የጥምቀት በዓል መልከ ብዙ ብቻ ሳይሆን በርካታ ትርጉሞች ያለው፤ ይሄንኑ መልክ እና ትርጉሙን መስሎና ሆኖ ማክበርን የሚጠይቅም ነው፡፡ የጥምቀት ትርጉሙ እንደ እምነቱ ተከታዮች የጥምቀቱ ባለቤት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት አምነው የመቀበላቸውን፤ የአዳኝነት እና ከመከራ ወደ ድህነት (መዳን) የማሻገሩን ምስጢር በዓደባባይ የሚመሰክሩበት፤ በንስሃ እና ይቅርታ ውስጥ ሆነው ስለተደረገላቸው ነገር ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበትን ሁነት የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአምላካቸውን የማዳን ባህሪ ብቻ ሳይሆን በማዳን ጉዞው ውስጥ የፈጸማቸውን የትኅትና እና ራስን ለዓላማ መስጠትን ተላብሰው የሚገልጡበት ነው፡፡
የጥምቀት መልኩም እንደ ትርጉሙ ሁሉ የበዛ እና የላቀ ነው፡፡ ይሄ መልኩ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን የብዝሃነት መልክ አንጻር ሲቃኝ በእጅጉ በኅብር ደምቆ እንዲገለጥ የሚያደርገውን ውብ እሴት ይላበሳል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን እንደ አገር የጥምቀት ክብረ በዓልን ሲያከብሩ መልከ ብዙ ሆነው፤ በብዝሃነታቸውም ኅብር ፈጥረውና በጋራ ደምቀው በመሆኑ ትልቅ ቦታን ሰጥተው የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡
ከጥምቀት በዓል እሴቶች አንዱ ትህትና ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ግብሩ ከትኅትና ተነጥሎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዴት ቢሉ፣ የጥምቀት በዓል ሲከበር ክርስቶስ እየሱስ ፈጣሪ ሳለ በፍጡር፣ አምላክ ሳለ በሰው፣ ጌታ ሳለ በአገልጋዩ እጅ በትህትና ዝቅ ብሎ የተጠመቀበት ዕለት ነውና፡፡ ፈጣሪ ከቆመበት የጌትነት ስፍራ ዝቅ ብሎ ትኅትናን ያሳየበት ይሄ እውነት ደግሞ፤ ትእቢትን በትህትና የመሻር፣ እብሪትን በትዕግስት የመተካት ልዕልናን ያሳየበት፤ የሰው ልጅም እንዲሁ የአምላኩን ቃል ተቀብሎ ለታላቅ ተግባር መታዘዝን ያስተማረበት ነው፡፡ በመሆኑም በዓለ ጥምቀቱ ሲከበር ሰዎች ይሄን ትኅትና ሊላበሱና ትኅትናንና ዝቅ ብሎ መታዘዝን ገንዘባቸው ሊያደርጉ የተገባ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ትኅትናን ሀብቱ፣ መታዘዝን ገንዘቡ ያደረገ ሕዝብ ደግሞ የትናንት እሴቱን አጥብቆ፤ የዛሬ ስጦታውን ወደተሻለ ዕድል ለውጦ እና የነገ ተስፋውን በትጋት አጅቦ ለማሳካት የሚጥር ባለ ተሰጥዖ ትውልድ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ትናንቶቹ የነበራቸው የትኅትና እና የመታዘዝ ሀብት ዛሬን እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፤ የዛሬው ሕዝብም ከዛሬ የተሻገረ የሰብዕና እሴት ኖሮት ነገን የመሥራት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሄ ግን በተደላደለ መንገድ የሚጓዝ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ጥምቀቱን የሚያከብር ሕዝብ ትኅትናን ጨምሮ የጥምቀቱን እሴቶች ሀብቱ ካደረገ ይሄን ለማድረግ የሚያግደው ምድራዊ ኃይል አይኖርም፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የከተራ እና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ «እኛ የዛሬው ትውልዶች ለአገራችን ፊት ቀዳሚዎቿ እንደሆንን ማመን ይገባናል። እኛ መከራዋን ሳንቀበል ለኢትዮጵያችን ምቾት፣ ዝቅታውን ሳናይ ለአገራችን ከፍታ፣ ጨለማውን ሳንጎበኝ ለልጅ ልጆቻችን ብርሃን እንደማይመጣ ማወቅ አለብን»፣ ሲሉ መናገራቸውም ይሄንኑ ሃቅ ያረጋገጡበት ነው፡፡
እውነት ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው እንዳሰፈሩት ሁሉ፤ አገራችን በድህነትና እርዛት የጠየመ ፊቷን፣ በኋላቀርነትና በጉስቁልና የተፈተነ መልኳን በአዲስና በብርሃን የመተካት ኃላፊነት እያንዳንዳችን ትከሻ ላይ ወድቋል። ኃላፊነታችንን በአግባቡ ከተወጣን የማናፍርባትን አገር፣ የሰለጠነች ኢትዮጵያን፣ የምንኮራበት ታሪክን ለልጅ ልጆቻችን ማስተላለፍ እንችላለን። ቅድመ አያቶቻችን ዋጋ ከፍለው በማለፋቸው ዛሬ የምንኮራባቸውን አገራዊ እሴቶች እንዳገኘን ሁሉ፤ እኛም ለመጪው ትውልድ ተመሳሳዩን ማድረግ ይጠበቅብናል።
በመሆኑም የጥምቀት በዓል በትርጉሙም ሆነ በመልኩ የሚገለጹ አያሌ ጉዳዮች የበዓሉን ከፍ ያለ እሴት የሚናገሩ ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህን እሴቶች የእምነቱ ተከታዮች በጥቅሉ ሕዝቡ ገንዘቡ አድርጓቸው በዓሉን እንዲያከብር የግድ የሚሉ ናቸው፡፡ ይሄን ሲያደርግ አንድነቱን፣ ይሄን ሲያደርግ ሰላሙን፣ ይሄን ሲያደርግ ብልጽግናውን፣ ይሄን ሲያደርግ የሰውነትንና የአገርን ከፍ ያለ ዋጋ መረዳትን ያረጋግጣል፡፡ ይሄ እንዲሆን ደግሞ ትኅትና እና መልካምነትን ከበዓለ ጥምቀቱ እሴት ወስደን ገንዘባችን ልናደርግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015