ሰላም ለሰው ልጅ አልፋና ኦሜጋ ነው። መሽቶ እንዲነጋለት ፣ አመታት ተቆጥረው ትውልዶች መጥተው እንዲሄዱ፣ ያሰበውን ሰርቶ በሰራው እንዲረካና ከትናንቶች ዛሬን የተሻለ አድርጎ ለማለፍ ሰላም ወሳኝ ነው።
እንደ ሀገርም ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ አድገት ወሳኝ አቅም ነው። ያለ ሰላም ሀገርን ማሰብ የዋህነት ከዛም በላይ ነው። የአንድ ሀገር ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ሆነ ሰብአዊ ልማቶች ያለሰላም የሚታሰብ አይደለም።
ለዚህ ደግሞ በአንድ ወቅት በሰላማቸው ብቻ ሳይሆን ሰላማቸውን ተከትሎ የተሻለ ሕይወት ማሳያ የነበሩ እንደ ኢራቅ፣ ሶሪያ ፣ ሊቢያን ማየት ተገቢ ነው። እነዚህ ሀገራት ሰላማቸውን ከተነጠቁ ማግስት ጀምሮ እስከዛሬ የሀገር ወግ አጥተው የምናያቸው ሚስጢሩ ሌላ አይደለም፤ የሰላም እጦት ነው።
እነዚህ ሀገራት በእጃቸው ለነበረውና ቀደም ሲል ፈጥረውት /ተከብረው ለኖሩበት ሀገራዊ ገጽታቸው መጥፋት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ሰላማቸውን መጠበቅ አለመቻላቸው ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ኃላፊነት አለመፍጠራቸው ነው።
እኛም ብንሆን በተመሳሳይ መልኩ በእጃችን የነበረውን ሰላም አቅለን በማየታችን የገባንበት ጦርነት ሀገርን እንደሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ ከትቶ እንደነበር የምንረሳው አይደለም። ይህንን ሀገራዊ ስጋት ለመቀልበስም እንደህዝብ ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል መገደዳችንም እንዲሁ።
ዛሬ ላይ ደግሞ የጽልመት ስጋት ተገፍፎ ስለ “ሰላም” ማውራት ከጀመርን ሰነባበትን። በጦርነት እየጠፋ ስላለው ህይወት በየሰከንዱና ደቂቃው ስንጨነቅ የነበረው ጊዜ እየከሰመ ይመስላል። እጅ መጠቋቆም ትተን እጅ መጨባበጥ ላይ ደርሰናል። ስለወደመው ሳይሆን መልሰን ስለምንገነባው እየተነጋገርን ነው። ይሄ ሰላም ሲሆን የሚሰማና የሚደመጥ ትኩስ ዜና ነው።
ሰላም ሲሆን በጥላቻ መተያየትና መረጋገም ሳይሆን ስለጋራ ደህንነት፣ ስለቅንነትና መተባበር ነው የምንነጋገረው። ጥፋተኛውና በጥባጩ ማንም ይሁን ማን ላለፉት ዓመታት በሰሜኑ ክፍል ነግሶ የነበረው ውጥረት፣ ሞት፣ ውድመት በተቃራኒው ሆኖ “ኢትዮጵያ” ስለምትባል የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፣ የአኩሪ ታሪክ ሀገር ሉአላዊነትን የማስከበርና “በቅኝ አልገዛም” እምቢ ባይነት ምሳሌ ስለሆነችው ሀገራችን እየተነጋገርን ከርመናል።
ዛሬ ላይ ማንም ቢያሾልቅ ገበናችንን ያይብን የነበረውን የቤት ግድግዳችንን ሽንቁር ለመዝጋት በጋራ እየሰራን ነው። አውድማ የዋለው ገመናችን ፀሃይ እየሞቀው የነበረው ምስጢራችን ፋታ አግኝቶ በመልካም ነገር እየተካነው ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ገና ነው። ብዙ እርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል።
ብልሃት፣ ትእግስት፣ መተማመን እና ወንድማማችነት ትኩሱን የሰላም ዜና ለማፅናት የሚያስፈልጉ ነገሮች ናቸው። ለዚህ ደግሞ ሁለቱም አካላት በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ከወደሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የምንሰማው መረጃ ይጠቁመናል።
ዳር ድንበሩን ለማስከበር ደፋ ቀና የሚለው የመከላከያ ሰራዊት፣ ጓዳ ጎድጓዳውን ሌት ተቀን የሚጠብቀው የፌደራል ፖሊስ ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በጦርነት ታምሶ የነበረውን ቀጣና ሰላም ለማስጠበቅ እየሰሩ ይገኛሉ። ከሰላሙ ጎን ለጎን የወደሙና የተበላሹ የመሰረተ ልማቶችን ለመመለስ በመብራት ኃይል፣ በኢትዮ ቴሌኮም፤ በውሃና ፍሳሽ እና ሌሎችም ተቋማት የሚደረገው ርብርብ በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው። ይህ የሚያሳየን ሰላም ሲሆን ሀገር እንደሚቃና፣ የጠፋው እንደሚተካ ቁስል እንደሚሽር ነው።
ሰላም ሲሆን ኢትዮጵያውያን ትንፋሽ ወስደው ኑሯቸውን ስለማሻሻል ሀገራቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና ስለማለት ለማሰብ ይችላሉ። መንግስት እጁ የተቀፈደደበትን ጦርነት በሰላም በመቀየሩ ዜጎች ስለሚጠቀሙበት የመሰረተ ልማት ግንባታ መጠናቀቅና አዳዲስ የልማት ግቦችን ወደ ማስቀመጥ ፊቱን እንዲያዞር ያግዛል። ከሰሞኑ የሰማነው “የፀረ ሙስና” ትግል ጅማሮ የዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
“ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንዲሉ በሰሜኑ ክፍል በተደረገ ጦርነት ምክንያት አንገታቸውን በመንግስት ጉያ ውስጥ ወሽቀው ሲዘርፉና ሲመዘብሩ የከረሙ ወንበዴዎች አሁን የሰላም ጭምጭምታ ሲሰሙ መግቢያና መውጫ እየጠበባቸው ይገኛል።
መንግስትም ትንፋሽ ሲያገኝ ክፉና ደጉን ፋታ በማግኘቱ መለየት ሲችል የሀገርን ሌማት የሚቦጠቡጡ ሙሰኞች ላይ በትሩን ለመዘርጋት ሲሰናዳ ተመልክተናል። ይህ የሆነው ግጭቶችና አለመግባባቶችን በሆደ ሰፊነት ለመፍታት ስለተሞከረና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ስለተቻለ ነው።
ዛሬ ላይ “ይህንን ከተማ በድል ተቆጣጠርን፤ ያኛውን ተራራ ደመሰስን” ከሚል ዜና ወጥተን ሕወሓት በእጁ ያሉ ከባድ መሳሪያዎችን አስረከበ ወደሚሉ ዜናዎች ተሸጋግረናል።ይሄ የሰላም ውጤት ነው። ማንም ይሁን ማን፤ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ፍቃደኛ በመሆኑ ሊመሰገንና ሊበረታታ ይገባዋል።
ኢትዮጵያና ዜጎቿ ባለፉት አምስትና አራት ዓመታት በብዙ ጭንቅ ውስጥ አልፈዋል። ለውጡ ይዞት የመጣው ማእበል፣ ሰርተው የሚበሉ፣ አርሰው የሚያድሩ ድሆችን ህልውና ተፈታትኗል። በሰሜኑ ክፍል በተደረገው ጦርነት ንፁሃን ተገድለዋል፣ ሴቶችና ህፃናት ተፈናቅለዋል ሀብት ንብረታቸውን አጥተዋል።
በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍል አሁንም ድረስ ሉአላዊቷን ሀገር የሚፈትኑ ችግሮች እንዳሉ ቢታመንም በሰሜኑ ክፍል የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ሀገር የማዳን ትግል ወደ ሰላማዊ መንገድ መጥቶ መረጋጋት መስፈኑ ግዙፍ ተስፋን የሚጭር ነው።
ሰላም በመሆኑ ምክንያት ለጦር መሳሪያ የሚውል ሀብት ለሀገር እና ለዜጎች እፎይታ ለሚሰጡ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ሲውሉ ማየት ትልቅ ስኬት ነው። ሰላም መሆኑ “የጭቃ ጅራፋቸውን” የመዘዙ ህገወጥ ደላሎችን እና ነጋዴዎችን ቅስም የሰበረ ነው። ህዝቡን በጥብጠው ጥሩ ሊጠጡ የቋመጡ ቡድኖችን ሴራ የሚያከሽፍ እርምጃ ነው።
ሰላም በመሆኑ ዲፕሎማቶች ፊታቸውን የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳዎች፣ የንግድ ስምምነት ስትራቴጂዎች፣ የሀገር ገፅታ ግንባታ ርብርብ ላይ እንዲያደርጉ እድል የሰጠ ነው። በሀገር ውስጥ ሲደረግ የነበረው የሰሜኑ ክፍል ጦርነት መቋጫ በመበሰሩ ምክንያት ባለሀብቶችና በኢንቨስትመንት መዋእለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው አካላት ሃሳባቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑ የሚያግዝ እድልን የፈጠረ ነው።
አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሰላሙን ተከትሎ የመተባበርና አብሮ የመስራት አጀንዳን ይዞ ተሰልፏል። ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እና በሌሎች ምክንያቶች እንዳይመጡ እቀባና ምክረ ሃሳብ በማውጣት ተጠምደው የነበሩ ሀገራት ሃሳባቸውን ቀይረው በአዲስ ቅኝት በሀገሪቱ ስላለው ሰላምና መረጋጋት ማውራት ጀምረዋል።
የሀገሪቱን ገጽታ በተናበበ መንገድ ሲያጠለሹ የነበሩ የመገናኛ ብዙኃንም ዛሬ ከዛ መውጣት ጀምረዋል። ከዛ መንገዳቸው ተመልሰው ሀገራዊ እውነታዎችን የሚገልፁ ዘገባዎችን ዘግበዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የውስጥ ችግሮቻችንን በሰላም ለመፍታት ባሳየነው ሆደ ሰፊነት ነው።
በኮሮና ወረርሽኝና በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የሀገራችንን ገፅታ የምንገነባበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ “ጭርሱን” ሊባል በሚችል ሁኔታ ተዳክሞና ቆሞ ነበር።
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እንዲሁም አርኪዮሎጂካል ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም በእነዚህ ሁለት ክስተቶች ምክንያት የውጪውም ሆነ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ድብታ ውስጥ ገብቶ ስራ አጥነትም ሰፍኖ ነበር። ዛሬ የኮሮና ወረርሽኝ እረፍት በመስጠቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ሆደ ሰፊነት በማሳየቱ ምክንያት ዘርፉ ዳግም መነቃቃትና ማንሰራራት እየቻለ ነው።
ከሰሞኑ በጦርነት አውድማነት መጠቀሚያ የነበሩ የሰሜኑ ክፍል “ሰላም” በመሆኑ ምክንያት ዳግም የቀድሞ ግርማ ሞገሳቸው ተመልሶ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን ሲያስተናግዱ መመልከት ችለናል። ለዚህ “ገናን በላሊበላ” “ጥምቀትን በጎንደር” እና በመላው ኢትዮጵያ እጅግ ባማረና በደመቀ ኢትዮጵያዊ ስነስርዓት ተከብሮ ሲያልፍ አይተናል።
በግጭት አካባቢ የሚኖረው ሕዝባችን የጥይት ድምጽ ሳይሰማ ማደሩ ብቻ ሳይሆን ፤ ወደ ሰላማዊ ህይወቱ በመመለሱ ቀዬዎቹ ሕይወት ሕይወት መሽተት ጀምረዋል። ሕጻናት በግቢ፣ከብቶች በመስክ መቦረቅ ጀምረዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት “ወደ ኢትዮጵያ እንዳትመጡ” ሲሉ የነበሩ የአንዳንድ ኤምባሲዎች ማስጠንቀቂያ ቀርቶ እራሳቸው አምባሳደሮቹ በላሊበላና ጎንደር ሲምነሸነሹ ታዝበናል። ይሄ የሰላሙ ውጤት ነው ብለን በደስታ ተቀብለናል።
በጥቅሉ ሰላም ሲሆን ዜጎች እፎይታን ያገኛሉ። ጥላቻ በፍቅር ይሸነፋል። በግርግር የሚመዘብር አግበስባሽ የሚገባበት እምጥ ይጠፋዋል። በእነዚህ መልካም ነገሮች ምክንያት ሰላምን ምርጫችን ልናደርግ የግድ ይለናል።
ዛሬ የጀመርነው የሰላም ጉዞ ረጅም እርቀት እንዲሄድ የሁላችንንም ርብርብ ይሻል። በጊዜ ቆይታ እንዳንፋዘዝና እጃችን የገባውን እድል እንዳናጣ ቀናነትና ፍቅርን ገንዘባችን አድርገን በጋራ ብንሰራ መልካም ነው።
“ብረትን እንደ ጋለ ነው መቀጥቀጥ” እንደሚባለው ሁሉ ሰላማችንንም እንደያዝነው ተረባርበን እስከመጨረሻው ማስጠበቅ ይኖርብናል ፤ ስለ ሰላም የከፈልናቸው ዋጋዎች ብቻ ሳይሆኑ ላልተገባ ጦርነት የከፈልነው ዋጋ የቱን ያህል ውድ እንደሆነ በአግባቡ ልናጤን ይገባል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015