በወጣትነት ዕድሜው ድህነትን ለማሸነፍ ከላይ ታች ብሏል። የቤተሰቦቹ የገቢ መጠን የሚያኩራራ ስላልነበር የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ ነበረበት። የተለያዩ ፍላጎቶቹን ለማሟላትም ወደ ሥራ ዓለም የገባው በአፍላነት እድሜው ነበር። ስኬትን አልሞ የተነሳው ይህ ወጣት ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር በእግሩ ተጉዞ ሠርቷል፤ ተምሯል። ብሩህና ፈጣን አዕምሮውን ተጠቅሞ ኑሮን ለማሸነፍ ገና በማለዳ የተነቃቃው ወጣት ዛሬ ረፋዱ ላይ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል። አመሻሹም ያማረና የሰመረ እንደሚሆን ዕምነቱ የጸና ነው።
‹‹ወጣትነት ትኩስ ኃይል ነው›› እንደሚባለው ትኩስ ኃይሉን አሟጦ በመጠቀም ውጤታማ መሆን የቻለው የዛሬው የስኬት እንግዳችን ወጣት ዳግም ጥበቡ ይባላል። በአዳማ ከተማ የሚገኘው የናፍሌት ሆቴል ባለቤት ነው። ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ባሌ ሮቤ ከተማ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያው በባሌ ሮቤ ነው የተከታተለው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዳማ ከተማ በመከታተል በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል። ተማሪም ሆኖ ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችለውን ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ነበር የሚያሰላስለው።
ውጤታማ ተማሪ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት ዳግም፤ በወቅቱም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለ ይናገራል።እርሱ ግን ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትን ምርጫው አላደረገም። ከዚያ ይልቅ በፍጥነት ሥራ ይዞ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ በመቀየስ ዕይታውን ወደ አላጌ የግብርና ኮሌጅ አደረገ። ኮሌጁ ለሶስት ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ወደ ሥራ የሚያሰማራ በመሆኑ ምርጫው ትክክለኛ ነበር። በአላጌ የግብርና ኮሌጅ ለሶስት ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሎ እንዳጠናቀቀ የሀሳቡ ተሳክቶለት ደመወዝተኛ መሆን ችሏል። በወቅቱም በቦስት ወረዳ በአንድ የገጠር ቀበሌ የልማት ጣቢያ ውስጥ ሥራ መጀመሩንና የወር ደመወዙም 530 ብር እንደነበር ያስታውሳል።
‹‹ከደሃ ቤተሰብ የተገኘው እንደመሆኔ የነበረኝ አማራጭ በቶሎ ገንዘብ ማግኘት ቢሆንም የማገኘው ገንዘብ ሕይወት የማይለውጥ እንደሆነ በመረዳቴ ብዙ እንድሞክር አድርጎኛል›› የሚለው ወጣት ዳግም፤ አዋጭ የሆኑ የንግድ ሥራዎችን በማሰብ ያወጣና ያወርድ እንደነበርም ያስታውሳል። ከማሰብ ባለፈም ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሉ ኑሮን ለማሻሻልና ሕይወትን ለመለወጥ መማር የግድ መሆኑን በማመን ከሥራ ውጭ ቅዳሜና እሑድ ረጅም መንገድ በእግሩ ተጉዞ ለመማር ያደረገውን ጥረትም አጫውቶናል።
በወር ደመወዝ ሕይወትን ከመምራት በተጨማሪ የትምህርት ወጪ ሲጨመርበት ብዙ ርቀት መጓዝ አላስቻለውም። ሌሎች አማራጮችን ከመፈለግ ያልተቆጠበው ወጣት ዳግም፤ ለስኬት ጉዞው መሰረት የጣለ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረለት። አዳማ ከተማ የረር ፋብሪካ አካባቢ የተለጠፈው ክበብ እናከራያለን የሚል ማስታወቂያ ነበር አጋጣሚውን የፈጠረው። ማስታወቂያውን ተከትሎ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማወቅና ለመረዳት ጊዜ አላጠፋም። በወቅቱ ሥራውን መጀመር የሚያስችል ምንም አይነት ግብዓትና መነሻ ካፒታል ባይኖረውም እድሉን ማሳለፍ እንዳልፈለገ ያስታውሳል።
ለኪራይ የተዘጋጀው ክበብ ማብሰያና መመገቢያ ቁሳቁሶችን አሟልቷል። ይሁንና በወር ሁለት ሺ ብር ኪራይ ይጠይቃል። ለኪራይና ለሥራ ማንቀሳቀሻ የሚሆን በቂ የሆነ ገንዘብ እንደሌለው ቢያውቅም ተነሳሽነቱና ፍላጎቱ ስለነበረው አማራጭ በማፈላለግ በክበቡ ለመሥራት ወሰነ። ለክበቡ የተጠየቀውን ወርሃዊ ኪራይ በግማሽ ከፍሎ ቀሪውን ደግሞ እየሠራ መክፈል እንዲችል ትብብር በመጠየቅ ነበር ችግሩን ለመፍታት የሞከረው።
ወደ ሥራው በገባ ጊዜ ታዲያ ከክበቡ ኪራይ በበለጠ ግብዓት አሟልቶ ምግብ አብስሎ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ትልቁ ፈተና እንደነበር ያስታውሳል። ማንኛውም ችግር መውጫ ቀደዳ ያለው መሆኑን የሚያምነው ወጣት ዳግም፤ ለዚህም መላ መዘየድ እንዳለበት አመነ። በመሆኑም ከክበቡ አጠገብ የነበረ የህግ ኢንስቲትዩት ኮሌጅን እንደ ወርቃማ ዕድል ተጠቅሞ የአድራሻ መረጃ የያዘ (ቢዝነስ ካርድ) በማዘጋጀት ለተማሪዎቹ በተነ። መዝገብ በማዘጋጀትም ከእያንዳንዱ ተማሪ መቶ ብር በድምሩ 30 ሺ ብር ሰብስቦ በብድር ሊመግባቸው ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ወጣት ዳግም፤ የቢዝነስ ሥራውን በዚህ መልኩ ከሻይ ክበብ እንደጀመረ አጫውቶናል።
ሥራውን በጀመረበት ወቅትም ሌላ ወርቃማ ዕድል መጠቀም እንደቻለ ያጫወተን ወጣት ዳግም፤ በወቅቱ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ከመንግሥት በሚያገኙት ድጋፍ ይሠሩ ነበር። ወጣት ዳግምም የዚሁ ወርቃማ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ሥራውን ማሳለጥ ችሏል። በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅቶ ባገኘው ፈቃድ ‹‹ፈለ ጅሬኛ›› በሚል መጠሪያ አነስተኛ ምግብ ቤት ከፍቷል። ‹‹ፈለ ጅሬኛ›› የሚለው የኦሮሚኛ ቃል ፍቺ የኑሮ መፍትሔ የሚል ሲሆን፤ መጠሪያውንም ያገኘው የቢዝነስ አጀማመሩን ከሚያውቁት ደንበኞቹ እንደሆነ ነው የሚናገረው።
መንግሥት በሰጠው አራት በአራት በሆነች ኮንቲነር ውስጥ ወጣት ዳግም እራሱ እያበሰለና እያስተናገደ የምግብ ሥራውን አጣፍጦና አቀላጥፎ መሥራት በመቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን ችሏል። ከኮንቲነር በተጨማሪም በተለያዩ የመንግሥት የስብሰባ አዳራሾች የሻይ ቡና አገልግሎት በመስጠት ሥራውን እያሰፋ በመሄድ ከጥቃቅን ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ተሸጋግሯል።
ወጣቱ፤ በ500 ብር መነሻ ካፒታል እንዲሁም በዕውቀት፣ በድፍረት፣ ከፍተኛ በሆነ ውስጣዊ ፍላጎትና ትጋት የጀመረው ቢዝነስ ወደ ትላልቅ ሆቴሎች ለመሸጋገርም አላዳገተውም። እናም በአዳማ ከተማ በተለያየ ምክንያት ሥራ ያቆሙ ትላልቅ ሆቴሎችን በመከራየት ሥራውን ማስፋፋት የቻለ ሲሆን፤ በዚህም ናፍሌት ሆቴል መወለድ ችሏል።
ናፍሌት ሆቴልን ከመገንባቱ አስቀድሞ በተለያየ ምክንያት የተዘጉ ሆቴሎችን በኪራይ ወስዶ የመሥራት ሃሳብ የመጣለት ወጣት ዳግም፤ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ሁለት ትላልቅ ሆቴሎችን በመቶ ሃያ ሺ ብር እና በሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ተከራይቶ ሠርቷል። በዚህም የሆቴል ሥራውን ከማስፋፋት ባለፈ ሥራውን በጥልቀት የማወቅና ልምድ የመቅሰም አጋጣሚን ፈጥሮለታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞቹን ቁጥርም እያበራከተ ለመንግሥትና ለግል ድርጅቶች ቢዝነስ ካርዱን አሰራጭቶ በማስተዋወቅ አድማሱን አስፍቷል።
በሆቴል ኢንዱስትሪው እራሱን በሚገባ ያስተዋወቀው ወጣት ዳግም፤ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ቅንጡ የሆነውን ናፍሌት ሆቴል አዳማ ከተማ ላይ ገንብቷል። በአንድ ሺ 600 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈውና ሰባት ፎቆችን የያዘው ናፍሌት ሆቴል ለግንባታ ብቻ ሰባት ዓመታትን የፈጀበት መሆኑንም አጫውቶናል።
ሆቴሉ ደረጃቸውን የጠበቁ 38 ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በተለይም ለከፍተኛ ባለስልጣናትና ለአገር መሪዎች ቅንጡ ማረፊያ መሆን የሚችሉ ናቸው። ከመኝታ ክፍሎቹ መካከልም ሶስቱ የተለዩና ከፍተኛ ደህንነት ባላቸው መሳሪያዎች የሚጠበቁና በአይነታቸውም የተለዩ ናቸው። አዳማ ከተማ በኮንፍረንስ ቱሪዝም የምትታወቅ እንደመሆኑ ናፍሌት ሆቴልም ከሚሰጣቸው የሆቴል አገልግሎቶች መካከል ዋነኛው የኮንፍረንስ ቱሪዝምን መሰረት ያደረገ ነው። በዚህም በሆቴሉ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ዋና አዳራሽ በተጨማሪ ሰባት የስብሰባ አዳራሾችን ይዟል። አዳራሾቹም በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ከመሆናቸው በላይ እያንዳንዱ የስብሰባ አዳራሽ በድረገጽ (ኦንላይን) የሚገናኙበት ቴክኖሎጂም ተዘርግቶላቸዋል። በተጨማሪም በመሰብሰቢያ አዳራሾች ውስጥ ና ፕሮፌሽናል የሆኑ ዘመናዊ ካሜራዎች የተገጠሙ በመሆኑ ለጋዜጠኞች ምቹ እንደሆነ ወጣት ዳግም አጫውቶናል።
በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በትኩረት ለመሳተፍ እየሠራ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ዳግም፤ ናፍሌት ሆቴል በፍራንቻይዝ የንግድ ስምምነት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሆቴሉ ሥራ እንዲጀምር የማድረግ ሃሳብም አለው። ለዚህ የሆቴሉ መስተንግዶና አገልግሎት ከሌሎች መሰል የንግድ ዘርፎች የተለየ ሆኖ እንዲታወቅ የራሱን ባህል መፍጠር ችሏል።
‹‹ወደ ሆቴል ቢዝነስ ያመጣኝ ችግር ነው›› የሚለው ወጣት ዳግም፤ ድህነት የሚመጣው ካለመስራት ነው ብሎም ያምናል። ለዚህም ታዲያ ሰርተን መለወጥ የምንችልባት በተፈጥሮ የታደለች ውብ አገር ያለን ህዝቦች ነን፤ ዳቦ መሆን የሚችል አፈርና ከመልከአ ምድሩ ጋር የተስማማ የአየር ጸባይ ያለን በመሆኑ ሰርተን መለወጥና ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል። ‹‹ሁሌም ቢሆን እችላለሁ በሚል ስሜት ካለን ከትንሹ ነገር መነሳትና ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚለው ወጣት ዳግም፤ እርሱ ትንሽ ከተባለው ጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ በመሥራቱ ብዙ እንደተማረ ነው የሚናገረው።
ጥቃቅንና አነስተኛ የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ቢችልም፤ በውስጡ በርካታ ትሩፋቶችን አግኝቻለሁ በተለይም በጋራ መሥራት ትልቅ ቦታ ለመድረስ የሚያስችል አቅም እንዳለውና ከጥቃቅንና አነስተኛ ማትረፍ እንደቻለ ያነሳው ወጣት ዳግም፤ ‹‹እንቁላል ከሌለ ዶሮ እንደማይኖር ሁሉ፤ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮች ከሌሉ ትላልቅ የሚባሉ ነገሮች አይኖሩም›› በማለት ከዘርፉ ያገኘውን ጠቀሜታ አስረድቷል።
ናፍሌት ሆቴል በአሁን ወቅት 150 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በቀጣይም ለ15 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠርና ፔሮል ላይ ሲፈርሙ የማየት ሕልም እንዳለው ወጣት ዳግም አጫውቶናል። በተለይም ሆቴሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ከፍ በማድረግ በራሱ ባህልና ስታንዳርድ ቀዳሚና ተጠቃሽ ሆቴል እንዲሆን እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ይህንን ለማሳካትም በርትቶና ጠንክሮ መሥራት ብቻ በቂ ነው። ናፍሌት ሆቴልን በተለያዩ ከተሞች ከማስፋት ባለፈ በአፍሪካ ጭምር በሆቴል ቱሪዝም ተደራሽ የመሆን ዕቅድ ያለው እንደሆነም ተናግሯል።
ብዙ ሰዎች ባላቸው ነገር የሚረኩ በመሆናቸው ለላቀ ውጤት ሲተጉ አይታይም የሚለው ወጣት ዳግም፤ እርሱ ግን ደሃ ከሆነው አርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘ መሆኑን ደጋግሞ ለራሱ በመንገር ድህነትን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ይናገራል። በጥረቱም ዛሬ ከደረሰበት ስኬት ደርሷል። ድህነት በሥራ ይወገዳል ብሎ በማመን ሌት ተቀን የሚሠራ በመሆኑም ዛሬ ከደረሰበት የስኬት ከፍታ በላይ ነገ ከፍ እንደሚል በጽኑ ያምናል።
ከ530 ብር ደመወዝ ተነስቶ ዛሬ በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በመሳተፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል ባለቤት መሆን የቻለው ወጣት ዳግም፤ ቀድሞውኑ ከድህነት ጋር ተስማምቶ መኖርን አልፈቀደም። ከዛ ይልቅ ድህነትን ድል መንሳት የሚቻለው በሥራ መሆኑን አምኖ የወጣትነት ትኩስ አቅሙን አሟጦ ተጠቅሟል። ሙሉ ጊዜውንም ለሥራና ሥራ ብቻ አውሏል። በዚህም ውጤታማ መሆን ችሏል። ወጣቶችም ከዚህ ብዙ መማር ይችላሉ የሚለው ወጣት ዳግም፤ ‹‹ወጣቶች ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ብቁና ንቁ መሆናቸውን አውቀውና ተረድተው እችላለሁ በሚል ስሜት ከአነስተኛ ሥራ እንዲጀምሩ መክሯል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም