የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የሚያስፈልገው አንድ ሰራተኛ(ባለሙያ) በሆነ ዘርፍ ላይ ዕውቀት ለመጨመር ነው። ይህም በመጀመሪያ ዲግሪ ከሚያውቀው በላይ ልዩ ክህሎት ለማዳበር ማለት ነው። በአጭሩ በአንድ ጉዳይ ላይ የዳበረና የበቃ ግንዛቤ እንዲኖረው ማለት ነው፡፡
የሦስትኛ ዲግሪ(ዶክትሬት) ደግሞ ከዚህም በላይ የበለጠ በአንድ ጉዳይ ላይ የጠለቀ ዕውቀት እንዲኖር ነው። ይህ የትምህርት ደረጃ ስሙ ራሱ ‹‹ፒ ኤች ዲ›› ነው የሚሰኝ። የእንግሊዘኛ ምሕጻረ ቃሉ ሲብራራ፤ Doctor of Philosophy የሚል ነው። ፊሎሶፊ ከተባለ እንግዲህ በተማረበት ዘርፍ ውስጥ ጠያቂ እና ተመራማሪ መሆን አለበት ማለት ነው።
ከዚህ የትምህርት ደረጃ የሚጠበቀው ጥናትና ምርምር ነው፤ አዲስ ዕውቀት መፍጠርና ማግኘት ነው። ለማህበረሰብ ችግር ፈቺ የሆነ የጥናት ግኝት ማምጣት ነው፡፡
ምንም እንኳን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ጥናቶችን መሥራትና መፍትሔ መፈለግ ቢጠበቅም፤ ቢያንስ ግን ከሦስተኛ ዲግሪ በላይ ደግሞ የበለጠ የሚጠበቅ ነው። የመማር ጥቅሙ ንቁ እና የሰለጠነ ዜጋ በመፍጠር የበለጸገች አገር መገንባት ነው። መቼም ለማንም ግልጽ ስለሆነው ስለትምህርት ጥቅም አናነሳም።
ከላይ የተጠቀሱትን የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ጥናቶች ለመሥራት፣ በአንድ ዘርፍ ላይ ብዙ ባለሙያ ለመፍጠር፣ በአጠቃላይ የሰለጠነ እና የበቃ ዜጋ ለመፍጠር ሰዎች በነፃነት መማር አለባቸው፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ትዝብቴን የማነሳው። ይሄውም የጥናት አማካሪዎች ነገር ነው። በዚሁ ምክንያት ትምህርቱን አቋርጠው የተውት ሁሉ አሉ። ‹‹ጥናትህ ትክክል አይደለም፤ ለመመረቅ አያበቃም›› የተባሉትን ማለቴ አይደለም። እሱማ ትክክለኛና መሆንም ያለበት ነው። ለመመረቅ የማያበቃ ጥናት የሰራ ሰው ዲግሪው ሊሰጠው አይገባም፡፡
ትልቅ ችግር የሆነው የአማካሪዎች አምባገነንነት ነው። አማካሪ ማለት ተማሪው ለሚሰራው ጥናት፤ እንዴት መሥራት እንዳለበት፣ ምን ግብዓቶች መጠቀም እንዳለበት፣ በሚሰራው የጥናት ርዕሰ ጉዳይ አግባብነት ላይ አስፈላጊነቱን መንገር፣ ከጥናቱ መነሻ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ጀምሮ ጥናቱን የሄደበትን መንገድ መከታተልና የሚጨመረውን ማስጨመር የሚቀነሰውን ማስቀነስ፤ በአጠቃላይ ተማሪው ውጤታማ ጥናት እንዲሰራ ማማከር ነው።
ብዙ ተማሪዎች ሲያማርሩ የምንሰማው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። እንኳን በተደጋጋሚ ማግኘት አንድ ጊዜ ለማግኘት እንኳን ሌላ ጥናት ነው። በዚያ ላይ ተማሪዎች አማካሪዎቻቸውን እንደተማረ ሰው ሳይሆን ልክ እንደ በረሃ ሽፍታ ነው የሚፈሯቸው። የተማረ ሰው የሚያናግሩ ሳይሆን የሆነ አስፈሪ ኃይል የሚያናግሩ ነው የሚመስል፤ እየተንቀጠቀጡና እየተሽቆጠቆጡ ነው፡፡
ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ደግሞ ሁሉም ማለት ባይቻልም አንዳንዶች በሚያሳዩት ቁጣና ግልምጫ ምክንያት ነው። ስልክ ሲደወልላቸው ‹‹ለምን ደወልክ/ሽ›› ብለው የሚሳደቡ አማካሪዎች አሉ። ቢሯቸው በተደጋጋሚ ሲኬድ አይገኙም፤ በስልክ እንኳን ቀጠሮ ለመያዝ እንዳይቻል ደግሞ የሚቆጡም አሉ።
አንዳንዶቹ ደግሞ (የተሻለ የሚባሉት) ተደጋጋሚ ቀጠሮ ይቀጥሩና በቀጠሩት ቀን ሁሉ የማይገኙ ናቸው። እነዚህ ቢያንስ ከሚሳደቡትና ከሚቆጡት ይሻላሉ፤ ከዚያ አንፃር ተመስገን ቢያሰኝም ጥናቱ ግን በአግባቡ እየተሰራ አይደለም። ለራሳቸው የግል ሥራ ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው። በዚህ መሃል የተማሪው ጊዜ ይባክናል፤ መመረቅ ካለበት ጊዜ ያልፋል፡፡
እንደሚታወቀው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እንደ መጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ አይደለም፤ የሚመራው ሕይወት አለው። ልጆች ይኖሩታል፤ የተቀጠረበት መደበኛ ሥራ አለ። የትምህርት ክፍያ የሚከፍሉት ከወር ደሞዛቸው ላይ ከልጆቻቸው አፍ ላይ ነጥቀው
ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ነው የሚማረው። የተትረፈረፈ ጊዜ አለው የሚባል አይደለም። ቀልቡን አጥቶ የሚማረው ትምህርት ቶሎ እንዳያልቅለት እንኳን እንዲህ አይነት ማጓተት ያጋጥመዋል። ከዚህም ሲከፋ ደግሞ የአማካሪው ግልምጫና ቁጣ ሌላ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይከተዋል ማለት ነው።
ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ በሰፊው የሚገመተው አማካሪዎቹ የግል ሥራዎቻቸው ወይም ሌላ ተጨማሪ ሥራ ላይ ስለሚሆኑ ነው። ሌላ ሥራ መሥራት የለባቸውም እንዳይባል ደግሞ እነርሱም የቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው። ከደሞዝ የሚገኘው ገቢ ደግሞ ምን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። የዶክተር እና ፕሮፌሰር ልጅ ተጎሳቁሎ ቢታይ፣ መሰረታዊ ነገሮችን ያላሟላ ሆኖ ቢታይ አስቸጋሪ ነው። ምንም እንኳን ምሁርነት በቅንጦት ነገሮች ባይገለጽም ቢያንስ ግን ልጆቻቸው ሲጎሳቆሉ ማየት ልክ አይሆንም።
መፍትሔው ምን ይሁን? ቢባል፤ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ነው። ይሄ ነገር ቀላል ነገር አይደለም። የአንድ አገር መንግሥት ከየትኛውም ዘርፍ በላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ለትምህርቱ ዘርፍ ነው፤ ምክንያቱም ሌላው ሁሉ የሚስተካከለው በትምህርት ነው። ምንም እንኳን የአገሪቱ አቅም ቢታወቅም ቢያንስ ግን በእንዲህ አይነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ለሚሰማሩት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
ይሄ ሲባል ግን ችግሩ የግል ሥራ መሥራታቸው ብቻ ላይሆን ይችላል። የግል ወይም ተጨማሪ ሥራ መሥራታቸው ጊዜ እንዳይኖራቸውና ቀጠሮ እንዳያከብሩ ያደርጋል እንጂ ተማሪ እንዲሳደቡ አያስገድድም። እንዲያውም በራሱ ችግር የቀረ አማካሪ ይቅርታ ነው እንጂ መጠየቅ የነበረበት መገላመጥና ማመናጨቅ አልነበረም። ይህን ድርጊት ለሚፈፅሙ ምሁራን ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል፡፡
በመማር ላይ ያለ ሰው መብቱን ላይጠይቅ ይችላል፤ ምክንያቱም ይፈራል። መምህሩን ‹‹ኃላፊነት ስለተሰጠህ ላገኝህ ይገባል›› ሊለው አይችልም፤ ምክንያቱም ይጎዳኛል ብሎ ይፈራል። ያለው አማራጭ እየተሽቆጠቆጠ መኖር ነው፤ ይሄ ደግሞ ባርነት ነው። ትምህርት ደግሞ በነፃ አዕምሮ ሲሰራ እንጂ በእንዲህ አይነት ባርነት ውስጥ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡
ለመሆኑ ግን በዚህ ሁኔታ የሚሰራ ጥናት ምን አገራዊ ችግር ይፈታል?
የሰዎች መማር ጥቅሙ ወረቀት ለመያዝ ብቻ መሆን የለበትም። ግለሰቡ ወረቀቱን ስለያዘ የደረጃ ዕድገት ወይም ሹመት ያገኝ ይሆናል። እንደ አገር ከታየ ግን የለብለብ ጥናት ችግር ፈቺ አይሆንም። ግለሰቡም የሚማረው ችግር ፈቺ ጥናት ለመሥራት ሳይሆን ወረቀቱን ይዞ የደረጃ ዕድገት ለማግኘት ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ውጤታማ ጥናት የሚሰራው ተማሪው ተገቢውን አማካሪ ሲያገኝ ነው። አማካሪው የሚሰራውን ጥናት እየተከታተለ ሊያበስለው ይገባል፤ ወይም ብቁ አይደለም ብሎ ሊጥለው ይገባል። ይህ አሰራር ቢለመድ ኩረጃ እና ጥናቶችን በሰው የማሰራት መጥፎ ልማድ አይዳብርም ነበር፡፡
በተለይም የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ እንደ ሸቀጥ ገበያ ላይ ሊውል ምንም አልቀረውም። በየኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ‹‹ፕሮፖዛል እናማክራለን›› እየተባለ ይጻፋል። ይህ የዳቦ ስሙ ቢሆንም ውስጡ ሌላ ነው።
ይህ የሚሆንበት ምክንያት አማካሪዎች በሚገባ ስለማይከታተሉትና የተሰራውን ጥናት አገላብጠው ስለማያዩት ነው። ሥራዬ ብለው ቢያዩት ከኢንተርኔት የተለቃቀመ መሆኑን ይደርሱበት ነበር።
ስለዚህ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ያለ የመመረቂያ ጥናት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መንግሥትም ችግሩ ምን እንደሆነ ወረድ ብሎ ማየት አለበት። ምሁራኑም መምህርነት እንደ ሻማ እየቀለጡ ማብራት ነውና እየተጎዱም ቢሆን ከልባቸው ይስሩ፤ ቢያንስ ቀላሉን ነገር መገላመጡንና መሳደቡን ቢተውት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም