የወጣቶች አገልግሎት በበዓላት ወቅት ከፍተኛውን ሥፍራ እየያዘ መምጣቱ ለብዙዎቻችን አዲስ አይደለም። በተለይ በተለያዩ ሃይማኖቶች ክብረ በዓላት ላይ እየተለመደ መጥቷል። ባህል ሆኖም ቀጥሏል። በዚህ ወቅት በርካታ ወጣቶች በተለያየ መልኩ ይሳተፋሉ። ወጣቶች በመዝሙር፤ በእልልታና በዘፈን በማጀብ የሚያደምቁ የበዓላት ጌጦች ናቸው። ከዚያም አልፈው የሰላም ዘብና ጠበቆች ሲሆኑ ይታያሉ። የማህበራዊ መስተጋብር አጋፋሪዎችም እየሆኑ ያገለግላሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረውና በአዲስ አበባ ከንቲባዋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የቀጠለው ማዕድ የማጋራት ተግባር በእነዚህ ወጣቶች ተጠናክሮ እየተሠራበትም እንደሆነ በተለያየ መልኩ እየተመለከትነው ነው። በየትኛውም ዐውድ ዓመትም ሆነ የንግሥ በዓላት ጊዜ ነዳያን የሚጎርሱት ሲያጡ አይታይም። እንዲያውም ከእነርሱ አልፎ ተርፎ የበዓላቱ ታዳሚዎች ሲመገቡም እናስተውላለን። ይህ ደግሞ ለተቸገሩና ለተራቡ ሰዎች መድረስ እንደሆነ ማንም አይክደውም።
ይሄንና ሌሎች የወጣቶችን መልካም ተግባር ከምናይበት አንዱ በዓል ደግሞ ዛሬ እያከበርነው ያለነው የጥምቀት በዓል ነው። የጥምቀት በዓል ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ደግሞ ወጣቱ በበዓሉ ላይ ያለው ተሳትፎ በእጅጉ ጨምሯል። ወጣት እንዳልካቸው ዐቢይ በቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ለጥምቀት በዓል ዝግጅት ደፋ ቀና እያሉ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች የእንዳልካቸውም ላብ በሥራ ጠፍ ጠፍ እያለ ነበር።
የታቦታቱን ምንጣፍ በመሸከምና በማንጠፍ ለዓመታት ሲሳተፍ ነበር። አሁንም ያንኑ ተግባሩን ለማስቀጠል እየሠራ ሳለ ነው ያገኘነው። ወጣቱ ተወልዶ ያደገው በዚያው በቤተክርስቲያን አካባቢ በመሆኑ በተለያዩ የንግሥ በዓላትና በተለይም በመስቀልና በወርኃ ጥር በሚከበረው የጥምቀት በዓል ዝግጅት ላይ ከታዳጊነቱ ጀምሮ ሲሳተፍ ኖሯል።
እሱ እንደሚለው፤ በቤተክርስቲያኑ ወጣቱ በተለያየ መልኩ በበዓሉ ዝግጅት ይሳተፋል። በተለይ የጥምቀት በዓልን እሱን ጨምሮ በቤተክርስቲያኑ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በልዩ መንፈሳዊ አቀባበል ነው የሚያከብሩት። በዓሉ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በዚሁ አግባብ እንዲከበር በትጋት ይሠራሉ። ከሥራቸው አንዱና ዋነኛው ደግሞ በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ማድረግ ነው። ይሄም በዓሉን የተመለከተ እንቅስቃሴ ባለበት ቦታ ሁሉ የሚተገበር ሲሆን፤ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች አካባቢያቸውን ጨምሮ እነሱ አጅበውት የሚሄዱት ታቦት የሚንቀሳቀስበትን ቦታ ሁሉ ነቅተው የሚጠብቁበት ነው፡፡
የበዓሉ ታዳሚ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ በበዓሉ ላይ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ባለስልጣናትን እንዲሁም ምዕመናንን መጨናነቅ እንዳይኖርባቸው መንገዶችን በመክፈት ያስተናግዳሉ። በዚህ በዓል ላይ ለዚህ ሲባል የሚመደብ ፖሊስ ቢኖርም ወጣቶች አስፈላጊና ጥንቃቄ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በቡድንና በጾታ ተከፋፍለው ፍተሻ ያካሂዳሉ።
በርካታ ወጣቶች የሰው መጨናነቅን ለመቀነስ ምዕመናንን በማስተባበር ጭምር ይሳተፋሉ። ለታቦታቱ ምንጣፍ በማንጠፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። በተለይ የቅዱስ ዑራኤል ወጣቶች አካባቢው ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ዘወትርም ሆነ በንግሥ በዓላቶችና እንዲህ ባለው በዓል ለአደጋ እንዳይጋለጥ እየሠሩ ይገኛሉ። እንዲሁም ሌሎች ለየት ያሉና ለብሔራዊ ገጽታ ግንባታ ፋይዳ ያላቸውን የፈጠራ ሥራዎች የሃይማኖቱን ሥርዓት በጠበቀ መልኩ ይዘው ይቀርባሉም፡፡
ኮሮና በመጣበትና ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ በሆነበት ቤተክርስቲያን ሳይቀር እነዚህ ወጣቶች በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ ነበር። አንዱ ምዕመናኑ አገልግሎቱን በጥንቃቄ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ አቅመ ደካሞች፤ አረጋውያንና ነዳያን ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመውደቃቸው ከሆቴሎች እንዲሁም ከተለያዩ ባለሀብቶች ገንዘብ በማሰባሰብና ከየኪሳቸው በማዋጣት ማዕድ ማጋራቱ ላይ ሲተጉ ነበር። ማዕድ የማጋራቱ ተግባር አሁንም በእንደዚህ እንደ ጥምቀት ባሉ ታላላቅ በዓላትና በሌሎች የንግሥና ወርኃዊ በዓላቶች ላይ በቋሚነት ያደርጋሉ።
‹‹ያለ ወጣቶች ተሳትፎ አገር የወደፊት ራዕይ ሊኖራት አይችልም›› ሲል አስተያየት የሰጠንን ወጣት ታምሩ መርጋ ብዙ ጊዜ የሚሳተፈው በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ ታቦታት የአብዛኞቹ ማደሪያ በሆነውና እንደ ከተማ አስተዳደር የበዓሉ ሥነሥርዓት በደምቀት በሚከናወንበት ጃን ሜዳ ነው። በዚህም እሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች አካባቢውን ለበዓሉ ዝግጁ ማድረግ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ፅዳት የጀመሩት በዓሉ ገና ሳምንት ሲቀረው ነው። በዓሉ በሰላም እንዲከበርና በዓሉ እንዳይስተጓጎልና የሃይማኖቱን ተከታይን የሚጎዳ ተግባር እንዳይፈጸም በዓሉ እስኪጠናቀቅ እንደሚሠሩ ይናገራል። ተሳትፏቸው በማግስቱ በሚከበረውና ከማደሪያው ወደ ማረፊያው በሚገባው የቅዱስ ሚካኤል በዓልም ይቀጥላል።
በአካባቢው ብቻ ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በንግሥ በዓላቸው ምክንያት በጥምቀት ዕለት ወደየ ደብራቸው የማይመለሱና እስከ ንግሳቸው የሚቆዩ ታቦታት ባሉበት ቦታ ሁሉ እየሄዱ በዓሉን በዝማሬ፤ በዘፈንና በእልልታ እንደሚያደምቁም አጫውቶናል። ከዚያ ባሻገር ያዘጋጁትን ንፍሮ፤ ዳቦ፤ እንዲሁም እንጀራ በወጥ ለበዓሉ ታዳሚዎች በተለይም በኑሮ ውድነት ለተቸገሩና ለነዳያን የማብላት መርሐ ግብርን ያከናውናሉ።
ወጣቱ እንደሚለው፤ ወጣቶቹ የንግሥ ወጣቶች ብቻ መሆን የለባቸውም። አገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መሳተፍ አለባቸው። ከሃይማኖታዊው ባሻገር ባህላዊ እሴቶቻቸውንም ጠብቀው ማቆየት ይገባቸዋል። ቤተክርስቲያኗም ሆነች በየደረጃው ያለው የመንግሥት ኃላፊ ወጣቱን ለአገር ግንባታ መጠቀም አለበት።
ከየእምነቱ አባቶች ጋር በመቀናጀት በዕለቱ እንደ ተከበረው የጥምቀትና ሌሎች በዓላት የተሰበሰበው ወጣት እንደ መስቀል ወፍ እስኪበተን ሳይጠብቁ ለአገሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው። ከቤተክርስቲያኒቱ አንዱ የሆነውንና ባህላዊ እሴት የሚደመረውን በገና እንዲማር ማድረግ በራሱም ትልቅ ነገር ነው። ወጣቱን እንዲህ ባለው የተቀደሰ አገልግሎት ተሳትፎ ራሱንና አገሩን ከሚጎዱ ክፉ ሥራዎች እንዲታደግ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል።
ወጣቱ በቅዱስ መጽሐፍ ሮሜ 13፥7 «ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ» ያለውን አዛውንቶችንና አቅመ ደካሞችን በበዓሉ ከሚደረግ ግፊያና ከመጨናነቅ ከመታደግ ጀምሮ ክብር መስጠትም ያስፈልጋል። በተለይ የሃይማኖት አባቶች የወጣቱን ጉልበት ከመጠቀም ባሻገር ብዙ መሥራት የሚችሉት ነገር አለ። ይህም ተከታታይነት ያላውና ለሕይወቱና ለአገሩ የሚጠቅም መንፈሳዊና ግብረገባዊ ትምህርት እያስተማሩ ማሳደግ ላይም መሥራት ነውና እርሱን ሊያስቡበት ይገባል ይላል።
ወጣት ምንታምር ወንድማገኝ በምስካይ ኅዙናን መድኃኔዓለም ታቦት ሽኝት ላይ ምንጃርኛ ዘፈንን ከእስክስታ ጋር አጅባ የምታከብር ናት። በየዓመቱም የተለያዩ ዘፈኖችን በመዝፈንና በጭፈራ እያደመቀች ታቦታቱን እስከ ማደሪያቸው ትሸኛለች። ጥምቀት ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም በመዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘፈንም የሚደምቅ እንደሆነ ታምናለች። ስለዚህ እርሷም ይህንን ነው የምታደርገው።
የዘፈን እሴቶች በዩኔስኮ በተመዘገበው ጥምቀት ተለይተው መታወቅ አለባቸው። በዓሉ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊም ነው። ስለዚህም የእምነቱ አባቶችና የመንግሥት አካላት ማህበራዊ መስተጋብሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሁነቶችን በሙሉ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ አለባቸው። ምክንያቱም ባህልን ማክበር ሰላምና ልማትን መፍጠር ነው። እኛም ይህ ባህላዊ እሴት ይጠናከር በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። መልካም የጥምቀት በዓል!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015