ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላም ካለ ልማት አለ፤ ኢንቨስትመንት አለ። እንደልብ ተዘዋውሮና ያሻውን ሰርቶ መግባት፣ ነግዶ ማትረፍ ፤ ተምሮ መመረቅ ወዘተ ሁሉንም ነገር ማድረግ ይቻላል። ለአንድ አገር ልማትና እድገት ሰላም ከምንም በላይ ዋጋ አለው፡፡ ለዚህም ነው ሰላም ዋጋው የማይተመን ፣ በምንም አይነት ምድራዊ መመዘኛ የማይሰፈር ለ ሰው ልጆች እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ መ ሰረታዊ ጉዳይ ነው የሚባለው።
አገር ዋልታና ማገር ቢኖረው ምሰሶው ሰላም ከሌለ ግን እንደ አገር መቆም አይችልም። ህንጻ ቢገነባም ሰላም ከሌለ ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ተረጋግቶ አይኖርም፣ ኖሮም አይሰራም ፣ ነግዶም አያተርፍም። ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ ሰላምን ማለምና ስለሰላም መስበክ ይገባል። ያለ ሰላም ምንም ዓይነት ራዕይና ተስፋዎችን ማሳካት አይቻልም፡፡ ከሌሎች አገሮች ለማየት የቻልነውም ይሄንኑ ነው። እነሊቢያ እዚህ ቀረ የማይባል ዘመናዊ ህንጻዎችን በአገራቸው ገንብተው፤ የኢኮኖሚ አቅማቸውን አሳድገው ዜጎቻቸውን ቅንጡ ኑሮን ቢያኖሩም በሰላም መጥፋት ግን ሁሉ ዛሬ ዶግ አመድ ሆኖ ህንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። የመንና ሶሪያም በተመሳሳይ ይሄው እጣ ገጥሟቸው ዜጎቻቸው ለስደት ተዳርገዋል።
ይሄ ዛሬ በዓይናችን ያየነው በቅርበት የምናውቀው ክስተት ነው። ልንማርበት የሚገባ ነው። ‹‹ብልጥ ልጅ ስህተትን ከሰው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱ ›› የሚል አንድ አባባል አለ። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሁለቱም የመማሪያ እድሎቻችን ከፊታችን ቀርበው አይተናልን። ስለዚህ ከሌላውም ከራሳችንም ስህተት ተምረን ዛሬ ያገኘነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መስራት ይጠበቅብናል። አሁን ያገኘነው ሰላም ስንት ወንድሞቻችንን ከሞት ፣ ስንቶቹን ወገኖቻችንን ከመፈናቀልና ከረሃብ እንደታደገ፤ ስንት ለጦርነት ይወጣ የነበረን ፋይናንስ ለልማት እንዳዋለ አይተናል። ስለዚህ ለሰላም ዘብ መቆም ፣ ሰላምን ከምንም ነገር በፊት ማስቀደም ያስፈልገናል።
‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› የሚል አንድ የአበው ተረት አለ። አሁን ግን መባል ያለበት ሰላም ካለ በሰማይም መንገድ አለ ነው። ሰላም ከሌለ በየትኛውም አቅጣጫ በየትኛውም የሰማይ ርቀት ላይ መንቀሳቀስም ሆነ ሌሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ለሰው ልጆች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያስፈልገው ሰላም ነው። ስለዚህ የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ዋነኛው ግዴታና ሃላፊነት የመንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡
በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መርሆዎች ሙሉ ለሙሉ ተተግብሮ ሳያልቅ እንኳን በአገር ላይ የተገኘው ሰላም ቱሪስቶች ያለ ስጋት ወደ አገራችን እንዲፈሱ አድርጓቸዋል። የውጭ አገር ዲፕሎማቶች አገራችንን መጎብኘት እንዲችሉ ዕድል ሰጥቷቸዋል፤ ሌላም ሌላም። ይሄ የሚያሳየው የሰላም ዋጋ የማይተመን መሆኑንና ስለሰላም ሁሉም ወገን መክፈል የሚገባውን ዋጋና መሰዋዕትነት መክፈል እንዳለበት ነው ።
ስራ አጡ ስራ የሚያገኘው ፤ የውጪ ንግድ የሚስፋፋው የአገር ኢኮኖሚ የሚጠገነው ኢንቨስትመንት ሲስፋፋና ባለሀብት በስፋት ኢንቨስት ማድረግ ሲችል ነው። የአገር ውስጡም ሆነ የውጪው ኢንቨስተር ምቹ ሁኔታዎችን ካገኘ ይበልጥ ይሰራል እንጂ አይሸሽም። የሰላም አለመኖር ደግሞ በተቃራኒው ባለሀብትን ያርቃል። ስራአጥ በሀገር ላይ እንዲበረክት ያደርጋል። ወንጀል ይስፋፋል፤ ሙስና፤ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይናቸውን አፍጥጠው ይመጣሉ።
ሰሞኑን በደብርብርሃን ከተማ የተመለከትናቸው ግዙፍ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የሰላም ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ ከሰላም የምናገኘው ትርፍ ሕዝብን ተጠቃሚ አገርን ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ግለሰብን በቤተሰብ ደረጃ ቤተሰብን በኅብረተሰብ ደረጃ ኅብረተሰብን እንዲሁም አገርን የሚለውጥ ነውና ትኩረት ልንሰጠው ይገባል።
ለኢንቨስትመንት በተሰጡት መሬቶች ላይ የታቀዱት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ስራ ካልገቡ የአገራችንን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች መቅረፍ አንችልም፡፡ የኑሮ ውድነትን መለወጥ የሚቻለው በዘላቂነት ምርታማትን በማሳደግ ነው፡፡ ምርታማነት የሚያድገው ደግሞ የተጀመሩ አምራች የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ በመሆኑ ሁሉም አካል በየአካባቢው ያለውን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015