‹‹የሥጋ ደዌ በሽታ ታማሚ ነኝ። በዚህ ምክንያት በሕብረተሰቡ መገለሌ ለረጅም ጊዜ ከኖርኩበት አካባቢ እንድርቅ አድርጎኛል። ቤት ንብረቴን መሸጥ ነበረብኝና ቤት ንብረቴንም አሽጦኛል›› ይሄን አስተያየት የሰጡን በተለምዶ ቆሼ እየተባለ የሚጠራውና ዘነበወርቅ ወይም አለርት ሆስፒታል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ እናት ናቸው። ወይዘሮ ዘውዴ ዘበነ ይባላሉ። የተወለዱት ሥፍራውን ለመንገር ፈቃደኛ ባልሆኑበት የገጠር መንደር እንደሆነም ነግረውናል። እንዳጫወቱን ከትውልድ መንደራቸው የወጡት በ15 ዓመታቸው ነው። ምክንያታቸው ደግሞ ወርቅ በወርቅ ናት ተብሎ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ በሚነገርላት አዲስ አበባ ከተማ ሰርቶ ለመለወጥ ነበር።
ሆኖም ሸገር ላይ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ስላልሆነላቸው ለጋውን የታዳጊነት ዕድሜያቸውን ከአሜሪካ ጊቢ እስከ ካዛንቺስ በሚባሉ አረቄ ቤቶች ኮማሪነት ነው ያሳለፉት። እንደዚህም ሆነው መልከ መልካም ነበሩና እሳቸውን ብለው በየአረቄ ቤቱ ጎራ የሚሉ በርካታ ወዳጆች በማፍራታቸው ደህና ገንዘብ መያዝ ችለዋል። የራሳቸው ቪላ ቤትና መጠጥ ቤትም ለመክፈት በቅተዋል። ቢሆንም ትዳር ሞክረው አያውቁም። ፈጣሪ ከደህና ወዳጆቻቸው መካከል ከአንዱም ልጅ አልሰጣቸውም። በዚህ ሁኔታ በካዛንቺስ ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ ኖረዋል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የሥጋ ደዌ በሽታ ተጎጂ በመሆናቸው ከካዛንቺስ በመልቀቅ አሁን ላይ እየኖሩ ወዳሉበት ዘነበወርቅ አካባቢ ለመሄድ ተገደዱ።
‹‹ከጣት ጥፍሬ ነው የጀመረኝ። የጥፍሬን ስሮች እየጠዘጠዘ ያመኝ ነበር። በብርቱም ያሳክከኝ ገባ። ጆሮዬን ጭምር ስለሚበላኝ አከዋለሁ። የኋላ የኋላ አፍንጫዬንም ይይዘኝ ገባ›› የሚሉት እናት ዘውዴ እንዳወጉን እነዚህን አዳዲስ ምልክቶች ቢያዩም ደፍረው ወደ ሆስፒታል አልሄዱም።
እጅ እግራቸው ቆሳሰለ። እንዲህ ሆነው መውጣት አፈሩ። ይሄን ያዩትና በመጠጥ ቤታቸው የቀጠሯቸው ሰራተኞቻቸው ጥለዋቸው ጠፉ። መቆሳሰላቸውን ያየ የአካባቢው ሰው ሁሉ ተጠየፋቸው። ደፍሮ የሚጨብጣቸው ቀርቶ ከርቀት ሰላም የሚላቸው አጡ። የሚያውቃቸው ሰው ሲያያቸው እንዳላየ ማለፍና መንገድ አሳብሮ መሄድ ጀመረ። በለቅሶና በሌሎች ማኅበራዊ ኩነቶችም መሄድ አቆሙ። ሰው እንዳያያቸው ይደበቁም ጀመር። በዚህ መካከል በሰው ጥቆማ አለርት ሆስፒታል ሄዱ። ዘግይተው በመሄዳቸው እጅ እግራቸውን ከቁስሉ ማዳን ባይቻልም ለወራት አልጋ ይዘው በተደረገላቸው ሕክምና በሕይወት መቆየት ቻሉ።
ግን ወደ ቤታቸው ቢመለሱም የቅርብ ጎረቤቶቻቸው እንኳን ሊቀርቧቸው አልቻሉም። እጅና እግራቸው በቁስሉ እጅግ ተጎድቶ ነበርና ‹‹ዘውዴ ቆማጣዋ›› የሚል ቅጽያ ስም ሰጧቸው። በዚህ መልኩ በደረሰባቸው መገለልም ቤት ንብረታቸውን በቀላል ዋጋ ሸጠው ዘነበወርቅ አካባቢ ቆሼ ከትመው በቅርበት ሕክምናቸውን በመከታተል በልመና መኖር ጀመሩ።
‹‹ዘውዴ ተቆምጣ ትለምናለች ብሎ ካዛንቺስ ጉድ አለ›› ይላሉ። ከዚህ በኋላ ዘውዴ ማንንም መፍራት አቆሙ። መደበቃቸውም ቀረና በ36 ቁጥር አውቶቡስ ከዘነበወርቅ ካዛንቺስ በመመላለስ ‹‹ከማያውቁት መንፈስ ቅድስ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል›› ብለው ኑሯቸውን በልመና ተያያዙት።
‹‹በልጅነቴ ቢሞትም አባቴ የሥጋ ደዌ በሽተኛ መሆኑን የቆማጣ ልጅ እያሉ ከሚሰድቡኝ ጎረቤቶቻችን ተረድቻለሁ›› የሚሉት ሌላው የሥጋ ደዌ ተጠቂ አቶ ዘገየ ብሩ ሆኖም እሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው ለበሽታው ትኩረት ሳይሰጡትና ወደ ሆስፒታል ሄደው በመመርመር መላ ሳይፈልጉለት መኖራቸውን ያወሳሉ። በፊታቸውና በሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ የተለያዩ ቁስሎች ይወጡባቸው እንደነበር ያነሳሉ። ከጊዜ ብዛት ቁስሎቹ ፀንተው የአልጋ ቁራኛ እንዳደረጓቸውና ሲመረመሩ የስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂ መሆናቸው መረጋገጡንም ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት በሕብረተሰቡ የተለያየ መገለልና መድሎ ሲደርስባቸው መቆየቱንና ተደብቀውና ራሳቸውን አግልለው ለመኖር መገደዳቸውን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር የፋይናንስና አስተዳደር ኃላፊ አቶ አብይ አባተ እንደሚሉት ከበሽታው ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ውስጥ ስር የሰደደው የአመለካከት ችግር ተጠቂዎቹ ራሳቸውን አግለው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። በዚህ የተነሳ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በዘነበወርቅ በተለይም ቆሼ በሚባለው ቦታ በሀረር ገንደ ሴሮ፤ በኦሮሚያ ሻሸመኔ ኩየራ፤ በሌሎች በተከለሉ ሥፍራዎች ለመኖርና በጫናው ራሳቸውን ለማግለል መዳረጋቸውን ማሳያ ያደርጋሉ። ማህበሩ 20 ሺህ የሚጠጉ አባላት አሉት›› የሚሉት ኃላፊው አመለካከቱ በቀላሉ ሊወገድ ባይችልም አሁን ላይ ለውጥ እንዳለም አንስተዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች የአድቮካሲና መብት ጥበቃ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁን እንደሚሉት ተጠቂዎቹ ለመገለል የሚዳረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። በሽታው በሕብረተሰቡ ዘንድ ባለው የተዛባ አመለካከት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ተደርጎ ይታሰባል። በዚህም የተነሳ ተጠቂዎቹ ራሳቸውን አግልለው በከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለብቻቸው እንዲኖሩ የተደረገበት ነበር። በሽታው በፈጣሪ ቁጣ እንደመጣባቸውም አድርጎ መቁጠር አለ። ከዚህ በፊት የነበረው መገለል በቃላት ሊገለፅ ከሚችለው በላይ ከባድ ነበር። አሁን ላይ ተሻሽሎ ለውጦች መጥተዋል። ሕብረተሰቡ ውስጥ ሆነው በሽታውን በሕክምና እየተከታተሉ የሚሰሩበትና የሚኖሩበት ሁኔታም ተፈጥሯል።
ይሁንና አሁንም በርካታ ቁጥር ያለው የሕብረተሰብ ክፍል እነሱን የሚያይበት አተያይ ትክክል ባለመሆኑ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በየጊዜው በተለይም በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደ አገር ይሰራሉ። በሥጋ ደዌ በሽታ ምክንያት የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል መሥራት እንደሚችሉ ማሳየት አስፈላጊም ነው። ዘንድሮም በዓሉ የፊታችን ጥር 22 ‹‹የሥጋ ደዌን በሽታ አንዘንጋ›› በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይትና በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች ተከብሮ ይውላል። እ.ኤ.አ. ከ1953 ጀምሮ ጥር 30 ቀን የዓለም የሥጋ ደዌ ቀን ተብሎ መከበር የጀመረ ሲሆን በአገራችን ዘንድሮ ለ24ኛ ጊዜ ይከበራል። በዓሉ እንደ አገር የሚከበረው በተጠቂዎቹ ላይ ስር ሰዶ ያለውን አመለካከት መቅረፍ በሚያስችል ሰፊ ንቅናቄና ፓናል ውይይት ነው።በዚህም በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቅረፍ የተሻለ አስተሳሰብ እንዲሰፍንና ተጠቂዎቹም በሕብረተሰቡ ውስጥ ሆነው እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊነታቸውን እንዲያረጋግጡ ያስችላል።
ከክርስቶስ ልደት በፊት መከሰቱ የሚነገርለት የሥጋ ደዌ በሽታ መንስኤው ማይኮባክቲሪየም ሌፕራይ ነው። በሰው ቆዳ ላይ, እንዲሁም በmucous membranes እና በነርቭ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም ላይ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው ይሰቃያሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም