ሰላም ለዜጎች ወጥቶ የመግባት፣ ሰርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት፣ እንዲሁም በሕይወት የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፤ በአገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ውስጥ ተኪ የሌለው ጉዳይ ነው። ያለ ሰላም ልማት፣ ያለ ሰላም ሰርቶ መኖር፣ ያለ ሰላም ወልዶ መሳም፣ ያለ ሰላም ወጥቶ መግባት፣… በጥቅሉ ያለ ሰላም ምንም ማድረግ አይቻልም። ለዚህም ነው ሰላም ከሁሉም በላይ ለአንድ አገር እና ለሰው ልጆች ሁሉ በእጅጉ አስፈላጊ ነው የሚባለው።
በኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር ውስጥ እየወደቀ በመጣው ሰላም ምክንያት፤ በተለይ ከ2005 ዓ.ም በኋላ ለውጡን በፈሩ ኃይሎች አቀጣጣይነት በበርካታ ቦታዎች በተለኮሱ ግጭቶች፤ በሂደትም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት አገር እና ሕዝብ ወድ ዋጋ ከፍለዋል።
በዚህም ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ከፍ ላለም የሥነልቡና ቀውስ ተዳርገዋል፤ ሀብት ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ከሞቀ ቤትና ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግርና እንግልት ተዳርገዋል። አገርም እንደ አገር ዜጎቿን ብቻ ሳይሆን በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብቷን አጥታለች። ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መልክና መገለጫቸውን በመቀያየር አንድ ጊዜ ብሔርን፣ ሌላ ጊዜ ሃይማኖትን፣ ሌላም ጊዜ ሌላ አጀንዳ በመፍጠር እዚህም እዚያም በሚለኮሱ ግጭቶች በርካታ ችግሮች እየታዩ ናቸው።
ይህ ግጭት እና አለመረጋጋት ዜጎችን ላልተረጋጋ ኑሮ፣ አገርንም ለከፋ ችግር እየዳረጋት ብቻ ሳይሆን፤ በተለይም በኦሮሚያ ክልል እና አጎራባች አካባቢዎች ላይ እንደ አሸባሪው ሸኔ ላሉ ኃይሎች አጋጣሚውን ላልተገባ ዓላማቸው እንዲጠቀሙበት ዕድል የፈጠረም ሆኗል። ለምሳሌ፣ አሸባሪው ሸኔ በወለጋ፣ በሸዋ፣ በጉጂ እና በሌሎችም የክልሉ ዞኖች ላይ በሚፈጽማቸው የሽብር ተግባራት በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀልና ከፍ ላለ ሥነልቡናዊ ጫና የዳረገ ሲሆን፤ በሀብትና ንብረት ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት ማድረሱ የሚታወቅ ነው።
ይሄን የሽብር ቡድኑን የሽብር ተግባር ከመግታት አኳያም መንግሥት የሰላም ማስከበር ስራን እያከናወነ ሲሆን፤ በተወሰደው ርምጃም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላትና አመራሮች እጅ በመስጠት ላይ እንደሆኑ እየተገለጸ ነው። ተቆራርጠው የቀሩትም ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች እየሸሹ በመበታተን ላይ ይገኛሉ። ይሄ ደግሞ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለውን ርምጃ ውጤታማነት የሚያሳይ ሲሆን፤ ይሄን የሰላም ማስከበር ርምጃ የበለጠ ውጤታማና የሚገኘውን ሰላምም ዘላቂ ከማድረግ አኳያ የየአካባቢውን ሕዝብ አሳትፎ መስራት ወሳኝ መሆኑም ታምኖበት በዚሁ ላይ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ በወለጋ የተለያዩ ዞኖች እየተንቀሳቀሱ ከየአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር እየተወያዩ ሲሆን፤ በዚህም ኅብረተሰቡ ይሄንን የሽብር ኃይል በመታገልም ሆነ ሌሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ከመንግሥት ጎን ሆኖ የድርሻውን መወጣት በሚችልበት አግባብ ላይ መክረዋል። በምስራቅ ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ተገኝተው ከየዞኖቹ ከተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይትም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
በክልል ደረጃ ችግሩ ከፍ ብሎ በሚስተዋልባቸው በተለይም ምዕራብ እና በምስራቅ ወለጋ አከባቢዎችም ሆነ በጉጂ፣ በምዕራብ ሸዋ እና ሌሎችም አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደ የመጣውን የሰላም ችግር ከመፍታት አኳያ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ካለው የሰላም ማስከበር ርምጃ ጎን ለጎን ሕዝቡን የማወያየት እና የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ እየተሄደበት ያለው መንገድ ተገቢም፤ ለውጤት የሚያበቃም ነው። ምክንያቱም ልማት ብቻ ሳይሆን ሰላምም ሕዝብን ሳያሳትፉ በአንድ ወገን የሕግ ማስከበር ርምጃ ብቻ ከግቡ የሚደርስ አይሆንምና ነው።
በመሳሪያ አፈሙዝ ብቻ ሰላምን ለማስፈን የሚቻል ቢሆንም እንኳን፤ የተገኘውን ሰላም ማቆየት የሚቻለው የሰላም ሂደቱ ላይ ኅብረተሰቡን አወያይቶና አሳምኖ ማሳተፍ፤ ሕዝቡንም የሰላሙ ባለቤት ራሱ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ነው። ስለሆነም በጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራው በተጨማሪ የተገኘውን ሰላም ማጽናት እና ዘላቂ ማድረግ ይገባል። ኅብረተሰቡ ያመነበትና የተሳተፈበት የሰላም ስራ ባለቤቱ ራሱ ሕዝቡ ስለሚሆን በባለቤትነት ይዞ ያዘልቀዋል። በመሆኑም የሚፈለገውን ሰላም ለማምጣት ሕዝብን አሳትፎ ለመስራት አመርቂ ውጤት ይኖረዋልና የተጀመረው ሕዝባዊ ውይይት ውጤታማ በሆነ መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም