የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ይመደባል። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩም የሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረግ የህብረተሰቡን ኑሮ ፈትኖታል። በተለይም ለነዳጅ የሚያደርገው ድጎማ መነሳቱ በትራንስፖርት ዘርፉ በነበረው ችግር ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆኑ የሕዝብ የእሮሮ ምንጭ ከሆነ ውሎ አድሯል
በመሰረቱ ድጎማ መነሳትን አስመልክቶ ባለፈው ወር የትራንስፖርት ዋጋ እንዲጨምር ባይደረግም ድጎማ የተነሳባቸውም ሆነ ድጎማው የቀጠላባቸው የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሻቸው የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ተስተውሏል፤ ሕጋዊ ጉዞ መስመሮችን አቆራርጠው እየጫኑ የተጓዦችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ (በተቀመጠ የተሳፋሪ ቁጥር) አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ሲነጠቁ በአደባባይ ታይቷል።
ከነዚህ የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መካከል ለዛሬ ማየት የፈለኩት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን /ባጃጆችን ጉዳይ ነው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች በመዲናዋ የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ በሕግ እውቅና ከተሰጣቸው አመታት አልፈዋል። በተለይም ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርቶች በማይገቡባቸው አካባቢዎች ዋነኛ አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው።
የእኛ ሰፈር ምንም እንኳ ለከተማ ቅርበት ያለው (ከስድስት ኪሎ በግምት ከ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ) ቢሆንም፤ ለታክሲም ሆነ ለአውቶብስ መነሻ ባለመሆኑ (ከላይ እየሞሉ ስለሚመጡ) አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪ በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆችን) ይጠቀማል።
እነዚህ ባጃጆች የነዋሪዎችን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ጊዜያትም በአብዛኛው አሽከርካሪዎች ከተቀመጡ ታሪፎች ውጪ የራሳቸውን ታሪፍ በማውጣት ሕዝቡን ላልተገባ ወጪ ሲዳርጉት ቆይተዋል፤ አሁንም እየዳረጉት ይገኛሉ። ሕዝቡም እነዚህን ሃይሎች ሀይ የሚልለት በመጥፋቱ የሚጠይቁትን ለመክፈል ተገድዷል።
በእርግጥ መንገዱ ስንፍና ካልያዘ በስተቀር በእግር ከ 15 እስከ 20 ደቂቃ የሚወስድ ነው። ይህንን ተሳቢ አድርጎም የመዲናዋ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የጉዞ ታሪፉ ሶስት ብር ፤ የሚጫነውም ተሳፋሪ ሶስት ሰው ብቻ እንዲሆን ወስኗል። በመሰረቱ ታክሲም ቢሆን መንገዱ አጭር በመሆኑ ከዚህ በላይ አያስከፍልም ነበር።
ይሁንና እነዚህን ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች የሚመራው ማህበር በራሱ ፈቃድ የአንድ ጉዞ ታሪፉን አምስት ብር አድርጓል፤ የሚጫኑትም ተሳፋሪ (ትራፊክ እስከሌለ ድረስ) ከአምስት ሰው አንሶ አያውቅም። ችግሩ በአደባባይ የሚከናወን ከመሆኑ አንጻር ህብረተሰቡ ችግሩን ተቀብሎ ለመሄድ ተገድዷል።
ከዚህ የከፋው አሳዛኙና የመንግሥት ያለህ ያስባለው እውነታ፤ እነዚህ አሽከርካሪዎች ከሰሞኑ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ አነሳ፤ የመለዋወጫ እቃ ዋጋ ጨመረ ብለው በገዛ ፍቃዳቸው ይጭኑበት የነበረውን ዋጋ ከአምስት ብር ወደ ስምንት ብር ያለ ይሉኝታ በማህበራቸው ስም ከፍ ማድረጋቸው ነው።
1.5 ኪሎ ሜትር ለማይሞላ የጉዞ መስመር በአንድ ጊዜ በአንድ ሰው ሶስት ብር መጨመር ምን ማለት ነው፤ ማህበር የሚባለውስ አካል የጉዞ ታሪፍ የማውጣት የሕግ ባለመብት ያደረገው ማነው?” ይህ የትኛውም ባለጤነኛ አእምሮ ሰው ሊያቀርበው የሚችለው ጥቄያ ነው። መልሱም ቢሆን ለማንም የተሰወረ /የሚሰወር አይሆንም።
እርግጥ ባለሶስት እግሮቹም ሆነ ሌሎቹ በዘርፉ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ ሊጨምር ይችላል። እየሆነ ያለው ግን ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም። ይህንን ክፍተት ለመሸፈን በአንድ ሰው ሶስት ብር ጨምሮ የተሳፋሪዎችን ቁጥር ከ3 ወደ አምስት ማሳደግ የግድ ሊሆን አይችልም።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደ ትራንስፖርት አገልግሎቱ የገቡት የነዳጅ ፍጆታቸው ሆነ የግዥ እና የመለዋወጫ ወጪያቸውም ዝቅተኛ መሆኑ በመንግሥት ደረጃ ተጠንቶና አዋጭ መሆኑ ተረጋግጦ መሆኑ መረሳት ያለበት አይመስለኝም።
አብዛኛው ሕብረተሰብ የአሽከርካሪዎቹን ሕገወጥ ተግባር ቢቃወመውም፤ ችግሩን ማስቆም የሚያስችል አቅም በማጣቱ የጠየቁትን እየከፈለ መሳፈሩን ቀጥሏል። ቀደም ሲል እንዳልኩት ጉዳዩ በአደባባይ በድፍረት የሚካሄድ በመሆኑም ለሚመለከተው ክፍል አቤት ማለቱ ትርጉም የሰጠውም አይመስልም።
እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ትራፊክ ፖሊሶች መዳረሻቸው ላይ ቆመው ትርፍ የጫኑት ሲቀጡ እናስተውላለን፤ ያም ቢሆን ግን ህብረተሰቡ ከትርፍ መጫኑ በላይ የእግር እሳት የሆነበት ያልተገባው የዋጋ ጭማሬ ጉዳይ ነው።
አሽከርካሪዎቹ ከታሪፍ በላይ የሚጠይቁት ገንዘብ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ነው። በጣም የሚያሳዝነው ጭማሪ ለምን የሚል ፤ ለመብቱ የሚከራከር ከተገኘ ‹‹ካልፈለክ ውረድ!›› የሚል ምላሽ ነው የሚያጋጥመው። ድንገትም የተባለውንም ከፍሎ የመሄድ እድል ላያገኝ ሁሉ ይችላል (አድማ ይዘው ሁሉም እንዳይጫን ሊሊያደርጉት ይችላሉ)።
በአካባቢው እየሆነ ያለው ነገር ፍጹም ሕገወጥ ነው፤ ይህንን የአደባባይ የሕግ ጥሰት የሚመለከተው አካል (የአዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ባለሥልጣን) ፈጥኖ ሊያርመው ይገባል ። እስካሁንም ለችግሩ ፈጥኖ የመፍትሄ እርምጃ (ሕጋዊ እርምጃ ) አለመውሰዱ የቱን ያህል ከፍ ያለ የአሰራር ክፍተት እንዳለበት ያመላከተ፤ የቱን ያህል የተጣለበትን የሕዝብ ሃላፊነት መወጣት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደማይገኝ የጠቆመ ነው።
በዚህ ረገድ ባለሥልጣኑ በአካባቢው የተከሰተውንና ነዋሪውን በከፍተኛ ደረጃ ዋጋ እያስከፈለ ያለውን ያልተገባ የትራንስፖርት አገልግሎት በአግባቡ ተከታትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ፈጥኖ ሊወስድ ይገባል። እያንዳንዱ የትራንስፖርት አገልግሎት በተቀመጠለት ታሪፍ መሰረት ተግባራዊ መሆኑንም በተጨባጭ ማረጋገጥ ይኖርበታል ። ይህንን በማድረግ ለተሳፋሪዎች ጥያቄ ፈጥኖ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። ለዛሬ አበቃሁ።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም