ኢትዮጵያ በሙስና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷን በመጠቆም፤ በየዓመቱ ቢሊዮኖችን ከሚመዘበሩ ሀገራት መካከል አንዷ ስለመሆኗ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ባለፈው ዓመት ያወጣው መረጃ ያመላክታል። በሀገር ህልውና ላይ የተደቀነው ሙሰኝነት ዛሬም እንደ ትናንቱ ያልተሻገርነው ችግር ሆኗል።
በሃያ ሰባት ዓመቱ የኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ስርቆት እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ ይወደስ ስለነበር ኢትዮጵያዊ የጨዋነት እሴታችንን ፈተና ላይ ጥሎታል፤ ኢኮኖሚያችንን አድቅቆታል፤ ኑሯችንን አመሰቃቅሎታል። በተለይም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰርቶ ሳይሆን ሰርቆ መክበረ እንደዝና መታየት ጀምሯል። የሙስና ተዋናዮቹ ጉዳይ ክብደት እያጣ ፣ተግባሩም ከመጥፎ አተያይ ወደ መልካምነት እየመጣ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን የተጣባቸው ክፉ በሽታ ሆኗል።
በአገሪቱ መረን የለቀቀውን ሌብነት አደብ ለማስያዝ ህግ የማስከበር ዘመቻ መጀምሩ ይታወቃል። …”ኮሚቴ ተቋቋመ..” ወዘተ የሚሉ ዜናዎች እዚህም እዚያም ይሰማሉ። ጅማሮው ይበል ያሰኛል። በተጀመረው ርምጃ መሠረት መንግሥት ከላይ እስከ ታች የተዘረጋውን የሌብነት ሰንሰለትን መበጣጠስ የሚያስችል እርምጃ ይወስዳል ብዬ እጠብቃለሁ ።
በርግጥ ከመጣንበት መንገድ እና መንገዱ ከፈጠረው ጉራማይሌነት አንጻር የመንግሥት የጸረ- ሙስና ትግል በቀላሉ ስኬታማ ይሆናል የሚል እውነት የለኝም። ከፍያለ ቁርጠኝነትና ጥንቃቄ ጭምር የሚፈልግ ነው።
እንደ ሀገር የተንሰራፋውን ሙስና ለመከላከል ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ማቋቋሟ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በሁለት አስርተ ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን እንደሠራ ቢገለጽም ሙስናን ከመቀነስ ይልቅ ተንሠራፍቶ የሀገሪቱ ብሔራዊ ስጋት የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
የሚገርመው ሌብነት የተንሰራፋውም ሌብነትን የሚዋጋ ተቋም በኮሚሽን ደረጃ የተዋቀረውም በነዚያ ዓመታት ነበር። ሆኖም ሙስና መልኩን እየለዋወጠና እየተንሰራፋ ሲመጣ እንጂ ሲከስም አላየንም። አሁንም ያ ታሪክ እንዳይደገም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የነብርን ጭራ ይዞ መልቀቅ አደጋን ማባባስ ስለሚሆን እስከመጨረሻ መፋለም የግድ ይላል።
ሰሞነኛው የሙስና ዘመቻ በተለያዩ ጊዜያት አጀንዳ ነበር። ታዲያ ዘመቻው ፣ ርብርቡ ፣ ዜናው የአንድ ሰሞን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያለሙ አልነበሩም። ዛሬ የትናንት ውጤት እንደመሆኑ፤ ለትግሉ ስኬት ከትናንቱ አካሄድ የዛሬን ጅማሮ በአግባቡ መመርመር ያስፈልጋል።
በሀገራችን የነዋሪነት መታወቂያ ከማውጣት፣ የባንክ ብድር እስከመውሰድ ባሉ፤ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ደረጃዎች በሚገኙ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ሙስና የተለመደ ነው። ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።
መንግሥትም ቢሆን ሀገሪቱ ላይ የሚስተዋለው ሙስና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አምኖ ወደ ርምጃ መግባቱን እያሳወቀ ነው። ጉዳዩ እሳት ከማጥፋት ያለፈና ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ ከሆነ እሰየው የሚያስብል ነው።
የሚወሰደው እርምጃ ትላልቅ አመራሮችን ፣ ሹማምንትን ታሳቢ ያደረገና ከዘመቻ ሥራ በላይ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን ይኖርበታል የሚል የጸና እምነት አለኝ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ታሪክ ራሱን መድገሙ አይቀሬ ይሆናል።
ትናንት አይኑን አፍጥጦ የነበረው ሌብነት በዳቦ ስሙ ሙሰኝነት ክብደት አጥቶ፤ ተግባሩም ከመጥፎ አተያይ ወደ መልካምነት ተለውጦ ዛሬም የሀገር ስጋት ሆኗል። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል“ የሚለው ሀገራዊ አባባልም ለችግሩ መባባስ አቅም ስለመሆኑ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
አባባሉ ስልጣንን የሀብት ማካበቻ አጋጣሚ አድርጎ ይወስዳል። ታዲያ ህዝብ መሪን ይፈጥራል ፤ መሪም ከህዝብ ይወለዳል! የሚል አመክንዮ ባለበት ማህበረሰብ ይህን አባባል ሰምቶ የስልጣን እርካብ የረገጠን ሹመኛ ለሌብነቱ እርሱን ብቻ ተወቃሽ ማድረጉ ተገቢ አይደለም። ህዝቡም እንደህዝብ የራሱን ድርሻ ሊወስድ ይገባል።
ወደ ዋናው ነጥባችን ስንመለስ፤በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስናን የማጥፋት ርብርቡ ከዘመቻ ባለፈ ቀጣይነት ያለው ርምጃ ይሻል። መንግሥት በወንጀሉ ላይ ተሰማርተው በሚገኙ አካላት ላይ የሚኖረው የተጠያቂነቱ ደረጃ ከፍ ፣ ቆፍጠን ፣ ጀገን ማለት አለበት፤ ሁልጊዜ አሳዎችን ብቻ ማጥመዱ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ ሊሆንም አይችልም።
በተጨማሪ ሙስና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ከባድ አደጋ መደቀኑን በመረዳት እያንዳንዳችን ዛሬ ላይ መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ በመክፈል መንግሥት ችግሩን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝና ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ መተባበር ይገባል።
አሁን እንደሚስተዋለው በዜጎች መካከል የሰማይና የምድር ልዩነት አለ። አንዱ የእለት ጉርሱ ጉዳይ ያስጨንቀዋል፤ ሌላው በሙስን እና በተጭበረበረ መንገድ ከሚፈለገው በላይ ሀብት አካብቶ ቅንጡ ኑሮ ይኖራል። ሙስና ጥቂቶችን አበልጽጎ ብዙኋኑን የሚያራቁት በመሆኑ ምስቅልቅል ማህበራዊ ሕይወት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።
ከዚህ አንጻር ሙስናን መዋጋት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆን አለበት። ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ለሁሉም ዜጋ የተመቸችና የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ሙስናን መታገል ያስፈልጋል። አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የሚፈጽመው ሌብነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወላፈኑ ሁላችንንም ሊያቃጥለን ስለሚችል ከመንግሥት ጋር ቆመን ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል ባይ ነን።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015