(ክፍል አንድ)
የዛሬ መጣጥፌ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በማትኮሬ በይደር ያቆየሁት ሃሳብ ነው። የአሜሪካን ነገር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ምህዳር ላይ ያለው ተጽዕኖ ከፍ ያለ ስለሆነ በቅርብ ሆኖ እግር በእግር መከታተልንና መተንተንን ግድ ይላል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የገጠመን ተጽዕኖ የአሜሪካንን ጉዳይ ችላ ልንለው የማይገባ እንደሆነ ያረጋግጣል። የአገራችን የውጭ ጉዳይም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችን ሲቀረጹም ዓለመአቀፍ ሁኔታውንና አሰላለፉን ለይምሰልና ለላንቲካ ላይ ላዩን ሳይሆን በጥልቀት መተንተን፣ መተርጎምና መበየን ይጠበቅባቸዋል። በተለይ የአሜሪካና የምዕራባውያን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት መታየት አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ነው የአጋማሽ ዘመን ምርጫውን ላነሳሳ የወደድሁት።
የአሜሪካ መንግሥትና ሕዝብ እንደ ሰው ሲወከል አጎት ሳም በመባል ይታወቃል፡፡ ስረወ – ሀረጉ US የሚለው ምህጻረ ቃል ነው፡፡ United States US የተሰኘውን የተለመደ የወል ስም (Uncle Sam) በሚል መጠቀም የተጀመረው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ” አጎታችንን ! ? ” እንዲህ ካስተዋወቅኋችሁ ሌላ ተያያዥ ጉዳይ ላንሳ። በብዛት ከአሉታዊ ብያኔና አንድምታ/ pejorative ጋር ይያያዛል እንጂ፤ ከዩናይት ስቴትስ ሰሜናዊ ግዛት የሆኑ አሜሪካውያንና ሌሎች ያንኪስ yankees በሚል ቅፅልም ይጠራሉ ፡፡”
Yankees go home ! ” አሜሪካ በሃይልና በመንፈስ ከያዘቻቸው አገራት ከካናዳ ፣ ምስራቅ ጀርመን ፣ ቬትናም ፣ ጃፓንና ሌሎች አገራትን፤ ለቃ እንድትወጣ የሚጠይቅ መፈክር ነው፡፡ የእኛዎቹ የ60ዎቹ ትውልድ መፈክሩን በአደባባይ ማስተጋባቱ ያስታውሷል፡፡ በዓለምአቀፍ ግንኙነት፣ በዲፕሎማሲያዊ ማህበረሰብ ኮሪደርና በብዙኃን መገናኛ ደጋግመን የምንሰማው የጨረተ cliche የሚመስል ግን አሁንም ስራ ላይ ያለ አባባል አለ፡፡
“አሜሪካ ስታነጥስ የተቀረው ዓለም ጉፋን ይይዘዋል፡፡ “/When the U.S. sneezes, the world catches a cold./ይህን ምሳሌዊ አነጋገር ለመጀመሪያ ጊዜ በ1813 ዓ.ም የኦስትሪያ ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል የነበረው ልዑል ክሌመንስ ዌንዜል ሲጠቀመው፤ “ፈረንሳይ ስታነጥስ የተቀረው አውሮፓ ጉፋን ይይዘዋል፡፡ ” በሚል ነበር ፡፡ በጊዜው የናፓሊዎን ፈረንሳይ ልዕለ ኃያል ነበረችና፡፡
በሂደት የአሜሪካ ልዕለ ኃይልነት እየገነነ ሲመጣ “ፈረንሳይ ” የሚለው ፤ “በአሜሪካ ” “አውሮፓ” የሚለው ደግሞ ፤በ ” ዓለም ” ተተክቶ ፤ ” አሜሪካ ስታነጥስ የተቀረው ዓለም ጉፋን ይያዛል ” ሆነ፡፡ ከቀደመው የልዑል ዌንዜል አባባል ይልቅ ይህ አባባል ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ተናኘ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በ” ቻይና “ይተካ ይሆን የሚለውን እድሜ ሰጥቶን አብረን የምናይ ይሆናል።
ለመግቢያ ያህል ይሄን ካልሁ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ላምራ። አይደለም የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ይቅርና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ጃኔት የለን ስለ ኢኮኖሚው አንዲት ቃል ጣል ቢያደርጉ፤ አገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም ኢኮኖሚ ላይ በአዎንታ ወይም በአሉታ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ስለአሜሪካ ምርጫ የምፈተፍተው በአንድም በሌላ በኩልም ጥላው ማጥላቱ ስለማይቀር ነው። የዛን ሰሞኑ ምርጫም ደረጃው ይለያይ እንጂ በእኛም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከአሜሪካ እንጥሻዎች እንደ አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሪፐብሊካኖች እንደ ፎከሩት፤ አሜሪካንን በቀይ ማዕበል የሚያጥለቀልቁ ከሆነ ማለትም የታችኛውን ምክር ቤት ወይም ኮንግረሱን፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ወይም ሴኔቱን ጥርግርግ አድርገው የሚያሸንፉ ከሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ሆነ፤ የዴሞክራቶች ፖሊሲዎች ሊቀለበሱ ካልሆነም ሊስተጓጎሉ ይችላሉ። አሜሪካ ለዩክሬ የምታደርገው ድጋፍ ሊቀዛቀዝ ፤በአንጻሩ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የነበረው የተካረረ ፖሊሲ ሊለዝብና ወይይት ሊጀመር፤ ለዩክሬን በገፍ ጦር መሳሪያ ማቅረቡና የዶላር ድጋፉ ጋብ ብሎ ለድርድር በሯን እንድትከፍት ግፊት ሊደረግባት ይችላል።
ይሄን ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል አገራትና የአውሮፓ ሕብረት፤ በዩክሬንና በራሽያ ላይ ላይ የሚያራምዱት ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ባይቀየር እንኳ በተወሰነ ደረጃ ለዘብ ማለቱ አይቀርም ይላሉ ተንታኞች ፤ ዴሞክራቶችን ሃሳብ ላይ የጣላቸው ሌላው አብይ ጉዳይ የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን የማይቀበሉና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ቡራኬ ያገኙ እጩዎች መበራከት ነው። እነዚህ እጩዎች አሸንፈው በኮንግረሱም ሆነ በሴኔቱ መቀመጫ የሚያገኙ ከሆነ የዴሞክራሲ ጉዳይ ጥያቄ ላይ ይወድቃል።
አሜሪካ የምትመጻደቅበትና እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እሴት የምታየው ዴሞክራሲ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ እንደ የመንግሥታቱ ድርጅት UN፣ የዓለም ባንክ፣ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም፤ ያሉ ተቋማትን በመመስረት ከ75 ዓመታት በላይ ሉላዊነትን GLOBALIZATION እያቀነቀነች ቤቷ ግን በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ክፍፍልና ልዩነት እየተናጠ ነው። ከአገሬው ግማሽ ያህል የሚሆነው መራጭ የ2020 ምርጫ ተጭበርብሯል ብሎ የሚያምንና የምትመጻደቅበትን ዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ ጥሏል። የሪፐብሊካንና የዴሞክራት አባላት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ልዩነታቸው ተካሯል። አይን ለአይን ለመተያየት እንኳ አቅቷቸዋል።
ቀኝ አክራሪዎችና ክሪስቲያኖች በህልውናችን ላይ አደጋ ተደቅኖብናል በማለት አሜሪካ ትቅደም! የሚል ሕዝበኛ populist የሆኑትን ትራምፕ እንደ መሲህ ማየት በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ደግሞ ክፍፍል እየፈጠሩ ነው። አሜሪካ እንዲህ በልዩነትና በክፍፍል እየተናጠች ሳለ ዛሬም የዓለም ፖሊስና የዴሞክራሲ ፊደል አስቆጣሪ ለመሆን፤ የምታደርገውን ጥረት የታዘቡ ፤ የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች በማለት በሀሰተኛ መረጃና በሴራ ፖለቲካ ዜጎቿ መከፋፈላቸውን በአብነት ያነሳሉ። ለነገሩ የዴሞክራሲ ነገር አበቃለት የተባለው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕና ወደ 75 ሚሊዮን የሚጠጉ ደጋፊዎቻቸው የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት አልቀበልም ያሉ ዕለት ነው።
ለነገሩ አሜሪካ ከብሔራዊ ጥቅሟ የምታስቀድመው ነገር እንደሌለና ወጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሌላት ብዙዎች ይተቻሉ። በነገራችን ቀይ ቀለም የሪፐብሊካን መለያ ሲሆን ሰማያዊ ደግሞ የዴሞክራት ነው። ቀዩ ማዕበል አሜሪካን ቢያጥለቀልቅ ኖሮ፤ ከፍተኛ በጀት የተያዘለት የፕሬዚዳንት ባይደን የአየር ንብረት ለውጥ እና “አሜሪካ ተመለሰች!”/America is back/የተባለለት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ጥያቄ ይነሳባቸዋል። በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ኋይታውስን በያዘው ፕሬዚዳንትና በፓርቲው ላይ እንደሚሰጥ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል።
ኋይታውስን የያዘው ፓርቲ በገባው ቃል መሰረት ኃላፊነቱን ካልተወጣ በኮንግረስና በሴኔቱ የያዛቸውን መቀመጫዎች ሊያጣ ይችላል ተብሎ እንደተሰጋው ኮንግረሱን ለሪፐብሊካኖች አስረክቧል። የዴሞክራት ፓርቲ ደግሞ በጠባብ ልዩነት ሴኔቱን የተቆጣጠረ ሲሆን በጆርጂያ ሕዳር 25 ቀን፣2022 ዓም በተካሄደ ድጋሚ ምርጫ፣ ዴሞክራቱ ራፋየል ዋርኖክ ሪፐብሊካኑን ሔርሻል ወከር በጠባብ ልዩነት በማሸነፍ ዴሞክራቶች ሴኔቱን በ51 መቀመጫ ሲያሸንፉ፤ ሪፐብሊካኖች ደግሞ 49 መቀመጫ ዎችን በመያዝ በሴኔቱ የነበራቸውን ተቀራራቢ ድምጽ አጥተዋል።
ካለፈው ነሐሴ ወዲህ የፕሬዚዳንት ባይደን ተቀባይነት ከ50 በመቶ በመውረዱ፤ በኮንግረሱም ሆነ በሰኔቱ፤ መቀመጫዎችን ልናጣ እንችላለን ብለው ሰግተው የነበር ቢሆንም ውጤቱ የተፈራውን ያህል ሳይሆን ቀርቷል። በርከት ያሉ መቀመጫዎችን ቢያጡ ኖሮ ለሥልጣን ያበቋቸውን ፖሊሲዎች ማስፈጸም ይቸገሩ ነበር በ2024 ዓም በሚካሄደው ምርጫም ባይደንም ሆነ ፓርቲያቸው የመመረጥ ዕድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ሊጥለው ይችል ነበር።
በአንጻሩ ዴሞክራቶች በሁለቱ ምክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫቸውን ቢያጡ ኖሮ፤ ፕሬዚዳንት ባይደን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተለሙትን ዕቅድ፤ በመንግሥት የሚደገፍ የጤና መርሀ ግብራቸውን፤ ጽንስ የማቋረጥ መብትን ፤ የጠመንጃ መያዝ መብትን ለመቆጣጠር የሚያግዙ መመሪያዎችን አውጥቶ ለመተግበር ይችሉ ነበር።
ሪፐብሊካኖች ኮንግረሱን በአብላጫ ድምጽ ስለተቆጣጠሩ የዴሞክራቶች ዕቅዶች ሳንካ ይገጥማቸዋል ተብሎ ተሰግቷል። በጥር 6 ቀን፣ 2021 ዓ.ም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የምርጫ ውጤቱን አልቀበልም ባለማለታቸው፤ ደጋፊዎቻቸው በወቅቱ የምርጫ ውጤቱን ለማጽደቅ በካፒቶል ሒል ተሰብስበው የነበሩ፤ የምክር ቤት አባላትን እንዲያስቆሙ በጠየቁት መሠረት ደጋፊዎቻቸው እንደ ዴሞክራሲ ቤተመቅደስ የሚቆጠረውን፤ ካፒቶል ሒልን በኃይል ጥሰው በመግባት ሒደቱን ከማስተጓጎላቸው ባሻገር የጸጥታ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ይሄ ጥቃት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱና በሕገ መንግሥቱ ላይ የተሰነዘረ ነው በሚል፤ አጣሪ ኮሚቴ አዋቅረው ምርመራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ምርመራውን እስከ ታህሳስ መጨረሻ እናጠናንቃለን ቢሉም፤ በዚህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ሪፐብሊካኖች በተለይ በኮንግረሱ አብላጫ መቀመጫ ስላገኙ ይሄ ምርመራ ምዕራፍ ሳያገኝ ይቋረጣል። ትራምፕም ከተጠያቂነት ያመልጣሉ ብለው ሰግተዋል።
በዚህ ምትክ የጆ ባይደን ልጅ ሀንተር ከቻይና ጋር ያልተገባ የስራ ውል ተፈራርሟል እየተባለ ስለሚቀርብበት ክስ፤ የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን በጥድፊያ ተጠራርገው ሲወጡ ስለተፈጠረው ቀውስ እናጣራለን ብለው ምርመራ ሊጀምሩ ይችላሉ እንደተባለው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን አዳዲስ ተሿሚዎችን በተለይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሹመት የምክር ቤቱን ይሁንታ ማግኘት ይቸገራሉ።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም በተለይ ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አጣብቂኝ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ፕሬዚዳንቱ ይህ ሁሉ ሲሆን እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም የአስፈጻሚነትና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን በመጠቀም ፤ሪፐብሊካኖች በተለይ ስለጽንስ ማቋረጥ፣ ስለስደተኞችና ስለታክስ የሚያቀርቧቸው ሕጎች ቢጸድቁም ስራ ላይ እንዳይውሉ ማገድ ይችላሉ።
የአጋማሽ ዘመን ምርጫው በ2024 ዓ.ም የሪፐብሊካን የፕሬዚዳንታዊ እጩ ማን ሊሆን እንደሚችልም ያመላክታል ተብሎ ይጠበቅ የነበር ቢሆንም ትራምፕ አበክረው እጩነታቸውን ይፋ አድርገዋል። በዚህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ፕሬዚዳንቱ የደገፋቸው የሪፐብሊካን እጩዎች ማሸነፍ ካልቻሉ ፓርቲው ትራምፕ እጩ ሆነው እንዲቀርቡ ላይደግፋቸው ይችላል። ይልቅ የፍሎሪዳ ገዥ ሮን ዲሳንቲስ በዚህ ምርጫ በ20 በመቶ አብላጫ ስለአሸነፉ የ2024 የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ።
ዴሞክራቶች እንደፈሩት የአጋማሽ ዘመን ምርጫው ከኮንግረስም ሆነ ከሴኔት መቀመጫዎች ብዙ ስላላሰጣቸው እፎይ ያሉ ይመስላል። ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ለበርካታ ቀናት የኔቫዳና አሪዞና ድምጽ ቆጠራ ውጤት ባይታወቅም የጆርጂያ ግን አሸናፊውን መለየት ባለመቻሉ በ2ኛ ዙር ምርጫ እንዲለይ ተወስኖ ድምጽ መሰጠት ተጀምሯል።
የእነዚህ ምርጫ ክልሎች ውጤት ሲታወቅ ሪፐብሊካኖች ሴኔቱንም ሆነ ኮንግረሱን በጠባብ ልዩነት ሊቆጣጠሩ ይችላሉ ቢባልም ዴሞክራቶችን አላስጨነቀም። እንዲያውም ያሸነፉ ያህል ነው ውጤቱን ያከበሩት። በምርጫው ማግስት ፕሬዚዳንት ባይደን ከነጩ ቤተ መንግሥት በሰጡት መግለጫ ዴሞክራሲ አሸንፏል። ብለዋል።
የ2020 ምርጫ ውጤት የማይቀበሉና በፕሬዚዳንት ትራምፕን ይደገፉ የነበሩ አምስት እጩዎች በመሸነፋቸውና ሪፐብሊካኖች የተሰጋውን ያህል ስላልቀናቸው ነው እንግዲህ ባይደን ዴሞክራሲ አሸንፏል ያሉት። ዴሞክራቶችና የእነሱ ወገን የሆኑ ሚዲያዎች “የምርጫ ከሀዲዎች” (election deniers) የትራምፕ ታማኝ ደጋፊዎች፤ በኮንግረስም ሆነ በሴኔቱ ሊያሸንፉ ይችላል በሚል ዴሞክራቶችና ሉላውያን ማለትም ምዕራባውያንና የአውሮፓ ሕብረት፤ ምጥ ተይዘው ነው የሰነበቱት። ለነገሩ ምጡ ቀለል ያለ ቢመስልም ገና አልተገላገሉም።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን የመመለስን ዕድል ያሰጋቸው እነ ኔቶ፣ የአውሮፓ ሕብረት፤ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋምና በአጠቃላይ ሉላዊነት (Globalization) የሚያቀነቅኑትን ነው። ባለፈው ወር ለንባብ የበቃው The economist መጽሔት በምርጫ ውጤቱ አውሮፓና አጋሮቿ እፎይ አሉ በማለት ነው ሰሞነኛውን ጭንቅ የገለጸው። በቀጣዩ የመጣጥፌ የመጨረሻ ክፍል የምርጫ ውጤቱን አንድምታ ሰፋ አድርጌ የምሄድበት ይሆናል ።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም