ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ የምሁራን ሚና የማይተካ ነው። ምሁራን ለዘመናት ያካበቱት ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም የጨለመውን በማብራት፤ የጎበጠውን በማቃናት፤ የተበላሸውን በማስተካከል ሀገርና ሕዝብን ወደ ተቃናው መንገድ የመም ራት ኃላፊነት አለ ባቸው።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በተደራራቢ ችግሮች ለሚፈተኑና አዲስ የብልጽግና መንገድን ለሚሹ ሀገራት ምሁራን መልካም ተምሳሌት ሆነው መጪውን ጊዜ ማሳመር ይችላሉ። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ድንቅ ልጆቿ የምትፈልገውም ሸክሟን የሚያቀሉላትና ችግሮቿን የሚጋሩላትን የመፍትሄ ሃሳቦችን ነው።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች፤ በታሪክ የበለጸገች፤ በጀግንነቷ የተመሰገነች፤ በአብሮ መኖር ዕሴቷ የታወቀች የነጻነት ሀገር ብትሆንም በዚያው ልክ የርስ በርስ ጦርነት የማያጣት፤ በተለያዩ ጉዳዮች የምትታመስ፤ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም ተስኗት በድህነት አረንቋ የምትናጥና የሀብታም ድሃ ሆና የኖረች ሀገር ነች። ስለዚህም በሁለት ተቃርኖ መሃል የምትገኘው ሀገር ከታቃርኖዋ ገላግሎ አዲስ የእድገት ጎዳና መጓዝ ትፈልጋለች። ይህንን አዲስ ጎዳና በማመላከት ረገድ ደግሞ ምሁራንን የሚስተካከል የለም።
ምሁራን በዕለት ተዕለት ስራቸው ተማሪዎችን ከማነጽ ባሻገር ሀገር የተጋረጠባትን ችግር እንድትሻገር መፍትሄ በማመላከት ጭምር የማይተካ ምሁራዊ ሚና አላቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ወቅት በተፈራረቁባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ትከሻዋ የዛለ፤ ወገቧ የጎበጠ በመሆኑ አለሁልሽ የሚሏት የተማሩ ከልጆቿን የምትሻበት ወቅት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ የተጋረጠባት ችግር ከኢኮኖሚ አልፎ የሉዓላዊነት ተግዳሮት መሆኑንም መረዳት ከምሁራን የተሰወረ አይደለም።
ኢትዮጵያ በተዛባ ትርክት ከአንድነት ይልቅ ወደ ልዩነት ስታመራ ቆይታለች። ከአብሮ መኖር ይልቅ ልዩነት፤ ከመደማመጥ መጯጯህን፤ ከጋራ ብልጽግና ይልቅ ጥሎ ማለፍ ፤ ከእውነት ይልቅ ውሸት ባህል እንዲሆን ታቅዶ ተሰርቶባታል። ይህ መጥፎ ባህል ደግሞ ድህነትና ጉስቁልናን ከማስፋፋቱም ባሻገር እንደ ሀገር አብሮ ለመዝለቅ እንቅፋት መሆኑ አልቀርም። ስለዚህም ከምሁራን እነዚህ ለዓመታት የተዘሩ እሾክና አሜካላዎች የሚነቀሉበትንና መጪው ትውልድም በተረጋጋ ሀገር ውስጥ እንዲኖር መፍትሄ ማመላከት ይጠበቃል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት ውስጥ አልፋለች። በጦርነቱ ምክንያትም በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። የሀገር ገጽታም ጎድፏል። ስለሆነም ምሁራን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የተጀመረውም ሀገራዊ ምክክክር ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃንና በግብረ አበሮቻቸው ሲጎድፍ የቆየውን የኢትዮጵያን ገጽታ የማስተካከልና ኢትዮጵያ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች ሀገር መሆኗን ማሳየትም የምሁራን አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምሁራንን አስተዋጽኦ የምትፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። ስለዚህም ምሁራን ያላቸውን ሚና በመረዳት ለሀገር ዕድገት፣ ሉዓላዊነት እና ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ ይገባል። በተለይም እዚህም እዚያም የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኙና የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ፍሬ እንዲያፈሩ በማስቻል ረገድ ምሁራን ሀገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም