በዴሞክራሲያዊ ስርአት የመንግስት ስልጣን ምንጭና ባለቤት ህዝብ ነው። በዚህም ምክንያት የስልጣን መንበሩን የያዘው መንግስት የህዝብ አገልጋይ ነው ተብሎ ይታሰባል። ዲሞክራሲ የህዝብ፣ በህዝብ እና ለህዝብ የቆመ ስርአት (a government of the people, by the people and for the people) ነው ሲባል ይህንኑ እውነታ የሚያንጸባርቅ ነው። በዲሞክራሲ ስርአት የመንግስት ህልውና በህዝብ ፍላጎትና ምርጫ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የህዝቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታትና ጥያቄዎቹን መመለስ ይጠበቅበታል።
በዲሞክራሲ ስርአት የመንግስት ጥንካሬና ውጤታማነት ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በምርጫ ወቅት በተገባው ቃል መሰረት ትክክለኛ የህዝብን ጥያቄና ፍላጎት በቅንነትና በታማኝነት መመለስ መቻሉ ነው። ይህ ደግሞ ህዝብ በመንግስት ላይ የሚኖረው እምነት ከፍ እንዲል ከማድረጉ በዘለለ በህዝብና በመንግስት መካከል የተሻለ መቀራረብ እና የሰመረ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ከዚህ በተቃራኒው በህዝብ ፈቃድ ወደ ስልጣን የመጡ ተመራጮች ለህዝብ የገቡትን ቃል ችላ በማለት ከህዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲሰሩ መገኘታቸው የተለመደ ነው። ይህ ሁኔታ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ብሎም ድጋፍ እንዲነፈገው ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል እንደ አንዱ ይጠቀሳል። “የመንግስት ተአማኒነት” ሲባል ዜጎች በመንግስት ፤ በመንግስት ተቋማትና መዋቅሮች፣ መንግስት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ላይ እንዲሁም በየተዋረዱ ያሉ አመራሮች ለህዝብ የገቡትን ቃል መጠበቅ በቻሉበት ደረጃ ፤ በብቃታቸው፤ በሃቀኝነታቸውና በታማኝነታቸው ላይ ህዝቡ ያለው ዕምነት ማለት ነው።
በሌላ አነጋገር መንግስት በአዋቀራቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መዋቅሮች አማካኝነት በስልጣን ላይ ያሉት አመራሮች/ባለስልጣናት በሚሰጡት አገልግሎት ልክ ህዝቡ የሚሰጠው የዕውቅና ሰርተፊኬት ወይም በኛው አማርኛ ‹ቅቡልነት› ነው ማለት ይቻላል።
ዜጎች በጥቅል መንግስት በሚባለው አካል ላይ ካላቸው አመኔታ በተጨማሪ ለልዩ ልዩ መንግስታዊ ተቋማትና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አመራሮች የተለያየ አመኔታና ዕይታ ሊኖራቸው ይችላል። በሌላ አነጋገር በጥቅሉ በመንግስት ላይ ካላቸው አመኔታ በተለየ በህግ አውጭው ፤ በህግ ተርጓሚው፤ በመከላከያውና በፖሊስ እንዲሁም በሌሎች የህግ አስፈጻሚ አካላት… ላይ የተለያየ እምነትና እይታ ሊኖራቸው ይችላል ማለት ነው።
ዜጎች በመንግስት ላይ የሚጥሉት የአመኔታ መጠን እንደ የሀገሩ የመንግስት ስርአት ይለያያል። ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ባሉ የፕሬዝዳንታዊ መንግስታዊ ስርአትን በሚከተሉና ፕሬዝደንቱ በቀጥታ በህዝብ በሚመረጥበት ሀገር በግል በፕሬዝደንቱ ላይ የሚኖር የህዝብ እምነት በአጠቃላይ ለአገዛዙ ተቀባይነት ማግኘት ወሳኝ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ አለ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፓርላሜንታዊ ስርአትን በሚከተሉ ሀገራት ደግሞ መሪው ለስልጣን የሚበቃው በቀጥታ በህዝብ ተመርጦ ባለመሆኑ በመሪው ላይ የሚኖር አመኔታ በገዢው ፓርቲ፣ በአስፈጻሚውና በህግ ተርጓሚው ላይ ለሚኖረው አመኔታ ወሳኝነት ላይኖረው ይችላል።
የህዝብ አመኔታ ለአንድ ፖለቲካዊ ስርአት ቅቡልነትና ቀጣይ ህልውና ወሳኝ ጉዳይ ነው። የህዝብ ተሳትፎ የሌለበትና ድምጹ የማይሰማበት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው የውክልና ዲሞክራሲ የህዝብን አመኔታና ቅቡልነት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም የህዝብ አመኔታ ማሽቆልቆል የውክልና ዴሞክራሲን እውን መሆን የሚገዳደር ነው። ምክንያቱም የዲሞክራሲ ሰርአት/ ተቋማት ቅቡልነትና ህልውና ህዝቡ ባለው አመኔታ ላይ ስለሚመሰረት ነው።
ህዝብ በመንግስት እና በተቋማቶቹ ላይ አመኔታውን ሲጥል የሚወጡ ፖሊሲዎችንና የልማት እቅዶችን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። እንዲሁም መንግስት ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪዎች ያላቸው ተገዥነት ይጨምራል። ለተፈጻሚነታቸውም የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ በማድረግ በኩል ያለው አበርክቶ የላቀ ነው።
ከዚህ የተነሳም የህዘብ አመኔታ በአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ ቁልፍ ነገር ነው። ስለሆነም የመንግስት ፖሊሲ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከቻለ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲጨምር ያደርጋል። በሌላ በኩል መንግስት ያወጣውን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከተሳነው ፖሊሲው የዜጎችን አመኔታ እንዳላገኘ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
የህዝብ አመኔታ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃትና ማደግ ያለው ድርሻም ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ አኳያ የህዝብ አመኔታ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ያለ ስጋት ወደ ስራ እንዲሰማሩ፣ በርካታ አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ እና የተሳለጠ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል። በተቃራኒው የህዝብ እምነት ማጣት ከላይ የተዘረዘሩት ጠቀሜታዎች እንዳይኖሩ በማድረግ ሀገርና ህዝብን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። ይሄውም በስራ ላይ ያሉ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ለማክበር እና ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ካለመሆን ጀምሮ የብሔራዊ ስጋት ምንጭ እስከ መሆን የሚደርስ አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚያስረዱት በተወሰነ ደረጃ ወይም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የህዝበ እምነት ማጣት ትልቅ ችግር ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም የአምባገነን አገዛዝ ባለበትም ሆነ በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ ዜጎች የገዛ መንግስታቸውን መጠራጠራቸው የተለመደና ተፈጥሯዊ በመሆኑ ነው። በዛው ልክ የመንግስት ሹማምንት የቱንም ያህል ቅንና መልካም ሰዎች ቢሆኑም በማንኛውም ወቅት ለህዝብ የገቡትን ቃል ሊዘነጉ፣ ችላ ሊሉና ከህዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲፈጽሙ መገኘታቸው እንግዳ ነገር አይደለም።
አደጋ የሚሆነው ግን ችግሩ መከሰቱ ሳይሆን መንግስት ለህዝብ እምነት ማጣትና ለቅሬታው መከሰት መንስኤ ለሆኑ ጉዳዮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በተለመደው አካሄድ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን የሚመርጥ ከሆነ ነው። በአንድ ወቅት የህዝብ አመኔታ ያጣ መንግስት በሌላ ጊዜ የህዝቡን ስሜት ተረድቶ በሚወስዳቸው እርምጃዎችና ውሳኔዎች የህዝብ አመኔታና ድጋፍ መልሶ ሊያገኝ ይችላል።
በተመሳሳይም በሆነ ወቅት የህዝብ እመኔታ የነበረው መንግስት በሌላ ወቅት አመኔታው ተሸርሽሮ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል። ይህ የሚያሳየው ዜጎች በመንግስታቸው ላይ አመኔታ የሚጥሉት መንግስት ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት እንደሚቆም እርግጠኛ ሲሆኑ ብቻ መሆኑን ነው። የመንግስት የመታመን ጉዳይ ሊመጣ የሚችለውም መንግስት ራሱ ስለ ራሱ መልካም ስራዎች ስላወራና ስለሰበከ ሳይሆን ዜጎች ራሳቸው መንግስት መልካም ነገር እየሰራላቸው መሆኑን በተጨባጭ ሲያዩና ሲገነዘቡ ብቻ ነው።
ዜጎች መንግስት ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ ትክክለኛውን ስራ እየሰራ ነው ብለው ሲያምኑ ከፍተኛ እምነት ይጥሉበታል። በሌላ መልኩ ከዜጎች ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ስራ እየሰራ ነው ብለው ሲያስቡ ደግሞ አመኔታ ይነፍጉታል። ቁም ነገሩ የህዝብ አመኔታ መሸርሸር ገደቡን አለማለፉና በሀገር ላይ የከፋ ቀውስ አለማስከተሉን ማረጋገጥ ነው።
የህዝብ አመኔታ ፋይዳው እጅግ ብዙ ቢሆንም በየተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሪፖርቶችና በህዝብ አስተያየት ጥናት ውጤቶች መሰረተ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው አመኔታ በበርካታ ሀገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆልቆለ (trust deficit) መጥቷል። በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የህዝብ ቅሬታ፣ አመጽና እና ግጭት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማሉ። ደረጃው ይለያይ እንጂ የህዝብ አመኔታ መሸርሸር በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ ቁንጮ ተብላ በሚነገርላት አሜሪካ እና ሌሎች ምእራባዊያን ሀገራት ሳይቀር በተጨባጭ ሲከሰት ይስተዋላል።
ለምሳሌ አሜሪካውያን በአሁኑ ወቅት በመንግስት ላይ ያላቸው እምነት ከምንጊዜም እጅግ በወረደ ደረጃ እንደሚገኝ የተለያዩ ጥናቶችና የህዝብ አስተያየት መለኪያ ባሮ ሜትሮች ያመላክታሉ። Pew Research Center የተሰኘው ታዋቂ የጥናት ማእከል እ.አ.አ በ 2022 የህዝብ አመኔታን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው አንድ ጥናት ከአስር አሜሪካውያን ሁለቱ ወይም 20% ብቻ የሚሆኑት በመንግስት ላይ እምነት እንዳላቸው አመላክቷል። ይሁንና እ.አ.አ በ1958 በተደረገ የህዝብ አስተያየት ጥናት ሶስት አራተኛ (3/4) የሚሆኑ አሜሪካውያን በመንግስታቸው ላይ አመኔታ የነበራቸው ሲሆን ይህም በሌሎች ጊዚያቶች ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ትልቅ ቁጥር ተደርጎ ይወሰዳል።
ከዚያ በኋላ ግን በ1960 ዎቹ የበቬትናም ጦርነትን ተከትሎ እንዲሁም በ 1970 ዎቹ በሪቻርድ ኒክሰን አስተዳደር የወተር ጌት ቅሌት ባስከተለው መዘዝ እና በሀገሪቱ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የህዝብ እምነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሽቆልቆል ችሏል። ይህ ሁኔታ በ1990 መጨረሻ አካባቢ በሀገሪቱ የተከሰተውን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ መሻሻል እያሳየ የመጣ ሲሆን ሴፕቴምበር 9/2011 ከተከሰተው የኒዮዎርኩ የሽብር ጥቃት በኋላ የህዝብ አመኔታ እንደገና ሊያንሰራራ ችሏል። አሁን ደግሞ የህዝብ አመኔታ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
የህዝብ እምነት ማጣት በብዙ ሀገራት ከፍ ያለ የፖለቲካ ኪሳራ አስከትሏል። አሁንም በማስከተል ላይ ነው። ለምሳሌ የዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርአትን በሚከተሉ ሀገራት በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የሀገርና የህዝብን ጥቅም ወይም ፍላጎት ማሟላት አለቻሉም ተብሎ ሲታሰብ አልያም የዜጎች እምነት እየቀነሰ ሲሄድ የሀገሪቱ ፓርላማ የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ በማድረግ መሪዎቹ በሀላፈነታቸው እንዲቀጥሉ ወይም ከስልጣናቸው ዘወር እንዲሉ የሚደረግበት አካሄድ እንግሊዝና ጃፓንን በመሳሰሉ ሀገራት የተለመደ ነው።
