‹‹ወጣትነት ትኩስ ኃይል ነው›› እንደሚባለው አብዛኞቹ ወጣቶች ውስጣቸውን አድምጠው፤ አካባቢያቸውን አስተውለው፤ አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን ለመፍጠር በርትተው ይተጋሉ። የበረታው የትጋት ጉዟቸውም ገና በጠዋቱ ያማረና የሰመረ ሆኖ ዘመናቸው ብሩህ ይሆናል። እነዚህ ወጣቶች ታዲያ የሕይወትን ቁልፍ በእጃቸው ማስገባት የቻሉ በመሆናቸው በሕይወት የተለያዩ ገጾች መኖር ያጓጓቸዋል እንጂ አያስፈራቸውም። ጉጉታቸውም ይበልጡኑ ለማደግና ለመለወጥ ነው። እንዲህ አይነት ወጣቶች የፈልጉትን እስኪያገኙ ደከመኝን አያውቁም። የሚፈልጉትን ለማግኘትም ሕይወት የጠየቀቻቸውን መስዋእትነት ሁሉ ይከፍላሉ።
በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በርካታ ወጣቶች ስራ ቆመው አይጠብቁም፤ በሥራ ፈጠራዎች ተጠምደው ለራሳቸውም ለሀገራቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶች ነገሮችን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ ጥልቅ ፍላጎት አላቸው። የዛሬዋ የስኬት እንግዳችንም ገና በጠዋቱ የተፈጠረችበትን ዓላማ ለማወቅ ራሷን ጠይቃለች፤ መርምራለች። ለጥያቄዋ ባገኘችው ምላሽ መሰረትም ትኩረቷን ሴቶችና እናቶች ላይ በማድረግ በጋርመንት ሥራ ላይ ተሰማርታ ስኬታማ ለመሆን በቅታለች።
የገባችበት የጋርመነት ስራ ደግሞ ብዙዎቻችን ልናስብ እንደምንችለው ዘመናዊ የስፌት ማሽኖችንና በዘመናዊ መንገድ የተመረቱ ግብአቶችን በመጠቀም ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ ወጣቷ ለአገር በቀል ዕውቀት በተለይም ለእጅ ሥራ ጥልቅ ፍቅር ያላት በመሆኑ የአገር ባህል አልባሳት ማምረት ዘርፍን ተቀላቅላለች። ዘርፉን በመቀላቀሏ በአገር ውስጥ ያለው የጋርመንት ዘርፍ ገና ያልተነካ አቅም እንዳለው በሚገባ ተረድታለች። በአሁኑ ወቅትም በጋርመንት፣ በስፌት፣ በሽመናና የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን በመሥራትና በማሰልጠን እንዲሁም ለሽመና ሥራ የሚያገለግሉ ማሽኖችን አምርታ ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች።
ገና በአፍላ ዕድሜዋ ለውስጣዊ ጥያቄዋ ምላሽ አግኝታ የተፈጠረችለትን ዓላማ እየኖረች ያለችው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ወጣት ሀዊ ደበሌ ትባላለች። ወጣቷ፤ የኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ እና የጌቦ ማኑፋክቸሪንግ መስራችና ባለቤት ናት። እነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች የየራሳቸው ተግባር አላቸው፤ ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ በጨርቃ ጨርቅ ምርትና በስልጠና ላይ የሚሰራ ሲሆን፣ ጌቦ ማኑፋክቸሪን ደግሞ ጨርቃ ጨርቅ ማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።
ወጣት ሀዊ ወለጋ ጊንቢ ነው የተወለደችው፤ እስከ አምስት ዓመቷ ወሊሶ ቆይታለች፤ ከዚያም ወደ ቢሾፍቱ አቅንታ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዚያው በቢሾፍቱ ተከታትላለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ተመርቃለች። ጎበዝ ተማሪ እንደነበረች የምትናገረው ወጣት ሀዊ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እንደወጣች የሥራ ዓለሙን የተቀላቀለችው በመምህርትነት ነው።
የባንኪንግና ፋይናንስ ትምህርትን በተለያዩ የግል ኮሌጆች ከመጀመሪያ ዓመት እስከ ተመራቂ ተማሪዎች ድረስ አስተምራለች። ይሁንና በዚህ ሙያ አልዘለቀችበትም፤ ወጣት ሀዊ ማስተማር በትክክልም የተፈጠረችለት ዓላማና ህልም እንዳይደለ ውስጧ ይነግራት እንደነበር ታስታውሳለች። የማስተማር ሥራዋን አቋርጣ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የተፈጠረችለትን ህልም ፍለጋ የአዕምሮዋን ጓዳዋን ትበረብር ጀመር። ለጥያቄዋ መልስ እስክታገኝም ከሥራ ውጭ ሆና ራሷን ፈልጋለች።
በፍለጋዋም ‹‹ከራስ በላይ ለሌሎች የመኖር ዓላማ›› የሚለውን ትልቅ ሚስጥር ማግኘት እንደቻለች የምትገልጸው ወጣት ሀዊ፣ በወቅቱም ከሰማይ መና ይወርዳል በማለት እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። ሕልሟን ለማሳካት አዕምሮዋን ተጠቅማለች። ምን መሥራት እንዳለባትና ለሰዎች ምን ማድረግ እንደምትችል አቅዳ ተንቀሳቅሳለች። በእንቅስቃሴዎቿ ሁሉ ታዲያ ሴቶችን ቀዳሚ በማድረግ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ያለችውን ሃሳብ አውጥታ አውርዳለች።
እንዲህ ያለ ሰፊ ሃሳብ ስታወጣና ስታወርድ በነበረችበት ወቅት ታዲያ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል በሯን አንኳኩቶም ነበር። በውጭ አገር የማስተርስ ትምህርት እድል የቀረበላት ሀዊ ግን ከአገር የመውጣት ምንም አይነት ፍላጎት የላትም፤ በዚህ የተነሳም የትምህርት ዕድሉን ወደ ጎን በመተው የተፈጠረችለትን ዓላማ ለማሳካት መውተርተሯን ቀጠለች። የትምህርት ዕድሉን ላቀረበላት ተቋም ከአገር የመውጣት ፍላጎት የሌላት መሆኑን በመግለጽ፤ ህልሟን ማሳካት እንድትችል ሊያግዟት የሚችሉት ካለ አግዙኝ በማለት ጥያቄ ማቅረቧን ታስታውሳለች።
ህልሜ ‹‹ሰዎችን መርዳት፣ የሰዎችን ሕይወት መቀየርና የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው›› የምትለው ወጣት ሀዊ፤ ውጭ አገር የመሄድ ፍላጎት ባይኖራትም፣ በአገሯ ሠርታ መለወጥና ለሌሎች የመትረፍ ዓላማዋን ዕውን ለማድረግ አግዙኝ ብላ ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ መጀመሩን ትናገራለች።
ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ ህብረትን፣ አንድነትን አብሮ መሥራትንና ማደግን መሰረት አድርጎ የተመሰረተ መሆኑን የምትገልጸው ወጣት ሀዊ፤ ሥራውን ስትጀምር በጋርመንት እንደሆነ ትገልጻለች። ወደ ሥራው በገባችበት ወቅት ታዲያ በጋርመንት ውስጥ አስፈላጊ የተባሉ የተለያዩ ግብዓቶችን በአንድ ላይ ማግኘት አልቻለችም። ለዚህም መፍትሔ ያለቻቸውን ሃሳብ በማመንጨት ሁሉም ነገር በአንድ ቦታ መከናወን እንዲቻል ጋርመንት፣ ሽመና፣ ጥልፍና ሌሎች የእጅ ሥራዎችን ጭምር መሥራቱን ቀጠለችበት።
በልጅነት ዕድሜዋ በአሻንጉሊት ላይ መጥለፍና መስፋት ታዘወትር እንደነበር የምታስታውሰው ወጣት ሀዊ፤ በውስጧ ተዳፍኖ የኖረ ፍላጎቷን ለማቀጣጠል ብዙም ማገዶ አልፈጀባትም፤ በቀላሉ ወደ ሥራው መግባት ችላለች።
በጋርመንት ውስጥ በስፌት ከጀመረችው ሥራ በተጨማሪ ስልጠና በመስጠትም ተሰማርታለች። በስፌት ሥራ የገጠማትን የጨርቅ እጥረት ለመፍታት ወደ ሽመና እንደገባች የምትናገረው ወጣት ሀዊ፤ ወደ ሽመናው በገባች ጊዜም ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። በተለይም እናቶች በቤት ውስጥ ሆነው ጥጥ መፍተል፣ ዳንቴል መሥራትና የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን መሥራት የሚችሉበትን ዕድል ፈጥራለች።
ሥራ ሥራን እየወለደ ሄደና በቤት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስን በእጅ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ተረዳች፤ ለአብነትም በቃጫ የሚሠሩ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶችን ጨምሮ በቀርከሃ የሚሰሩ የቤትና የወጥ ቤት ዕቃዎች እንዲሁም በሰበዝ የሚሠሩ የተለያዩ ቁሳቁስን በመሥራት ለገበያ ታቀርባለች። የእጅ ሥራዎቹን አምርቶ ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የዕድ ጥበብ ዘርፍ የሆነው የእጅ ሥራ ጥቂቶች ጋ ብቻ እንዳይቀር ብላ፣ ለብዙዎች እንዲተላለፍ በዘርፉ ስልጠናም እየሰጠች ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት በኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ ሽመናን ጨምሮ የተለያዩ የእጅ ሥራ ስልጠናዎችን ሰልጥነው 290 የሚደርሱ ዜጎች ወደ ስራ ገብተዋል፤ እነዚህ ዜጎች በድርጅቱ ሥራ ተፈጥሮላቸዋል። ስልጠናውን አግኝተው ወደ ሥራው የገቡት አብዛኞቹ የቤት እመቤቶችና በተለያየ ምክንያት በቤት ውስጥ የቀሩ እናቶች በመሆናቸው ሥራውን ወስደው በቤታቸው እየሠሩ ይገኛሉ።
‹‹አብዛኛው ሥራ ማሽን የማይፈልግና በእጅ የሚሠራ በመሆኑ ስልጠናው እነዚህ እናቶች በቤታቸው ሆነው መሥራት እንዲችሉ አድርጓቸዋል›› ያለችው ወጣት ሀዊ፤ ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግም ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ማሽን በማይፈልጉ የእጅ ሥራዎች ላይ እንደሆነ ትናገራለች።
እሷ እንዳለችው፤ በአሁኑ ወቅት ሰዎች ለእጅ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ገበያ አላቸው። በተለይም የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ በአገር ውስጥ በስፋት የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥራው አዋጭና ተመራጭ ነው። በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል በመሆኑም ማንም ሰው በቀላሉ ስልጠናውን ወስዶ በቤት ውስጥ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ያስችለዋል።
አሁን ያለውን ገበያ አስመልክታ ወጣት ሀዊ እንዳለችው በእጅ የሚሠሩ ማንኛቸውም የእጅ ሥራዎች ሰፊ ገበያ አላቸው። ለአብነትም የገና በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው የገና ኤግዚቢሽን ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ ምርቶቹን ይዞ ወደ ገበያው የወጣ ቢሆንም ኤግዚቢሽኑ ሳይጠናቀቅ ምርቶቻቸውን ጨርሰው እንደተመለሱ አስታውሳለች። ይህም በእጅ ሥራ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ያሳያል ብላለች።
የሸክላ ሥራን ጨምሮ የቃጫ፣ የሽመና እና ከቀርከሃ የሚሠሩ የተለያዩ ቁሳቁስን በማምረትና በማሰልጠን ሥራ ላይ የተሰማራቸው ወጣት ሀዊ፤ በሽመና የምታመርታቸውን ምርቶች በአብዛኛው ተደራሽ የምታደርገው ለዲዛይነሮች እንደሆነ ነው ያስረዳችው። ዲዛይነሮችም ከእሷ የገዙትን የሽመና ልብስ ወይም ጨርቅ እሴት በመጨመር በተለያየ ዲዛይን አዘጋጅተው ለገበያ የሚያቀርቡ ይሆናል።
በኤልቢ ከሚመረቱ ምርቶች መካከል ሸክላ አንዱ ሲሆን ሸክላው ላይ የተለያየ ዲዛይኖችን በመሳል ለአበባ ማስቀመጫና ጌጥ ሆኖ አገልግሎቶች ይሰጣል። ሌላው የስፌት ሥራ ሲሆን የስፌት ሥራ ለግድግዳ ጌጥ ከመሆን ጀምሮ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ቅርጫቶችም ይሠራሉ። ሌላው የሽመና ውጤት የሆነው የአንገት ልብስ፣ ጋቢ፣ የተለያዩ አልባሳት የሚሰሩበት ጣቃ ጨርቅ፣ ምንጣፍና ሌሎችም ይመረታሉ። ከቀርከሃም እንዲሁ ኩባያን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ያቀርባሉ።
‹‹ኢትዮጵያዊ በሆኑና በተፈለጉ ጊዜ ሁሉ በቀላሉ በሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች ማለትም ጥጥ፣ ቃጫ፣ ሰበዝና አለላ እንዲሁም ቀርከሃን ተጠቅመን መሥራታችን አዋጭ አድርጎናል›› የምትለው ወጣት ሀዊ፤ ምርቶቹንም በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ አስችሎናል ትላለች። ማህበረሰቡም በሀገር ውስጥ ምርት በተለይም የእጅ ሥራዎችን የመጠቀም ልምዱ እየሰፋ የመጣበት ወቅት እንደመሆኑ በዘርፉ ብዙ መሥራት እንደሚገባ ጠቁማለች።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ባህልና እሴቶች መካከል አገር በቀል የሆኑና ሸማኔው የሚጠበብባቸው የአገር ባህል ጥበቦችን ጨምሮ የሸክላ ሥራ፣ የስፌትና የቃጫ፣ የዳንቴል ሥራና የተለያዩ የእጅ ሥራዎች የሚከወኑት በሴቶች መሆኑን የጠቀሰችው ወጣት ሀዊ፤ እነዚህን ባህላዊ የእጅ ሥራዎች ከእናቶች መውረስና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ከእሷም እንደሚጠበቅ ትናገራለች። ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግን ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መቋቋሙም ለዚሁ እንደሆነ ነው ያመለከተችው።
‹‹ሴት የጀርባ አጥንት ናት›› የምትለው ወጣት ሀዊ፣ ሴት ሁሉን ነገር መሥራትና መሸፈን እንደምትችልም ነው ያረጋገጠችው። ለሴት ዕድል መስጠትና ሴትን ማብቃት ማለት በተዘዋዋሪ ቤትን፣ አካባቢን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን ማብቃት መሆኑን ገልጻለች። ከድርጅቱ ሰራተኞች አብዛኞቹ ሴቶች የመሆናቸው ሚስጥርም ይሄ ነው በማለት ታብራራለች።
ሴቶች የሚያገኙትን ገቢ ቤተሰባቸው ላይ የሚያውሉ ናቸው። ስለዚህ ለሴቶች አቅም በመፍጠር የቤትና የማህበረሰብን እንዲሁም የሀገርን አቅም ማጠንከር ይቻላል ባይ ናት።
በአሁኑ ወቅት በሽመናው ላይም ሴቶች እየሠሩ ይገኛሉ። ድርጅቷ የሚያመርተው የሽመና መስሪያ ማሽን ከቀርከሃ ተሻሽሎ የተሠራ ሲሆን፣ ለእዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ የሽመና ማሽኑ መሻሻሉም ሴቶቹ ማሽኑን በቤታቸው አስገብተው መሥራት እንዳስቻላቸው ነው ያጫወተችን። የሽመና ማሽኑ ከዚህ ቀደም የተሠራ አለመሆኑን የገለጸችው ወጣት ሀዊ፤ ማሽኑ ለሽመና ሥራው ምቹና ቀላል መሆኑን ትናገራለች። ከዚህ ቀደም ሸማኔው ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ምቹ ባልሆነና ሁለት ሜትር ርዝማኔ ባለው ከእንጨት የተሠራ የሽመና መሳሪያ ይጠቀም እንደነበር ታስታውሳለች።
ወጣት ሀዊ ወደ ሽመና ሥራ ስትገባ ማሽኑ ምቹና ቀልጣፋ አልሆነላትም። በዚህ መነሻነት እንጨቱን በቀርከሃ በመቀየር ሁለት ሜትር የነበረውን ርዝማኔም እንዲሁ ወደ አንድ ሜትር በማሳጠር በቀላሉ መገጣጠምና ተፈትቶም በቤት ውስጥ መቀመጥና መሥራት የሚያስችል የሽመና ማሽን መሥራት ችላለች። እንጨቱ ከጊዜ ብዛት የመጣመም ባህሪ ያለው በመሆኑ ነው ቀርከሃን ምርጫ ያደረገችው። ቀርከሃ በጣም ጠንካራና ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል እንደሆነም በጥናት ማረጋገጥ ችላለች።
በአሁኑ ወቅትም ይህን የሽመና ማሽን በማምረት ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች። በአብዛኛውም በጡረታ ተገልለው በቤት ውስጥ ያሉና በተለያየ ምክንያት መውጣት ያልቻሉ የማህበረሰቡ አካላት ማሽኑን በመግዛት እንዲሁም ስልጠናውን በኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ ወስደው በቤታቸው ሸማዎችን ማምረት ይችላሉ።
ወጣት ሀዊ እንዳለችው፤በኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ የሚሰጠው ስልጠና ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወራት ይወስዳል። በአንድ ወር ስልጠና የአንገት ልብስና የምንጣፍ ሥራን መልመድ ይቻላል። እስከ ሶስት ወር የሰለጠነ ሰው ደግሞ የሽመና ሥራን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ ይችላል። በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰልጣኝ ወደ ተቋሙ እየመጣ ሲሆን፣ የማሽን ፍላጎትም እንዲሁ ከፍተኛ ሆኗል። ኤልቢ በአሁኑ ወቅት በአንድ ዙር 200 ሰልጣኞችን ለማሰልጠን ተዘጋጅቷል።
ለሰዎች መኖር የሚል ትልቅ ሃሳብን ሰንቃ የተነሳችው ወጣት ሀዊ፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የተፈናቀሉና አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች። ስድስት ህጻናትን የምግብ፣ የልብስና የትምህርት ወጪያቸውን በመሸፈን ታሳድጋለች።
ትልቅ ሃሳብና ከፍተኛ ፍላጎት ይዛ የተነሳችው ወጣት ሀዊ፤ ወደ ሥራው ስትገባ ሁለት ሚሊዮን መነሻ ካፒታል ይዛ ነበር፤ ብዙ መሰናክሎች ገጥመዋት እንደነበርም ታስታውሳለች። በአሁኑ ወቅትም ካፒታሏ 20 ሚሊዮን ላይ ደርሳለች።
በቀጣይም 30 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የኢንቨስትመንት ቦታ ሰንዳፋ ላይ ተረክባ ፋብሪካ እየገነባች ትገኛለች። ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ 10 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የጠቆመችው። በተጨማሪም ኤልቢ ማኑፋክቸሪንግ በቀጣይ አምስት ዓመት ስደስት ሚሊዮን ሰዎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማሰማራት ትልቅ ዕቅድ ያለው መሆኑን ወጣት ሀዊ ገልጻለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም