እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ከምንታወቅባቸው እሴቶች አንዱ ለሀገራችን ያለን ከፍተኛ ፍቅር ነው። ይህ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ፤ ሀገርን እንደ ሀገር በዘመናት መካከል ማቆም ያስቻለ ትልቁ ማህበራዊ ማንነታችን ነው።
በዘመናት ውስጥ ከፍ ባለ መስዋእትነት ጭምር የተገነባው ይህ እሴታችን፤ እንደ ሕዝብ በየትኛውም ሁኔታ /በክፉም በደጉም/፤ በየትኛውን አካባቢ /በሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ/ ሳይሸረሸር ከፍ ባለ መታመን እስከ ዛሬ ድረስ ሕያው ሆኖ በእያንዳንዳችን የልብ ጽላት ውስጥ የተቀረጸ ነው።
እስከ ትናንት ድረስ በየዘመኑ ሀገርን አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተቃጡ ጥቃቶችን መከላከል /ማምከን የተቻለው፤ ሀገርም አድጋና በልጽጋ ለማየት ትውልዶች በየዘመኑ ባደረጉት ጥረት እና በከፈሉት ዋጋ እንዲሁም ይሄው ማህበራዊ እሴታችን በፈጠረው አቅም ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን /የዲያስፖራው ማህበረሰብ/ ሁለንተናዊ በሆነ መልክ ለሀገራቸው እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የዚህ እውነታ አንዱ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ በመሆን ያበረከቱት እና እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ብዙ ዋጋ ከፍለው ያገኙትን በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት በሀገር ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ አቅም መሆን ችለዋል።
በተለያዩ የሙያ መስኮች በራሳቸው ወጪና ተነሳሽነት የእውቀት ሽግግሮችን በመፍጠር ዜጎች የአዳዲስ እውቀት፤ ክሂሎት እና ቴክኖሎጂ ባለቤቶች አድርገዋል። በዚህም ሀገር እንደ ሀገር ተጠቃሚ የምትሆንበትን የተሻለ እድል ፈጥረዋል።
በተለያየ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ /የጤንነት፣ የመፈናቀል፣ የኑሮ …ወዘተ/ ላሉ ዜጎች ፈጥነው በመድረስ ለወገን አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። በዚህም የሕይወት ተስፋ የዘሩባቸው ዜጎቻችን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም።
ሀገር በተቀናጀና ያልተገባ ዓለም አቀፍ ጫና ውስጥ በወደቀችበት ጊዜ፤ ስለ ሀገራቸው እና ሕዝባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ አደባባዮችን አጣበው ከፍ ባለ ድምጽ ጮኸዋል ዓለም ስለ ሀገራቸው ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ሳይታክቱ ታግለዋል። በዚህም ሀገራቸው ኢትዮጵያን ከፍ ካለ ስጋት መታደግ ችለዋል።
ሀገር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በነበረችባቸው ወቅቶች ሀብት ከማሰባሰብ ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በመላክ ሀገር እና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሄዱበት እርቀት ስለ ሀገራቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት በተግባር ያሳየ ነው።
ከዚህም ባለፈ ስለሀገራቸው መተኪያ የሌላት ሕይወታቸውን ለመስጠት ባህር አቋርጠው የመጡ የዲያስፖራ አባላትን ማየት መቻላችን፤ ዲያስፖራው የቱን ያህል ለሀገሩ የጸና ፍቅር እንዳለው፤ ይህ ፍቅሩ ውድ ሕይወቱን ሳይቀር መስዋእት ለማድረግ ዝግጁ እንዳደረገው አመላካች ነው።
ይህ ለሀገሩ ካለው ፍቅር የተቀዳው የዲያስፖራው ያለፉት አራት ዓመታት ንቅናቄ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ካጋጠማትና ለህልውናዋ ስጋት ከሆነው ተግዳሮት ለመታደግ የነበረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ይታመናል።
ዲያስፖራው በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች የተለያየ አመለካከትና አቋም ቢኖረውም፤ ሀገር ችግር ውስጥ በወደቀች ጊዜ ልዩነቶቹን ሁሉ ወደ ጎን ትቶ ስለ ሀገሩ አንድ ሆኖ በአንድ ድምጽና አቋም የቆመበት እውነታ በሀገሪቱ የዲያስፖራ ታሪክ ውስጥ ደምቆ የሚታይና በመጪዎቹ ትውልዶችም የሚዘከር ነው።
ከዚህ አንጻር መንግስት ለዲያስፖራው ማህበረሰብ በአደባባይ የሰጠው እውቅና ተገቢ፣ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው። ዲያስፖራው በቀጣይም በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል በሚል መንፈስ ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ እንዲሳተፍ ዕድል የሚፈጥርም ነው።
እውቅናው ከዚህም በላይ በመንግስትና በዲያስፖራው መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር መንግስት ለጀመረው ለውጥ ስኬት አንድ ትልቅ አቅም የሚሆን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለሚደረገው ርብርብም የዲያስፖራውን አቅም ለመጠቀም እንደ መልካም ጅማሮ የሚቆጠር ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም