ሙዚቃ ሕይወት ነው፤ ይሄ እሙን ነው። ሙዚቃ ሕይወት እንዲሆን አስቀድመው ያላቸውን ነገር በሙሉ ለሙዚቃ የሚሰጡ ታላላቅ የሙዚቃ ጠቢባን ደግሞ የሙዚቃ ሕይወት ካስማ ናቸው። እነርሱ በልዩ ፈጠራ ተጠበው ሙዚቃን ይወልዷታል፤ ነብስ እየዘሩም ሕይወት እንዲኖራት ያደርጓታል።
ኢትዮጵያ የታላላቅ የሙዚቃ ፈጣሪዎች መፍለቂያ እንደመሆኗ በየዘመናቱ ለሙዚቃ ተፈጥረው ለሙዚቃ የኖሩና ሙዚቃን ያኖሩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ድምጻዊያንን ማንሳት ይቻላል።
በዛሬው የዝነኞች ገጻችን ከሰሞኑ የጥምቀት በዓል ላይ “ሶባ” የተሰኘውን 26ኛ የሙዚቃ አልበሟን ለበዓል ስጦታ ይዛ ብቅ ትላለች ተብላ የምትጠበቀውና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ገናና ስም ስላላት ታላቅ ድምጻዊት የሕይወት ጉዞ እንዲሁም የሙዚቃ ስራዎቿና አዲሱን የአልበም ስራዋን ጨምሮ አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት ወደናል።
ብዙዎች ቆመው ካጨበጨቡላቸውና ክብርና አድናቆትን ከቸሯቸው ሴት ድምጻዊያን መሃከል አንዷ የሶል ሙዚቃ ንግስቷ አስቴር አወቀ ለመሆኗ ምንም አያጠራጥርም። ከ70ዎቹ ጀምሮ በጣም ብዙ የሙዚቃ ስራዎችን በመስራት ለረዥም አመታት በርካታ ስራዎቿን ለሕዝብ በማቅረብ የሙዚቃ አፍቃሪያንን የሙዚቃ ጥም አርክታለች።
አስቴር አወቀ ወደ ሙዚቃው አለም የተቀላቀለችው ገና በ13 አመቷ ቢሆንም በዚያ እድሜዋ የማይጠበቅ ግሩም የሆነ የሙዚቃ ተሰጥኦ ባለቤት መሆን በመቻሏ ከአድማጮች አልፋ የሙዚቃ ባለሙያዎችንም ጭምር ማስደመም የቻለች ታላቅ የሙዚቃ እንስት ናት። ጅማሬዋን የተመለከቱ ሁሉ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ትልቅ ተስፋን ጥለውባታል። እሷም ይህንን ተስፋ በማለምለም የሙዚቃውን አለም ለማነቃቃት ችላለች።
የሙዚቃ ሙያዋን የጀመረችው በሀገር ፍቅር ቲያትር በድምፃዊነት እና በተወዛዋዥነት በመቀጠር ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ የውዝዋዜ እና የዘፈን ስራዎቿ ጊዜ የብዙነሽ በቀለ ፣ሂሩት በቀለ እና የሙሉቀን መለሰን ስራዎች በመጫወት እንደጀመረች ትናገራለች። በወጣትነት እድሜዋም ከበርካታ እውቅ ባለሙያዎችና የተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር በመጣመር ስሟን ለማስጠራት የቻለችባቸውን ስራዎች በየዘመኑ ለመስራት በቅታለች። ለአብነት ያህልም ከኮንቲኔንታል ባንድ፣ ሆቴል ዲአፍሪክ ባንድ፣ አይቤክስ ባንድ እና ሸበሌ ባንዶች ጋር የተለያዩ ዝግጅቶችን አቅርባለች።
ከዚያም በዝነኛው አሊ ታንጎ እገዛ ከባንድ ወጥታ በራሷ መዝፈን የጀመረችው አስቴር አወቀ፣ በተለይ ከውብሸት ፍስሃ ጋር በመሆን ነጠላ ዜማዎችን በታንጎ ሙዚቃ ቤት አከፋፋይነት ለሕዝቡ ማድረስ ጀመረች። ዘጠኝ የተለያዩ ካሴቶችን ለአድማጭ ያቀረበችው አስቴር “ሙናዬ” የተሰኘ አልበሟን ካሳተመች በኋላ ወደ አሜሪካን አቀናች።
በዚህ ጊዜ አስቴር ከሙዚቃው ተነጥላ ወደ አሜሪካን ለመሄድ ባትፈልግም ነገር ግን ጉዞዋን የግድ ያደረገባት አንድ ምክንያት ነበር። ይሄውም አስቴር በሙዚቃው ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቷም ጎበዝ ነበረችና ቤተሰቦቿ ደግሞ በሙዚቃው ሳይሆን በትምህርቷ ገፍታ እንድትሄድ በማሰብ ዘጠኝ የተለያዩ አልበሞችን ከሰራች በኋላ ትምህርቷን እንድትቀጥል ነገሮችን አመቻችተው ወደ አሜሪካን ለመላክ ተሰናዱ።
በመጀመሪያ ላይ በቤተሰቦቿ ግፊት ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ እሷም የዘፈን ህይወት ይህን የመሰለ ውጤትን እንደሚያመጣ በወቅቱ እርግጠኛ ባለመሆኗ የዘፈኑን ሙያ ወደጎን በማለት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1981 ለትምህርት ወደ አሜሪካን አገር፣ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ እንደተጓዘች እራሷ በአንደበቷ ትናግራለች። ሆኖም ግን ሙዚቃውን ጥላ ሳንፍራንሲስኮ የገባችው አስቴር ነገሮች ሁሉ እንዳሰበችው አልሆን ይላታል። ሙዚቃዎቿ በልቧ ሽው እያሉ ሆድ ያስብሷታል፣ እሷ ከዚህ ማዶ ሆና ከወዲያ ማዶ ይጣሯት ጀመሩ። ኑሮውም ለየቅል እየሆነ ደስታን ስለነፈጋት ደስታዋን የምታገኝበትን ስለትክክለኛ ቦታዋ ማሰብ ጀመረች። ለሁለት አመታት ያህል በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከዚያው ከቆየች በኋላ ያቆመችውን የሙዚቃ ሕይወት የምትቀጥልበትን የሁለተኛውን ምዕራፍ አጋጣሚ አገኘች። በወቅቱ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግብዣ ያቀርቡላት ነበርና ከብዙ ማሰላሰል በኋላም ግብዣቸውን ተቀብላ ወደ ዋሽንግተን በመጓዝ ኢትዮጵያ ላይ ሞርዳ ግሩም ቅርጽ ያሲያዘችውን ግሩም ድምጿን በምድረ አሜሪካ ማስረቅረቅና ታዳሚውን ሁሉ አጃኢብ ማሰኘቷን ቀጠለች።
በሙዚቃው አለም ውስጥ በርካቶች በየጊዜው ብቅ እያሉ ዝነኝነታቸውም ብልጭ እያለ ሲከስም አስቴር አወቀ ግን በየዘመናቱ ዝነኝነቷን ከስራዎቿ ጋር እያደሰች እስከዛሬም ድረስ በሁሉም ኢትዮጲያዊና የሙዚቃ አፍቃሪ ልብ ውስጥ መዝለቅ የቻለች ድምጻዊት መሆኗ ለየት ያደርጋታል። ላለፉት 30 አመታት ገደማም ሙያዋን እያሳደገች ዝነኛ ሆና የዘለቀች ድምፃዊት ናት።
አስቴር በስራዋ የሀገሯን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የውጭ ሀገር የሙዚቃ አድማጮች ቀልብ መሳብ በመቻሏ ከብዙ የሌላ ሀገር ዜጎች አድናቆትን ከማትረፏም ባሻገር ከተለያዩ የሙዚቃ ሰዎችና ካምፓኒዎች ጋር ጭምር የስራ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ችላለች። በዚህም ከሲቢኤስ ኮርፖሬሽን ጋር የሰባት አመት ኮንትራት ለመፈራርም በቅታለች። በተመሳሳይም ከሌላ ከእንግሊዝ ሀገር ካምፓኒ ጋር ሌላ ኮንትራት ተዋውላ ስራዎቿን አበርክታለች። ታዋቂው ታይም መፅሄትም ላይ በአዲስ አይነት የሙዚቃ ስልት ዘርፍ ላይ ትልቅ አድናቆትን ተሰጥቷታል። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1990 በወጣው “ካቡ” በተሰኘው አልበሟ ‘CMJ New Music Charts’ ላይ ለአራት ሳምንታት ከፍተኛ ቦታ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን በ’Billboard’s World Music Charts’ ላይ ደግሞ ለአስር ሳምንታት በአስር ምርጥ ዝነኛ ሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ ተካቶ ቆይቷል።
አስቴር አብዛኛውን ቆይታዋን ያደረገችው በውጭ ሀገራት ላይ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ትልልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በጃንሜዳ፣ አዲስ አበባ ስታድየም፣ ሸራተን አዲስና ሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ ጊዜያት አድርጋለች። ከዚህ ባሻገር በሀገራችን በተደጋጋሚ እየደረሰ በነበረው የረሃብ አደጋ ሰለባ የሆኑትን ወገኖች ለመርዳት በተደረገው ጥረት “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” የሚለውን መሪ መፈክር ተቀብላ ወደሃገሯ በመምጣት በሙያዋ አስተዋፅኦ አበርክታለች።
ለኢትዮጵያ ሀገርዋ ያላትን ፍቅርም ጥልቅ በሆኑ የሙዚቃ ስሜቶች በማንጎራጎር ሀገር ወዳድ የሀገር ልጅ መሆኗን አስመስክራለች። በአንድ ወቅት የራስሽን ዘፈን ስትሰሚ ምን ይሠማሻል? ተብላ ስትጠየቅ እንዲህ በማለት ነበር የመለሰችው “ተለዋዋጭ ነው፣ በወጣትነት ጊዜዬ በጣም አፍር ነበር፤ የኔን ዘፈን ሳልዘፍን መኪናዬ ውስጥ አልገባም ነበር፣ የኔን ዘፈን ሳልዘፍን እቤቴ አልገባም ነበር። ምክንያቱም ሁሌም በሰማሁ ቁጥር ይህን እንዲህ ማድረግ ነበረብኝ የምላቸው ስሜቶች ይሰሙኝ ነበርና። አሁን ግን ዘፈኖቼን በሰማኋቸው ቁጥር በጊዜው የነበሩትን ነገሮች ቁልጭ አድርገው ስለሚያስታውሱኝ ደስ ይለኛል።”
በሌላ ጊዜ ደግሞ በምኒሊክ መፅሄት በተደረገላት ቃለ መጠይቅ ላይ እራሷን በራሷ እንድትገልፅ ተጠይቃ የሰጠችው ምላሽ “አስቴር አወቀ በጣም ደግ፣ ስስ ቆዳ ያላትና ትልቅ ለመሆን የምትፈልግ ሴት ናት። መፈቀርም ማፍቀርም የምትፈልግ ናት። ሌላ ትርጉም ሊሰጣት አይገባም ከተፈቀረች ይበቃታል። ሌላ ነገር አትፈልግም” የሚል ነበር።
የአንድ ሴት ልጅ እናት የሆነችው አስቴር አወቀ የግል ህይወቷን ከሰው ሸሸግ አድርጋ ከአደባባይ ይልቅ ከእይታ ወጭ ሆኖ መስራትንም የምትመርጥ አይነት የሙዚቃ ሰው ናት። በስራዎቿም ስኬታማና የተዋጣላት ብትሆንም ትልቅ የመድረክ ፍርሃት እንዳለባት ጭምር ትገልጻለች። ይሁን እንጂ ከመድረክ ላይ ቆማ ስታቀነቅን ፍርሃቷን ወደሚያሸንፍ ሙዚቃዊ ተመስጦ ገብታ ሌሎችንም ስለምታስገባ ማንም ይህንን ሊያስተውልባት አይችልም። እሷ በድምጽ ብቻ ሳይሆን በውዝዋዜና ዳንሱም የተካነች በመሆኗ የመድረክ ላይ ትርኢቶቿ መሳጭና የቀዘቀዘ ውስጣዊ ስሜትን የሚያግሉ ናቸው። እሷ ቆማ እያቀነቀነች በእስክስታና ዳንሱ አብሯት የሚውረገረግ እንጂ ቁጭ ብሎ የሚመለከት አይኖርም።
ሙዚቃዎቿ ከጆሮ አልፈው የልብን ግርግዳ የሚነቀንቁ በመሆናቸው ብዙዎች ሙዚቃዎቿን እያደመጡ ከውስጣዊ ስሜታቸው የመነጨ የእንባ ጅረት ከአይኖቻቸው አፍሰዋል። ደጋግመው እያደመጡት ግጥሙ ከአንደበታቸው ዜማውም ከልባቸው አልጠፋ የሚላቸው በርካቶች ናቸው። ሙዚቃዎቿ በአብዛኛው በሀገርና ፍቅር ላይ የሚያጠነጥኑ ቢሆኑም በየዘመናቱ በሰራቻቸው ስራዎች ያልዋኘችባቸው የሀሳብ ባህሮች እምብዛም አይስተዋሉም።
በዘመን አይሽሬ ድምጿ እና ከመድረክ አያያዟ በተጨማሪ በራሷ ተወዳጅ ግጥምና ዜማዎቿ የምትታወቀው ድምጻዊቷ ከዚህ በፊት በነበራት ስኬታማ ቆይታዋ የሸክላ አልበሞችን ጨምሮ ሃያ አምስት የሚደርሱ ዘመን አይሽሬ ተወዳጅ የሙዚቃ አልበሞች እና ሁለት ነጠላ ዘፈኖችን ለሙዚቃ አፍቃሪያን ማድረስ የቻለች ሲሆን፣ እነሆ አሁን ደግሞ ሀያ ስድስኛ የሆነውን “ሶባ” የተሰኘ አዲስ አልበም ይዛ ከተፍ ብላለች፡፡ ይህንንም መረጃ በያዝነው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ የተዋወቀውና ከመቶ በላይ አንጋፋና ወጣት ተወዳጅ ድምጻዊያንን በጋራ ለመስራት ያስፈረመው ሰዋሰው የተሰኘው መልቲ ሚዲያ ገልጿል። አስቴር አወቀ ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር የተፈራረመችውም ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ሲሆን በወቅቱም የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስነ-ስርዓቱ ላይ ታድመውበት ነበር።
አዲሱ አልበሟ አስር ስራዎችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህ መሃከልም አንደኛው ሙዚቃ ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ እጅግ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በምስል ተቀነባብሮ ተዘጋጅቷል። አድናቂዎቿና የሙዚቃ አፍቃሪያን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ይሄው አልበሟም ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተለቆ በደማቁ የጥምቀት ሳምንት ሌላ ድምቀት ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም የሚለቀቅበት ጊዜ ለአንድ ወር መራዘሙን መረጃዎች ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም 25ተኛ በነበረው ጨዋ የተሰኘው አልበሟ የሶል ንግስትነቷን በሚገባ ያረጋገጠችበት ሲሆን በ26ተኛው ሶባም የበለጠ የምትደመጥበት የምን ጊዜም ምርጥ አልበሟ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም