በኢትዮጵያ ከሁለት አመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የሰላም ስምምነት በመፈራረም መቋጫውን ያገኘው የሰሜኑ እርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ጭሯል። ከግጭቱ በኋላ መንግስትና ህወሓት ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ መንገድ በመሻታቸው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ቀጥሎም በኬኒያ ናይሮቢ የሰላም ስምምት ተፈራርመዋል። ይህንኑ ተከትሎም በፌደራል መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የልኡካን ቡድን መቀሌ ገብቶ ከህወሓት አመራሮች ጋር የገፅ ለገፅ ውይይት አካሂዷል።
በዚህም የፌደራል መንግስት ያለገደብ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባና የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እያደረገ ነው። በተመሳሳይ ህወሓትም በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ታጣቂዎቹ ከያሉበት ተሰብስበው ወደካምፕ እንዲገቡ እያደረገና ታጥቋቸው የነበሩ ከባድ መሳሪያዎችን ለሃገር መከላከያ ሰራዊት እያስረከበ ነው።
ከዚህ በተረፈ ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የትግራይ ክልልና የኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነት ቀጥሏል። በአዲስ አበባና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የትግራይ ተወላጆችም ትግራይ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ተገናኝተዋል። የትግራይ ተወላጅ አትሌቶችም በአትሌት ደራርቱ ቱሉ ተመርተው ወደመቀሌ አቅንተው ቤተሰባቸውን፣ ዘመዶቻውንና ጓደኞቻቸውን አግኝተው የናፍቆት ጥማቸውን ቆርጠዋል። ይህን ሁሉ ታዲያ የፈጠረው ሰላም እንጂ ጦርነት አይደለም። ሰላም ሲሆን የማይመለስ ነገር የለምና።
እንግዲህ ከጦርነቱ በኋላ ሰላም በመስፈኑ ከሁሉ በላይ የትግራይ ህዝብ እፎይ ብሏል። የጦርነትን መጥፎ ገፅታ በሚገባ አይቶታልና ሰላምን ከማንም በላይ ይፈልገዋል። ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም ከትግራይ ክልል ህዝቦች ጋር በጋብቻ፣ በደም፣በቃንቋ፣ ሃይማኖት ብሎም በልዩ ልዩ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተሳስረዋልና ሰላሙን ይፈልጉታል። ስለዚህ መንግስትና ህወሓት አሁን ላይ የሰላም ትርጉሙ ምን እንደሆነ በሚገባ ተረድተዋልና በጦርነት ውስጥ እንደመቆየታቸው የነበራቸውን ቁርሾ ወደጎን በመተው ከልባቸው ታርቀው የመጣውን ሰላም ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
የእርቅ ትርጉምና ሂደቶች
መንግስትና ህወሓት ወደ እርቅ ከመሄዳቸው በፊት የእርቅን ውስጣዊ ትርጉም በሚገባ ሊያውቁ ይገባል። ፕሮፌሰር ህዝቅያስ አሰፋ ‹‹የሰላምና እርቅ ትርጉምና መንገዶች›› በሚል ርእስ በ2006 ዓ.ም ባሳተሙት መፅሃፍት የእርቅን ትርጉም እንዲህ ያብራራሉ፡-
‹‹እርቅ›› ማለት በከባድ ፀብና ይህም ባስከተለው መጎዳዳት፣ ጥላቻና መፈራራት ምክንያት ተለያይተው ተራርቀው፣ ተቆራርጠው የነበሩ ሰዎች የወደመውን የጋራ ኑሯቸውን እንደገና ለመገንባት የሚጓዙበት ሂደት ነው። /እዚህ ጋር ሰዎች ተብሎ የተጠቀሰው መንግስትና ህወሓት ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። / እርቅ የጥቅል ሰላም ግንባታ ዘዴና ዓላማ ነው። ስለዚህ እርቅ ትርጉሙ ይህ ከሆነ ሂደቱ የሚከተሉትን እርምጃዎች ያጣቃልላል።
1ኛ. በግጭቱ ተካፋይ የሆኑት ወገኖች ሁሉ በግጭቱ ግዜ በሌላው ላይ የፈፀሙትን በደልና ጉዳት በሀቀኝነት መንፈስ ማመን /መቀበል/ እና ሃላፊነት መውሰድ፤
2ኛ.ይህም በደል ስህተት መሆኑን በማመን እውነተኛ ፀፀትን መግለፅ፤
3ኛ.ከተበደለው ሰው ከልብ ይቅርታን መጠየቅ፤
4ኛ.ተበዳዩ ለበዳዩ ይቅርታ መስጠት፤
5ኛ.ተበዳዩን ጉዳት ከመድረሱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ ወይም በደሉ ያስከተለውን ጉዳት መካስ፤
6ኛ. በደሉ እንደገና እንደማይፈፀም አስተማማኝ የሆነ ማርጋገጫ መስጠት፤
7ኛ. ከግጭቱና ካስከተለው ጉዳት በመማር የሁለቱንም ወገኖች ጥልቅ ፍላጎትና ጥቅም የሚያራምድ፣ የሚያጎለምስና የሚያስተሳሰር አዲስ ግንኙነቶችን መመስረትና አዲስ እቅዶችን መቀየስ፤
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት እርምጃዎች አንድ በአንድ ትርጉማቸው ምን እንደሆኑና ተፈፃሚም እንዲሆኑ ምን ምንን እንደሚጠይቁ ማወቁ ተገቢ ነው። እነዚህ ነጥቦች ከላይ ከላይ ሲታዩ በተለምዶ አነጋገር ‹‹እርቅ›› ከሚባሉት ጋር ተመሳሳይ ቢመስሉም ውስጣቸው ምን ያህል የተለዩ መሰረተ ሃሳቦች እንዳሉባቸው በጥንቃቄ መመልከት
ያስፈልጋል።
1ኛ. ሃላፊነት መቀበል
የመጀመሪያው የእርቅ ርምጃ ሌላው ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰው ወገን የፈፀመውን በደል ማመንና ሃላፊነት መውሰድ የሚል ነው። የተፈፀመው በደል ከተካደ ወይም ከተደበቀ እውነተኛ እርቅ ላይ መድረስ አይቻልም። አውነቱ መውጣት አለበት። ያለ እውነት ዘላቂ እርቅ አይመጣም።
በመጀመሪያ ሙሉውን እውነት በሁሉ ገፁና ትርጉሙ ለማወቅና ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። እያንዳንዳችን እውነትን የምናየው በህይወት ልምዳችን በታነፀ መነፅር ነው። የህይወት ልምዳቸን ከሰው ወደ ሰው እንደሚለያይ ሁሉ መነፅሩም ይለያያል። ስለዚህ እውነቱን በገሃድ ለማውጣት በምንፈልግበት ግዜ እያንዳንዱ የግጭቱ ወገን ሀቁን እንዴት እንደሚመለከተው መመርመር አስፈላጊ ይሆናል። ሁሉም ወገኖች ሀቁን በተመሳሳይ ሁኔታ ካላዩት ‹‹እኔ ነኝ ልክ›› ከሚል ፉክክርና ግትርነት አልፎ ባላንጣዎቹን ወደ ሃላፊነት መቀበልና ወደ ፀፀት፤ ከዚያም ወደ እርቅ ለመምራት አይቻልም። ሁሉም የግጭቱ ወገኖች ለሀቁ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ሲሆን ወደ እርቅ ለመጓዝ እንዲችሉ ከፍተኛ ችሎታ ያለው አስታራቂ እንደሚያስፈልግ ፤የአስታራቂውም ሚና የባላንጣዎቹን የአመለካከት ልዩነት ማጥበብና ሁሉም ወገኖች የሚዩት ሃቅ በተቻለ መጠን ተመሳሳይ እንዲሆን መርዳት ይሆናል።
ሁለተኛ፤ አንዳንድ እውነታ አልፎ ሲወጣ ይበልጥ የሚያራርቅ፣ የሚለያይና የሚያጣላ ሊሆን ይችላል። የዳኛ ሃላፊነቱ ፍርድን መስጠት እንጂ የማስታረቅ ስላልሆነ፣ የሚወጣው እውነት በባላጋራዎች ግንኙነት ላይ ያለው ውጤት ብዙ አያሳስበውም። ነገር ግን የእርቅ ስራ ለማቀራረብ እንጂ ለማራራቅ ስላልሆነ እውነትን የማውጫው ዘዴ በጣም በላቀ ጥበብ መሆን አለበት። እውነት ይደበቅ ወይም ይሸፈን ማለት ሳይሆን የእውነት አወጣጡ ዘዴ ሀቁን ሁሉም ወገኖች ሊያዩትና ሊያዳምጡት በሚችሉት ሁኔታ መሆን ይኖርበታል።
ሶስተኛ፤ እውነቱን ብቻ ማውጣት ሳይሆን ፤ እውነቱ እንዴት ነው የወጣው የሚለው ጥያቄ ለእርቅ መሳካት ብዙ አስተዋፅኦ አለው። በዳዩ እውነቱን ያወጣውና ሃላፊነቱን የተቀበለው ብዙ ተፅእኖ ተደርጎበት፣ በህግ ተገዶ፣ ወይም ራሱን ከቅጣት ለማዳን በሚል አስተሳሰብ ሲሆን ለእርቅ ያለው ግንዛቤ የላላ መሆኑን ይጠቁማል።
በአንጻሩ በዳዩ የፈፀመው በደል ስህተት መሆኑን አውቆ በራሱ ተነሳሽነት የሚደርገው የጥፋት መናዘዝና ሃላፊነትን መቀበል ለእርቅ ያለው ፍላጎት ጠንካራ መሆኑን ስለሚያመላክት ተበዳዩ ከጥላቻና ፍርሃት ወደ እርቅ ለመጓዝ የመጀመሪያዎቹን እርምጃዎች እንዲወስድ ያበረታቱታል። ያስታራቂው ሚናም ይህንን ርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታትና መደገፍ ይሆናል።
አራተኛ፤ በዳይና ተበዳይ የሚለው መለያ ሁልግዜ ግልፅ ሆኖ አይገኝም። በተለይ ግጭቱ ለረጅም ግዜ የተካሄደ ሲሆን ፤ አንድ ግዜ በዳይ የሆነው ወገን በሌላ ግዜ ተበዳይ፤ ወይም ተበዳይ በዳይ ሆኖ እንገኘዋለን። ከዚያም በላይ ግጭት ቢያንስ ሁለት ወገኖች ስላሉት ብዙውን ግዜ ለግጭቱ ሁለቱም ወገኖች ድርሻ ያላቸው ሆነው እንገኛቸዋለን። አንደኛው ወገን ሙሉ በሙሉ በዳይ፤ ሌላው ሙሉ በሙሉ ከበደል ነፃ የሚሆኑበት ሁኔታ የለም። ነገርግን ሁለቱም ትንሽም ይሁን ትልቅ ያደረሱትን ጉዳት ቢቀበሉና ሃላፊነትን ቢወስዱ ለእርቁ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
2ኛ.ፀፀት
የእርቅ ሁለተኛው እርምጃ የግጭቱ ተሳታፊዎች ያደረሱት ጉዳት ስህተት መሆኑን በይፋ ማመንና እውነተኛ ፀፀትን መግለፅ ነው። ፀፀትን ስንገልፅ የተደረገው ድርጊት ስህተት ነው ከማለታችንም በላይ በስህተቱ ማዘናችንንና ድርጊቱን ማውገዛችንን፣ከድርጊቱም ለመራቅ ዝግጁነታችንን እናመለክታለን። ይህ እርምጃ ተበዳዩ በበዳዩ ላይ አጥፍቶት የነበረውን እምነት መልሶ መገንባት እጀንዲጀምር በር ይከፍትለታል፤ ያበረታታዋል። ፀፀቱ ከእውነተኛ ስሜት የመነጨ ሲሆን እርቁ የጠነከረ ይሆናል።
3ኛ. ይቅርታ መጠየቅ
ከተበዳዩ ሰው ይቀርታ መጠየቅ ለፈፀምነው በደል ያለንን ሃላፊነት አወረድን ማለት አይደለም። ይቅርታ መጠየቅ ትክክለኛ ትርጉሙ ‹‹በድያለሁ፤ ጉዳት አድርሻላሁ፣በዚህ ምክንያት የነበረንን ግንኙነቶችንና ያጋራ ህይወት ለማቋረጥ አስተዋጽኦ ማድረጌ ይገባኛል። ነገር ግን ግንኙነታችንን ዋጋ ስለምሰጠው ቀድሞ እንደነበረው እንዲመለስ የተበዳዩን ፍቃድ እጠይቃለሁ፤ ያደረኩትን ስህተት እንዳርም እድል ይሰጠኝ›› ማለት ነው። ይህም ማለት ከበደልነውና ካዋረድነው ሰው ፊት ራሳችንን ዝቅ አድርጎ መቅረብ ማለት ነው።
4ኛ. ይቅርታ መስጠት
በዳዩ ይቅርታ ሲለምን ፤ይቅርታ መስጠት ወይም አለመስጠት የተበዳዩ ነፃ መብት ነው። ይቅርታ መስጠት ከልብ የመነጨ ሳይሆን በተፅእኖ ወይም በግፊት የመጣ ከሆነ እውነተኛ እርቅን አያፈራም። ምን አልባት በፍራቻ ወይም በይሉኝታ ምክንያት ተበዳዩ በአፉ ብቻ ይቅር ብያለሁ ቢልም በልቡ ያለው ቂምና የበቀል ፍላጎት ጠፍቷል ማለት አይደለም።
ተበዳዩ ይቅርታ ሲሰጥ የበዳዩን ሃላፊነት ፍቄያለሁ ማለቱ ሳይሆን ‹‹ምንም መብቴ ቢረገጥም፣ ክብሬ ቢዋረድም፣ በተፈፀመብኝ በደል ምክንያት የፈራሁትን ቁጣ፣ ጥላቻ፣ ቁጭትና ቂም ወደ ጎን ለመተው ጥረት ለማድረግና ከተባደዩ ጋር ያለኝ ግንኙነት እንዲሻሻል በሩን ለመክፈት ዝግጁ ነኝ ማለቱ›› ነው።
ይቅር ባዩ ይቅር የሚለው ቁጣውንና ቂሙን እንጂ የበዳዩን ሀላፊነት አይደለም። በዳዩ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር ግንኙነታቸውን ለመጠገን የጠነከረ ፍላጎት እንዳለውና ይህንንም ዓላማ ለመፈፀም የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለበዳዩ ማሳመን አለበት።
5ኛ.ተበዳዩ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስና መካስ
ተበዳዩ በተፈፀመበት ጉዳት ምክንያት በስቃይ ላይ እያለ/በተለይ በዳዩ በፈፀመው በደል ተጠቃሚ ሆኖ ሲገኝ/፤ በሁለቱ መካከል ትርጉም ያለው ያለው እርቅ ለመፍጠር ያስችግራል። በዳዩ በተቻለ መጠን ተበዳዩ ከጉዳቱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ መርዳት ይኖርበታል። ይህ ሁልግዜ ቀላል አይደለም። አንዳንድ ጉዳቶች ከተፈፀሙ በኋላ ወደቀደመው ሁኔታቸው መመለስ አይቻልም።
ሰው ከሞተ አይመለስም፤ አንዳንድ አካል ከጎደለ ለመተካት፣ ወይም አንዳንድ ጉዳቶች ከተፈፀሙ እንዳልበሩ ለማድረግ አይቻልም። በእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ መክፈል ግዴታ ይሆናል። ይህ ነው በእርቅና በፍትህ መካከል ያለው ግንኙነት። ተበዳዩን ኩጉዳቱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ ትልቅ የፍትህ ስራ ነው።
6ኛ. በደሉ እንደማይደገም ማረጋገጫ መስጠት
በተበዳዮች በኩል ለእርቅ አንድ ትልቅ እንቅፋት በዳዩ መልሶ ይጎዳኝ ይሆናል የሚል ፍራቻ ነው። በርግጥም ይቅርታና መታረቅ እንደገና ለጉዳት መጋለጥና ወንጀለኞች እንደገና ወንጀላቸውን እንዲፈፅሙ እድል መስጠት ከሆነ አደገኛ ነው። ለዚህ ነው ብዙ ግዜ ይቅርታንና እርቅን ተበዳዮች በፍርሃት፣ የሰብአዊ መብት አስከባሪዎች በጥርጣሬ መልክ የሚያዩዋቸው። እርቅ ራስን እንደገና ለጉዳት መዳረግ የለበትም። ይህ እንዳይሆን ጥፋቱ እንደማይደገም በዳዩ አስተማማኝ የሆነ ማረጋገጫ መስጠት አለበት። እርቅ ማለት ለመለወጥ ውሳኔ ማድረግ ነው።
7ኛ. አዲስ ምእራፍ መክፈት
እርቅ የሚቀጥለውና ቁንጮ የሆነው እርምጃ፤ ከግጭቱና ካስከተለው ጉዳት በመማር የሁሉንም የግጭት ወገኖች ጥልቅ ፍላጎትና የጋራ ጥቅም የሚራምድ፣ የሚያጎለምስና የሚያስተሳስር አዲስ ግንኙነቶችን መመስረትና አዲስ እቅዶችን መቀየስ ሲቻል ነው። ይህንን እርምጃ በቀድሞ ባላንጣዎች መካከል ለግንኙነታቸው ‹‹አዲስ ምእራፍ መክፈት›› ተብሎ ሊጠራ ይችላል።
እንግዲህ እርቅ ማለት እነዚህን ሰባት እርምጃዎች በመከተል በግጭቱ ወገኖች ውስጥና መካከል የሚፈጠረው የአካል፣ የማቴሪያልና የመንፈስ መጠገንና መሻር፤ ከዚያም የሚወለደው አዲስ ዝምድና ነው። በርግጥ እርቅን የሚያመጡት እነዚህ ሰባት እርምጃዎች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። እንደ ሁኔታው፣ እንደባህሉ የተለያዩ ወይም ተጨማሪ እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እውነተኛ እርቅ እንዲሆን ከተፈለገ ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ሰባት እርምጃዎች የሚጠይቁትን ማሟላት ግድ ነው። ቢቻል የእርምጃዎቹ ቅደም ተከተል ከላይ እንደተዘረዘሩት ቢሆን ለእርቅ ስራ ያመቻል። ሆኖም ቅደም ተከተሉን መከተል ካልተቻለ፤ ዋናው ዓላማ በአንድ መንገድ ወይም በሌላ የሰባቱን እርምጃዎች ግዴታዎች መፈፀም ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም