ወርቅ ከአፈር ተለይቶ ወርቅ የሆነው በእሳት ተፈትኖ አንጸባራቂ ገጽታን በመላበሱ ነው። ይህ በእሳት ውስጥ አልፎ የፈጠረው አንጸባራቂነቱ ደግሞ ለስሙ ግዝፈትም ከፍ ላለው ዋጋውም ምክንያት ሆኖታል።
ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ናቸው። ከፍ ያለ ታሪካቸው፣ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግስታቸው፣ የሰብዕና ልዕልናቸው፣ ወኔና አልበገር ባይነታቸው፣ ኅብረትና አሸናፊነታቸው እንደ ወርቅ በዘመናት እሳት ተፈትነው የገነቡት ልዕልናቸው ነው። ሆኖም በየዘመኑ በሚገጥሟቸው ፈተናዎች መውጣት መውረዳቸው፤ አልፎ አልፎም በፈተናዎቹ ተደነቃቅፈው መንገዳገዳቸው የማይካድ ሃቅ ነው።
ይሄን የመንገዳገድ ታሪክ ከመቀየር አኳያ ደግሞ በየዘመናቱ የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም፤ ከ2010ሩ አገራዊ ለውጥ በኋላ የተከናወኑ ተግባራት ግን ለችግሮቹ መፍትሄ ይዘው ስለመምጣታቸው መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የለውጥ ማግስት የሪፎርም ስራዎችና ውጤቶቻቸው ሲሆኑ፤ በተለይ የጸጥታ፣ የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥልቅና ምሳሌያዊ የሆነ ማሻሻያ ተጠቃሾች ናቸው።
አገር እንደ አገር ሉዓላዊነቷ ተጠብቆና ተከብራ እንድትኖር፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ የደህንነት ስጋት ሳይኖርበት ሙሉ አቅምና ትኩረቱን በልማት ስራዎች ላይ እንዲያውል ከፍ ያለውን ሚና የሚወጡት የፀጥታ ተቋማት ላይ የተደረገው ሪፎርም ከዕለት ዕለት ከፍ እያለና የኢትዮጵያን የከፍታ ግስጋሴ ልክ እያመላከተ የሚገኝ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ ከለውጡ ማግስት በመከላከያ እና ፌዴራል ፖሊስ ላይ የተደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ሪፎርም፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በድል እንድትወጣ አድርጓል።
በተለይ በመከላከያው ዘርፍ የተሰራው የሪፎርም ሥራ ኢትዮጵያ በውስጥም ሆነ በውጪ ጠላቶቿ የተቃጣባትን አደጋ በብቃት እንድትመክት እና ጥላቶቿን አሳፍራ ሉዓላዊነቷን አስከብራ እንድትሻገር ያደረገ ነው። በኔትዎርክ ተጠልፎ አገራዊ ወኔ እንዲርቀው ተደርጎ የተሰራበትን ተቋም ወደ ኃያልነትና አሸናፊነት ማንነቱ እንዲመለስ፤ ከሜካናይዝድ፣ ከአየር ኃይል፣ ከባህር ኃይል፣ ከቴክኖሎጂና መሰል የጦር ኃይሎች ተነጥሎ እና በአቅም ተዳክሞ እንዲገለጥ የተፈረደበትን ተቋም ሁሉን አቀፍ ኃይል ፈጥሮና በቴክኖሎጂ ተደግፎ፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂውን አውቆ በሚጠቀም የሰው ኃይል ተደራጅቶ በድል ላይ ድል እንዲጎናጸፍ ማድረግ ተችሏል።
ከሁለት ዓመታት ፈታኝ የጦርነት ውሎው ማግስት ከሰሞኑ የተገለጠው እውነትም የዚህ አንድ ማሳያ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያም በፈተናዎች ውስጥ የምትበረታ፣ በችግር ውስጥ የተሻለ እድል መፍጠር የምትችል፣ በጦርነት ውስጥም ሆና የመሻገሪያ አቅም የምትገነባ ታላቅ አገር መሆኗን ያረጋገጠችበት ነው። ምክንያቱም ሰሞኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ሌሎች የጦር ከፍተኛ አዛዦች በተገኙበት የታየው የኢትዮጵያ የጦር አቅም፤ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊቃጡባት የሚችሉ ጥቃቶችን የመመከትና በድል የማጠናቀቅ አቅም ብቻ ሳይሆን፤ ጥቃት ለመፈጸም ያሰቡ ኃይሎች ቆም ብለው ደጋግመው እንዲያስቡ እና ካልተገባ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ነው።
ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልታሳካው እየተጋች ላለችበት የብልጽግና ጉዞ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የሁሉም ነገር መሰረቱም፣ ማሰሪያውም ሰላም ነውና። ሰላም ደግሞ ስለፈለጉትና ስላወሩለት የሚመጣ አይደለም። አንዳንዴም ሰላምን ለማደፍረስ የሚሻ ኃይል ቢነሳ እንኳን አደብ ማስያዝና ያሰበውን ሳያፈጽም ማስቀረት እንደሚቻል አቅም መኖሩን ማሳየት መቻል የግድ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ላለፉት ዓመታት በፈተና ውስጥ ያሳለፈች ቢሆንም፤ በአንድ በኩል ሰላሟን ለማረጋገጥ እየሰራች፤ በሌላ በኩል በተገኘው ፋታ የልማት ተግባራትን ሳታቋርጥ ዘልቃለች። ለሰላሟ መሰረት፣ ለልማቷም አጋዥ የሚሆናትን የሰላም አስከባሪና አጽኚ ኃይልም ገንብታለች።
ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ሂደት ውስጥ የማድረግ አቅም ያለው ኃይል የመፍጠር ዋናው ርምጃ ነው። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሉ እንደነበረውም፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ እና ሌሎችም የደህንነት ተቋማት እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማድረግ አቅም፤ ውጊያን የማስቀረት አቅም፤ ውጊያም ሲጀመር በአጭር የመቋጨት አቅም ያላቸውን ኃይሎች እውን ለማድረግ ተሰርቷል። የዚህ ሥራ ዋነኛ ዓላማም ጠንካራ፣ የማይደፈር እና በቀላሉ የማይቆረጥም ኃይል ሲኖር ጠላት ውጊያን ደጋግሞ እንዲያስብ እና እንዲያስቀር ስለሚያደርግ ነው። ይሄ እውን የሚሆነው ደግሞ የጦር ክንፎች (አየር ኃይል፣ ሜካናይዝድ፣ እግረኛው እና ሌላውም ምድብተኛ) ተናብበው እና በቴክኖሎጂ ታግዘው መስዋዕትነትንና ኪሳራን በመቀነስ በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ድል ማሳካት ሲችሉ ነው።
በዚህ መልኩ የጠነከረ ኃይል መገንባት እና ይዞ መገኘት ደግሞ ለኢትዮጵያ ጸንቶ መቆም ድርሻው ተኪ የሌለው ነው። ከዚህም በላይ የእነዚህ ኃይሎች ከፍ ያለ ልዕልናን መላበስና መያዝ ኢትዮጵያ ልታሳካ ያሰበችውን ልማት እውን እንድታደርግ ምቹ መደላድልን ይፈጥራል። በሌላ ገጹም የኢትዮጵያ የልማት ምንጭም ድልድይም ሆኖ የሚያገለግል ነው። አለፍ ሲልም እንደ ወርቅ ተፈትኖ በተፈጠረ አቅም እና በተገነባ ልዕልና ውስጥ አገርን ከፍ የማድረግ፤ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ድልድይ ሆኖ የማሻገር ድንቅ የተግባር ጉዞ ማረጋገጫም ሕያው ምስክር ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም