‹‹ይሄ ትውልድ ጠንካራ ነው ብዬ አስባለሁ›› -አንጋፋው ጋዜጠኛና መምህር አስፋው ኢዶሳ

የብዙዎች የትዝታ ማህደር በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከጋዜጠኝነት እስከ ኃላፊነት ሠርተዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮግራም ዝግጅት ክፍል፤ በኅብረት ትርኢት በመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ በዜና ክፍል ከባልደረቦቻቸው ጋር ተወዳጅ ሥራዎችን ለተመልካቾች አቅርበዋል። 20 ዓመታትን በጋዜጠኝነት ለ16 ዓመታት ደግሞ በመምህርነት አገልግለዋል። መምህርነትን እንዳቆሙ በጋዜጦች ላይ በአምደኝነት ለዓመታት ሠርተዋል። እኚህ ሰው የዛሬው «የሕይወት ገፅታ »እንግዳችን የሆኑት አንጋፋው ጋዜጠኛና መምህር አስፋው ኢዶሳ ናቸው።

ትውልድና እድገት

አሮጌው ተሸኝቶ አዲስ ዓመት በሚበሰርበት፤ የአደይ አበባ ጋራ ሸንተረሩን በሚያፈካበት በወርሀ መስከረም፤ በእንቁጣጣሽ በዓል እለት በትውልድ አካባቢያቸው በደቡብ ምእራብ ሸዋ ወሊሶ ከተማ ጋዜጠኛና መምህር ጋሽ አስፋው ኢዶሳ ተወለዱ። ጊዜው ደግሞ 1944 ዓ.ም ነበር። እርሳቸው ‹‹ችቦ በርቶ፤ ሰው ሁሉ ተኝቶ ዶሮ ጩኸት ላይ መስከረም አንድ እቺን ምድር ተቀላቀልኩ›› ይላሉ፤ ኢትዮጵያውያን በተስፋ ተሞልተውና ደምቀው በሚውሉበት ዓመት በዓል መወለዳቸውን እየተናገሩ።

አባታቸው ግራዝማች ኢዶሳ ለትምህርት ልዩ ስፍራ የሚሰጡ ሰው ናቸው። ልጆቻቸው በቀለም ትምህርት የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ በፅኑ ይፈልጋሉ። በእዚህ ምክንያት ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር በጊዜው በትውልድ መንደራቸው በሚገኝ ቄስ ትምህርት ቤት በአምስት ዓመታቸው ገቡ። ‹‹በጊዜው እናቴ ፈቃደኛ አልነበረችም፤ በአምስት ዓመቱ ከእናቱ የሚለየው የፍየል ልጅ ግልገል ብቻ ነው›› በማለት ከባለቤታቸው ጋር እንዳልተስማሙ ያስታውሳሉ። ሆኖም የአባት ራዕይ አሸንፎ ጋሽ አስፋው በሁለት ታላላቅ ወንድሞቻቸው እሽኮኮ እየተደረጉ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ማቅናቱን ተያያዙት። የአስኳላን በቄስ ትምህርት ቤት አሀዱ ብለው ጀመሩ።

በቄስ ትምህርት የጀመረው የአንጋፋው ጋዜጠኛ የሕይወት ጉዞ ቀጥሎ መደበኛ ትምህርትን በ1952 ዓ.ም በወሊሶ ከተማ በመንደራቸው ወሉ በሚገኝ የካናዳውያን ትምህርት ቤት ገቡ። ካናዳውያኑ ከአባታቸው ጋር ትውውቅ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ከትምህርት ውጪ በእምነት ተፅእኖ እንዳያደርጉባቸው አሳምነው መደበኛ ትምህርታቸውን ጀመሩ። በስምንት ዓመታቸው አንደኛ ክፍል የገቡት ጋሽ አስፋው ሁኔታውን ሲያስታውሱ ‹‹እንግሊዘኛ ቋንቋና ሌሎች ትምህርቶችን በነጮች እንማር ነበር፤ በእረፍት ጊዜ፣ የመረብና የእግር ኳስ ጨዋታ መኖሩ የበለጠ ትምህርቱን እንድወደው አደረገኝ›› ይላሉ። በሚሽን ትምህርት ቤቱ እስከ አራተኛ ክፍል መማራቸውን እየተናገሩ። ሆኖም ከአራት በኋላ ትምህርቱ ስለማይሰጥ የግዴታ ከመንደራቸው ወሉ ወደ ወሊሶ ከተማ መሄድ ስለነበረባቸው ከ5 እስከ 12ተኛ ክፍል በራስ ጎበና ዳጬ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማራቸውን ይናገራሉ።

‹‹በትምህርቴ ጎበዝ ነበርኩ። ከአንድ እስከ አራት አንደኛ ነበር የምወጣው›› የሚሉት እንግዳችን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል በእዚሁ እንደቀጠሉ ያስረዳሉ።

በ13 ዓመት ሚዜ

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ አሰፋ አምስተኛ ክፍል እያሉ አንድ ፈገግ የሚያሰኝ አጋጣሚ ነበራቸው። መለስ ብለው ሲያስታውሱት ፈገግታን ያጭር እንጂ ትምህርታቸውን እስከ ማቋረጥ የሚያስገድድ ነበር። ሁኔታው እንዲህ ነው። በአካባቢው ባህል በልጀነት ሚዜ ለመሆን መታጨት ነበር። እርሳቸውም በአንድ አጋጣሚ ለሚዜነት ይታጩና በአባታቸው ፍቃድ አግኝተው ራቅ ወዳለ ቦታ ያመራሉ። በጊዜው አባታቸው አዲስ አበባ ነበሩ። ሆኖም ጋሽ አሰፋ ሚዜነቱን አጠናቀው ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱ ነበር።

ሁኔታውን ሲያስታውሱ ‹‹ሚዜነቱ ሞቀኝ መሰለኝ በእዚያው በነበርኩበት ቦታ ትምህርቴን ትቼ ለብዙ ቀናት ቆየሁ፤ አባቴ ከአዲስ አበባ ሲመለስ ትምህርት አለመጀመሬን ሲያውቅ በጣም ተቆጥቶ መለሰኝ›› በማለት ይናገራሉ። በእዚያ ፈተና አመለጣቸው። ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱት አባታቸው ከዳይሬክተሩ ጋር በመምከር ይቅርታ ጠይቀው ውጤታቸው ታይቶ ዳግም እንዳይለምዳቸው ተገስፀው፤ አባታቸውም ‹‹አይለምደኝም፤ ዳግም ለሚዜነት አልሰጥም ልጄን›› በማለት ይቅርታ ጠይቀው ነበር። አባታቸው የልጃቸው ትምህርት ቤት መሄድ በእጅጉ የሚፈልጉ ቢሆንም ባህሉን ለማክበርና ‹‹እምቢ›› ላለማለት የገቡበት ግዴታ ነበር ልጃቸውን ከትምህርት ሊያሰናክል ጫፍ ደርሶ የነበረው።

ሥነ ጽሑፍና ሚኒሚዲያ

አንጋፋው ጋዜጠኛ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታቸው በሥነ ጽሑፍ እና ሚኒሚዲያ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በተለይ ከጓደኛቸው አበራ ለማ ጋር በሥነ ጽሑፍ እንዲሁም በክርክር ክበባት ውስጥ በንቃት ይሳተፉ ነበር። ጊዜውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ‹‹በትምህርት ቤታችን የክርክርና የሥነ ጽሑፍ ክበብ ነበር። የክርክር ክበቡን እኔ ነበርኩ የምመራው›› ይላሉ። ከመደበኛው ትምህርታቸው ባሻገር ረጅሙን የእድሜያቸውን ክፍል በጋዜጠኝነት ለማሳለፍ ምክንያትና መሠረት የሆናቸው በትምህርት ቤቱ ያደርጉ የነበረው ተሳትፎ ነበር።

ደራሲ አበራ ትውልድ መንደሩ ሰላሌ ቢሆንም ለትምህርት ወሊሶ ከተማ በመምጣቱ ምክንያት ጓደኛ ሆነዋል። አንድ ክፍል ጋሽ አስፋው ቢቀድሙትም በክበቦች ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ጥብቅ ወዳጅነት ነበራቸው። የሥነ ጽሑፍ ክበቡን ደራሲ አበራ እየመራ በሚታተመው መጽሔት ላይ ጽሑፎችን በመጻፍ ይሳተፉ ነበር። ይህ ዝንባሌያቸው ለአባታቸው ማመልከቻዎችን እስከ መጻፍ አድርሷቸዋል።

‹‹በጊዜው ሬዲዮ የመስማት ፍቅር ነበረን። ከሞቃድሾ ድረስ የሚመጣ ፍሪኩዌንሲ እንሰማ ነበር። የሚያመልጠን ምንም ፕሮግራም የለም›› የሚሉት ጋሽ አሰፋ፤ በሱማሌኛ፣ በኦሮምኛ እንዲሁም በአማርኛ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ያዳምጡ እንደነበር ይናገራሉ። ለሥነ ጽሑፍ እንዲሁም ለሬዲዮ ዝግጅቶች ዝንባሌ ማሳየታቸው ኋላ ኋላ ለጋዜጠኝነትና ለመምህርነት ሙያቸው ትልቁን መሠረት ጥሎላቸው አልፏል።

ከፍተኛ ትምህርት- የመምህርነት ሙያ

አንጋፋው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛና መምህር ጋሽ አስፋው ለመምህርነት ልዩ ቦታ ይሰጡ ነበር። በተለይ በአርት ትምህርቶች (እንደ ታሪክ፣ ጂኦግራፊና በመሳሰሉት) የተለየ ችሎታና ፍላጎት ስለነበራቸው ለመምህርነት የሸፈተ ልብ ነበራቸው። ቀደም ሲልም የሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት አጋጣሚ በቤታቸው በነበረ ጎጆ ቤት ውስጥ ሰሌዳና ጠመኔ አዘጋጅተው የሰፈሩን ልጆች ሰብስበው ያስተምሩ ነበር። ይህ ዝንባሌያቸው 12ተኛ ክፍልን ሲጨርሱ የመምህርነት ሙያ ለመቀላቀል ወደ ኮሌጅ ለማምራት ምክንያት ሆናቸው።

ጊዜው 1963 ዓ.ም ነው። ጋሽ አስፋው 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁበት ወቅት ነበር። መደበኛውን ትምህርት ሲያጠናቅቁ በ1964 ዓ.ም ወደ ኮሌጅ ያመሩት በተግባረ ዕድ ግቢ ያስተምር የነበረውን የመምህራን ኮሌጅ ነበር። በዛም አማርኛን በ ‹‹ማይነር›› እንግሊዘኛ ቋንቋን ደግሞ ‹‹ሜጀር›› በማድረግ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርትን ለሁለት ዓመት ተከታተሉ።

የመምህርነት ሙያ ከመመረቃቸው በፊት ቀደም ሲል በነበረው ፖሊሲ ምክንያት ብሔራዊ አገልግሎት መስጠት ነበረባቸው። እርሳቸው የደረሳቸው ቦታ በጊዜው የኢትዮጵያ አካል በነበረችው ኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥ ነበር። ‹‹ልዑል መኮንን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው እጣ የወጣልኝ፤ በእዚያ አንድ ዓመት አስተማርኩ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ከመመረቃቸው በፊት ብሔራዊ አገልግሎት በእዚህ መልኩ መስጠታቸውን እና በመምህርነት ሙያ በዲፕሎማ መመረቃቸውን ይገልጻሉ።

ጋሽ አስፋው በአስመራ ከትምህርት ባሻገር ጥዑም የወጣትነት ጊዜም ነበራቸው። ከደቡብ ምእራብ ወሊሶ ከተማ ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ (ኤርትራ) በማቅናት አዲስ ባሕል፣ መልከዓ ምድር እና የማህበረሰብ ሥነ ልቦና ጋር ተወዳጅተው፤ ወዳጅ ዘመድ አፍርተው ነው የተመለሱት። ኢትዮጵያን በተሻለ ለማወቅና ከማህበረሰቡ ጋር ለመተዋወቅ ብሔራዊ አገልግሎቱ እንደረዳቸው ያምናሉ። ከእዚህ ሁሉ ልምድ ጋር ነበር በ1967 ዓ.ም ተመርቀው አዲሱን የሕይወት ምእራፍ የጀመሩት።

ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ

አንጋፋው ጋዜጠኛና መምህር በመንደራቸው በሰሌዳና ጠመኔ ታናናሾቻቸውን በማስተማር የጀመሩት መምህርነት እግርና እጅ አውጥቶ ወደ ይርጋለም ይዟቸው ነጎደ። በወቅቱ የተመረቁ ተማሪዎችን ቀጥታ ወደ ሥራ የሚመድበው ትምህርት ሚኒስቴር አስፋው ኢዶሳን በመምህርነት የመደባቸው ይርጋለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። በእዚያ በእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርነት ነበር የጀመሩት።

በይርጋለም በመደበኛ መምህርነት ሥራቸውን ጀመሩ። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ሥራቸውን እርሳቸው በሚፈልጉት መንገድ እንዳላከናወኑ ይገልጻሉ። በተለይ በመምህራኑ፣ በመንግሥት ሠራተኛው እና በማህበረሰቡ ዘንድ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት የተለያዩ እሰጣ ገባዎች ይከሰቱ የነበሩበት ጊዜ ነው። ወዲያው ደግሞ የእድገት በኅብረት ዘመቻ አዋጅ ነበር። በእነዚህና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በይርጋለም መቆየት ምርጫቸው አልነበረም። በመሆኑም ዝውውር ጠይቀው ወደ ሀዋሳ ተመደቡ። በይርጋለም ስምንት ወር ሀዋሳ ደግሞ አንድ ዓመት በማስተማር የመጀመሪያ የሥራ ዘመናቸውን አሀዱ ያሉት ጋሽ አስፋው ሕይወት ደግሞ ወደሌላ አቅጣጫ ወሰደቻቸው። ይህኛው የሕይወት ምእራፋቸው ደግሞ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይወስደናል።

ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን- ሌላኛው የሕይወት ገጽ

በሀዋሳ በመምህርነት የመቀጠል ፍላጎት አልነበራቸውም። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ከአንድ ማስታወቂያ ጋር አፋጠጣቸው። ጋሽ አስፋው ከልጅነታቸው ከጋዜጦችና መጽሔቶች ጋር ወዳጅነት አላቸው፤ ማንበብ ይወዳሉ። ለገና በዓል እረፍት አዲስ አበባ መጥተው ኮተቤ አካባቢ ከአንድ ጓደኛቸው ጋር ተቀምጠው ጋዜጣ ሲያነቡ ግን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን

ዜና አዘጋጆችን ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱን ይመለከታሉ። ሥራ ስለነበራቸው በሕጉ መሠረት ለፈተና መወዳደር የማይቻል ቢሆንም መዝጋቢውን ሥራ እንደሌላቸው አሳመኑ። ለፈተና ስማቸው ሲለጠፍ ጓደኛቸው አንብቦ ሀዋሳ ድረስ በመሄድ ነገራቸው። መጥተው ተፈተኑ። በወቅቱ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት በሚባለው ግቢ ውስጥ ለፈተና ከተቀመጡት 150 ሰዎች መካከል አንደኛው ጋሽ አስፋው ነበሩ።

‹‹በወቅቱ አልፋለሁ ብዬ ባልገምትም ጥሩ ሠርቼ ነበር ፈተናውን›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ዳግም ጓደኛቸው ፈተናውን እንዳለፉ ብስራት ይዞ ሀዋሳ ድረስ ሄዶ እንደነገራቸው ያስታውሳሉ። ጋሽ አስፋው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሠራተኛ መሆናቸውን ያረጋገጡት ታዲያ ሚያዝያ 8 ቀን 1968 ዓ.ም ነበር። ይህንንም ተከትሎ ለሦስት ወራት የቆየ ሥልጠናን መውሰዳቸውን ይናገራሉ። በእዚህም የፅንሰ ሃሳብና የተግባር ትምህርቶች በተካተቱበት ስልጠና፣ ገዳሙ አብርሃ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ግዮን ሀጎስ፣ ሞገስ ተክለሚካኤል ፣ ማዕረጉ በዛብህ፣ በዓሉ ግርማ እና ሌሎችም አሰልጥነዋቸው ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅለዋል። ይህ ስልጠና ለጋዜጠኘነት ጅማሯቸው ትልቅ መሠረት ነበር።

ጋሽ አስፋው የመጀመሪያ የጋዜጠኘነት ሥራቸውን የጀመሩት በዜና ዝግጅት ነው። በጊዜው ብቸኛ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእዚህ መስክ መሥራት ትልቅ ክብርና ኩራት የሚያጎናፅፍም ነበር። በእዚህ ምክንያት የተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ወቅታዊ ዜናዎችን በምስል፣ በድምፅ እያቀናበሩ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ጀመሩ። ከእዚህ ቀደም በተመልካችና አድማጭነት ይከታተሉት የነበረውን የመገናኛ ብዙኃን ሥራ ራሳቸው ይሠሩት ጀመር። በእዚህ ሙያ በልዩ ፍላጎትና ሙያዊ ፍቅር ሥራቸውን ለመሥራት በተማሪ ቤት እያሉ በክበባትና በሚኒሚዲያ ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው ጠቅሟቸዋል። በእዚህ መልክ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዜና ክፍል ለስድስት ዓመታት ቆይተዋል።

ቀጥሎ የተዘዋወሩት ወደ ፕሮግራም ክፍል ነበር። በእዚያ ኪነ-ጥበባት የሚል ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ የድራማ፣ የሥነ ጽሑፍና፣ ኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን (ድራማን ጨምሮ) ሂስና ትንተናዎችን በማቅረብ ሲሠሩ ቆዩ። ብዙም ሳይቆዩ ግን ‹‹ተጓዥ ካሜራችን›› የሚል ዝግጅት ተጀመረ። ይህ ዘግጀት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች የሚያስተዋውቅ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን የሚያሳይ እና የተፈጥሮ ሀብቶቸን የሚያስቃኝ ነበር። ስለዚህ ዝግጀት ሲናገሩ ‹‹ወድጄው ነበር። ምክንያቱም ከእኔ ጋር የሚሄድ ነበር›› በማለት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ከባልደረቦቻቸው ጋር ድንቅ ደንቅ ፕሮግራሞችን መሥራታቸውን ይናገራሉ።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ አስፋው መጀመሪያ በ‹‹ተጓዥ ካሜራችን›› የሠሩት ሥራ አሁን የወንጂ ደንዲ ኢኮሎጅ የተሠራበትን አካባቢ (የወንጪ የተፈጥሮ ሀብት) ነበር። በጊዜው አካባቢው የነበረው የቱሪስት መስህብ በአካባቢው ካሉ ነዋሪዎችና ከጥቂት ሰዎች በስተቀር አይታወቅም ነበር። ወደ ስፍራው ለመድረስ በመኪና የሚያስኬደውን በመኪና ቀሪውን ካሜራ በአህያ ጭነው፣ በእግር በመጓዝ፣ ገበሬው ጎጆ አዘጋጅቶላቸው፣ ጀልባ ተከራይተው ነበር። በወንጪ ለሰባት ቀናት ቆይተው ውቡን አካባቢና የተፈጥሮ ፀጋ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ ችለዋል። ይህ ፕሮግራም በጊዜው በነበረው የጥቁርና ነጭ ምስል ነበር የተላለፈው።

የጋዜጠኛው የመጀመሪያ የጉዞ ሥራ መነጋገሪያ ሆነ። ቱሪስት ኮሚሽን በጊዜው ስለእዚህ አካባቢ ብዙም እውቀት አልነበረውም። በኢቲቪ አለቆቻቸውም ሥራው ተወዳጅነት አግኝቶ ነበር። በጊዜው የሸዋ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ የነበሩት ኮሎኔል ደበላ ‹‹ባስቸኳይ የኢትዮጵያ ገጠር መንገዶች በአምቦ በኩል ጥርጊያ መንገድ እንዲሠራ›› በማለት አዘዙ። የወንጪን ማህበረሰብ እና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ በጎ ተፅእኖ የፈጠረ ፕሮግራም ሆነ። ታሪካቸውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ከትዝታቸው ጨልፈው ከሚያጫውቱት የቀደመ ሥራቸው ውስጥ በ1975 ዓ.ም የተላለፈው የወንጪው ፕሮግራም ቀዳሚ ነው።

ቀጣይ በ‹‹ተጓዥ ካሜራችን›› የሠሩት ፕሮግራም የሶፉመር ዋሻ እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በመጓዝ የፋሲል ግንብ እና የቱሪዝም ሀብቶችን (በተለይ በቅርሱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ) የቅርስ ጥበቃ ተቋምን በማነጋገር ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ችለዋል። በእዚህ ፕሮግራም ሌሎች ተወዳጅነትን ያተረፉ መስህብ ቦታዎችን በማዘጋጀትም ማቅረብ ችለዋል። ከቅርብ አለቃቸው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች አለመግባባት የነበራቸው ቢሆንም በሠሯቸው ድንቅ ድንቅ ፕሮግራሞች ምክንያት ግን ‹‹ጥሩ አለቃና ምንዝር›› ሆንን በማለት በጊዜው ስለነበረው ተፅእኖ ፈጣሪ ስራቸው በፈገግታ ተሞልተው ይናገራሉ።

ወደ ኃላፊነት

አንጋፋው ጋዜጠኛ ለሁለት ዓመት በፕሮግራም አዘጋጅነት ሠሩ። ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ኃላፊ በመሆን ተመደቡ። በኃላፊነት ቆይታቸውም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራዎች የሚያሻሽሉ ተግባራትን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሠርተዋል።

የሥራ ዘመናቸውን መለስ ብለው የሚያስታውሱት አንጋፋው ጋዜጠኛና መምህር አስፋው፤ በኃላፊነት ዘመናቸው ከሠሩት ሥራ ውስጥ የወጣቱን ቀልብ የሚስቡ መዝናኛዎችን እንዲዘጋጁ ማስተባበር ነበር። በእዚህም ወቅቱ የፍቅር ሙዚቃ መጋበዝ የሚያስጠይቅበት፣ በአንጻሩ አብዮትን የተመለከቱ ሙዚቃዎች እንዲቀርቡ የሚገፋፋበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

‹‹ሁሉም ጉዳይ በፖሊሲና በፖለቲካ አጥር ውስጥ የተካተተበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል›› በማለት ጋሽ አስፋው መለስ ብለው ያስታውሳሉ። በተለይ በሥራቸው የነበረውን ‹‹ወጣቶች›› የተሰኘ ፕሮግራም ያነሳሉ። በእዚያም ፕሮግራም በእርሳቸው ስር ተፈራ አስማረ፣ ሰለሞን አስመላሽ፣ ሮማን ተገኝ አብረዋቸው ይሠሩ ነበር። በድራማና ኅብረ ትርዒት ዝግጅቶች ደግሞ ዘካሪያስ ኃይለማርያም፣ አምሳለገነት ይመር፣ ታደሰ ተስፋዬ አብረዋቸው እንደነበሩ ይናገራሉ። ‹‹ጥበባዊ ይዘት ባላቸውና ለወጣቶች በሚዘጋጁ መሰናዶዎች ላይ የአብዮት ሙዚቃን አብዝቶ መጋበዝ አድማጭ ተመልካችን የሚስብ አልነበረም›› በማለት የወጣቶች መሰናዶ አድማጭ ተመልካቾችን በሚስብ መንገድ ለማቅረብ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸውን ይገልጻሉ። ‹‹የዛሬ ወጣት ከታላላቆቹ ምን ይማራል?›› በሚል ነባር ምሁራንን፣ የምርምር ግኝት ያደረጉ አጥኚዎችን፣ ከጀግኖች ማህበር የሚመጡ ሰዎችን በማቅረብ ለወጣት ልምድ እንዲሰጡ ማድረግ እንደጀመሩም ይናገራሉ። በተጨማሪም ከአብዮታዊ ሙዚቃ ወጣ ያሉ ሙዚቃዎችንም ደፈር ብለው መጋበዝ ጀመሩ። በእዚህ ተግባራቸው የተደናገጡ አንዳንድ ባልደረቦቻቸው ቢኖሩም ደፈር ብለው ውሳኔ በመስጠታቸው በውጤቱ የነበረውን ተፅእኖ መስበር መቻላቸውና በአለቆቻቸው ተግባሩ መወደዱን ይናገራሉ።

ጋሽ አስፋው በፕሮግራም ክፍል ኃላፊነት ከበርካታ ባልደረቦቻቸው ጋር በስምምነት ትዝታን የሚያጭሩ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። ‹‹የሕጻናትና ልጆች ፕሮግራም ጥሩ ትጋት ያላቸው አዘጋጆች ነበሩት›› ይላሉ፤ በተለይ ጋዜጠኛ ትሩፋት ገብረየስ፤ እቴነሽ ሸዋፀጋ፣ ጤንነት ደቻሳ፣ ሃይማኖት ተስፋዬ፣ ፕሮግራሙን በቋሚነት መሥራታቸውን ይናገራሉ።

በተለይ አቶ ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)፣ አስረስ በቀለ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም ላይ የዝግጅቱ ቅመሞች እንደነበሩ፤ አልፎ አልፎ በኃላፊነት ቦታ በመሆናቸው አንዳንድ ማስተካከያዎች ከማድረግ ውጪ ተወዳጅ ሥራዎች ያቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ። ከመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆች በተለይ በኅብረት ትርኢት ድራማ ነባር አዘጋጆች አምሳለገነት ይመር፣ ታደሰ ተስፋዬና አፈወርቅ ማና እና ከመሳሰሉት ባልደረቦቻቸው ጋር ተወዳጅ የሥራ ዘመን ማሳለፋቸውን ይገልጻሉ። በኃላፊነት ቦታ ለስደስት ዓመታት ቆይታ አድርገው የደርግ ሥርዓት በኢህአዴግ እስኪለወጥ ድረስ (እስከ 1983 ዓ.ም) ቆይተዋል። ከእዚያም በተደረገ ለውጥ የፕሮዳክሽን ክፍል ተጠባባቂ ኃላፊ በመሆን ተመድበው ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሠርተዋል። ዳግም ወደ ፕሮግራም ክፍል ኃላፊነት በተጠባባቂነት በመመለስ ዳግም ሥራቸውን እስከለቀቁበት 1988 ዓ.ም ሚያዚያ 8 ድረስ በእዚህ ኃላፊነት ላይ ቆይተዋል።

የጋዜጠኛነት ትምህርት ቤት

ጋሽ አስፋው ሁለት አስርት ዓመታትን ካገለገሉበት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመለያየት ጊዜያቸው ደረሰ። ምክንያቱ ደግሞ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት (School of Journalism) ለመክፈት የሚደረገውን ዝግጅት መስማታቸው ነበር። ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ከመምጣታቸው አስቀድሞ መምህር ነበሩ፤ በኢቲቪም የካበተ ሙያዊ ልምድ አላቸው። እነዚህ ተደምረው ገና በምስረታ ላይ ለነበረው የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህርነት ፍላጎት አደረባቸው። ጥያቄውን ለወቅቱ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አስራት አቅርበው ተቀበላቸው። ምክንያቱም ለመምህርነት ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ከሚወዷቸው ሁለት ሙያዎች ሳይነጠሉ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ ምስረታው ወደተበሰረው ትምህርት ቤት ለመቀላቀል ዝግጅታቸውን ማድረግ ጀመሩ። በሆላንድ ሀገር ለትምህርት ክፍሉ ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ለአራት ወር የአሰልጣኞች ስልጠናን ወስደው መጡ። ለአስር ወራት ተጨማሪ ዝግጀት አድርገው ቀጥታ ወደ ጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ተቀላቀሉ።

የጋዜጠኝነት ትምህርት ምስረታ ላይ በካሪኩረም ቀረፃው ሁለት እንግሊዛዊያን እርሳቸው፣ ፀጋዬ ሀይሉ፣ ዶክተር ናርዶስ አበበ፣ ሰብስቤ ከበደ፣ አጋረደች ጀማነው እና ሌሎችም በጋራ በመሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እርሳቸውም በ1989 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ቤቱ መምህር በመሆን ማገልገል ጀመሩ። የተወሰኑ ጊዜያትን በማስተማር ከቆዩ በኋላም የኤሌክትሪኒክስ ሚዲያ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ለአራት ዓመታት በኃላፊነት እና በመምህርነት ሲሠሩ ቆዩ።

ጋሽ አስፋው በጋዜጠኝነት ትምህርት ከኃላፊነት እስከ መምህርነት ጡረታ እስከወጡበት 2004 ዓ.ም ድረስ ለ16 ዓመታት አገልግለዋል። ጡረታ ቢወጡም ግን ያለ ሥራ አልተቀመጡም። በግል ጋዜጣ ህትመት የሚታወቀው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ አቋቁሞት በነበረው የቪዲዮ ዲፓርትመንት ውስጥ ለአምስት ዓመታት ሠርተዋል። በእዚህ ሳይገደቡ ለጋዜጦች በብዕር ስም አምደኛ ሆነው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፅፈዋል። አሁን ደግሞ የግል ታሪካቸውን የሚተርክ መጽሐፍ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

‹‹በሥራ ቆይታዬ ብዙ ልምዶችን አግኝቻለሁ፤ ብዙ የታዘብኩት ነገርም አለ። እነዚህን ከሕይወት ታሪኬ ጋር አጣምሬ የግል እይታዬን በመጽሐፍ ለማዘጋጀት እየሠራሁ ነው›› የሚሉት አንጋፋው ጋዜጠኛና መምህር ጋሽ አስፋው፤ የሕይወት ልምዳቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ ልዩ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

ቤተሰብ

ጋሽ አስፋው አሁን በሕይወት ከሌሉት ባለቤታቸው ሦስት ወንድ ልጆችን ወልደዋል። በወጣትነት ዘመናቸው ከትዳር በፊት አንድ ሴት ልጅም አፍርተዋል። ልጆቻቸው በትምህርት የላቀ ደረጃ ደርሰዋል። ሁለቱ ወንዶች የኮምፒውተር ባለሙያ ሲሆኑ፤ አንዱ ልጃቸው በባዮሜዲስን ፒኤች ዲ ምሩቅ ነው። ስለ ልጆቻቸው በትምህርት መላቅ ሲናገሩ ‹‹ጋዜጠኛ ስትሆን ቤተሰብህን ትጎዳለህ፤ ሥራህ ላይ ብቻ ትኩረት ታደርጋለህ፤ ነገር ግን ባለቤቴ በጣም ጎበዝና ጠንካራ ስለነበረች ልጆቻችን ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል›› በማለት አሁን በድንገተኛ ሕመም በሞት የተለዩት ባለቤታቸው የእርሳቸውን ክፍተት በመሙላት እና ልጆቻቸውን መልካም ቦታ ላይ እንዲደርሱ አስተዋፅኦ በማድረግ የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው ይናገራሉ።

‹‹ይሄ ትውልድ ጠንካራ ነው ብዬ አስባለሁ›› የሚሉት ጋሽ አስፋው፤ ብዙዎች በትውልዱ ላይ እምነት ሲያጡና አሉታዊ ምልከታ ሲኖራቸው መመልከት እንደሚያስደንቃቸው ይናገራሉ። ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን መደገፍ ከተቻለ፣ በምርምሩና በልዩ ልዩ መስኮች ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ጠንካራ እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ጥቂቶች በአለሙና በአካባቢ መጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ እየተዋጡ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን የትውልዱ አካል የሆኑ ወጣቶች ወደ መስመር ለማምጣት ሁሉም መረባረብ አለበት በማለት የሕይወት ዘመን ምክራቸውን አካፍለውናል።

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበራቸውን ቆይታ በእዚሁ ምክረ ሃሳባቸው ቋጭተዋል። እኛም መልካሙን ሁሉ ተመኝተንላቸው የዛሬውን የሕይወት ገፅታ ዳሰሳ አበቃን። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You