በተመሳሳይም አንዳንድ መሪዎች የነደፉት ፖሊሲ ወይም ዕቅድ ድጋፍ አላገኝ ሲልና የመተማመኛ ድምጽ ሲነፈገው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቃሉ። ከዚህ በተጨማሪም የህዝብ እምነት መልሶ ለማግኘት ይፋ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታያል። ጃፓን ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናት። ጃፓን ውስጥ ጠቅላይ ሚንስትሮች የህዝብ አመኔታ ሲሸረሸር ፈጣን ፖለቲካዊ ውሳኔ በመወሰን ስልጣን ቶሎ በመልቀቅ ይታወቃሉ። ለምሳሌ ከ2006 እስከ 2012 ባለው ስድስት አመት ገደማ ጃፓን ስድስት ጠቅላይ ሚንስትሮችን ለዋውጣለች።
በእንግሊዝም ተመሳሳይ ተሞክሮ አለ። በዚህ ረገድ ሀገሪቷ በስድስት አመታት ውስጥ አምስት ጠቅላይ ሚንስትሮችን ለውጣለች። ለምሳሌ በቅርቡ ተሹመው የነበሩት ሊዝ ትረስን ብንወሰድ ስልጣን ላይ የቆዩት ለስድስት ሳምንታት ብቻ ነው። እኚህ ጠቅላይ ሚኒስቴር ብዙ ሳይቆዩ ከስልጣን እንዲወርዱ የተገደዱበት ምክንያት ለገቡት ቃል አልታመኑም በሚል በደረሰባቸው ጫና ነው። የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሩን እና ቴሬዛ ሜይም ተመሳሳይ እጣ ያጋጠማቸው መሪዎች ናቸው።
ሌላው ተቀባይነት ያለው (Legitimate) የመንግስት ሰርአትን ለመገንባትና የህዝብን እምነት ለማሳደግ ሀገራት ከሚወስዱት እርምጃዎች መካከል ከህዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች የፖሊሲ ሪፎርም፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ (አሜንድመንት) እንዲሁም ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት ነው። ከዚህ አኳያ አሜሪካ ወደ 27 ጊዜ ፣ ፈረንሳይ 24 ጊዜ፣ ደቡብ አፍሪካ 17 ጊዜ፣ ህንድ 103 ጊዜ የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረጋቸው ከዚሁ መሰረተ ሀሳብ በመነሳት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
በሌላ በኩል አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ለይስሙላ ብቻ ሳይሆን በተግባር ነጻ፣ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ በማካሄድ ቅቡልነት (ሌጅትመሲ) ያለው መንግስት ለመመስረትና ዲሞክራሲያዊ ሰርአትን ለመገንባት ጠንክረው እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ በአህጉራችን ጋናን፣ ሴኔጋልን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ቦትስዋና… ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በጥቅሉ እነዚህና መሰል እርምጃዎች ከለውጥ ጋር ለመራመድ፣ የረጋ ሀገረ መንግስትን ለመመስረት እና የህዝብ አመኔታን ለማሳደግ በር ይከፍታሉ። ችግሮች ሳያድጉ እንዲቀጩም ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ መንግስትንና የመንግስት ስርአትን ያለማመን ችግር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው። በታሪካችን በተለይ ከዘውዳዊ ስርዓት በኋላ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ የሚያደረጋቸው በርካታ ግፍና ወንጀሎች በዜጎች ላይ ተፈጽመዋል። ሀገሪቱ ለብዙ ዘመናት ህዝቡን በማፈን፣ በማስጨነቅ፣ እንዲሁም ግድያን ጨምሮ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽሙ በቆዩ መንግስታትና መሪዎች መዳፍ ስር ያለፈች በመሆኗ አብዛኛው ህዝብ ለመንግስትና ለፖለቲካዊ ተቋማት ያለው አመለካከትና እይታ አሉታዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። “ፖለቲካን በሩቁ” የሚለው የቆየ ሀገራዊ ብሂልም ይህንኑ ታሪካዊ እውነታ መሰረት ያደረገ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ስም ምለውና ተገዝተው ወደ ስልጣን የመጡ መንግስታትና መሪዎች በቃል አልገኝ ብለው ያሻቸውን ፖሊሲና ህግ ህዝቡ ላይ ሲጭኑበትና በተለያየ መንገድ በደል ሲፈጽሙበት ስለኖሩ ለመተማመን በር ከዘጉ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። ቀደም ባሉት ሰርአቶች ገዢዎቹ ውግንናቸው ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ማደላደል ላይ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው ሲሰሩ መቆየታቸው፣ የሚሰሯቸው ተግባራት የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት የማይመጥኑ መሆናቸው ይታወቃል።
ሀገርን በማሳደግ ወደ ዲሞክራሲ ከማምራት ይልቅ ዲሞክራሲን የሚያቀጭጩ ተግባራትን በመፈጸም ሀገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲመሩት በርካታ አመታት ተቆጥረዋል። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች አላስፈላጊ ሁኔታዎች ተደማምረው ህዝብና መንግስት የማይግባቡ አካላት እንዲሆኑ አድርጓል። በዛው ልክ መንግስትና የህዝብ አገልጋይነትም እንዲፋቱ አድርጓል። እነዚህ ሁኔታዎች ሄደው ሄደው ህዝብ ያለማመኑ ስሜት ወደ ቅሬታ ቅሬታው ደግሞ ወደ ብሶት እና ብሶቱ በጊዜ ሂደት ወደ ተቃውሞ እንዲያመራ ምክንያት ሆኖ አሁን እየታየ ያለው የለውጥ ሂደት ላይ ደርሰናል።
በ2010 ዓ.ም አጋማሽ የተደረገውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ አመራር በህብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና በህዝቡ ዘንድ ያለውን መጥፎ ስሜት ለመቀየር የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም እስረኞችን በመፍታት፣ የቀድሞ የመንግስት አስተዳደር በአገዛዝ ዘመኑ ለፈጸማቸው ኢ-ፍትሀዊ ድርጊቶች ህዝብን ይቅርታ በመጠየቅ፣ በውጭ ሆነው ስርአቱን በትጥቅና በሰላማዊ መንገድ ሲቃወሙና ሲታገሉ የነበሩትን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጓል። የተከሰሱባቸው ወንጀሎች እንዲሰረዙ በማድረግ ከህዝብ ጎን መቆሙን አረጋግጧል። በዚህ ሳቢያም ይህ መንግስት የኔ መንግስት ነው የሚል አስተሳሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ሊፈጠር ችሏል። ይሁንና ከተወሰኑ ወራቶች በኋላ መንግስት በብዙሃን ዘንድ በተወሰነ መልኩ እምነት እያጣ እንዲሄድ ያደረጉ ምክንያቶች እዚህም እዚያም ተፈጥረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በአንድ በኩል ሪፎርሙ ወደ ታችኛው የመንግስት እርከንና ልዩ ልዩ ተቋማት አልወረደም፤ የህግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም የሚሉ ሃሳቦች ሲንጸባረቁ ይስተዋላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከማህበራዊ እሴቶቻችንና ዘመናትን ካስቆጠረው ባህላችን ጋር የማይሄዱ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ ታይተዋል።
አልፎ አልፎ በየቦታው ሲከሰቱ የነበሩትን ግጭቶች፣ የሰላም መደፍረስ፣ የህዝብ መፈናቀሎች፣ ጽንፍ የወጣ የብሔረተኝነት አስተሳሰብ..ወዘተ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርገው ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም አልፎ አልፎ የግልጸኝነት፣ የተጠያቂነትና የፍትሀዊነት መርህና አካሄድን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ አንደምታዎች የሚነሱ እንደመሆኑ መጠን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ለፖለቲካ ቅሬታ መፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል።
ይህንን ቅሬታ አስወግዶ መተማመን ለመፍጠር መንግስት ድክመቶቹን ማረም፣ በተለይ ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ፣ ዜጎችን በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህን ደግሞ በየደረጃው ካሉ ባለሥልጣናቱ ሊጀምር እንደሚገባ የብዙዎች እምነት ነው።
ዳግም መርሻ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም