የፖለቲካ ውጥንቅጥ፣ የኑሮ ውድነት፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ ስደት፣ መፈናቀልና ሌሎችም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች በምድራችን እየበዙ መጥተዋል። የሕይወት ትግሉ በርትቷል። የኑሮ ውጣ ውረዱ አይሏል። የእርስ በርስ ፉክክሩና ፍትጊያው ጨምሯል። ገንዘብ አልበረክት ብሏል። ፍቅርም እንደዛው። እነዚህና መሰል ስንክሳሮች ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው። ከመንገድም እያስቀሩ ነው።
አንዳንዴ የትግላችን፣ የጥረታችን፣ የልፋታችን ውጤት መና የቀረ የሚመስልበት ጊዜ አለ። ውጥናችን ውሃ አልቋጥር፣ ጠብ አልል ሲለን፣ መንገዱ ሁሉ ረዥም፣ በሮች ሁሉ ዝግ፣ ጩኸቱ ሁሉ ሰሚ አልባ ሲመስለን በመጨረሻ የምንወስደው መፍትሄ ነገር አለሙን ሁሉ መተውና መሸነፍ ይሆናል። ከዚህ በኋላ አበቃ ማለት እንጀምራለን። እንኳን እኛ ቀርቶ ሌሎች እንኳን እንዳይበረቱ ‹‹እባክህ እኛም ብለነው ብለነው አቅቶን ነው›› እያልን ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን።
ነገር ግን ሰው መልፋት፣ መትጋት፣ መታገልና መሮጥ ያለበት የት ነው? ሰው ተስፋ መቁረጥ ያለበት የት ደረጃ ሲደርስ ነው? የመንገዱ ማለቂያው የት ነው? ውጤቱን ዛሬ ያላየነው ነገ ሁሉ ውጤት አልባ ሆኖ ሊቆጠር ይችላልን? በታሰበው ጊዜ ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይችል ነገር ነው ማለት ነው? መንገዱስ እኛ የያዝነው ብቻ ነው? በሌላስ መንገድ ሊሞከር አይቻልምን? ለመሆኑ ከማቆምና ከመቀጠል የትኛው ይመረጣል? ከማቆም ምን ይገኛል? የሚሉትና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን መመለስ ይገባል።
ከተስፋ መቁረጥ በቀር የሚጓዝ ሰው ጊዜው ይረዝም ይሆናል እንጂ አንድ ቀን የሚፈልገው ቦታ ይደርሳል። የቆመ ሰው ግን እንኳንስ ወደሚፈልግበት ለመሄድ ይቅርና ወደተነሳበት ቦታም ተመልሶ አይደርስም። የሚታገል ሰው አንድ ቀን ያሸንፋል። የቆመ ሰው ግን ሳይማረክ እጁን ሰጥቷል። ደጋግሞ የሚያንኳኳ ሰው ከተኙት ሰዎች ውስጥ አንዱን መቀስቀሱ አይቀርም። ማንኳኳት ያቆመ ግን እንኳንስ ሊቀሰቅስ ቀርቶ እራሱም የተኛ ነው።
የሚሄድ መኪና ጋራዥ ይደርሳል። የቆመ መኪና ግን ባለበት ይወላልቃል። ለማሸነፍ ትልቁ መፍትሄ አቋምን መቀየር ሳይሆን መንገድን መቀየር ነው። የተለያዩ ነገሮችን መሞካከር ሳይሆን አንድን ነገር በተለያዩ መንገዶች መሞከር ነው። የተለያዩ ነገሮችን ማየት ሳይሆን አንድን ነገር በተለየ አንግል ለማየት መቻል ነው። ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ማመንታትን መቁረጥ መቻል ነው። የምታገኘውን ሞት ከመመኘት የማታገኘውን ሕይወት በሚገባ መኖር መቻል አለብህ።
ለዚህ አስረጂ የሚሆን አንድ ተረት እናንሳ፡-
ሁለት እንቁራሪቶች አንድ ላይ ሆነው እየተጓዙ ነበር። አንዷ ቀጭን ሌላኛዋ ወፍራም። እንዳጋጣሚ ሆኖ በገረወይና የተሞላ ወተት አገኙና ተንሰፍሰው ገቡበት። ገብተውም በገረወይና ውስጥ ያለውን ወተት እስኪበቃቸው ድረስ ጠጡ። ሲጠግቡ መውጣት ፈለጉ። ይሁንና ገረወይናው ውስጡ ያዳልጥ ነበርና መውጣት አልቻሉም። እግራቸውን ባንቀሳቀሱ ቁጥር ወተቱ እያዳለጠ እዛው ይመልሳቸዋል። ከገረወይናው ለመውጣት ከጠዋት እስከማታ ሲሞክሩ ውለው ደከማቸው። በዚህም ድካም እንጂ ትርፍ አላተረፉም።
‹‹በምን ቀን ነው እዚህ ወተት ውስጥ የገባነው›› እያሉ ቀናቸውን ይርግሙ ጀመር። የሚያማክሩት ሽማግሌ፤ የሚማክሩት ባለሙያ በአካባቢያቸው አልነበረም። ወደኋላ ተጉዘው የሰሟቸውንና ያዩትን ነገሮች ሁሉ አስታወሱ ነገር ግን ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነገር ማስታወስ አልቻሉም። ወደሰማይ ቢፀልዩ እንኳን ፀሎታቸው የተሰማ አልመስል አለ። አንዳች ፈጣን መልስ አላገኙምና በአካባቢያቸው የሚያልፉ ሰዎችም ሆኑ ሌሎች እንቁራሪቶች ድምፃቸውን ሰምተው ከማለፍ በቀር ዞር ብለው ሊያዩዋቸው አልፈቀዱም። አንዳዶቹም ከገረወይና ውስጥ የሚሰማው የእንቁራሪቶች ድምፅ ከተለመደው ውጭ ነው ብለው ለማሰብና ለመርዳት አልቻሉም።
ወፍራሟ እንቁራሪት ተስፋ ቆረጠች። ‹‹በቃ ከድካም በቀር ያተረፍነው ነገር የለም፤ ለመውጣት መታገሉን ማቆም አለብን›› አለች። ቀጭኗ እንቁራሪት ግን ‹‹የለም! ከተስፋ መቁረጥ የምናገኘው ምንም ነገር የለም ተቀምጦ ከመሞት እየታገሉ መሞት፤ ተሸንፎ ከመሞት እያሸነፉ መሞት፤ እጅ ሰጥቶ ከመሞት እጅን አሰርቶ መሞት፤ አልችልም ብሎ ከመሞት እችላለሁ ብሎ መሞት የተሻለ ነውና ተስፋ መቁረጥሽን አቁሚ›› አለቻት።
ወፍራሟ እንቁራሪትም ‹‹እስኪ ተመልከቺ ከጠዋት ጀምሮ ለፋን፤ የጠጣነው ወተት እንኳን እስኪጠፋ ድረስ ለፋን፤ ከሰማይም ሆነ ከምድር የደረሰልን አንዳች ሃይል የለም። የእኛም ድካም ውጤት አላመጣም። አንዳንድ ጊዜ የምናደርገው ሁሉ ቀልድ ይመስለኛል። ተምቦጫረቅን! ተምቦጫረቅን! ወይ በውሃ የሚቦጫረቁትን ልጆች አይነት ደስታ አላገኘን፤ ወይ ደግሞ ከዚህ ቦታ መውጣት አልቻልንም። ታዲያ የልፋታችን ዋጋ ምንድን ነው? እዚህ ቦታ መልፋታችንን እንኳን ያወቀለን የለም›› አለች።
ቀጭኗ እንቁራሪትም ‹‹የሚረዳን ብናገኝም እንኳን የምንጠቀመው እኛ፤ ለመውጣት የምናደርገውን ተጋድሎ ካላቋረጥን ብቻ ነው። ከልምድ መፍትሄውን የምናገኘው እኛ፤ ጥረታችንን ካላቋረጥን ብቻ ነው። አንድ ቀን ይህንን ችግር ልናሸንፍ የምንችለው እኛ እየጣርን ከቀጠልን ብቻ ነው›› ብላ መለሰችላት።
‹‹ባለፈው ጊዜ አታስታውሺም ቅቤ ውስጥ የገቡት ሶስት እንቁራሪቶች ምን ሆኑ?›› አለቻት ወፍራሟ እንቁራሪት። ይህን ስትጠይቃት ጊዜ ወፍራሟ እንቁራሪት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እያቋረጠች ነበር። ‹‹ለምን የተሸነፉትን ትጠቅሻቸዋለሽ? ከተሸነፉት መማር ያለብን እኮ ለምን ተሸነፉ የሚለውን እንጂ የጥረት መጨረሻው መሸነፍ አይደለም። ሽንፈት እኮ ትምህርት አያስፈልገውም። ሽንፈት እኮ ልምድ አያስፈልገውም። ሽንፈት እኮ እውቀት አያስፈልገውም። ሽንፈት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ብቻ ይበቃዋል። ለሽንፈት ምሳሌ መጥቀስ አያስፈልግም። ሽንፈት ማለት በቀላሉ የሚደረስበት ነገር ነው። ሳትለፊ የምታገኚው ነገር ነው። ምሳሌ፣ አርአያ፣ ልምድ፣ እውቀት፣ ጥበብ የሚያስፈልገው ድል ብቻ ነው። ስኬት ብቻ ነው። እርሱ በቀላሉ ስለማይገኝ ካገኙት ሰው ልምድና ጥበብ መቅሰም ያስፈልጋል›› ብላ ነገረቻት።
በዚህ ጊዜ ቀጭኗ እንቁራሪት ወተቱን በእግሯቿ መምታት አላቆመችም ነበር። እግሯ እየዛለ ወገቧ እየከዳት ቢመጣም ከወተቱ ላይ ተደግፋ ለመስፈንጠር ጥረቷን አላቆመችም። ወፍራሟ እንቁራሪት ቀጥላም ‹‹ይኸው አንቺ በመልፋት ላይ ነሽ ግን ምን አመጣሽ? ቢያንስ ተስፋ ቆርጬ ከድካሜ እፎይ ያልኩት እኔ አልሻልም?›› አለቻት። ‹‹ፈፅሞ አትሻይም›› አለቻት ቀጭኗ። ‹‹እንዴት?›› አለቻት ወፍራሟ፤ ቀጭኗም ‹‹ቢያንስ እኔ ተስፋ አለኝ። አንቺ ግን የለሽም። እኔ በጥረት ውስጥ ደስታን አገኛለሁ አንቺ ግን በሀዘን ውስጥ ነሽ። ጥረት እኮ ባይሳካ እንኳን ደስታን ያጎናፅፋል። ከቁዘማና ከድብርት ነፃ ያወጣል። የሚጥር ስለነገ ያቆመ ስለትላንት ያስባል። የሚጥር ስለኑሮው ያቆመ ስለሞት ያስባል። በሩጫ ዓለም በመጀመሪያው ዙሮች ቀዳሚውም መጨረሻውም እኩል ናቸው። እንደውም አንዳንዴ ተሸናፊው ከአሸናፊው የተሻለ መስሎ የሚታይበት ጊዜ አለ። ግን ደወል ይደወላል። ያን ጊዜ አሸናፊውም ተሸናፊውም ይለያል።
‹‹በይ አንቺ እቴ! አይሰለችሽ ቀጥይ እኔ ግን በቃኝ። አንዳች ነገር ጠብ ላይል ምን አለፋኝ! ምን አደከመኝ!›› አለቻት ወፍራሟ እንቁራሪት። ቀጭኗም ቀጠል አድርጋ ‹‹ቢያንስ ቢያንስ ደክሞሽ ሳታስቢው መሞት እየቻልሽ እንዴት አይንሽ እያየ ሰጥመሽ ትሞቻለሽ›› አለቻት። ወፍራሟ ግን አቆመች። ቀስ በቀስ ወደታች መስመጥ ጀመረች። ቀጭኗ እንቁራሪት ልትረዳት ሞክራ ነበር። ነገር ግን ውፍራሟ ምንም ጥረት ስላላደረገች የእርሷ እርዳታ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም። የሌላ ሰው እገዛ ውጤት የሚያመጣው የራስ ጥረት ካለ ብቻ ነው። አፉን ያልከፈተ ሰው ማጉረስ፤ ላለተነፈሰውም ሰው ቦነስ መስጠት አይቻልም።
ወፍራሟ እንቁራሪት ቀስ በቀስ ወደወተቱ ስር ተነሸራታ ገብታ ሰጥማ ሞተች። ቀጭኗ እንቁራሪት ግን አሁንም ጥረቷን አላቋረጠችም በእግሯ አንዳች ነገር ለመቆንጠጥ እየሞከረች ትታገላለች። አንዳንድ ጊዜ የወፍራሟ ጓደኛዋ እንቁራሪት መፍትሄ ይሻላል እያለች ታስባለች። ግን ደግሞ የጓደኛዋን መሞትና የእርሷን መኖር ስታይና እንዲዚህ ማሰቧን ትቃወማለች። አንዳንድ ጊዜ ቆም ብላ ምን ሊመጣ እንደሚችል ታስባለች። ግን ምንም ነገር ታጣበታለች። ያን ጊዜ የምታደርገው ነገር ትክክል ይሁን ስህተት ማረጋገጥ ትቸገራለች።
በእርሷና በጓደኛዋ መካከል ያለው ልዩነት የመሞቻው ጊዜ ይሆን ብላም ታስባለች። እንዲህ እያሰበች እግሯንም እያወናጨፈች ሌሊቱን በድካም አሳለፈች። እናም ነጋ። ከነጋም በኋላ እግሯን ማወናጨፏን መስፈንጠሪያዋን መፈለጓን ተያያዘችው። እኩለ ቀን ድረስ ምን የተፈጠረ አዲስ ነገር አልነበረም። እኩለ ቀኑ አለፍ እንዳለ እግሮቿን ስታወናጭፍ አንድ ነገር ነካች። ልቧ በደስታ ቀጥ ሊል ነበር። ‹‹ከየት ተገኘ? እስካሁን ድረስ እንዴት አላገኘሁትም›› አለች። ለካስ ላለፉት ሰዓታት ወተቱን በእግሯ ስትመታው ወተቱ ተንጦ ተንጦ ሄዶ ቅቤ ሆኗል። ያን ጊዜ እግሯ የሚረግጠው ነገር አገኘ። ቅቤውን ረግጣ ከገረወይናው ውስጥ ዘላ ወጣች። ‹‹ይብላኝ ተስፋ ቆርጦ ለሚያቆም እንጂ የጣረ አንዳች ነገር መውጪያ ያገኛል›› አለች ምድር ላይ ስትደርስ።
ይህ ተረት ብዙ ያስተምራል። ከመቆም ምንም አይገኝም። በቃኝ ብሎ ተስፋ ከመቁረጥ አንዳች ትርፍ የለም። ነገር ግን በጥረት ውስጥ ደስታና ጥንካሬ አለ። በጥረት ውስጥ ተስፋና አሸናፊነት አለ። ትጋት ከቁዘማና ከድብርት ነፃ ያወጣል። የሚጥር ስለነገ ያቆመ ስለትላንት ያስባል። የሚጥር ስለኑሮው ያቆመ ስለሞት ያስባል።
ዛሬ ላይ የሚታዩ ነገሮች ሰዎችን ለጊዜው ተስፋ ሊያስቆርጡ ይችላሉ። የኑሮው ሁኔታ፣ ውጣውረዱ፣ እንግልቱ ሊያሰለች ይችላል። እዛም እዚም የሚደመጡ የሰዎች ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀልና ሰቆቃ ያሳምማሉ። ሰላምና መረጋጋት መጥፋቱም እጅግ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ነገር ግን ከዛሬ ነገ ይሻላልና የነገውን ጥሩ ለማድረግ ዛሬ ላይ ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል። ተስፋ ከመቁረጥ ተስፋ ማድረግ ይሻላልና።
እናም ወዳጄ ብትወድቅ ብተከፋም ያለኸውና የምትኖርበት እዚቹ ምድር ላይ ነው። ስለዚህ ተፍጨርጨርባት፣ ስራባት፣ እስከ መጨረሻው ጣር። መቼም መብቴ ብለህ ወደህ መርጠህ ወደዚች ምድር አልመጣህ። ምድሯም አንተን ለማኖር ምንም አልጠበባትም። ስለዚህ ወደዚች ምድር እስከመጣህ ድረስ የመጨረሻውን የሞት ፅዋ እስክትጎነጭ ድረስ በምድሯ ላይ ስራ። በተስፋ ህይወትህን አድስ ፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም