እየተጋመሰ ያለው ጥር ወር ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ ወሩ የመኸር አዝመራ የመሰብሰቡ ስራ የሚጠናቀቅበት፣ አርሶ አደሩ አንጻራዊ እፎይታ የሚያገኝበት ወቅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አርሶ አደሩ ይህን ወቅት ሌላ ልማትም እያዋለው ይገኛል፡፡ ይህን ወቅት በአፈር መሸርሸር ሳቢያ ለምነቱ እየተሟጠጠ ያለውን መሬቱን በተፋሰስ ልማት የሚያክምበት ማድረግ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በሀገሪቱ በዚህ ወር የተፋሰስ ልማት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ይከናወናል፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ዝግጅት አድርጎ ነው ስራው እንዲፈጸም የሚያደርገው፡፡ ዘንድሮም እንዳለፉት ዓመታት መንግስት ለዚህ የተፋሰስ ስራ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ከጥር ወር 2015ዓ.ም ጀምሮ ለሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉን አስቀድሞ አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የተፋሰስ ልማት ስራው እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለውም አርሶ አደሩ በዓመታዊው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው ላይ ተጠምዷል፡፡
ሚኒስቴሩ አምስት ሺህ የማኅበረሰብ ተፋሰሶችን ለማልማት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርጾ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሶ፣ የዚህ ወቅት ሥራም ፊዚካል የሚባለው ወይም በውጫዊው የልማት ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እንደ ሀገር ለተያዘው ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጥረትም በጉዳት ከልማት ውጭ የሆነ መሬት በአፈር ጥበቃ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመሬት አቅርቦት የማሻሻል ሥራ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያመለከተው፡፡
በሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ አፈርን በጎርፍ ከመሸርሸር መታደግ የሚያስችሉ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ እርከን በመስራት፣ ጋቢዮን በመገንባት፣ እነዚህ ስራዎች በተከናወኑባቸው አካባቢዎች የዛፍና የመሳሰሉትን ችግኞች በመትከል በተከናወነው የተፋሰስ ልማት በክረምት ወቅት በጎርፍ የሚታጠበውን ለም አፈር ለመቀነስ እየተቻለ ይገኛል፡፡
የአባይ ግድብን ሊደርስበት ከሚችለው የደለል አደጋ መታደጊያው አንዱ መንገድ ይሄው የተፋሰስ ልማት ስራ መሆኑ ግንዛቤ ተይዞበት ለዓመታት የተፋሰስ ልማት ተሰርቷል፤ እየተሰራም ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻውንም ከተፋሰስ ልማት ጋር በማስተሳሰር በበጋ ወቅት የተሰሩትን እርከንና የመሳሰሉትን የአፈር ጥበቃ ስራዎች በክረምቱ የዛፍና የተለያዩ እጽዋት ችግኞችን በመትከል በአካባቢዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
የተፋሰስ ልማትን ማካሄድ ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሀገሪቱ አሁን ብቻ አይደለም በመጪዎቹ ጥቂት የማይባሉ አመታትም ኢኮኖሚዋ ከግብርና ስራዋ ጋር በእጅጉ ቁርኝት እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ ግብርናው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጡን፣ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ማገልገሉን ይቀጥላል፡፡ ግብርናው መዋቅራዊ ለውጥ እስከሚያመጣ ድረስ ብዙ ሊሰራበት የግድ ነው፡፡
ለዚህም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከሚደረግ ርብርብ በተጨማሪ ለምርትና ምርታማነት ወሳኙ የሆነውን አፈር መጠበቅ የግድ ይሆናል፡፡ ለእዚህ የአፈር ጥበቃ ስራ ደግሞ የተፈሰስ ልማት ወሳኙ መሳሪያ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማቱ የአፈር መሸርሸርን ብቻ ሳይሆን ለማስቀረት የሚረዳው፣ የዓለማችን ችግር እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል፣ የዓባይ ግድብን ከደለል ለመታደግ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ አኳያም የተፋሰስ ልማቱ ላይ ርብርብ ማድረግ የግድ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ሀገሪቱ በተፋሰስ ልማት ዓመታትን የዘለቀች እንደመሆኗ በልማቱ በኩል አርሶ አደሩን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በልማቱ ላይ በቂ ግንዛቤ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል፤ አርሶ አደሩ በተፋሰስ ልማቱ ያካበተው እውቀት እንዳለም ይታሰባል፡፡ በመንግስት በኩል ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ይህን ሁሉ አቀናጅቶ ልማቱን ከአሁኑም በላይ አጠናክሮ ማከናወን የዚህ ወቅት ስራ መሆን ይኖርበታል፡፡
እንደሚታወቀው የተፋሰስ ልማቱ በሁለት መንገድ ነው ሲከናወን የቆየው፡፡ አንዱ በሴፍትኔት መርሀ ግብር ሲሆን ሌላው ደግሞ በማኅበረሰብ ደረጃ በዘመቻ የሚካሄደው ነው፡፡ በሴፍቲኔት መርሀ ግብር የሚካሄደው የተፋሰስ ልማት በጀትና ሰራተኞች ተመደበውለት የሚፈጸም ነው፡፡ ሌላውና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተፋሰስ ልማት ደግሞ በማኅበረሰብ ደረጃ በዘመቻ የሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ ነው፡፡
ይህ በማኅበረሰቡ ደረጃ የሚካሄደው የተፋሰስ ልማት የጥር ወርን ይዞ የሚካሄድ እንደመሆኑ ወቅቱን በሚገባ መጠቀም ይገባል፡፡ አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት ያለውን በቂ ጊዜ በመጠቀም፣ ግብርና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በማጠናክር የተፋሰስ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ብዙ መልማት የምትፈልግ ሀገር ናት፣ በአሁኑ ወቅት በእጇ ያለው ዋና የልማት መሳሪያዋ ግብርናዋ ነው፡፡ ግብርናዋ ደግሞ በእርሻ ስራ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከዚህ ግብርና ምርትና ምርታማነትን መጠበቅ የሚቻለው ለተፋሰስ ልማትም ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ በደን መመናመን ሳቢያ የሀገሪቱ ለም አፈር በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ ይህን አፈር መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የተፋሰስ ልማት ወሳኝ ስለመሆኑ ልማቱን በማካሄድ የታዩ ለውጦች አመላክተዋል፤ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ተከትሎ አፈርን ከመሸርሸር መታደግ እንደሚቻል ግንዛቤ ከመጨበጥም በላይ ማድረግ እንደሚቻል ታይቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደርቀው የነበሩ ምንጮች ውሃ ወደ ማፍለቅ የተመለሱበት፤ የተተከሉ ችግኞች ዛፍ በመሆን መሬቱን እየታደጉባቸው ሁኔታዎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአካባቢው ሸሽተው የነበሩ አእዋፋት እና የዱር እንስሳት የተመለሱበት ሁኔታ እንዳለም እየተገለጸ ነው፡፡
ይህ ሁሉ የተፈሰስ ልማቱን አጠናክሮ የመቀጠልን ፋይዳ በሚገባ ያመለክታል፡፡ አርሶ አደሩ ለበርካታ አመታት ልማቱን ያካሄደ እንደ መሆኑ ብዙ ተሞክሮዎችን አግኝቷል፡፡ በዚህ ላይ የግብርና ሚኒስቴር የዘርፉ ባለሙያዎች ምክርና ድጋፍ አብሮት አለ፡፡ ይህን አቅም በሚገባ በመጠቀም የተፋሰስ ልማቱን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም