ግብርና በኢትዮጵያ ጉርስም፣ ልብስም፣ ህልውናም ነው በሚል ይገለፃል። ይህም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በምግብ እህል ራስን ከመቻል ባለፈ በሀገር ምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ ሕይወት እድገት ውስጥ ያለውን ላቅ ያለ ሚና ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቁን ድርሻ ይዞ የሚገኘው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የበለጠ ተጠናክሮ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ በመንግሥት በኩል የግብርና ሥራውን የማዘመን ተግባር በልዩ ትኩረት መከናወኑ ቀጥሏል።
መንግስት ግብርናውን በበሬ በሞፈርና ቀንበር ከማከናወን ለመውጣት፤ በዝናብ ላይ የተመሰረተውን ግብርና በመስኖ የማጠናከር ስራ ውስጥ ገብቷል። በዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ ሲሆን፣ ባለፈው በጀት አመት 26 ሚሊየን ስንዴ በበጋ መስኖ ልማት ማግኘት ተችሏል።
ግብርናው በአነስተኛ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ሲከናወን ነው የኖረው። ይህም ግብርናው ለዘመናዊ እርሻ ምቹ እንዳይሆን እንዳደረገው በመገንዘብ አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ ስራውን እንዲያከናውን እየተደረገ ይገኛል። የኩታ ገጠም ማሳ እርሻም እየተስፋፋ መጥቷል። ይህ ሁኔታም የአርሶ አደሩን ማሳ በትራክተር ለማረስ፣ ምርቱንም በኮምባይነር ለመሰብሰብ ምቹ እድል እየፈጠረ ነው።
የኩታ ገጠም እርሻ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መስፋፋት የትራክተርን፣ የውሃ መሳቢያ ሞተርንና የኮምባይነርን አስፈላጊነት የግድ እያደረጉት መጥተዋል። በአርሶ አደሮች የህብረት ስራ ማህበራትና በአንዳንድ ጠንካራ አርሶ አደሮች እጅ ብቻ የነበሩት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች አሁን በሌሎች የተለያዩ መንገዶች አርሶ አደሩ መንደር በስፋት የሚገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በፌዴራል መንግስት እንዲሁም በየክልሉ ለየግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። የክልል መንግስታት እንዲሁም የቆላ አካባቢና መስኖ ልማት ሚኒስቴር ትራክተሮችን፣ ኮምባይነሮችንና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሮች በስፋት እያቀረቡ ናቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመኸር እርሻ በትራክተር ሲካሄድ፣ አዝመራውም በኮምባይነር ሲከናወን የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች አመልክተውናል። አንዳንድ የአርሲና ባሌ አካባቢ ወረዳዎች የሜካናይዜሽን አጠቃቀም ከፍተኛ ደረጃ መድረሱንም እየተገለጸ ነው።
እነዚህን የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከውጭ ለሚያስገቡ ቀረጥ ነፃ አሰራር ተመቻችቷል። በሀገር ውስጥም ለአርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ማሽነሪ አከራዮች ማሽነሪዎችን የተወሰነ ገንዘብ ከፍለው ሌላውን ሰርተው ሊከፍሉ በሚችሉበት አግባብ በሊዝ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለማሽነሪ አከራዮች የሜካናይዜሽን ማሽኖችን በብድር በሊዝ እያቀረበ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባንኩ የግብርና ፕሮጀክቶችን በመደገፍና የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ለአምስት ተከታታይ ዙሮች የግብርና ሚካናይዜሽን ኪራይ አገልግሎት በመስጠት ግብርናው ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ድርሻ እያበረከቱ ያሉትን ተጠቃሚ አድርጓል።
የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና ከአራት አመታት በፊት በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በአብዛኛው በግብርና ሜካናይዜሽን ታግዞ እየተከናወነ ይገኛል።
በግብርና ትራንስፎርሜሽንና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ‹‹ትብብር ለአረንጓዴ አብዮት በአፍሪካ›› (አግራ) የኢትዮጵያ ተወካይና የአፍሪካም ፕሮግራም መሪ ዶክተር ጥላሁን አመዴ የግብርና ሜካናይዜሽን ጉዳይ ‹‹የመፈጸም አቅም ጉዳይ ነው›› ይላሉ። የግብርና ሜካናይዜሽኑ የእርሻ ሥራውን በበሬና በትራክተር ማከናወን ብቻ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የእርሻ ሥራ በበሬ ሲከናወን ብዙ ሀብት (ሪሶርስ) ይፈልጋል። ብዛት ያለው የሰው ኃይልና በሬ ማሰማራትንም ይጠይቃል። ይህን ለማሟላት በሚደረግ ጥረት የእርሻ ሥራው መከናወን ባለበት ጊዜ ሳይከናወን ቀርቶ ጊዜ ያልፋል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ የግብርና ሥራ በአብዛኛው ክረምትን መሠረት ያደረገ ነው። ይሄን ጊዜ በወቅቱና በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ደግሞ ምርትና ምርታማነት እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይደርሳል።
‹‹ዝቅተኛ ምርት ሲመረት ደግሞ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት አስተዋጽኦ ሊኖረው ቀርቶ የምግብ ፍጆታንም ለማሟላት ያስቸግራል›› የሚሉት ዶክተር ጥላሁን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገበሬ ምንም በሬ የሌለው፣ወይንም ደግሞ በቂ የሆነ የእርሻ በሬ የሌለው በመሆኑ በአካባቢው አንድ በሬ ካለው ጋር በማጣመር በሬ የሌለው ደግሞ በሬ ያለው አርሶ አደር የእርሻ ሥራውን እስኪጨርስ በመጠበቅ ነው እርሻውን የሚያከናውነው ሲሉ ያብራራሉ። ይህም ከመፈጸም አቅም ማነስ ጋር እንደሚያያዝም ነው የጠቆሙት።
የግብርና ሜካናይዜሽንን መተግበር እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች ለመፍታት መልካም ጎን እንዳለው ዶክተር ጥላሁን ገልጸው፣ የተበጣጠሰ ማሳ ይዞ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለመተግበር መነሳትም ክፍተት ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ መሬቱን ለማረስ፣ ፀረተባይ መድኃኒት ለመርጨትና ተያያዥ ተግባራትን ለማከናወን የአንዱን መሬት አልፎ ሌላኛውን በትራክተር ለማረስ በራሱ አንድ ችግር ነው። በሌላ በኩል የትራክተር አገልግሎት የሚሰጠው ኩባንያ፣ ማህበር ወይንም ግለሰብ የተለያየ ወጭ ስላለበት በእንዲህ አይነቱ መንገድ መስራት አያዋጣውም። በአጠቃላይ የተበጣጠሰ ማሳን በትራክተር ለማረስ ክምቹነትም ሆነ ከዋጋ አንጻር አዋጭ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች በግብርና ሜካናይዜሽን ጥሩ እንቅስቃሴ እንደሚታይ ጠቅሰው፣ በሌሎች ደግሞ ደካማ መሆኑን ያመለክታሉ። ችግሮች እየታዩም በአንዳንድ በባሌ አርሲ አካባቢዎች አርሶ አደሮች በጋራ ማረስና በጋራ ምርት ለመሰብሰብ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ዶክተር ጥላሁን በግብርና ሜካናይዜሽን በኩል የግሉን ዘርፍ ማጠናከር ውጤታማ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ። የማሽኑ መኖርም ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ማሽኑን ሥራ ላይ ማዋል የሚችል ብቃት ያለው የሰው ኃይል ሊኖር እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ይህን በሚገባ ማጠናከር ካልተቻለ ማሽኑ ያለአገልግሎት ሊቀመጥ ይችላል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የጥገና ስራዎችም እርሻው አቅራቢያ ሊኖሩ ይገባል። በብልሽት ከአገልግሎት ውጭ የሆነ ማሽንም በሚሰራበት ቦታ ነው የጥገና ሥራው መከናወን ያለበት። ለጥገና አገልግሎቱን ከሚሰጥበት ቦታ ወደ ሌላ ሥፍራ ለማጓጓዝ መሞከር የጊዜና የወጭ ብክነት ያስከትላል። ይሄ ደግሞ የግብርና ሥራውን ያስተጓጉላል። እነዚህ በአቅም ግንባታና በተለያየ ድጋፍ መቀረፍ ይኖርባቸዋል።
የማሽን አገልግሎት እንዲያቀርብ በሚጠበቀው በግሉ ዘርፍ በኩልም የሚሰጠው አገልግሎት በረጅም ጊዜ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ያለው ግንዛቤም አነስተኛ መሆኑን ዶክተር ጥላሁን ያመለክታሉ። በዚህ ረገድም በረጅም ጊዜ ተጠቃሚነትን ታሳቢ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎችን ለይቶና አደራጅቶ ወደ ሥራው እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀው፣ እነዚህ ኩባንያዎች ከፍ ወዳለ ኩባንያ አድገው አገልግሎታቸውን የተሻለ እንዲያደርጉም ማበረታታት ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ።
ሜካናይዜሽን ለመሬት ለምነትና ለአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ እንዳለውም ነው የጠቆሙት። ‹‹በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጥሩ ገበሬ ተደርጎ የሚወሰደው ደጋግሞ የሚያርስ ነው›› የሚሉት ዶክተር ጥላሁን፣ ‹‹ይሄ አላስፈላጊ ነው። አፈሩን ያበላሻል።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ። ‹‹ደጋግሞ ማረስ መሬት ውስጥ ያለውን እርጥበት ለአደጋ ያጋልጣል፤ ብዙ ካርቦን ያለው በአፈር ውስጥ ነው። ተደጋግሞ በታረሰ ቁጥር የካርቦን አየር ተጋላጭነትን ይጨምራል።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
‹‹ይሄ ደግሞ ለአካባቢ የአየር ለውጥም መፈጠርም ምክንያት ይሆናል›› በማለት ያስረዱት ዶክተር ጥላሁን፤ እነዚህን ስጋቶች መቀነስ የሚቻለው በግብርና ሜካናይዜሽን አሰራር እንደሆነ አመልክተዋል። ትራክተር ከባህላዊ ማረሻ በተሻለ ገባ ብሎ በማረስ ያለውን ችግር ያስወግዳል ብለዋል።
ዶክተር ጥላሁን እንደሚያስረዱት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን መሬት ከማረስ፣ የደረሰ ሰብልን ከማጨድና ከመሰብሰብ ባለፈ ብዙ ጥቅሞችን የያዘ ተግባር ነው። የሜካናይዜሽን ስራ ከማምረት እስከ ገበያ የተሳሰረ ነው። ሜካናይዜሽን የኢንዱስትራላይዜሽን አካል ነው። ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከተቻለ በኋላ ምርቱ ገበያ ላይ ውሎ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት መቻል አለበት።
ምርቱን ጥሬውን ለገበያ በማዋል ብቻ ሳይሆን እሴት የተጨመረበት ምርትና አገልግሎት ያስፈልጋል። የተሻለ ገቢ ማግኘት የሚቻለው ምርቱን የተወሰነ ጊዜ አቆይቶ ገበያ ማውጣት ሲቻል በመሆኑ እንዲህ ያለው አሰራርም አብሮ ሊመቻች ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ ሜካናይዜሽንን ጥቅም ላይ የማዋሉ እንቅስቃሴ አንዴ ያዝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለቀቅ የሚደረግበት ሁኔታ ስለመኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ይህን አስመልክቶ የተጠየቁት ዶክተር ጥላሁን፤ የደርግ አገዛዝን ይወቅሳሉ። ‹‹ የደርግ ሥርዓት በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ የነበረውን የግሉን ዘርፍ ለማጥፋት ሲንቀሳቀስ ሜካናይዝድ የነበሩ እርሻዎች ተወርሰዋል። መሳሪያዎችም ባክነው ቀርተዋል›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
የደርግ ሥርዓት ወድቆ የተተካውም የኢህአዴግ ሥርዓት የሜካናይዜሽን አገልግሎት የበለጠ እንዲዳከም አድርጓል ነው የሚሉት። ከዚህ አንጻር ሜካናይዜሽን በኢትዮጵያ አዲስ አይደለም ግን አልተጠናከረም ብሎ መውሰድ ይቻላል ይላሉ።
አሁን ደግሞ በሜካናይዜሽን ላይ የተጠናከረ ሥራ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ስራው የተጠናከረና ዘላቂነት እንዲኖረው ሰፊ የእርሻ መሬትና አነስተኛ የእርሻ መሬት ባለባቸው አካባቢዎች ምን እንደሚያስፈልግ መለየት፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ እስከ ገቢ ሰፋ ባለ እቅድ መከናወን አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ቅልጥፍናን የሚጨምር ነገርም አብሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት። በአንድ ወቅት ላይ ሰብልን የሚያጠቃ ነፍሳት ተከስቶ ድሮን ጥቅም ላይ የዋለበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰው፣ እንዲህ ያለውን ቴክኖሎጂ ለአንድ ወቅት ችግር ከማዋል ያለፈ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላሉ።
የሜካናይዜሽን አገልግሎትን በመንግሥት ከመፈጸም በግል እንዲከናወን ማድረግ አዋጭ መሆኑን ያመለክታሉ። ለእዚህ ደግሞ ማህበራትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፣ መንግሥት የብድር አገልግሎትና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማመቻቸት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
ዶክተር ጥላሁን በጥሩ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀማቸው ኬንያንና ደቡብ አፍሪካን በአብነት ይጠቅሳሉ። የሀገራቱ አርሶ አደሮች እያንዳንዳቸው ትራክተር ወይንም አጭዶ መውቂያና መሰብሰቢያ ማሽን (ኮምባይነር) እንደሌላቸውም ጠቅሰው፣ የግብርናውን ሥራ የሚያከናውኑት ግን ሜካናይዜሽን መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም መሆን የቻለው ጠንካራ የሆነ የሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ስላላቸው ነው ያሉት ዶክተር ጥላሁን፣ አገልግሎት ሰጭው ቀድሞ ኮንትራት ወስዶ ነው ወደ ሥራ የሚገባው ይላሉ። ኮንትራቱንም መንግሥት እንደሚያስከብር ጠቁመው፣ በዚህ መንገድ አርሶ አደሩም የሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪውም እንደሚያተርፉ ገልጸዋል።
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015