በአንድ ወቅት የአንድ ማህበር አባላት የደም ልገሳ እንዲያካሂዱ የሚያነሳሳ ምክንያት ተከሰተ። ከሙስተቅበል የልማትና መረዳጃ ማህበር አባላት መካከል የአንድ ሰው ቤተሰብ አባል ትታመማለች። በወቅቱም የህመምተኛዋ ቤተሰቦች ደም እንደሚያስፈልጋት ይገለጽ ላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ የደም ባንክ ለታማሚዋ የሚያስፈልገው ደም እንደሌለ ይገልጻል። ይህ ጉዳይ ከጓደኛሞቹ ዘንድ ይደርሳል። በወቅቱም ተጣድፈው አስፈላጊውን ደም ይለግሳሉ። ለታማሚዋ ደም ከለገሱ በኋላ ወዲያውኑ ለቀጣይ መምከር ያዙ።
የማህበሩ አባላት በዚያች አጋጣሚ መነሻነት “ደም ሲፈለግ ብቻ መስጠት፤ ደም ለመውሰድ ብቻም ወደ ደም ባንክ መሄድ የለብንም” ብለው ቋሚ መርሀ ግብር ይዘው ደም ለመለገስ ተነሱ። የመጀመሪያውን ዙር ግንቦት ወር 2007 ዓ.ም በ15 አመራር አባላት የደም ልገሳ ጀመሩ። በሁለተኛው ዙር አባላቱን ያሳተፈ ልገሳ አካሄዱ። ጥሩ ውጤት አስመዘገበላቸው፤ ሂደቱም ቀጠለ።
የሶስተኛው ዙር ደም ልገሳ ህዝብ እንዲሳተፍ ቅስቀሳ ተደርጎ ተካሄደ። በወቅቱ በጎ በማድረግ ደም በመለገስ አቦጊዳ ሮ ትራክተር ማህበር በ30ኛው ዙራቸው 419 ሰው ደም እንዲለግስ በማድረግ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ክብረወሰኑን ይዘውት ነበር። “ይህንን ከፍተኛ ውጤት ህዝብ ቀስቅሰን ደም እንዲለግሱ በማድረጋችን መቀየር ቻልን።
በሶስተኛው የደም ልገሳ መርሃ ግብራችን ላይ 432 ሰው ደም ለገሰ።” ትላለች ወጣት ኢክራም። ሂደቱ ቀጥሎ አምስተኛ ዙር ላይ መድረሱን በመጠቆምም፤ በዚህ ጊዜ ትልቅ ዘመቻ ተደርጓል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በ10 ከተሞች የደም ልገሳ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡ 519 ሰዎች በፈቃዳቸው ደም በመለገስ ከፍተኛ ውጤትም ተመዝግቦበታል፡፡ እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም 14ኛው የደም ልገሳ መርሃ ግብር “ጀግንነት ማለት ለሰው ህይወት መትረፍ ምክንያት መሆን ነው” በሚል መሪ ሃሳብ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡ ይህንን ልምድ በቀጣይ አስፋፍተን እንሰራበታለን ትላለች፡፡
የሙስተቅበል የልማትና መረዳጃ ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ኢክራም ረዲ እንደምትገልጸው፤ ሙስተቅበል በ2002 ዓ.ም ከተለያዩ ስድስት የግል ትምህርት ቤቶች በ12ኛ ክፍል የነበሩ ተማሪዎች የተመሰረተ ተቋም ነው፡ ፡ ማህበሩ ሲመሰረት ወጣቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችልበትን ሁኔታ መምከርን ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡
ከስድስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተውጣጡ ተማሪዎች የተመሰረተው ማህበር የመጀመሪያ መጠሪያ ስሙ የነበረው ኢህሳብ (EHSEAB) ነበር፡፡ እያንዳንዱ ፊደላትም የሚወክሉት አባላቱ የተውጣጡበትን ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሴንቲ ሜሪ፤ እናት ትምህርት ቤት፤ ቀኝ አዝማች አንዳርጌ ትምህርት ቤት፤ ቤተል መካነ ኢየሱስ፤ ኢትዮ ፓረንትስ እና ሆሊ ሴቪየር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
መነሻ ሀሳቡ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መወደዱ አልቀረም። ሃሳቡን የሚደግፉ የተለያዩ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም እየተደመሩበት ቀጠሉ። በሂደትም የትምህርት ቤቶቹ ቁጥር ከስድስት ወደሃያና ሰላሳዎች አደገ። ሁሉንም የሚያማክል ሆኖ ስያሜ እንዲወጣለትም ተደረገ፡፡ “ሙስተቅበል” የልማትና መረዳጃ ማህበር የሚለውን ስያሜም ያዘ። ሙስተቅበል አረብኛ ቃል ሲሆን ተስፋን እና ወደፊትን የሚተነብይ ነው። ይህም “የዛሬ ወጣቶች የነገ ተስፋዎች ነን” የሚለውን እሳቤ እንዲወክልልን፤ እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችም በበጎ አድራጎት ተግባር እንዲሰማሩ ለማነሳሳት ታሳቢ በማድረግ ነው ስትል ኢክራም ትገልጻለች።
ማህበሩ በተመሰረተበት ዓመት በዋናነት መሰረት አድርጎ የተንቀሳቀሰው ተማሪዎች በአላትን ትርጉም በሌላቸው እና በማይጠቅሙ መንገዶች ሲያከብሩ ያዩትንና የታዘቡትን መሰረት በማድረግ ይህንንም ለመቀየር በመነሳሳት ነበር፡፡ “በተማሪዎች የሚከበሩ በዓላት ለምን ኢትዮጵያዊ ባህል ያልተላበሱ ይሆናሉ?” የሚል ጥያቄ ያኔ የማህበሩን አባላት ያነጋገረ ጉዳይ ነበር። ይህንንም አስተሳሰብ ለመቀየር በማህበሩ አባላት ተነሳሽነት በመውሰድ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ እሳቤውን በመቀየር ለበጎ ነገር ለማዋል ሁሉም የቤት ስራ ወሰዱ። በአላትን ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት በሚያስችል መንገድ እና ተግባር ለማክበር መነሻ በማድረግም ጀመሩ፡፡
በብዙ ምክንያቶች ልንለያይ እንችላለን የምትለው የማህበሩ ህዝብ ግንኙነት ወጣት ኢክራም፤ “የሁላችንም ደም አንድ ያደርገናል” የሚል አባባል የማህበሩ መርህ መሆኑን ትገልጻለች። ዛሬ የሰጠሁት ደም ነገ የሚታደገው የሰው ህይወት ምናልባትም ጋምቤላ፤ መቀሌ ወይም ሌላ ቦታ ሄዶ፤ ግን የሰው ህይወት “ይታደጋል!” በሚል እሳቤ መሆን አለበት። አንድ ጊዜ የምንሰጠው ደም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል አይደለም፡፡ በአንድ የለስላሳ መጠጥ ሊተካ የሚችል ነው። አንድ ጊዜ የሰጠነው ደም የሰው ህይወት ማዳን የሚችል መሆኑን የተገነዘብነውን ያህል በተግባር መተርጎም አለብን ባይ ናት፡፡ “ተነሳሽነቱ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ መፈጠር አለበት፤” ትላለች፡፡
እንደእርሷ ገለጻ፤ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ያወጣው መለኪያ እንደሚያሳየው፤ በአንድ አገር ውስጥ በዓመት ቢያንስ የህዝቡ አንድ በመቶ ያህል ደም መለገስ አለበት፡ ፡ የኛ አገር የደም ባንክ መረጃ ሲታይ ግን ይህንን አያሳይም፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት የሚሰበሰበው በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ደም ነው። በመሆኑም፤ በጣም ብዙ መሰራት አለበት። በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ደም በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በየጊዜው ደም የሚያስፈልጋቸው ህጻናትና እናቶች የመሳሰሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። የእነርሱ ስቃይ ሲታይም ምንም ዋጋ ለማያስከፍለው የደም ልገሳ ሰው እንዲተባበር እና የበለጠ እንዲሰራ ያነሳሳል፡፡
እስካሁን ድረስ በሚዘጋጁ የደም ልገሳ መርሀ ግብሮች ላይ ሰው በፈቃደኝነት ደም ለመለገስ ያለውን መነሳሳት አይተናል። ትብብሩ እና ድጋፉ አስደሳች ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም። በሌላ በኩል፤ በአንዳንዶቹ ላይ መሰላቸት ይታያል። ይህ በደም ልገሳ ላይ ባለ አነስተኛ ግንዛቤ ነው። በመሆኑም፤ ይህ ግንዛቤ መቀየር አለበት። አንድ ጊዜ የሚሰጥ ደም የተቸገረን ሰው ህይወት የሚያድን መሆኑን በመገንዘብ መነሳሳት መፈጠር አለበት ብላለች።
ማህበሩ ከዚህም በሻገር ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል። በዚህም በየዓመቱ የችግኝ ተከላ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ቤተሰቦች ህጻናትን የምግብ አስቤዛ፤ ለተማሪዎቹ ደግሞ የትምህርት ቤት ወጪያቸውን መሸፈን ማህበሩ ካከናወናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህንን ስራ የሚሰራው ከማህበሩ አባላት በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው። የማሀበሩ አባላቱ 210 ሲሆኑ፤ ከተማሪ እስከ ሰራተኞች ስብጥር አላቸው። በየወሩም ከዝቅተኛ የ50 ብር መዋጮ ጀምሮ እንደየደረጃቸውና አቅማቸው ያዋጣሉ፡፡
ከአባላቱ መዋጮ በዘለለ ማህበሩ በሚያደርገው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ የማህበሩ ደጋፊ/ተባባሪ አባላት በፈቃደኝነት በሚያደርጉት ድጋፍ እና ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው ሌሎች መርሃ ግብሮች የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ በሚያገኘው ገቢም ይንቀሳቀሳል፡፡ የደም ልገሳ መርሀ ግብር በዓመት ሶስት ወይንም አራት ጊዜ ይኖራል። በዚህ መርሃ ግብር ላይም ቲ ሸርትና አንስቶ የተለያዩ ቁሳቁሶች ይሸጣሉ። አንዳንድ መርሃ ግብሮችን ለማሰናዳት ገንዘብ ካላጠረን በስተቀርም ለአስተዳደር ወጪ በሚል የገንዘብ ድጋፍ አንጠይቅም ትላለች፡፡
በተለይም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመጨረሻ ዓመት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን እያከናወኑ ስልጠናም እየወሰዱ ይቆያሉ፡፡ ለከፍተኛ ትምህርት የሚዘጋጁበት እንደመሆኑም ለፈተና ይዘጋጃሉ። ተፈትነው ሲያጠናቅቁ በክረምት ላይ ሙስተቅበል እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ የዕውቅና መርሃ ግብር ላይ ጨረታ የሚቀርብ ዕቃ እና የምግብ ሽያጭ ይኖራል። ከዚህም ተጨማሪ ገቢ ይገኛል፡፡
እንደ ወጣት ኢክራም ማብራሪያ፤ የሙስተቅበል የልማትና የመረዳጃ ማህበር አመራሮችና አባላት ማህበራዊ ኃላፊነታችንን መወጣታቸውን ይቀጥላሉ። ትውልዱ በመልካም ስነ ምግባር እንዲታነጽ እና የሚጠበቅበትን ኃላፊነትም እንዲወጣ ለማድረግ ይሰራሉ። ለሰው ህይወት መትረፍ ምክንያት የሚሆኑ ወጣቶች እንዲፈልቁ ተግባራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ የደም ልገሳውንም መላ ኢትዮጵያን በማካለል ለመስራት አቅደዋል፡፡
ደም ለህይወት መትረፍ ዋስትና የሚሆነው ደም በማጣት የሚቀጠፈውን የሰው ህይወት በማሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በዝተዋል። በዚህ አጋጣሚም ደም መለገስ በጣም አስፈላጊ ነው። በመሆኑም፤ ሁሉም ሰው በፈቃደኝነት ደም ለመለገስ ሊነሳሳ ይገባል፤ መልእክታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በዘላለም ግዛው