የሕዝብ በዓላት መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩት አጠቃላይ በሆነው ሕዝብ ሁለንተናዊ ጥበቃ ሲደረግላቸው እንደሆነ ይታመናል። በዚህም በመላው ዓለም ብዛት ያላቸው ባሕሎች ትውልዶችን ተሻግረው ዛሬ ላይ መገኘት የሚያስችላቸውን ዕድል አግኝተዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ ዘመናትን ተሻግረው አሁን ላይ የቀደመ ሁለንተናዊ ሞገሳቸውን እና ክብራቸውን ተጎናጽፈው የሚገኙ ብዛት ያላቸው የሕዝብ በዓላት ባለቤት ናት። እነዚህ በዓላት ከበዓልነት ባለፈ ለሀገራዊ ማንነት መገለጫ የሆኑ መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴቶች መሆናቸው ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ አቅም ሆኗቸዋል።
በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችም በዓላቱ የያዟቸውን መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴቶች ከየትኛውም ዓይነት ጥፋት ለመታደግ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። “ሃይማኖትህንና ባሕልህን የሚያጠፋ ጠላት ስለመጣ ተነስ ” የሚሉ የክተት አዋጆች የዚህ እውነታ አንድ ማሳያ ናቸው።
መላው ሕዝብም የክተት አዋጆቹ የያዙትን ከፍያሉ እሴቶችን ታሳቢ በማድረግ ጨርቄን ማቄን ሳይል ውድ ሕይወቱን መስዋዕት ያደረገባቸው የታሪክ ምዕራፎችና ለዚህም የተከፈለው ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለማንነትና ለሕልውና የተከፈለ መስዋዕትነት ተደርጎ በታሪክ ምዕራፎች የተዘከረ ነው ።
አሁን ላይ በአደባባይም ሆነ በጓዳ የምናከብራቸው ብሔራዊ በዓላት ያለ ዋጋ ዘመናትን ተሻግረው እዚህ የደረሱ አይደሉም፤ በአንድም ይሁን በሌላ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ዋጋ ያስከፈሉ ፤ የመስዋዕትነት ታሪካችን አንድ አካል ናቸው።
ዛሬም ቢሆን እነዚህን በዓላት እሴታቸውን አስጠብቆ የመሄዱ እውነታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዓላቱን /በተለይም / የአደባባይ በዓላትን ለእኩይ ተግባር መዋያ በማድረግ ከበዓላቱ በስተጀርባ ያሉ ታላላቅ መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴቶችን በማደብዘዝ ሁለንተናዊ ሃገራዊ ቀውስ ለመፍጠር የሚጥሩ የውስጥ እና የውጪ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም።
በተለይም እንደ ጥምቀት ያሉ መንፈሳዊና ባሕላዊ ዕሴቶቻቸው ከፍ ያሉ የአደባባይ ሕዝባዊ በዓላትን የእኩይ ተግባራቸው ሰለባ ለማድረግ በቀደሙት ዓመታት ሆና በዚህም ዓመት ብዙ የጥፋት ኃይላት ተንቀሳቅሰዋል። ለዕኩይ ዓላማቸው ስኬትም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።
ይህም ሆኖ ግን ሕዝባችን ለበዓላቱ ካለው ከፍ ያለ ከበሬታ፤ ከዚያም በላይ በዓላቱ ማንነቱ/የእኔነቱ መገለጫ ከመሆናቸው የተነሳ ያሰቡት ሳይካላቸው ቀርቷል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ እነዚህን ሕዝባዊ በዓላት ጠብቆ ለቀጣይ ትውልዶች ከማስተላለፍ አንጻር ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻሉ የጥፋት ኃይሎቹ ተልዕኮ እንዲመክን ትልቅ ጉልበት ሆኗል።
የዚህ ዓመት የከተራ ሆነ የጥምቀት በዓል በሰላም ተጀምሮ የመጠናቀቁም ምስጢር፣የበዓሉ አከባበር ከስጋት ነፃ የሚያደርገው ሃገራዊ ዐውድ ኖሮ ሳይሆን መላው ሕዝባችን ለበዓሉ በስኬት ተጀምሮ እስኪያልቅ ሁለንተናዊ ጥበቃ በማድረጉ ነው።
ሕዝባችን በዓላቱንና በዓላቱ የተሸከሟቸውን መንፈሳዊና ባሕላዊ ዕሴቶች ጠብቆ ማክበር በመቻሉ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሕዝብ ከማንነቱ ጋር ያለውን የጠበቀ ትስስር በተጨባጭ ያሳየና በከፋፋይ ስብከቶች የማይወሰድ ጠንካራ ስብዕና ባለቤት መሆኑን በአደባባይ ያስመሰከረበት ጭምር ነው።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ በዓላቱ በያዟቸው መንፈሳዊና ባሕላዊ ዕሴቶች በተገነባበት ስብዕና በዓላቱን ጠብቆ ለትውልዶች ማስተላለፍ በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘቱ የጥፋት ኃይሎች ያሰቡትና የተመኙት እንዳይሆን አድርጓል። ይህ ደግሞ የሚበረታታና ከፍያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015