የጥምቀት በአል በመላው ኢትዮጵያ ካለፈው ረቡእ የከተራ በአል ጀምሮ በድምቀት ተከብሯል። ትናንትና ዛሬም ከጥምቀት በኋላ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በሚከበሩ ሀይማኖታዊ በአላት የበአሉ ስሜት እንዳለ ነው። ጥምቀት ከሀይማኖታዊ አንድምታው ባሻገር የአደባባይ በአል እንደመሆኑ የአለባበስ ነገር ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ይህ በአል በዩኒስኮ የማይዳሰሱ የአለም ቅርሶች አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ የአለባበስ ጉዳይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በእርግጥም በዚህ በአል ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉም በባህል አልባሳት በተለይም በነጭ አልባሳት አምረውና ደምቀው መታየት ኢትዮጵያን ከሌላው አለም የሚለያት አንድ ትልቅ እሴት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የባህል አልባሳት ኢንደስትሪው እየዘመነ ሲመጣ የባህል አልባሳት እጅግ አምረውና ባህላዊ እሴቱን ጠብቀው በስፋት መታየት ችለዋል። ይህ የአደባባይ በአል በተለይም የወጣቶች በአል ተደርጎ ስለሚታይ የወጣቶች በነዚህ የባህል አልባሳት መሳብ ሌላውም አለም የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋል ማለት ይቻላል።
ዛሬ ላጋራ የፈለኩት ትዝብት ግን ከዚህ በተቃራኒ በበአሉ ላይ የተስተዋሉ ኢትዮጵያንና ባህላዊ እሴቷን ስለማይገልጹ አልባሳት ነው። በርካታ ወጣቶች በዚህ ረገድ የሚመሰገኑ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከአለባበስ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ ስርአት አልባ ለብሰው ይታያሉ። በአልባሳት ዲዛይን ላይ የሚስተዋለውን የባህል መደበላለቅ ለጊዜው ወደ ጎን እንተወው። ብዙ ወጣቶች በዚህ በአል ላይ የዘመኑ ባህላዊ አልባሳትን መልበሳቸውን እንጂ ስለስነስርአቱና ኢትዮጵያዊ እሴቶች ትኩረት ሲያደርጉ አይስተዋልም። ይህ በአብዛኛው በወጣት ሴቶች አለባበስ ስርአት ላይ የሚስተዋል ነው። ጨርቁ ባህላዊ መሆኑ እንጂ የአለባበስ ስርአቱ ወይም ልብሱ የተሰራበት ዲዛይን ግድ የማይሰጣቸው ጥቂት አንደሉም። ለምሳሌ ያህል ቀሚሱ ምንም ያህል ባህላዊ ቢሆንም ዲዛይኑ ከእግር ጀምሮ በረጅም ስንጥቅ ጭንን ካለ ቅጥ አጋልጦ የሚያሳይ ከሆነ ኢትዮጵያዊ የአለባበስ ስርአት ሊሆን አይችልም። አልፎ ተርፎም በባህላዊ ጨርቅ የተሰራ በጣም አጭር ቀሚስ በዘመኑ አጠራር “ሱፐር ሚኒ” ለብሰው በበአሉ ላይ የሚታዩ አልጠፉም። ይህ ባህላዊ አልባሳትን ማዘመን አይደለም። ሰው የፈለገውን ለብሶ አደባባይ መውጣት መብቱ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ቢያንስ በእንዲህ አይነት ታላላቅ የአደባባይ በአላት ላይ መሆኑ ቀስበቀስ ስር እየሰደደ ከሄደ ያለንን አኩሪ የአለባበስ እሴት ሸርሽሮ ገደል እንዳይከተው መጠንቀቁ አይከፋም። የባህል አልባሳት ዲዛይነሮች በብዛት ባህልና እሴትን ጠብቀው እጅግ ማራኪ አልባሳትን በመስራት የሚመሰገኑ ቢሆንም አንዳንዶች የውጪ ገበያ ለመሳብ በማሰብ ሊሆን ይችላል ተገቢ ያልሆኑ ባህላዊ አልባሳትን ያቀርባሉ። ይሄ ዞሮ ዞሮ ለእኛው ጠንቅ ነው። ባህላዊ ጨርቆችንና ንድፎችን ተጠቅሞ በዘመናዊ መንገድ መስራቱ ለገበያም ይሁን ባህሉን ለማሳደግ ጥሩ ቢሆንም በዲዛይኑ ረገድም መጨነቅ ተገቢ ነው።
ማኅበረሰብ በመኖር መስተጋብር ውስጥ የሚፈጥራቸው ልምዶች በጊዜ ሂደት ወደ ባህልነት ያድጋሉ፡፡ ይህ ማኅበረሰባዊ ልማድ በጊዜ ዑድት ውስጥ የሚያድግ ፤ ከአንዱ ማኅበረሰብ ወደ ሌላ ማኅበረሰብ የሚወራረስ እንደ ሆነ ሁሉ በትውልድ መለዋወጥ ውስጥ ማኅበረሰብ ካለው ባህል ላይ የሚጠቅመውን እያነሳ እና ጎድቶኛል ያለውን እየጣለ ይሄዳል፡፡
ባህል ያልተፃፈ ግን ማኅበረሰቡ በስምምነት ያወጣው ሕግ ነው፡፡ ባህል የአንድ ማህበረሰብ መገላጫም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ኃይል ሳትገዛ የኖረች አገር መሆንዋ ማኅበረሰቡ የራሱን ቀለም ሳይለቅ ባህሉን ጠብቆ እንዲኖር ያደረገውም ለዚህ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያላቸው አገራት እንደ ኑሮ ዘያቸው መለያየት የሚገነቡት በርካታ ባህል አለ፡፡ ታድያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ነባር የነበሩ የመከባበር፣ የመደማመጥ እና የእርቅ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ ግጭት የነገሰበት መደማመጥ ያቃተው፣ መከባበር የተሳነው ማኅበረሰብ መታየት ጀምሯል፡፡ይህም በኢትዮጵያ ሰፊ የባህል ወረራ ስለመኖሩ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር መሰብሰብ መጀመሯና የቴክኖሎጂ መስፋፋት ለዚህ የባህል ወረራ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ፊልሞች ፣ የሙዚቃ ክሊፖች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚታዩ ክዋኔዎች በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይኸው የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ለባህል ወረራ መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ሁሉ የፋሽን ኢንደስትሪውም የራሱን ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
በአገራችን ለሚታየው የባህል ወረራ የቴክኖሎጂ ግንኙነት መጠናከር መስፋፋት ተጠያቂ የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የባህል ወረራ መሠረታዊ ችግሩ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ፣ፋሽንና ወዘተ መምጣት አይደለም፡፡ ችግሩ ለማኅበረሰቡ ቀደሞ አጠቃቀሙ ላይ ግንዛቤ ካለመፈጠሩ ጋር የተያያዘ ነው።
በ2006 ዓ.ም በባህል ወረራ ላይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው ለባህል ወረራው የመገናኛ ብዙሃኑ እና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ የነበረው ፖለቲካ ስርዓት በአገራዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ አገራዊ እሴቶች ጠባቂ አልባ ሆነዋል።
በ1950ዎቹ መጨረሻ ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት በኢትዮጵያ ሲመሠረት ከዚህ ቀደም የነበረውን አገራዊ እሴቶች ማስቀጠል አልቻለም፣ “የራስን ጥሎ የሰውን አንጠልጥሎ” ይሉት የፖለቲካ ባህል ዳብሮ ቆይቷል።
በዘመናዊው የፖለቲካ ስርዓት ቀደምት የኢትዮጵያ እሴት የነበሩ ልማዶች እንደ ኋላ ቀር እና የማይጠቀሙ ተደርገው መሳላቸው አሁን ለደርስንበት የባህል ውዥንብር አጋልጦናል። የማኅበረሰቡ የንባብ እና የውይይት ባህል ሊያድግ አለመቻሉ አሁን ለሚታየው የባህል መደበላለቅ ዳርጎናል።
የባህል ወረራን የሚዋጋ ማኅበረሰብን ለመገንባት ባህልን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ማኅበረሰብን ስለ እሴቶቹ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ ላይ በትኩረት መሠራት ይገባል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት የባህል ወረራ ችግሮችን በመለየት የመከላከያ ስልት ነድፎ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል። የባህል ወረራን በመከላከል እረገድ የወጡ ሕጎች ቢኖሩም የወጡትን ሕጎች ማስፈጸም ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖሩ ሚስጥር አይደለም። የባህል ወረራን መከላከል ለአንድ ተቋም የሚተው ሥራ አይደለም። ሁሉም ዜጋ በአካባቢው የሚመለከታቸው መጤ ተግባራት በመዋጋት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት አለበት። መጤ ባህልን በመዋጋት ረገድ የተለያዩ የሙያ ማህበራት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት አለባቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም