ያለፉት አራት ዓመታት ፤ በተለይም የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ሀገራችን እንደ ሀገር በብዙ መልኩ የተፈተነችባቸው ዓመታት ናቸው። በእነዚህ ዓመታት የሀገሪቱን ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረኮች በማጠልሸት አጠቃላይ የሆነውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያጋጠመን ተግዳሮት ከፍ ያለና ፈታኝ ነበር።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በአንድ በኩል እንደ ሀገር ይዘነው የተነሳነው ሀገር በቀል የፖለቲካና ኢኮኖሚ አስተሳሰብ፤በሌላ በኩል ደግሞ ከአስተሳሰቡ በስተጀርባ ያለው ራስን የመሆንና የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን ቁርጠኝነት በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ መፍጠሩ በዲፕሎማሲው መስክ ላጋጠመን ተግዳሮት ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ይታመናል።
ይህን በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ለመቀልበስ መንግስት ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ዳያስፖራውና መላው ሕዝባችን ከፍ ያለ ትግል አካሂደዋል፤ ትግሉ እጅግ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ፍሬ አፍርቶ ሀገር በአሸናፊነት ዘመቻውን በስኬት እንድትወጣ አስችሏታል። በሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥም አዲስ ምዕራፍ ማስመዝገብ አስችሏል።
ይህንን የዲፕሎማሲ ድል አስጠብቆ ማስቀጠል፤ በቀጣይ እንደ ሀገር ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ዋነኛ አቅም በመሆኑ መንግስት ይህንን የስኬት ተሞክሮ ቀምሮ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በዚህም ተጨባጭ የሆኑ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
ለዲፕሎማሲው ስኬት ባለድርሻ የሆኑ አካላትን /ትግሉን በገዛ ፈቃደቻው በሀገር ወዳድነት የተቀላቀሉ ዜጎችንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን/ ከማመስገን ጀምሮ በትግሉ የላቀ ድርሻ ለነበራቸው ዲፕሎማቶች እውቅና መስጠቱ እንደ መንግስት ድሉን አስጠብቆ ለመሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው።
ከዚያም ባለፈ ለዲፕሎማቶች እየተሰጡ ያሉ ሰፋፊ ስልጠናዎችና ስልጠናዎችን እና አቅምን ታሳቢ አድርጎ እየተካሄደ ያለው የአዳዲስ ዲፕሎማቶች ስምሪት፤ የተገኘውን ዲፕሎማሲያዊ ድል አስጠብቆ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
በተለይም ስልጠናዎች እንደ ሀገር በቀጣይ ሊያጋጥሙን የሚችሉ የዲፕሎማቲክ ተግዳሮቶችን ቀድሞ ከማወቅና አማራጭ መፍትሄዎችን ይዞ ከመንቀሳቀስ አንጻር ሊኖራቸው የሚችለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፤ ዲፕሎማቶቻችን ለተልዕኳቸው ብቁ ከማድረግ ባለፈ በራሳቸው የሚተማመኑና ለሀገር መከታ የሚያደርጋቸውን አቅም መገንባት የሚያስችል ነው።
ይህ መንግስት በዲፕሎማሲው መስክ እየፈጠረ ያለው ሁለንተናዊ ዝግጁነት፤በተለይም በልማት ድህነትን አሸንፈን የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የጀመርነውን የለውጥ ጎዳና በስኬት ለማጠናቀቅ የሚኖረው ጥቅም ከፍያለ በመሆኑ የሁሉንም ዜጋ ትኩረት የሚሻ ነው።
በተለይም በዲፕሎማቲክ መስኩ ያሉ የሀገሪቱ ምሁራን መንግስት የጀመረውን እንደሀገር በመስኩ ብቁ ሆኖ የመገኘት ጥረት በማገዝ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሀገራቸው ዲፕሎማት በመሆን ባላቸው አቅም ሁሉ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ለሀገር ዲፕሎማት ለመሆን ከሹመትም በላይ ዜጋ መሆን በቂ ነው።ይህንን ትልቅ የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት፤ ትናንት በዘርፉ ያጋጠመን ዓለም አቀፍ ተግዳሮት ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ እንደ ሀገር ልንከፍል እንገደድ የነበረውን ዋጋ ማሰብ ተገቢ ነው።
በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚኖረው ተግዳሮት የቱን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በመረዳት በዘርፉ ያሉ ምሁራን ፈተናዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ አሸንፎ መውጣት የሚያስችል አስተሳሰብ መገንባትና ለዚህ የሚሆን መናበብ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘውን ድል አስጠብቆ፤ በተሻለ መንገድ የማስቀጠል ኃላፊነት የመንግስትና የጥቂት ዲፕሎማቶች ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። ይህ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጨባጭ የታየ እንደመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ትልቅ ሀገራዊና ሕዝባዊ ተልእኮ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም