ወረዳዎችን ያስተሳሰሩት የውሃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች

እንዲህ እንደዛሬው ውሃ እግር አውጥቶ ወደ ሰዎች መኖሪያ ሥፍራ የሚሄድበት እድል ባለመኖሩ ሰዎች ውሃ ወዳለበት ቦታ ሄደው መስፈራቸው ግድ ነበር። ሰዎች አሰፋፈራቸው በአመዛኙ የውሃ መገኛዎችን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ የሀገራችንን ከተሞች በማየት ብቻ መረዳት ይቻላል። ውሃ ለሰው ልጅ ሕይወት መሆኑን ተከትሎ ለኑሮ የሚመረጡ ቦታዎችን ውሃ አላቸው ወይስ የላቸውም? ብሎ መጠይቅ የመጀመሪያ መስፈርት ተደርጎም ይወሰዳል።

ዛሬ ይህን ታሪክ የቀየሩ የውሃ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በሀገራችን የተለያዩ ክልሎች እየተከናወኑ ይገኛል። ውሃ ቦታውን ለቆ ያለተፈጥሯዊ ባህሪው ሽቅብ እየወጣ በየመንደሩ እየተንዠቀዠቀ ጉሮሮ ሲያረሰርስ፣ መሬትን ሲያረጥብ እና እጽዋትን ሲያለመልም መመልከት የተለመደ ሆኗል። ከሰሞኑ የሚዲያ አመራሮችና ጋዜጠኞች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ እና አርሲ ዞኖች የተመለከትነው የውሃ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ይህንኑ ሀቅ ያሳየን ነው፡፡

በጉብኝቱ መርሃ ግብር አስቀድመን የተመለከትነው በምእራብ አርሲ ዞን የሄበን -ነጌሌ- ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ነው። የፕሮጀክቱ ሥራ አስፈጻሚ አልይ አንጊሻ (ኢ/ር) እንዳስረዱት፤ ፕሮጀክቱ ሁለት ክልሎችን፣ ሰባት ወረዳዎችንና 72 ቀበሌዎችን በማስተሳሰር ውሃ ካለባቸው አካባቢዎች ውሃ ወደ ሌለባቸው ሥፍራዎች (በተለይም ቆላማ ቦታዎች) ንጹህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ የሚያደርግ ነው። ፕሮጀክቱ 28 የሚሆኑ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈርና ጥቂት ምንጮችንና ወንዞችን በመጠቀም ጭምር 590 ኪሎ ሜትር ዋናና የውስጥ ለውስጥ መስመሮችን በመዘርጋት የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል። እስከ አሁንም ከ516 ሺ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራሽ ማድረግ እንደቻለ አቶ አልይ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ካስቆፈራቸው 28 ጉድጓዶች በተጨማሪ ከደቡብ ክልል ወንዶ ገነት ከተማ አቅራቢያ የወንዝ ውሃ በመጥለፍ እያጣራ ረዥም ኪሎ ሜትር በተዘረጋው መስመር ምእራበ አርሲ ዞን አጄ ከተማ ወደሚገኘው ሪሰርቨር (የውሃ ታንከር) ይልካል። ከታንከሩ የሚነሳው ውሃም እጥረት ወዳለባቸው የከተማና የገጠር ቆላማ አካባቢዎች ይሠራጫል። መሠረተ ልማቱ ከምእራብ አርሲ ዞን አልፎ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ድረስ በመዝለቅ የሀላባ ቁሊቱ ከተማ የመጠጥ ውሃ ጥያቄን መመለስም ችሏል።

የውሃ መሠረተ ልማትን በገጠርና በከተማ ለማዳረስ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በሚገኘው ክፍያ ላይ ብቻ መመስረት ውጤታማ አያደርግም። በመሆኑም ፕሮጀክቱ ጎን ለጎን የራሱን የገቢ ምንጭ ለመፍጠርና አቅሙን ለማሳደግ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም የሄበን -ነጌሌ- ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሻሸመኔ ከተማ የሻላ ሆቴልን በመግዛት መጠቀም ያለ ገቢ እያገኘ ሲሆን፤ ሆቴሉ ይሸጥ ቢባል አሁን ባለው ገበያ 100 ሚሊዮን ብር ይገመታል። አንደኛ ደረጃ የውሃ ልማት ግንባታ ፈቃድና የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ማሽኖችን ከታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በተጨማሪ አንድ ሎደር በመግዛት ወደ ሥራ ለማስጀመር በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው።

የውስጥ አቅምን በማሳደግ ረገድም በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ተችሏል። ያሉት አቶ አልይ፤ ከሪፎርሙ በፊት በነበረው አሠራር አብዛኛዎቹ የውሃ ልማት ድርጅቶች ፓንፖች ወይም ቦርዶች ሲበላሹ ከውሃና ኢነርጂ ቢሮ መፍትሔ እንዲሰጥ ይደረግ ነበር። የወር ደመወዝ እንኳን መክፈል የማይችሉ የውሃ ልማት ተቋማትም ነበሩ። ከሪፎርሙ በኋላ ግን ፕሮጀክቱ የሰው ኃይሉንና አቅሙን በማቀናጀት፤ ማሽኖችን በመጠቀም በሠራው ሥራ በበጀት ዓመቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የተለያዩ የውሃ መሠረተ ልማቶችን ገንብቷል። ከእዚህ ቀደም ለኮንትራክተሮች የሚሰጣቸውን ሥራዎችም በራሱ አቅም ወደ መሥራት ተሸጋግሯል። በኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚከሰተውን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍም ሁለት የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን በ15 ሚሊዮን ብር በመግዛት ለአገልግሎት አብቅቷል። እስከ አሁንም አምስት የውሃ ጉድጓዶች በሶላር ኃይል እየሠሩ ናቸው።

ሶላር ኢነርጂ ተደራሽ ላልሆነባቸው ሦስት የውሃ ጉድጓዶች “አውቶማቲክ ቮልቴጅ ሬጉሌተር” የተባለ ማሽኖች አስገብቷል። ይህም የኤሌክትሪክ አቅም በሚያንስበት ጊዜ ማሽኑ በሚያጠራቅመው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱን ይሰጣል። ማሽኖቹ ከቱርክ ሀገር በ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ተገዝተው የገቡና እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር አዲስ ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ማሽኖቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚቆራረጥባት አርሲ ነጌሌ ከተማ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች ተመሳሰይ ችግር ያለባቸውን ከኤሌክትሪክ ተጽእኖ ነጻ ለማውጣት የሚሠራ እንደሆነ አቶ አልይ ተናግረዋል። ሌላው በእዚሁ በምእራብ አርሲ ዞን የተለመከትነው የአሳሳ-ዶዶላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ነው። ይህም መራሮን ጨምሮ ሦስት ወረዳዎችን ከማስተሳሰር ባለፈ ለገጠር ቀበሌዎችም ተደራሽ መሆን ችሏል። ፕሮጀክቱ የገቢ አቅሙን በማጠናከር በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች በሙሉ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ የንብ ማነብ ሥራ መጀመሩን ተመልክተናል።

ቀጣይ ምልከታችን በባሌ ዞን የሚኦ- አጋርፋ -ጋሰራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ነው። የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ ከሊል ሁሴን እንደሚያስረዱት፤ ፕሮጀክቱ እስከአሁን ባለው የሥራ ሂደት አራት ወረዳዎችን ማለትም ዲንሾ፣ ሚኦ ፣ አጋርፋ እና ጋሰራን አቅፏል። በቀጣይ የሥራ ምእራፍም ጎለልቻ፣ ጃራ፣ ጊኒር ከተማ እና ገጠር ቀበሌዎች በፕሮጀክቱ ተካተው በአጠቃላይ ሰባት ወረዳዎችን የሚያስተሳስር ይሆናል። ፕሮጀክቱ የውሃው መነሻ ከሆነው ዲንሾ ወረዳ ዳናቃ ወንዝ ጀምሮ ወደ ሌሎች ወረዳዎች እስከ አሁን የተዘረጋው ዋና መስመር 186 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።

በቀጣይ የሥራ ምዕራፍ ወደ ጊኒርና ጃራ ተጨማሪ መስመር ሲዘረጋ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ ይደርሳል። ፕሮጀክቱ በአራት የከተማ መስተዳድሮችና 45 ቀበሌዎች የሚገኙ ከ400 በላይ አባ ወራዎችን ተደራሽ በማድረግ ከ1ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። እስከ አሁን በተሠራው ሥራ በተለይም ለአሊ ከተማ እና ለዲንሾ ከተሞች ውሃ አቅርቦትን መቶ በመቶ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። በሌሎች ከተሞችና ቀበሌዎችም በተወሰነ መልኩ ማዳረስ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚሁ በባሌ ዞን በከፍተኛ ወጪ እየተሠራ ያለው የሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮከጅክትም ሌላው የጉብኝታችን አካል ነበር። ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል መጓተት የታየበት እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት በፈጣን የሥራ እንቅስቃሴ የሚገኝ ነው። የሮቤ ከተማን የውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከከተማዋ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ወንዝ መነሻውን ያደርጋል። የተለያዩ የውሃ የማጣሪያ ሂደቶችን አልፎ 4 ሚሊዮን ሊትር በሚይዘው ግዙፍ ሪዘርቨር/ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ውስጥ ገብቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሚያሰራጭ ሲሆን፤ ሥራውም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉብኝታችን ማገባደጃ የተመለከትነው በአርሲ ዞን የሉቁጬ-አሰላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ነው። የአሰላ-ሳጉሬ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ አደም አህመድ እንደሚያብራሩት፤ ቀደም ሲል የሳጉሬና የአሰላ ከተሞች ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር የነበረባቸው ናቸው። በተለይም የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች ለረዥም ጊዜ በመጠጥ ውሃ ችግር ውስጥ ኑረዋል። ዛሬ ለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባደረገው ድጋፍ የሉቁጬ- አሰላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል።

በሰዓት 216 ሜትር ኪዩብ ውሃ የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት የውሃ ጉድጓዶችን በማስቆፈርና መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት የከተሞቹን የንጹህ መጠጥ ውሃ እያቀረበ ይገኛል። 65 ኪሎ ሜትር የዋና መስመር ዝርጋታና 125 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የሥርጭት መስመር ዝርጋታዎች ተከናውነዋል። የገጠር ነዋሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ስምንት ቦኖዎችን በመገንባት አገልግሎት ላይ ማዋል ተችሏል። በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት የሚፈጠረውን የውሃ አቅርቦት መስተጓጎል ለማስቀረትም ጀኔሬተሮች፣ ትራንስፎርመሮችና ፓንፖች ተገዝተው ተገጥመዋል። ቀደም ሲል የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች ከ15 ቀን እስከ አንድ ወር ጠብቀው ውሃ ያገኙ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን በወርም የማይጠፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የከተማዋ የውሃ አቅርቦት ምላሽ ከመስጠት በተጓዳኝ ተቋሙ የራሱን የገቢ ምንጭ በመፍጠር ወደ አጎራባች ቀበሌዎችም ለማስፋፋት የጀመራቸው ሥራዎችም አሉ። የኢኮኖሚ አቅሙን ለማሳደግ ማሽኖችን ገዝቶ ለማከራየት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለውን ቦታም ከከተማ አስተዳደሩ አግኝቷል። የክፍያ ሥርዓቱን ዲጂታል በማድረግ በሁለት ዓመታት ውስጥ ይከፈል የነበረውን ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ብር ወደ 153 ሚሊዮን ለማሳደግ እቅድ ይዞ እስከ አሁን 105 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል።

የኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮና የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በምዕራብ አርሲ፣ በባሌና በአርሲ ዞኖች ለሚዲያ አመራሮችና ለጋዜጠኞች ያዘጋጁት የአምስት ቀናት ጉብኝት በተጠናቀቀበት ወቅት፤ የኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) ባደረጉት ገለጻ፤ በክልሉ መንግሥት፣ በዞኖች፣ በወረዳዎች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በኅብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ ከ3 ሺህ 600 በላይ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታስቦ 2 ሺህ 645 የውሃ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ተችሏል። በእዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ችለዋል። ሙሉ ለሙሉ ካልተጠናቀቁት ውስጥ እንደ ሀሎ ጎባ፣ ነጆ፣ ካለቻ አርበቴ፣ ቁኔ፣ ደደር፣ ቆንዳላ፣ ሀሮ ዋጮ፣ እና ሌሎችም በርከት ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ከ90 በመቶ በላይ ነው። እነዚህም በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ የሚጠናቀቁ ይሆናል፡፡

እስካሁንም ፕሮጀክቶቹ የተጓተቱት በግብዓት አቅርቦት ችግር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ችግሩ በመቀረፉ በፍጥነት በመሥራት በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ይሆናል። ለውጤታማነቱም የቢሮ ሙያተኞችና ኃላፊዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል። የሄበን- ነጌሌ- ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ የአሳሳ ዶዶላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ የባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የሚኦ- አጋርፋ -ጋሠራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና የሉቁጬ- አሰላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እንዲሁም የአሰላ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች አበረታች ውጤት የታየባቸው እንደሆኑና ለሌሎች የሚተርፍ መልካም ተሞክሮዎች ያሏቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

አንዳንድ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሌሎች ዘርፎች በመሠማራት የገቢ ምንጫቸውን በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት አበረታች ነው። ያሉት ኃላፊዋ፤ ለአብነትም በሆቴል ሥራ፣ በንብ ማነብ ሥራና በሌሎችም ሥራዎች የተሠማሩ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን አንስተዋል። ኅብረተሰቡም በአንዳንድ ቦታዎች የሚስተዋሉ የፕሮጀክቶች መጓተትን በትዕ ግስት መጠበቁና በልማቱ ላይ ተሳትፎ ማድረጉም የሚያስመሰግን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለአብነትም የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በውሃ ላይ ታሪፍ በመጨመር ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ችግራቸውን መፍታታቸው ያስመሰግናቸዋል ብለዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮና የኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ ለነበራቸው ድጋፍና አጋርነትም ኢንጂነሯ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ነጌሶ በበኩላቸው፤ ክልሉ ከለውጡ የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍና ውሃን ለማዳረስ አቅዶ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በእዚህም የመጠጥ ውሃ እጥረት የነበረባቸው ወረዳዎችንና የገጠር ቀበሌዎችን በማስተሳሰር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል። በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተደረገው ንቅናቄ ልክ እንደ በጋ ስንዴ ሁሉ አዲስ ታሪክ የተመዘገበበት እንደሆነም አስረድተዋል። አቶ ደስታ የውሃ አቅርቦትን እንደ መንገድና መብራት በከተሞችና በገጠር ቀበሌዎች የማስተሳሰሩ ጅምር የሚያበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ገና ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You