የአፍሪካ – ቻይና የንግድና የኢንቨስትመንት ትርዒት በአገሮቹ መካከል ያለውን ሁለገብ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ተገለጸ፡፡
የኢትዮ-ቻይና የኢንዱስትሪ አቅም የማጎልበት ትብብር ትርዒት (China –Ethiopia Industrial Capacity Cooperation Exposition) የሚል ስያሜ የተሰጠው የንግድና የኢንቨስትመንት ትርዒት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል በይፋ ተከፍቷል ፡፡
ትርዒቱ በኢትዮጰያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን እስከ ከህዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም በተለያዩ መርሀ ግብሮች ይቀጥላል፡፡
ትርዒቱ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በፍጥነት እያደገና እየተስፋፋ የመጣውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት አጋርነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርን ዒላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻገር ትርዒቱ የአፍሪካ ቻይና ትብብር መድረክ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ቻይና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር እንዳላቸው ገልጸው ትርዒቱ አዲስ ኩባንያዎችን በመሳብ ፣ በሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ማህበረሰቦች መካከል ሽርክና በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
በቻይና የዓለምቀፍ ንግድ ማስፋፋያ ምክር ቤት ኃላፊ ሄ ሴሎንግ በበኩላቸው ትርዒቱ የቻይና-አፍሪካ የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበቻ፣ የሁለገብ ትብብራቸው ማጠናከሪያ፣ የንግድና የኢኮኖሚ ቁልፍ አጋርነታቸው ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ያላትን ገንቢ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለፀው በትርዒቱ ላይ ከኢትዮጵያና ከቻይና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በቻይና ወገን ፣ በግብርና እና ምግብ ማቀነባበር፣ በቴክኖሎጂ ፣ በሆቴል ዘርፍ፣ በማዕድን፣ በመኪና ማምረትና በሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች የተሰማሩ የ46 ግዙፍ ኩባንያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የቢዝነስ ለቢዝነስ መድረክ ፣ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ መድረክ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉብኝት የትርዒቱ አካል እንደሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ በቢዝነስ ለቢዝነስና በኢንቨስትመንት መድረኮቹ ላይ በኢትዮጵያ ስላሉ የቢዝነስ እድሎች ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጥ እንዲሁም የኢትዮጵያና የቻይና ኩባንያዎች በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉት የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ትስስር እንደሚፈጥሩ ተወስቷል፡፡
መድረኩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፣ በቻይና የዓለምቀፍ ንግድ ማስፋፋያ ምክር ቤት፣ በቻይና አለም አቀፍ ኤግዚቪሽን ማዕከል እና በቻይና አፍሪካ የልማት ፈንድ ትብብር ነው፡፡