ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በመባል የሚታወቀው የቱሪዝም ዘርፍ በምጣኔ ሃብት ላቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡ ሀገሮች የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይነገራል። ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው የሰሩ ሀገራት ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። በአንጻሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በቱሪዝም ሀብት የታደሉ ሀገራት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው ማግኘት የሚገባቸው ሳያገኙ ቆይተዋል።
ለዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ለዘርፉ ተገቢ ትኩረት አለመሰጠቱን ተከትሎ ዘርፉ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የቱሪዝሙን ልማት ለማፋጠን የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና አሁን የቱሪዝሙን የእድገት ማነቆ በማስወገድ የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ የዲጅታል መተግበራዎችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በቅርቡ የቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ዲጅታል የሞባይል መተግበሪያ ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበታል። በዕለቱም የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደተናገሩት፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተቋቋመ ጀምሮ ለዘርፉ ልማት እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ለመፍታት የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።
የቱሪዝም ዘርፉ ለማዘመን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የክፍያ ሥርዓቱን የሚያሳልጥ እና በጎብኚዎች ዘንድ መተማመንን የሚገነባ የቱሪስት ስማርት ካርድ ሥርዓት፣ የፕሮሞሽን ሥራዎችን በማቀላጠፍ የቱሪስት መረጃ ፍሰትን ቀላልና ምቹ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ ማበልጸግ መቻሉን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
ይህ የቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን ያበለጸገው ዲጅታል የሞባይል መተግበሪያ በውስጡ የዲጅታል ውጤቶች እና የጉዞ ማበረታቻዎች ያሉት መሆኑን ነው በቱሪዝም ሚኒስቴር የዲጅታል ቱሪዝም ፕሮሞሽን አማካሪ አቶ አማኑኤል አጋዤ የሚገልጹት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ መተግበሪያውን በመጠቀም በአካባቢው ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪስት መስእቦች፣ በአቅራቢያቸው ያሉ ሆቴሎችን እና ባህላዊ ሬስቶራንቶችን እንዲሁም የመገበያያ ስፍራዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ጎብኚዎች የሆነ ቦታ /አካባቢ ላይ ቁጭ ብለው በአካባቢው የሚታዩ ነገሮች ሲፈልጉ በአካባቢው ሊጎበኙ የሚችሉ ቦታዎችን ያቀርብላቸዋል። አካባቢው ድረስ እንዴት መሄድ እንዳለባቸው፣ የሚሄዱበት ቦታ የአየር ንብረት ምን ይመስላል የሚለውን እና ስለቦታው አስቀድመው ማወቅ የሚገባቸው ነገሮች ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ። የሞባይል መተግበሪያ ጎብኚዎቹ ቦታው ድረስ በጂፒኤስ ታገዘው እንዲሄዱ ጭምር የሚረዳ ነው።
“መተግበሪያው ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በተጓዙ ቁጥር ነጥብ እየሰበሰቡ የሚሄድበትን አማራጭ የሚያቀርብ ነው” ያሉት አቶ አማኑኤል፤ አንድ ጎብኚ በጎበኛቸው ቦታዎች ብዛት ነጥብ እየሰበሰበ እንዲያከማች የሚያስችል ነው። ጎብኚው በሰበሰበው ነጥብ ልክ የሆቴል አገልግሎት፣ የመኪና እና የበረራ ቲኬት ቅናሽ ለማግኘት የሚያስችል እድል ይፈጥርለታል። ሌላው መተግበሪያ ለየት የሚያደርገው የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ነው። ቱሪስቶች ሲጎበኙ( ሲዝናኑ) የነበረውን ሁኔታ ወይም የጎበኙትን መስዕብ ፤ ፎቶ ተነስተው ወይም በአጫጭር ቪዲዮ መተግበሪውን በመጠቀም መለጠፍ ይችላሉ። እንደሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደፌስ ቡክ፣ እንደ ዩቲዩብ እና ቲክቶክ በሚደረጉ መስተጋብሮች በለጠፉት ፎቶና ቪዲዮ ልክ መወደድ(ላይክ)፣ ማጋራት(ሼር) እና ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው። ከዚህ በሻገርም ባገኙት ብዙ የመወደድ፣ የማጋራት እና ሀሳብና አስተያየት መጠን ማበረታቻ የሚያገኙበት ሥርዓት የተዘረጋለት ነው። ለእነዚህ ጎብኚዎች ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፉ በማለት ሚኒስቴሩ ማበረታቻ የሚሰጥ እንደሆነ ነው አቶ አማኑኤል የሚያስረዱት።
አንድ ጎብኚ ነጥብ ለመሰብሰብ ብዙ አማራጮች አሉት። የጎበኛቸውን ቦታዎች መወደድንና አጭር ማስታወሻ መጻፍ ነጥብ ያስገኛል። ለምሳሌ ባሌ ብሔራዊ ፓርክ ወደደኩት የሚል እዚያ ላይ አስተያየት ከጻፈ ነጥብ ያገኛል። ሌሎች የለጠፉትን ወይም ያጋሩት ምስል ወይም ቪዲዮ ከወደድ ነጥብ ያገኛል። አንድ ጎብኚ ቢፈልግ ፎቶ ወይም ቪዲዮ ሲለጥፍ ወይም ሲያጋራ ነጥብ ይሰበሰባል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ጎብኚ መጀመሪያ ሲመዘገብ እንኳን ደህና መጣህ ለማለት የማበረታቻ ነጥብ እንደሚሰጠው ያብራራሉ።
ጎብኚ ያልሆኑ ሰዎች የሚያገኙት ነጥብ ትንሽ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አማኑኤል ፤ ምክንያቱም ጎብኚ ካልሆኑ የሚያገኙት ነጥብ የተለጠፈውን መወደድን የሚገልጽ እንጂ ልምዱን ለማካፈል የሚያስችል አለመሆኑን ይናገራሉ። የነጥብ ማበረታቻ መስጠት ዓላማው ሌሎች ጎብኚዎች ለማበረታት የሚጠቅም ነው። ሰዎች የጎበኙትን ቦታ ሲለጠፉ ሌሎች ላይ መነሳሳትን በመፍጠር እንዲጎበኙት እንደሚያደርግ ነው የሚናገሩት። ‹‹ለአብነት እኔ ወንጪ በመጎብኘት ፈረስ ላይ ሆኜ የተነሳሁት ፎቶ ብለጥፍ ሌሎች አይተው እዚህ ቦታ መሄድ አለብኝ ብለው ማነቃቃትና መነሳሳትን እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል›› ይላሉ።
የሞባይል መተግበሪያ ለቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ ከቱሪስቱና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንጻር ነጣጥሎ ማየት እንደሚቻል የሚገልጹት አቶ አማኑኤል፤ ከቱሪስቱ አንጻር ሲታይ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት የት መሄድ፣ ምን መጎብኘት ፣ እንዴት መሄድ እንዳለባቸው፣ በአካባቢያቸው ያለውን የሆቴልም ሆነ ማረፊያ ቦታ፣ ሬስቶራንት እና የመሳሰሉትን መረጃዎች በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲበረታቱ ያደርጋል፤ አገልግሎቶችን በቅናሽ እንዲያገኙ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ ያደርጋል ብለዋል።
ከሚኒስቴሩ አንጻር የቱሪስት መረጃ(ዳታ) በመሰብሰብ የሚረዳ ሲሆን ምን ያህል ጎብኚዎች አንድን መስእብ እንደጎበኙትና የቆይታቸው ጊዜያቸው ለምን ያህል ጊዜ እንደነበር እና ሌሎችን መረጃ የሚሰጥ ነው። ሌላው ማዕከላዊ የሆነ አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ በጎብኝቱ ሂደት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመሰብሰብ ውሳኔ ለመስጠት የሚረዳ ግብዓት ለመስጠት እንደሚጠቅም ነው አቶ አማኑኤል የሚገልጹት። ሚኒስቴሩ እዚሁ ሆኖ ሁሉንም መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱሪስት መስዕቦች በተቻለ መጠን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
ሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ብዙ ሰዎች ተቀብለውት ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ይፋ ከተደረገ በሁለት ቀናት ውስጥ አምስት መቶ በላይ ሰዎች አውርደው ጥቅም ላይ እንዲውል እንዳደረጉት ይገልጻሉ። የእግር ጉዞ አዘጋጆች፣ እየተጠቀሙበት እና የማስተዋወቅ ሥራ እየሰሩበት እንደሆነ ጠቁመው፤ እንደመጀመሪያ ከተጠበቀው በላይ ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል። በተሰጠው ግብረ መልስ መሠረተም ከዚህ በላይ እንዲሻሻል የሚፈለጉ ብዙ ነገሮች ስላሉ እነዚህ ተሻሽለው ማስታወቂያ ከተሰራለት ደግሞ ከዚህ የበለጠ የቱሪዝሙን ማህበረሰብ የመጠቀም ባህልን ከፍ ያደርጋል ይላሉ።
በቀድሞ የቱሪዝም ድርጅት ከዚህ በፊት የበለጸገ ሞባይል መተግበሪያ ምድረ ቀደምት /ላንድ ኦፍ ኦሪጅን/ የሚባል እንደነበር ያስታወሱት አቶ አማኑኤል፤ ይህ የሞባይል መተግበሪያ በሚጫንበት ጊዜ ልክ እንደ ድረገጽ መረጃዎች ብቻ የሚሰጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌ ባሌ ተራሮች፣ ላሊበላ እና የመሳሳሉት የቱሪዝም መስዕቦችን በመጠቅስ ስለመስዕቦቹ የሚያብራራ ነው። ከአርተፊሻል ኢንተለጀንሲና ከጂፕኤስ ጋር የተገናኘ ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ባለመሆኑ ኋላቀር እንደነበር ያብራራሉ።
በግሉ ሴክተር የበለጸጉ ሞባይል መተግበሪያዎችም ቢኖሩም ውስን ቦታዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት። ለአብነት በሆቴል፣ በመኪና እና በመሳሰሉት ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ እንደሆኑ አንስተው፤ ሁሉን አቀፍ የሆነ መረጃን ለማግኘትና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ መተግበሪያዎች በጣት የሚቆጠሩ እንደሆነ አመላክተዋል።
መተግበሪያ እውን እንዲሆን ለማስተዋወቅ ከተለያዩ የማስተዋወቂያ ድርጅቶች ጋር ውል መፈረሙን የሚናገሩት አቶ አማኑኤል፤ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲያስተዋውቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ውጭ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ድረገጾችን በመጠቀም ዲጅታል መተግበሪያዎች ለማስተዋወቅ ፕሮግራም መያዙን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የመተግበሪያውን አጠቃቀሙን የሚሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎችን እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ቪዲዮዎቹ አልቀው ህብረተሰቡ ዘንድ ሲደርስ ብዙዎች እንደሚጠቀሙት ነው ያብራሩት።
የሞባይል መተግበሪያው የሚጠቀሙት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሲሆኑ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች መተግበሪያውን ተደራሽ በማድረግ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሞባይል መተግበሪያ ጋር የማስተሳሰር የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ነው የሚገልጹት። በተጨማሪም ባነሮች በምታዩበት ቦታዎች ላይ በመስቀል፣ ቪዲዮዎች መሥራት አውሮፕላን ውስጥ በመልቀቅ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአየር መንገድ ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑ ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፕሌይ ስቶር ላይ ገብተው ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› የሚለውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም አውርደው በመጫን መጠቀም ይችላሉ። አስተያየት ካላቸው በማስፈር በሚጓዙበት ሁሉን ያዩት፣ የመሰጣቸውን ነገሮች ቪዲዮና ፎቶ እያነሱ በማጋራት ነጥብ ይሰብሰቡ። በሰበሰቡት ነጥብ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲሁም መግቢያዎች ላላቸው መስዕብ የተቀመጡ ማበረታቻውን ቅናሾችን እና ነጻ ማግኘት የሚቻሉበት ሁኔዎች ተመቻችተዋል። በተጨማሪም ነጥብ አሰጣጡ እስከ አምስት ደረጃ ያለውን ስለሆነ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እውቅና የሚያሰጥ በመሆኑ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ እውቅና ለማግኘት ይጠቀሙ ሲሉ አቶ አማኑኤል መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ኢንጂነር መላኩ ሙካ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት የሳተላይት ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ናቸው። ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን የመተግበሪያውን ቴክኒክም የሚመሩት እርሳቸው ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሞባይል መተግበሪያ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው። አንደኛው ጎብኚዎች የተለያዩ መዳረሻዎችን በጂፕኤስ በመጠቀም እንዲያስሱ የሚያደርግ ሲሆን ማንኛውም ጎብኚ መዳረሻዎች ወዳሉበት እንዲሄድና በአካባቢው ያሉ የሆቴል፣ ሬስቶራንት እና የመሳሰሉት የተለያዩ አገልግሎቶችን ቦታው ድረስ መሄድ ሳያስፈልገው ባለበት ቦታ ሆኖ እንዲያወቅ የሚረዳ ነው። በተጨማሪም ለጉብኝት የሚሄድበት መዳረሻ የአየር ፀባይ ሳይቀር አስቀድሞ መረጃ እንዲያገኝ ያስችላል።
ሁለተኛው ጎብኚዎች ለጉብኝት የተለያዩ አካባቢ በሚሄዱበት ጊዜ ያገኙትን የጎብኝት ልምዶችን የሚያጋሩበት ነው። እንደ ፌስቡክ እና ኢንስተግራም ላይ እንደምናየው መረጃዎች የተለያዩ የቱሪስት መስእቦችን በማስተዋወቅ ብዙ ሰዎች እንዲጋሩት ለማድረግ የሚያገለግል ነው።
ሦስተኛው ጎብኚዎች መተግበሪያውን በመጠቀም የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሁ ባህሎች በሚያስተዋወቅበት እና ለሌሎች በሚያጋሩበት ጊዜ በሚሰበስቡት ነጥብ ማበረታቻ የሚያገኝበት ሥርዓት የተዘረጋለት ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክብረ በዓላትንና ፌስቲቫሎችና ብሔራዊ በዓላት ለማወቅ(ማግኘት) የሚያስችል ነው።
ከሞባይል መተግበሪያው በተጨማሪ ሚኒስቴር የሚቆጣጠርበት አድሚንስትሪሽን ዳሽ ቦርድ ተሰርቷል ያሉት አቶ መላኩ፤ ይህንን አድሚንስትሪሽን ዳሽ ቦርድ ተጠቀመው ወደ ሞባይል ሲስተሙ ማስገባት የሚፈልጉት ዳታዎች፣ ስታስቲኮችን እና ሪፖርቶችን እንዲሁም ግብረ መልሶችንም የሚያስገቡት እንደሆነ አመላክተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የሞባይል መተግበሪያ አብዛኛው የቱሪዝም መረጃዎችን እንዲያጠቃልል ተደርጎ የተሰራ ነው። እስከዛሬ ከተሰሩት ሰፊ የሆኑ ሥራዎችን ያካተተ ነው። ሁሉን ነገር በአንድ የያዘ ወደፊትም የተለያዩ ነገሮች እየተጨመሩበት እየሰፋ እና እየደገ የሚሄድ ነው። የቱሪዝም ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችል አንዱ ወጥ የሆነ በቱሪዝም ዘርፍ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ አሟልቶ የያዘ ነው።
መተግበሪያ ይፋ ከተደረገ በኋላ የሰዎችን አመላካከትን እንደቀየር የሚገልጹት አቶ መላኩ፤ ቱሪዝም ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ሀገሩን ማስተዋወቅ አካባቢ ያሉት የተለየ የቱሩዝም መስዕቦች የማወጣት ሥራዎች የመሥራት ግዴታውን መወጣት እንዳለበትም ያመላከተ ነው ይላሉ። መተግበሪያውን በመጠቀም የተለያዩ ሰዎች አካባቢያቸው ያሉ መስእቦችን በማስተዋወቅ በማጋራት ሌሎች እንዲያውቋቸውን በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲኖር ማስቻሉ ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም የበለጸጉት መተግበሪያዎች የውጭ ጎብኚዎች ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ ነበሩ ያሉት አቶ መላኩ፤ ይህም በኮቪድ ወቅት ሀገሪቱ በእጅጉ የጎዳ በመሆኑ ለሀገር ውስጥ ትኩረት በመስጠት ቱሩዝምን እንዲበረታታ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ መተግበሪያ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ስለሀገራቸው በቂ መረጃ ኖራቸው እንዲሰሩ የሚያበረታታ ስለሆነ ማንኛውም ሰው መተግበሪያው ከኦፕ ስቶር እና ከፕሌ ስቶር አውርዶ መጠቀም ይችላል ብለዋል።
በተለይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መተግበሪያውን በመጠቀም የሀገራቸውን የቱሪዝም መስዕቦች እንዲያስተዋወቁ ማድረግ ይጠበቃል። የጎበኙትን የተለያዩ መስእቦችን በማጋራትና በማስተዋወቅ ሀገራቸውን እንዲያውቁ በማድረግ አጋዥ በመሆን ሀገራቸውን መጠቅም እንዳለባቸው ነው አቶ መላኩ ለዝግጅት ክፍላችን ያሳወቁት።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015