ሰላም ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? በጣም ቆንጆ ነበር እንዳላችሁኝ እርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የጥምቀት በዓል የተከበረበት ነው፡፡ ልጆች በዓል እንዴት ነበር? በባህል አምራቹና ደምቃቹ እንዳሳለፋቹት እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔጋ በጣም ቆንጆ ነበር፡ ፡ በአል ሲመጣ እንኳን አደረሳችሁ መባባል ባህላችን ነውና እንኳን ለእየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ልጆች ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ስለጥምቀት በዓል ነው፡፡ በኢትዮጵያ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩ የሃይማኖት በአል አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ሀይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ ባሻገር በአደባባይ የሚከበርና በርካታ ሰዎችን የሚያሳትፍ በዓል ነው። ልጆች የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ በአደባባይ እንዲከበር የተደረገው መቼ እንደሆን ታውቃላችሁ? በኢትዮጵያ ታቦት ተሸክሞ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡
ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ ናዖድም ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ታቦተ ህጉ ወደ ጥምቀተ ባህሩ በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመዝሙር፣ ወንዶች በጭፈራና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡
ልጆች የጥምቀት በዓል ዋዜማው ከተራ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳስ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመፆር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ታጅበው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ ቤተ ክርስቲያን ጊቢ እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ” እንደሚባለው ከበአሉ በፊት ያዘጋጁትን ባህላዊ የሃገር ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ለዚህ በዓል ቀን የሚለበሰው ነጭ ልብስ ነው፡፡ አንዳንዶች አንድ ሰፈር የሚኖሩ ወይም ጓደኛሞች ከሆኑ በህብረት አንድ አይነት ልብስ በማሰፋት ይለብሳሉ፡፡
ታቦታት ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በህዝበ ክርስቲያኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ ዳቆናትና ቀሳውስት በባህረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያና ፅናፅን እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭና በወርቅ ቀለም ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረውና ተውበው፤ የክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው ዜማ ያቀርባሉ። በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሃንስ የተጠመቀበትን ተምሳሌት በማሰብ ስለሚከበር ህዝበ ክርስቲያኑ ለዚህ በዓል ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ የጥምቀት በዓል ጥር አስር እና ጥር አስራ አንድ ይከበራል፡፡ ጥር አስር ታቦታቱ ከማደሪያቸው ወጥተው ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ታጅበው የሚሄዱበት ሲሆን ጥር አስራ አንድ ደግሞ ታቦታቱ በተመሳሳይ ታጅበው ወደ ቤተ መቅደስ የሚገቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ጧት ምእመናኑ ከየቤታቸው ወጥተው የታቦታቱ ማደሪያ ድንኳኖች ወዳሉበት በመሄድ በካህናቱ ፀበል ይረጫሉ፡፡ በነገራችን ላይ ልጆች የከተራ ቀን እዛው ታቦቱ የሚያድርበት ቦታ የሚያድሩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡
ልጆች የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡
ልጆችዬ በጥምቀት የሎሚ ውርወራ አለ ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ አይደል? በዚህ በአል ላይ ከሃይማኖታዊ ስርአቱ ባሻገር የሚከወኑ ባህላዊ ስርአቶች አሉ፤ እነዚህ ባህላዊ ስርአቶች የውጭ ዜጎችን ቀልብ የሚስቡና ለሀገሪቱም የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ናቸው፡ ፡ ይህንን በዓል ለመታደም ባህር አቋርጠው የሚመጡ የውጭ ዜጎች ለሚጠቀሙት ነገር በሙሉ በዶላር ይከፍላሉ፤ ታዲያ ልጆች ኢትዮጵያ ገቢ አገኘች ማለት አይደል? ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበትና በጋራ የሚጫወትበት ዕለት ነው።
የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሀገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ይታደማሉ፡፡ ይህ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በጎንደር፣ በላሊበላ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱምና በአዲስ አበባ ከተሞች በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ ክርስቲያኑ ከውጪ ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ ታዲያ በዚህ በዓል ላይ ያስገረማቸውን ነገር በማስታወሻነት ለማስቀመጥ የተለያዩ ሰዎች የፎቶና የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን በመጠቀም እያነሱና እየቀረፁ ያስቀራሉ፤ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ደግሞ ለሌሎች በማሳየት ለቀጣይ አመት እንዲመጡ ይጋብዟቸዋል፡፡
እንግዲህ ልጆች የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ዳራው ይሄን ይመስላል ሃገራችን ኢትዮጵያ እነዚህን የመሰሉ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች የሚተርፉ በርካታ ባህሎች ያላት ኩሩ ሀገር ናት፡፡ ስለዚህ ያሉንን በርካታ ባህላዊ እና ይማኖታዊ በአላትንም ሆነ የተለያዩ ቅርሶችና ሃብቶች ጠንቅቀን መወቅ እና ለሌሎችም ማስተዋወቅ አለብን፡፡ ልጆች እናንተም እንዚህን ባህሎች እና በዓላት ማወቅ እና ለማያውቁት ማሳወቅ አለባችሁ፡፡ ለዛሬ እዚህ ላይ ላብቃ ሳምንት በሌላ ፅሁፍ እስክንገናኝ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ፡፡
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም