት ማሳደጊያዎች እየሰጠ ትምህርት እንዲማሩና በስርዓት ታንፀው እንዲያድጉ ከማድረግ ጀምሮ ሕይወታቸውን እየታደገላቸው መገኘቱን በእጅጉ ታደንቃለች።
‹‹ህፃናት በፍፁም ማረሚያ ቤትን ማየት የለባቸውም›› ይላሉ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር ዓለም ጥላሁን። ምክንያቱም ህፃናት ወደ ማረሚያ ቤቱ መጥተው እናቶቻቸው ወንጀል ሲነጋገሩ ከመስማት ውጭ ምንም መልካም ነገር የለምና ነው ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
ሆኖም አሁን ላይ 558 ታራሚ እናቶች በሚገኙበት በማረሚያ ቤቱ 28 ወንድና 22 ሴት በድምሩ 50 ህፃናት ይገኛሉ እናቶቻቸው ነፍሰ ጡር ሆነው እዛው ከወለዷቸው ውጭ አብዛኞቹን ህፃናት ከእናቶቻቸው ጋር ወደ ማረሚያ ቤቱ የላኳቸው ዳኞች ናቸው።
‹‹ዳኞች ኢንተርፖል ከኬኒያ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ካመጣት ሣራ ጋር የ14 ዓመት ልጇን ሰሚራንም የላከበት ማሳያ ነው። ሆኖም ይህችን ህፃን ዳኞች ወደ ማረሚያ ቤቱ ከመላክ ይልቅ ተነጋግረው በዛው ወደ ማሳደጊያ ሊልኳት ይችሉ ነበር። ማሳደጊያ ድርጅቶች ትዕዛዝ ቢሰጣቸው ይቀበላሉ።›› ይላሉ ምክትል ኮሚሽነሯ።
ኮሚሽነር ዓለም እንደሚናገሩትም አንድ እናት ሁለትና ሦስት አንዳንዴም እስከ አራት ልጅ ይዛ ወደ ማረሚያ ቤት የምትመጣበት አጋጣሚ አለ። ህፃናት ይዘው ወደ ማረሚያ ቤቱ ለሚገቡ እናቶች የራሱ ሕግና መመሪያ አለው። በሕጉ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናትን በማረሚያ ቤቱ ይዞ መግባትም ሆነ ማስቀመጥ እንደማይቻል በግልፅ ተደንግጓል። በርግጥ በፊት በፊት ከሁለት ዓመት በላይ የሆኑም ህፃናት ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚገቡበት አሰራር ነበር። አዲሱ ሕግና መመሪያ ከወጣ በኋላ ይሄ ቀርቷል። ይሁንና ፍርድ ቤቶች ዕድሜያቸው እስከ 10 ዓመት የደረሰ ህፃናትን ከእናቶቻቸው ጋር ይልካሉ። ማረሚያ ቤቱም ፍርድ ቤቶችን ላለመፃረር ይቀበላል። አንድ እናት 18 ዓመት ቢፈረድባት ህፃናትም ከእናታቸው ጋር 18 ዓመት ያለ ትምህርት እየተቀጡ ይቆያሉ።
እንደ ኮሚሽነር ዓለም ይሄ ማረሚያ ቤቱ እጅግ እየተቸገረበት ያለ አሰራር አሳሳቢም አሳዛኝም ነው። በመሆኑም ማረሚያ ቤቱ ዝም ብሎ እየተመለከተው አይደለም። የትምህርት ጊዚያቸው እንዳያልፍ ከእናቶቻቸው ጋር እየተነጋገረ ማዘር ትሬዛ፤ ሰላም የሕፃናት መንደርና ሌሎች የህፃናት ማሳደጊያዎች ይልኳቸዋል።
ይሁንና ኮሚሽነሯ እንደሚሉት አብዛኞቹ እናቶች በዚህ በኩል ፈቃደኛ አይደሉም። በፍፁም ልጆቻችን ለቤተሰብም ሆነ ለሕፃናት ማሳደጊያ መላክ አይፈልጉም። የእንዲህ ዓይነት ታራሚ እናቶችን አስተሳሰብ ለመቀየር ማረሚያ ቤቱ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ታራሚ አንዴ ልጇን ይዛ ከገባች በኋላ ለማሳደጊያም ሆነ ለቤተሰብ መስጠት አትፈልግም። ምክንያቱም ማረሚያ ቤቱ ለህፃናቱ እንክንካቤ ሲባል ምግብ አብስለው እንዲበሉ ያደርጋል። አንዳንዶቹ በልጃቸው ሰበብ ትኩስ ትኩስ ምግብ ስለሚበሉ ይሄን አጣለሁ በሚል ስጋት ልጃቸውን መስጠት አይፈልግም። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የይቅርታ ህግ ህጻናት ያላቸውን እናቶች ተጠቃሚ፣ ስለሚያደርግ በልጃችን ምክንያት በተሞክሮ እንፈታለን የሚል ምክንያት ስላላቸው ህጻናቱን በፍፁም መስጠት አይፈልጉም።
ለአብነትም የአንዲት ታራሚ ታሪክን ያነሳሉ። ልጅቱ የፊደል ራስጌና ግርጌን ሳትለይ በማረሚያ ቤቱ ከእናቷ ጋር ሆና ስድስት ዓመት ሞላት። ይሄኔም ማረሚያ ቤቱ መማር እንዳለባት እያሳሰበ ከእናትየው ጋር ተደራደረ። እናት በቀላሉ ፈቃደኛ ልትሆን አልቻለችም። ‹‹አስቡኝ አንዲት ልጅ ናት ያለችኝ። እኔ ከዚህ በኋላ ወጥቼ ልጅ አልወልድም፤ ዕድሜዬ ገፍቷል፤ እናም አንዲቷን ልጄን አጥቼ እንዴት ልሆን ነው›› በማለት የልጇን እድል ልታመክን የተቃረበች ሴት እንደነበረች ኮሚሽነሯ ይናገራሉ። ሆኖም ልጇን በየጊዜው በአመቻት ሁኔታ እንድታያት ቃል በመግባት እንደምንም አግባቧት። ልጅቱ ሰላም ህፃናት ማሳደጊያ ገባች።
የማረሚያ ቤቱ አመራሮች ህፃናት አገር ተረካቢ ናቸው በእናንተ ችግር ነው እዚህ የገቡት ቢያንስ መማር መቻል አለባቸው በማለት ከእናቶች ጋር ድርድር እያደረጉ ሌሎች ህፃናትንም ለማሳደጊያ ይሰጣሉ። አንዳንዴ እናትየው ድርጅቱ ሄዳ ልጇን እንድታይ ካልሆነ ልጅቷን ወደ ማረሚያ ቤት በማምጣት ከእናትየዋ ጋር ውላ እንድትመለስም ያደርጋሉ።
ያም ሆነ ይህ ግን በማረሚያ ቤት ሕይወት በዚህ መልኩ እየቀጠለ ነው። ህጻናቱም ባልሰሩት ወንጀል እየተቀጡ ፤ እንደእኩዮቻቸው ቦርቀው ሳያድጉ፤ ተምረው ለነገ ስንቅ ሳይዙ ጊዜ እንደዋዛ እያለፈ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም