ከፊቷ ብሩህ ፈገግታ አይጠፋም። ትህትና መለያዋ ነው። አንደበቷ መልካም ቃላትን፣ ያፈልቃል። ገጽታዋ ችግር ይሉትን ያየ አይመስልም። ቀርቦ ላዋያያት፣ ላናገራት ሁሉ ምላሽዋ የተለመደ ነው። ሁሌም በቀና ቃላት ትገለጣለች። በብሩህ ፈገግታ ትታያለች።
አንዳንዴ በጨዋታዋ መሀል ድንገቴ ዕንባ ሊያመልጣት ይሞክራል። ለዚህ አይነቱ ስሜት ፈጽሞ ፊት አትሰጥም። እንደምንም ራሷን ተቆጣጥራ ወደ ፈገግታዋ ትመለሳለች፤ በፈገግታዋ ውስጥ ታላቅ ሚስጥር ተቋጥሯል። በፈገግታዋ መሀል ብዙ መከራ አልፏል። በፈገግታዋ የትናንት ጽናት ከዛሬ ደርሷል። ጥንካሬ ሁሌም ከእርሷ ጋር ነው።
ከዓመታት በፊት
ወይዘሮ ያለም ብርሀን ሁሌም የትንሽ ልጇ ቅልጥፍና ያስገርማታል። ህፃኗ ገና አስራ አንደኛ ወሯን መያዟ ነው። ድንቡሽቡሽና ለዓይን የሚማርክ ተፈጥሮ አላት። ያየችውን ሁሉ የምትቀርብ ሳቂታ ህጻን። ያቀፋትን የምትወድ፣ የሳማትን የማትለቅ ልበ የዋህ ርግብ። አንዳንዴ ሁኔታዋ ሁሉ ያስገርማል። እንቅስቃሴዋ ከዕድሜዋ የቀደመ፣ ከአቅሟ የዘለለ ነው።
እናት ሁሌም ብልጠትና ቅልጥፍዋ ይገርማታል። ስትሮጥ አትደርስባትም፤ ስትፈጥን አትይዛትም። እሷ ለቤቱ ብርሀን ነች። በእሷ መኖር የቤቱን ዝምታ ይሰበራል፣ ጭርታው፣ ድብርቱ ይርቃል። ድክ ድክ ስትል ታጓጓታለች። እናቷ ሁሌም ከአንገቷ ስር ገብታ የወተት ሽታዋን ትም ጋለች።
ደግማ ደጋግማ ትስማታለች፣ ዓይኗን ጨፍና፣ ነገዋን እያሰበች፡ የሩቅ ህልሟን፣ የወደፊት ተስፋዋን ታልማለች። ሁሉም ወለል ብሎ ይታያታል። ልጇን ‹‹ጽናት›› ብላ ስትሰይማት በምክንያት ነው። ራሷን ለመቻል፣ አልፋ ለመሮጥ፣ በአሸናፊነት ለመቆም የፈጠነች መሆኑ ቢያስገርማት ‹‹ጽናት›› አለቻት።
ያለም ይህን ባስተዋለች ቁጥር ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። ከዚህ በኋላ ብትቸገር ጥቂት ነው። የእሷ እርግብ ከእጇ ወጥታ ለመብረር አትዘገይም። ጽናትን እያሰበች ይህን ቀን ትናፍቃለች። ልጇ ስትሮጥ፣ ስትፈነድቅ ይታያታል። ዛሬ ላይ ቆማ ነገን ታስባለች። ውስጧ በብሩህ ተስፋ፣ ፊቷ በደማቅ ፈገግታ ይፈካል። ያለም ጎበዝ ‹‹ሼፍ›› ነች። እጇን የሚያውቁ፣ ሙያዋን የሚሹ ሁሉ በመብራት ፈልገው ያገኟታል። በትወናም ልምድን ተክናለች።
በሙያው ልስራ ካለች ጠቀም ያለ ገንዘብ ታገኛለች። አሁን ግን ጊዜ ጉልበቷ የሚውለው ለልጇ ብቻ ሆኗል። ‹‹ስራው ይቅርብኝ ልጄን ላሳድግ›› ብላ ወሰነች። ይህን ማድረጓ ቆጭቷት አያውቅም። ክፍያዋ ልጇ ብቻ ነች። በትንሽዬዋ ጽናት ሁሌም ትኮራለች፤ ትደሰታለች።
አሁን ጽናት የአንድ ዓመት ሻማዋን ልትለኩስ አንድ ወር ብቻ ቀርቷታል። እናቷ ከዚህ በኋላ እንደማትቸገር ገባት። በባለቤቷ ገቢ ብቻ ማደሩ ‹‹ይብቃ›› ስትል ወሰነች። በውሳኔዋ ማግስት ለልጇ ሞግዚት ቀጠረች። እንዲህ ማድረጓ ሸክሟን አቀለለ። በቀደመ ስራዋ እንድትመለስ ዕድል ፈጠረ። ያለም ልጇን ከሞግዚቷ አላምዳ ስራዋን አንድ ብላ ጀመረች።
የመጀመሪያ ቀን ውላ ስትገባ ልጇ ከሞግዚቷ ተላምዳ አገኘቻት። ውስጧን ደስ አለው። ሁለተኛውን ቀን ደገመች። ምሽቱን ቤቷ ስትመለስ የህጻኗን ፈገግታና ቅልጥፍና እንደትናንቱ አገኘችው። አሁን የልጇን ናፍቆት ችላ በስራዋ ልትበረታ ግድ ይላታል። የዚያን ቀን ምሽትና ሌቱን ለተናፋቂ ልጇ ሰጥታ ማግስቱን ወፍ ሲንጫጫ ተነሳች። ዛሬ ሌላ ቀን ነው። ብርቱ ስራ ይጠብቃታል።
ሶስተኛው ቀን
ያለም ስራዋን ከጀመረች ሶስተኛ ቀን ተቆጥሯል። በዚህ ቀንም ውላ ስትመለስ ልጅዋን ናፍቃለች። በሩጫ ተጣደፈች። ቤት ስትገባ በሳቅ ፈንጠዝያ የምትቀበላት ጽናት እንደሰሞኑ አልሆችም። ፊቷ ገርጥቷል፣ ሰውነቷ ዝሏል፤ ትንፋሽዋ ልክ አይደለም። እናት ባልተለመደው ምልክት ክፉኛ ደነገጠች።
ጠዋት ትታት ስትወጣ እንዲህ አልነበረችም። እየተርበተበተች ሞግዚቷን ጠየቀች። የረባ መልስ አላገኘችም። ልጅዋን እየዳሳሰች፣ እያሻሸች፣ ትንፋሽዋን አዳመጠች። እየተነፈሰች ነው። ያም ሆኖ ትንሽዋ ርግብ እንደጠዋቱ አይደለችም። ታተኩሳለች፣ ታቃጥላለች፣ ወደላይ፣ ወደታች ያጣድፋታል። ይዛት ወደ ጤና ጣቢያ ሮጠች።
ስፍራው ስትደርስ ርዳታ አላጣችም። ነርሶቹ በትኩሳት የምትነድውን ልጅ ተቀብለው ሙቀቷን ለኩላት። ልኬቱ 40 ነጥብ 5 ዲግሪ ይላል። መጠኑ በአንድ ቁጥር ቢጨምር ህይወቷ እንደሚይተርፍ ሲነጋገሩ ሰማች። ልቧ መታ። ህጻኗን ለመርዳት ርብርቡ ቀጠለ። ሀኪሙ ሆዷን በእጆቹ እየነካካ፣ እየተጫነ ህመሙ የሳንባ ምች መሆኑን ተናገረ። በቂ ምርመራ ሳይኖር እንዲህ መባሉ ቢያስገርማትም እናት የተባለችውን ተቀበለች።
የጭንቅ ቀናት
ለማስታገሻ የተሰጣት መድሃኒት አላገዛትም። ትኩሳቱ፣ ወደላይ ወደታች ማለቱ ከቀድሞው ባሰ። ምሽቱን ህመሟ በረታ። አባት ራሷን ስታ የደከመችውን ህጸን ታቅፎ ወደ እናቱ ቤት ከነፈ። ልጁ ክንዱ ላይ የሞተች አስኪመስለው ተስፋ ቆርጧል። መላው ቤተሰብ ጭንቅ ገባ። መንቆራጠጥ፣ መደናገጥ ሆነ። በድንገት የትንሸዋ ልጅ ዓይን ፈጠጠ፣ መንዘፍዘፍ መንቀጥቀጥ ጀመረች።
ሁኔታዋ ቢብስ ልጅቷን ይዘው ወደ አንድ የግል ሆስፒታል ሮጡ። የሆስፒታሉ ሀኪሞች በሞትና ህይወት መካከል ያለችውን ህጻን ተቀብለው በጭንቅላቷ መርፌ ሰጧት። አሁንም ከባዱ ትኩሳት አልበረደም። የህፃኗ ዓይኖች ተከድነዋል፤ ሰውነቷ ዝሏል። ሀኪሞቹ ከሁኔታዋ አንድ ነገር ለማለት ያሰቡ ይመስላል። እየተያዩ ይነጋገራሉ።
ጥቂት ቆይቶ የምርመራ ውጤቱ ማጅራት ገትር ነው ተባለ። እናት በሰዓታት ልዩነት ሁለት አይነት ህመም መገኘቱ አስደንግጧታል። በሁለቱም ቦታዎች የተደረገው ምርመራ ግምታዊ መሆኑን አስተውላለች። በዚህ ጥድፊያ ስለተነገራት ውጤት እንደማይሆን ጠርጥራለች። ምንም ማድረግ አልቻለችም። የተባለችውን ሰማች። የሀኪሞቹን ቃል ተቀብላ የሚሆነውን ጠበቀች። አሁንም በህጻኗ ጤንነት የታየ ለውጥ የለም። ዓይኗቿ ተከድነዋል፣ ትኩሳቷ ጨምሯል፣ ራሷን ስታለች።
ማግስቱን በማለዳ ሆስፒታሉ አንቡላንስ አዘጋጅቶ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላካት። በጥቁር አንበሳም ተመሳሳይ ህክምና ተጀመረ። የህጻኗ ስስ ሰውነት እየተፈለገ ለ15 ቀናት መርፌው ቀጠለ። ስቃይዋ አልቆመም። አሁንም ትኩሳቷ ይነዳል፣ በየአፍታው ከትንንሽ ክንዶቿ ደም ይቀዳል።
እናት እርግጠኛ የሆነችበት አንድ እውነት አለ። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የተወሰደው ናሙና ውጤቱ ማጅራትገትር ስለመሆኑ አልጠቆመም። ይህ ቢታወቅም ማንም ከህጻኗ እጁን አላነሳም። ለህመሙ የሚታዘዙ መድሀኒቶችን በላይ በላዩ መስጠቱ ቀጠለ። መርፌውን ያለማቋረጥ ተጠቀጠቀች፣ በአፍንጫዋ ቱቦ ተሰክቶ እሰከ ጉሮሮዋ የዘለቀ ላስቲክ ውስጥ አካሏን አመሰው። የትንሽዬዋ ልጅ ነፍስ በእጅጉ ተጨነቀች።
ለህክምና ዙሪያዋን የሚከቧት ሁሉ የአንደበታቸው ቃል ተስፋ አስቆራጭ ሆነ። ደጋግመው ህጻኗ እንደማታይ፣ እንደማትሰማ ያረጋግጡ ያዙ። የእናት አንጀት ተቆረጠ። የልጇን ዳግም መንቃት፣ እያሰበች የትናንቱን ለዛዋን ናፈቀች።
ያልታሰበው
አንድ ማለዳ አንድ ሰው በሃኪሞች ታጅቦ ወደ ጽናት አልጋ ቀረበ። በቀናት ልዩነት የታማሚዎችን ጤንነትን የሚያረጋግጥ ዋና ሀኪም ነው። እናት ያለም ከዚህ በፊት አላየችውም። ልጅቷን በተለየ ትኩረት እያስተዋላት ቆየ። አስተያየቱ ከሌሎቹ ይለያል። የሚሉትን እያዳመጠ የህክምና ታሪኳን አንድ በአንድ ማንበብ ጀመረ። ወዲያው ግን ፊቱ ሲለዋወጥ አየችው። በካርዱ የተመዘገበው መረጃ በህጻኗ ደም ፈጽሞ የማጅራትገትር በሽታ ያለመኖሩን አረጋግጦለታል።
ሀኪሙ ይህን ከማወቁ በላይዋ የተሰካውን መሳሪያ ነቃቅሎ ጣለው። ፊቱ በከባድ ሀዘንና ድንጋጤ ተውጧል። በአስቸኳይ ልጅቷ ወደቤት እንድትሄድ ትዕዛዝ ሰጠ። እናት ያለም ስጋቷ አልቀረም። ጥርጣሬዋ እውን ሆኗል። አሁን ትንሽ ልጇ ያልተገባውን መድሀኒት ከአቅሟ በላይ ስትወስድ መቆየቷን አውቃለች። ለማን እንደምትጮህ፣ ወዴት አቤት እንደምትል ግራ ገብቷታል። ዕንባዋን እያዘራች ነው።
የሆነው ሁሉ ከሆነ በኋላ ያለም ከጎረቤቶቿ አንድ እውነት ሰማች። ለህጻኗ ህመም ምክንያቱ የመውደቋ ሚስጥር ነበር። ሞግዚቷ ልጅቷ በጭንቅላቷ ስለመውደቋ ሸሽጋት ኖሯል። በእናት ያለም ግምት የእሷ ህመም በተለምዶ ‹‹ቡኣ›› የሚባለውና በብዙ ልጆች ላይ የሚያጋጥመው ችግር ነበር።
አሁን ሁሉም ነገር በልጇ ላይ ክፉ አሻራውን አትሟል። ከእንግዲህ መፍትሄው አይገኝም። ያለም ለመኖር ታክል የምትተነፍስ ልጅ ይዛ ቀናትን ከወራት ቆጠረች። ዓመታት እንደዋዛ ነጉዱ። ለውጥ የለም። ጽናት እንደቀድሞው አትሮጥም፣ አትስቅም፣ አትጫወትም።
ህይወት ከዓመታት በኋላ…
እነሆ ወይዘሮ ያለም አበበ ዛሬ ኑሮን በአስቸጋሪው መንገድ ይዛዋለች። ትልቁ ልጇን ጨምሮ ለእሷና ለመላው ቤተሰብ ሲባል መስራት ይጠበቅባታል። አሁን ውድ ባለቤቷ ከጎኗ የለም። በፍቺ ከተለያዩ ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፤ ሶስት ነፍሶችን በወጉ ለማሳደር የሚጠበቀው የእሷ ጉልበት ብቻ ነው። ትናንት ‹‹ጽናት›› ብላ የምትጠራትን ልጅ ዛሬ ክርስቲያን ስትል ሰይማታለች።
ክርስቲያን እጅ አግሯ ታስሯል። አንገቷ ራሷን አይችልም። የሚወራውን አትሰማም፣ የምትፈልገውን አትጠይቅም። ህይወት ለያለምና ለቤተሰቧ በአዲስ መልክ ጀምሯል። የክርስቲያን ምግቦች የተለመዱ አይደሉም። ለእሷ እንጀራን በሽሮ ማጉረስ አይታሰብም። የፓምርስ ወጪ ቀላል አይደለም። ወንዱ ልጅ መማር፣ መልበስ ይኖርበታል። ይህ ሁሉ የእናትን እጅ ይጠብቃል።
ክርስቲያን ዕድሜዋ ከፍ ሲል ክብደቷ ጨምሯል። በወጉ ለማጠብ፣ ለማልበስና ለማዘል ፈተናው እየመጣ ነው። ህጻኗ አንዴ ማልቀስ ከጀመረች ሰዓታት ታስቆጥራለች። ይህን የሚችለው ደግሞ የእናቷ ትዕግስትና ሰፊ ትከሻ ብቻ ነው።
አንዳንዴ እናትና ልጅ ሲላቀሱ ሌቱ ይጋመሳል። ህጻኗ ለማልቀስ አይደክማትም፤ እናት እሷን በማቀፍ እጆቿ አይዝሉም፤ ሲብስባት በርከክ ብላ ፈጣሪዋን እንዲወስዳት ትማጸናለች። ወዲያው ግን የእናት አንጀቷ ይርበተበታል። ባለችው ተጸጽታ ትመለሳለች። እርፍትየለሽ ልጅዋን እንደ ዓመሏ ታባብላታለች። ለቅሶዋ አይቆምም፣ የበላችው አይረጋም፤ ሲነጋ አዝላት ወደ ሀኪም ቤት ትሮጣለች።
ክርሰቲያን ያለእሷ ህይወት የላትም። ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመተኛትና መነሳት ሁሉ የምትፈልገው የእናቷን እጆችና ጠረን ነው። ያለም ለእሷ ብቻ በሚገባ ቋንቋ ልጇን ታወራታለች፣ ታጫውታታለች። አዝላት አቅፋት ትውላለች፤ ተሸክማት ስትጓዝ አይደክማትም፤ አይሰለቻትም። ሁሌም ፈጣሪዋን ስታማርር፣ ስትበሳጭ አትታይም። ከዚህም የባሰ መኖሩን ታምናለች።
ሁሌም በክርስቲያን ተኝቶ መነሳት ፈገግታዋ የሚደምቀው ያለም ስለልጇ የማትሆነው የለም። ለእሷ ጊዜዋን፣ ጉልበቷን ዕድሜዋን ከፍላለች። ለእሷ ስራዋን፣ የምትወደውን የተውኔት ሙያዋን ረስታለች። ለእሰዋ አሁንም እየሞተች ልትኖር ዝግጁ ናት። ለእሷ ያለቻት እሷ ናትና ምንም ብትሆንላት አይቆጫትም።
አንዳንዴ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ትዘፍንላታለች። በወጉ ትሰማት ይመስል በጥሩ ቋንቋና አንደበት ታወድሳታለች፣ ታደንቃታለች። ይህኔ ትንሽዬዋ ልጅ ፊቷ በደስታ ይፈካል። የእናቷን መምጣት ትናፍቃለች። የዓይኗን ማረፊያ ትሻለች።
ለመኖር …
ያለም አንድ ወቅት መተዳደሪያዋ ዳቦ ደፍቶ መሸጥ ሆነ። ዳቦውን ለመጋገር በቂ ጊዜ ይፈልጋል። ሙሉ ጊዜዋ የክርስቲያን ነው። እሷ ለሊቱን ሙሉ የእናቷን ጉያ ትሻለች። ትንፋሽ ጠረኗን ትናፍቃለች። ያለም አንዱን ለመፈጸም ሌላውን መተው ይኖርባታል። ስራውና ክርስቲያን በእኩል ሲጋፉባት ቆም ብላ ታስባለች። ሁለቱም አይቀሬዎች ናቸው። ከማንም አትጣላም። ልጇን ከስራዋ አስማምታ ታስታርቃቸዋለች።
ዳቦው የሚጋገረው ለሌቱን ቆሞ በማደር ነው። ክርስቲያን ይህን ሰዓት እንድትለያት አትፈልግም። ከጎኗ ካልሆነች አምርራ ታለቅሳለች፤ ያለም ከስራውም፣ ከእሷም እያለች ወድቅቱን ትገፋለች። ሲነጋ ደንበኞቿ ትኩሱን ዳቦ ይገዟታል። አዲስ ቀን በሌላ ድካም ይጀመራል። ጎዶሎዋን ትሞላለች።
አንዳንዴ ክርስቲያንን አዝላ ስትወጣ ከኋላዋ እናትና ልጁን ባዩ ቁጥር ከንፈር መጣጮች ድምጽ ይከተላታል። ይህኔ ከልጇ ይልቅ የእነሱ ልማድ ይከብዳታል። እንዲህ አይነቶቹ ቢያናድዷትም ፈጽሞ አታስባቸውም። እንደ ሁልጊዜው በጥንካሬዋ ጸንታ አልፋቸው ትሄዳለች።
የእናትና ልጅ ፍቅር ከተለመደው ይለያል። ክርስቲያን በእጇ ምግብ መያዝ አትችልም። በእሷ ዘንድ አጣጥሞ መጉረስ ይሉት ልማድ አይታወቅም። ዘወትር ርሀብ ጥማቷን የምትለየው እናቷ ብቻ ነት። ምግብ ባሻት ጊዜ ያለም እንደ እናት ወፍ ያፏን አላምጣ ከአፏ ታደርሳለች።
ትንሽዋ ወፍ የእናቷ ከንፈር በተላወሰ ቁጥር አፏን ወደ አፏ ታስጠጋለች። ሁሌም ከጉንጯ ጠብቃ ትጎርሳለች። ለእሷ የእናቷ አፍና ጥርሶች የመኖሯ ዋስትና ናቸው። ዘወትር የላመ፣ የደቀቀውን፣ የጣፈጠ፣ የተመረጠውን ያቀብሏታል። ትንሽዋ ወፍ ምግቡ ከአፏ ሲደርስ ሳታላምጥ ትውጣለች፤ ትጠግባለች።
ሁሌም ለውሃ ጥማቷ የምትደርሰው እናቷ ብቻ ናት። ከሚጠጣው ፉት ብላ የልጇን ጎሮሮ ታርሳለች። የእርካታዋ ልክ አይጠፋትም። ፊቷን ጠራርጋ ሁለመናዋን አሳምራ እንደእናት ወፍ ለመብረር ልቧ የሚያርፈው እንዲህ ስታደርግ ነው።
ክርስቲያን ለእናቷ ደማቅ ውበት ነች። መቼም አፍራባት፣ ተሸማቃበት አታውቅም። ሁሌም ስለውብ ስጦታዋ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። እሷን ለማሳደግ ድካም ፈተናው ቢበዛም ከእንግዲህ ‹‹ደከመኝ፣ ይብቃኝ›› ለማለት አትደፍርም። ግን ለመጀመሪያ ልጇ ሳሚ በቂ ጊዜ እንዳልሰጠች ታውቃለች። ክርስቲያንን ስትል ከእሱ ጊዜና ፍቅር ሰርቃለች፣ ሳትንከባከበው ቆይታለች። ትንሹ ሳሚም ስለእህቱ ዋጋ ከፍሏል። የሚገባውን ትኩረት ማጣቱ አላኮረፈም፤ ዓመል አላወጣም። ፍቅር ገዝቶታል። ህይወት ገብቶታል።
ያለም ብርሀን ኑሮን ስትገፋ በከባድ ጫና ተውጣ ነው። ልጇን በየሰዓቱ ማገላበጥ፣ ያለዕንቅልፍ ቀናትን መሻገር፣ ያለእረፍት በስራ መባዘን ልማዷ ነው። ይህ መጨናነቅ ለሚጥል በሽታ ዳርጓታል። ህመሙ የህጻኗ ጭምር ነው። ሁለቱም ተመሳሳይ መድሀኒት ይወስዳሉ። ጉዳዩ ከበድ ቢልም በሀዘን አለመረረችም። እሱንም ‹‹ተመስገን›› ብላ ተቀብላለች።
ዛሬን…
አሁን ክርስቲያን 13 ዓመት ሞልቷታል። እነዚህ ዓመታት ለእናት ያለም ሻካራና ዥንጉርጉር ነበሩ። ባለፉት ጊዜያት ክፉ ደግ አይታለች፣ ወድቃ ተነስታለች፣ አልቅሳ ስቃለች። ከዓመታት በፊት ከጎኗ የነበረው ባለቤቷ ከልጃቸው ህመም ወዲህ በፍቺ ተለይቷታል። አልተቃወመችም፣ ውሳኔውን አክብራለች።
ዛሬ ልጇ ያለችበት ችግር የህክምና ስህተት መሆኑን ታውቃለች። ማንንም አልከሰሰችም፣ አልወቀሰችም። አሁን ትንሽዋ ወፍ እንዳሻት አትበርም፣ እናቲቱ ጠንካራ ክንፍ ሆናታለች። ሁሌም ለእሷ መኖር ማልዳ ትበራለች፣ በህይወት ጀልባ በጥልቁ ባህር ትቀዝፋለች። የእሷ መልህቅ አስኪዘረጋ ፈጽሞ አትደክምም። ከወደቧ አስክትደርሰ ዕንባና፣ ሀዘን አይከተሏትም። ያለም ለልጇ ጉልበትም ህይወት ናት።
የእሷ መኖር የክርስቲያን እስትንፋስ ነው። ቢከፋትም፣ አታለቅስም፣ ብታለቅስም አታመርም። በፈገግታ እየበራች ነገን በተስፋ ታልማለች። እንደ እናቲቱ ወፍ ማልዳ ትበራለች፤ አዎ! ትሮጣለች፣ ትከንፋለች፣ ህይወትን ልትቀጥል፣ ኑሮን ልታሳምር።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም