ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው። የግለሰብ ፣ የማኅበረሰብ ፣ የሀገርም ሆነ የዓለም ሕልውና መሰረት ነው። ከሰላም ውጪ ብዙ ነገሮችን ማሰብ የሚቀል አይደለም፤ ከዚህም የተነሳ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል፤ ስለሰላም ያለው ታማኝነት ካልሆነ በቀር ስለሰላም አያገባኝም የሚልን ፈልጎ ማግኘትም ቀላል አይደለም።
በተለይም ለውይይትና ለድርድር በሮችን በመዝጋት ከሚፈጠሩ ግጭቶች ተጠቃሚ ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። የሚያስከፍለውም ዋጋ ያልተገባ ከመሆኑም ባለፈ ለስሌት የሚመች አይደለም። በታሪክ ውስጥም የሚፈጥረው ጥቁር ጠባሳ ከፍ ያለና የትውልዶችን አንገት የሚያስደፋ ልብ ሰባሪ ክስተት እንደሚሆን ይታመናል።
ይህ ክስተት በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ መልኩን እየቀየረ ደጋግሞ በመከሰት ሕዝባችንን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎች እንዳስከፈለ ይታወቃል። ክስተቱ በራሱ የፈጠረው ሀገራዊ ድህነትና ጉስቁልና የትውልዶችን ልብ እስከ ዛሬ የሰበረና አንገት ያስደፋ ፤ የቀደሙ የደመቁ ታሪኮቻችንን ያደበዘዘ ወይም የደበቀ ነው።
አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ሀገራዊ ለሆነው ሰላም ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ከማጣታቸው የሚቀዳው ይህ ሀገራዊ ችግራችን፤ እነሱ ከትናንት መማር ባለመቻላቸው ዛሬ ላይ በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ዋጋ እንድንከፍል አስገድደውናል።
እንደ ሀገር በለውጡ ማግስት የነበረው ሀገራዊ ሰላምም ሆነ ለውጡን ተከትሎ በሕዝቡ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መነቃቃትና የለውጥ ተስፋ እንደ ሀገር ሀገርን ማሻገር የሚያስችል አቅም እንደነበረው ይታመናል። ይህንንም ብዙዎች ተስፋ አድርገው ነበር።
በተለይም የለውጡ ኃይል ለውጡን ካለፉት የለውጥ ዘመናት በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ያለሁከትና ደም መፋሰስ ለማስቀጠል የደረሰበት ውሳኔና ለውሳኔው የነበረው ቁርጠኝነት በመላው ሕዝባችን አግኝቶ የነበረው ተቀባይነት የለውጡ ባለቤት በራሱ ለሰላም የቱን ያህል የታመነ እንደነበር ያመላከተ ነው።
በርግጥ ለውጡ እንደታሰበው ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል የሚያስችለውን ተቀባይነት በሕዝቡ ውስጥ ቢያገኝም ፤የሰላሙ መንገድ ወደአሰብነው የጥፋት ጎዳና የሚያደርሰን መንገድ አይደለም በሚሉ ኃይሎች ለፈተና መጋለጡ የማይቀር ሆኖ አልፏል።ተፈትኖም ከብዙ መንገጫገጭ በኋላ ቆሞ መሄድ ችሏል።
ይህ ከሁሉም በላይ የሰላም መንገድ የቱንም ያህል በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍ አሸናፊነቱ ለጥያቄ የሚቀርብ አለመሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው፤ ከዚህም በላይ ሰላም አያተርፈንም ብለው የሚያስቡ ኃይሎች ሰላም ከተንከባከቡት አትራፊ እንጂ አክሳሪ እንዳልሆነ በተጨባጭ ያስተማረ ነው።
ለዚህ በተለይም በመንግስትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት፤ ሰላም የተገዛበት መርህ ምን ያህል ሰላም ለሚያከብራት ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ሰዓት ለሚፈልጋት ጭምር ትልቅ አቅም እንደምትሆን ያመላከተ ነው።
ይህ እውነታ ስለ ሰላም የተዛባ አመለካከት ያላቸውም ሆነ፤ ከሰላም አናተርፍም ብለው ለሚገምቱ እና ሰላምን በማናጋት አትራፊ እንሆናለን ብለው ለሚያስቡ ኃይሎች ተግባራዊ ትምህርት የሰጠ፤ ስለሰላም ካላቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተመልሰው ሰላምን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የተሻለ ዕድልን የሚፈጥር ጭምር ነው።
በሰላም ውስጥ አሸናፊ የሚሆነው ራሱ ለሰላም የተገዛ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሀገርና ሕዝብን ነው። ከዚህ አንጻር ስለ ሰላም የሚያስብ ኃይል እራሱን ለዚሁ ለተቀደሰ ዓላማ ማስገዛት ይኖርበታል።
ወደ ሰላም የመጡ ኃይሎችም፤ ሰላም በየትኛውም ሁኔታና ጊዜ ተሸናፊ እንደማያደርግ ፤ከዚህ ይልቅ አክብሮና ተንከባክቦ መያዝ ለራስ ፣ ለሀገር እና ለታሪክ ከፍያለ ክብር እንደሚያጎናጽፍ በአግባቡ ተረድተው ለዘላቂ ሰላም በታማኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም