በኢትዮጵያ በከፍተኛ ድምቀት በአደባባይ ከሚከበሩ ሐይማኖታዊ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱና ዋነኛው ነው። «ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ» ለተከታታይ ቀናት የሚከበረው የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ የበዓሉ ድባብ ከእምነቱ ተከታዮች ውጭ ባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጭምር አዎንታዊ ተጽእኖ ሲያሳድር ይስተዋላል። በተለይም በዓሉን ለማክበር ወደ አደባባይ የሚወጡ ታዳሚዎች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ደምቀው የሚታዩ መሆናቸው የበአል አከባበሩንና አካባቢውን ጭምር በእጅጉ የሚያደምቁበት እንዲሁም መንፈሳዊና ባህላዊ ጨዋታዎች የሚበዙበት መሆኑ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ አድርጎታል።
እነዚህ ስነስርአቶች የጥምቀት በዓልን ከሌሎች ሐይማኖታዊ በዓላት ልዩ ያደርጉታል። የበዓሉ አከባበር በአደባባይ የሚፈጸምና ከሕዝብ ባህል ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሀገር አልፎ የዓለምን ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
የጥምቀት በዓል ከሕዝብ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ሐይማኖታዊ በዓል ነው ሲባልም በዓሉ ከሐይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳው እጅጉን የጎላ በመሆኑ ነው። በሀገር ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የሚታደሙበት የጥምቀት በዓል ከዓመት ዓመት የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ቀልብ እየሳበ መምጣቱም ለዚሁ ነው።
እየደመቀና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እየሳበ የመጣው ይህ በዓል ሲነሳ አስቀድሞ የሚነሳው የአልባሳቱ ጉዳይ ነው። በዓሉ በተለየ ሁኔታ በአገር ባህል አልባሳት የሚደምቅ በመሆኑ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› በሚል ብሂል ህጻን አዋቂው፤ ሴት ወንዱ፤ ወጣት አዛውንቱ በአዲስ ልብስ ይዋባል፤ ያጌጣል። አብዛኛው ሰው ደግሞ በአገር ባህል አልባሳት አምሮና ደምቆ በዓሉን ለማክበር ወደ አደባባይ የሚወጣ በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።
የዝግጅት ክፍላችንም የአገር ባህል አልባሳትን በማምረትና በመሸጥ በስፋት ከሚታወቀው ከሰፊው የሽሮ ሜዳ ገበያ በመገኘት የበዓል ገበያን ቃኝቷል። በቅኝታችንም የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ገበያ ምን ይመስላል የሚለውን በማንሳት የሸማቹ እና የነጋዴውን ሃሳብ ተጋርተናል።
በርከት ያሉ ነጠላዎችን እንዲሁም ሙሉ ልብስ የሚባለውን ነጠላና ቀሚስ መሆን የሚችሉ የተለያዩ ጥለት፣ ቀለምና ዲዛይን ያላቸውን የአገር ባህል አልባሳት አቶ ኮዝዴ ኮርቃ አንዱ ይዘው ቀርበዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ገበያ ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ገበያው ቀዝቃዛ ነው።
አቶ ኮዝዴ ባለፈው ዓመት ይሄን ጊዜ ገበያው ሞቅ ደመቅ ያለ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ዘንድሮ ቀዝቃዛ እንደሆነና ገዢ እንደሌለ ይናገራሉ። በቀን አንድና ሁለት ነጠላ ቢሸጥ ፤ ከዛ በላይ የለም ይላሉ። ለገበያው መቀዛቀዝም የኑሮ መወደድ አንድ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ነው የሚጠቅሱት።
የጥሬ ዕቃው መወደድ ለገበያው መቀዛቀዝ ሌላው ምክንያት መሆኑንም ይናገራሉ። ለአብነትም ድርና ማግ ካለፈው ዓመት ዘንድሮ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ይጠቅሳሉ። አቶ ኮዝዴ በተመሳሳይ የአገር ባህል አልባሳቱም ዋጋ እንዲሁ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረው፣ አንድ ነጠላ በአማካኝ ከ550 እስከ 600 ብር እንደሚሸጥ ያብራራሉ።
‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› በማለት በዓሉን ቀልቧ ባረፈበትና አዲስ ነው ባለችው የአገር ባህል ቀሚስ ለማክበር የተለያዩ የሀበሻ ቀሚሶችን እያማረጠች ያገኘናት ወጣት ኢትዮጵያ አሞኜ፣ የአገር ባህል አልባሳት ከሌሎች በዓላት በተለየ ለጥምቀት በዓል አስፈላጊ እንደሆነ ትናገራለች።
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአልባሳቱ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደታየ ነው ያስረዳችው። በአንድ ቀሚስ ከሰባት መቶ እስከ አንድ ሺ ብር ድረስ ጭማሪ መኖሩን በማንሳት፤ ለአብነትም የዛሬ ዓመት በሁለት ሺ ብር ይሸጥ የነበረው ቀሚስ፣ አሁን ላይ እስከ ሶስት ሺ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ተናግራለች።
የአልባሳቱን አይነትና ዲዛይን በተመለከተም ወጣት ኢትዮጵያ፤ ካለፈው ዓመት የተለየና ሳቢ የሆነ ዲዛይንም እንደሌለ ነው ያነሳችው። ያም ቢሆን ግን ለበዓሉ ድምቀት ሰው እንደየ አቅሙና እንደየ ምርጫው መግዛት የሚያስችለው ነገር አለ ትላለች።
የአገር ባህል ልብስ በየጊዜው የሚገዛ እንዳልሆነ ጠቅሳ፣ እሷ አልፎ አልፎ አዳዲስ ፋሽን እና ዲዛይን ሲመጣ እንደምትገዛም አጫውታናለች። ነባሩ ልብስ ሲሰለቻት ለታናናሽ እህቶችና ለቤተሰብ በማስተላለፍ አዲስ ፋሽን ሆኖ የመጣውን የአገር ባህል ልብስ መግዛት ታዘወትራለች። በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ታድያ በዓሉን የምታደምቅበት የአገር ባህል ልብስ እንደሌላት ጠቅሳ፣ እሱን ለመግዛት እንደወጣችና ቀልቧ ያረፈበትን አንድ ቀሚስ ገዝታ ለመመለስ አቅዳለች። ለዚህም የሽሮ ሜዳ ገበያ ምርጫዋ እንደሆነና በገበያውም የተለያዩ አማራጮችን ማግኘት እንደሚቻል ተናግራለች።
የልጆች ልብስ ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ማህሌት ሽፈራው በበኩላቸው፤ የዓለም ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮሮኖ ቫይረስ ወረርሽኝ ጋብ ባለበት እንዲሁም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ቆሞ ኢትዮጵያ ሰላም በሆነችበት በዚህ ወቅት የጥምቀት በዓልን ለማክበር መዘጋጀታቸው እጅጉን አስደስቷታል። ‹‹ለፈጣሪ ምስጋና ይግባው›› ያሉት ወይዘሮ ማህሌት፣ ፈጣሪን በማመስገን አጠቃላይ የገበያውን እንቅስቃሴ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ይልቅ ዘንድሮ በጣም የተሻለና ጥሩ ነው፤ተመስገን ሲሉ ገበያውን ገልጸውታል።
የአገር ባህል አልባሳት በየጊዜው በተለያየ አይነት የሚሠራ በመሆኑ በየጊዜው አዳዲስ እና ለየት ያለ ሥራ ይታያል በማለትም፣ ካለፉት ዓመታት ይልቅ ዘንድሮ የተሻሉና ጥራት ያላቸው አልባሳት መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ካለፈው የገና በዓል ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ልዩነት እንደሌለም ይናገራሉ። ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ ከመኖሩ ባለፈ ጥራት ያላቸው አልባሳት ገበያው ላይ እየታዩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም የዘንድሮ የበዓል ገበያን ለየት ያደርገዋልም ብለዋል።
የዘንድሮ የጥምቀት በዓልም ካለፉት ዓመታት በበለጠ በጥሩ ሁኔታና ሞቅ ደመቅ ባለ መንገድ አንደሚከበር ዕምነታቸው መሆኑን በመግለጽም በዓሉን ከሚያደምቁት ዋና ዋና ነገሮች መካከል የአገር ባህል አልባሳት አንዱና ዋነኛው መሆኑን እሳቸውም ተናግረዋል።
ህጻናትና አዋቂዎች፤ ሴቶችና ወንዶች በተለያዩ የአገር ባህል አልባሳት ደምቀው የሚያከብሩት በዓል እንደመሆኑ እርሳቸውም ለልጆቻቸው ይህንኑ ባህል አድማቂ የሆነውን የአገር ባህል አልባሳት ገዝተዋል። የገበያው ሁኔታም ጥሩና ተመጣጣኝ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ማህሌት፤ በዋጋው ላይ የተለየ ሁኔታ መመልታቸውን ይናገራሉ። ካለፈው የጥምቀት በዓል ጋር ሲነጻጸር የሚታየው የዋጋ ልዩነት ብዙም እንዳልሆነና ተመጣጣኝ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የአገር ባህል አልባሳት ነጋዴዋ ወጣት አዜብ ለማ ‹‹የዘንድሮ የጥምቀት ገበያ እንደተጠበቀው አይደለም›› ትላለች። እሷ እንዳለችው፤ የጥምቀት ገበያ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቅና ነጋዴውም ሆነ ሸማኔው ጥሩ ሥራ የሚሠራበት ወቅት ነው። ይሁንና አሁን ላይ ያለው የገበያ እንቅስቃሴ በሚጠበቀው ልክ አይደለም።
‹‹ሰው አለ፤ ነገር ግን ጠያቂ ብቻ ነው እየገዛ አይደለም›› የምትለው አዜብ፤ ከዚህ ቀደም ለጥምቀት በዓል ብዙ ይሰሩ እንደነበር አስታውሳለች። ካለፉት ዓመታት ጋር ሲጻጸር ዘንድሮ የተቀዛቀዘ እንደሆነ ነው ያነሳችው። ለዚህም የኑሮ ውድነቱ አንዱ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው እሷም ያመለከተችው።
የአገር ባህል አልባሳት አቅርቦቱም በሚፈለገው መጠንና በተለያዩ አዳዲስ ሥራዎች ያልቀረበ መሆኑንም ወጣት አዜብ አንስታለች። በጥሬ ዕቃው ላይ በየዕለቱ የሚታየው ጭማሪ እንደልብ መሥራት እንዳልተቻለ ነው ያስረዳችው። ያም ሆኖ ግን ሸማኔውም ሆነ ነጋዴው ባለው አቅም ለበዓሉ ይመጥናሉ ያሏቸውን የተለያየ የጥለት አይነትና ዲዛይን ያላቸውን የአገር ባህል አልባሳት ለገበያ ይዘው መቅረባቸውን ተናግራለች።
ለሴት ለወንዱ፤ ለአዋቂና ለህጻናትና ለሁሉም በየአይነቱ የተዘጋጀው የአገር ባህል አልባሳት ዋጋን በሚመለከትም ካለፈው ዓመት የተለየ ጭማሪ ያልታየበት መሆኑን ወጣት አዜብም ጠቅሳለች። እያንዳንዱ ልብስ እንደ እቃው አይነት፣ ጥራትና ጥለቱ የሚለያይ መሆኑን ገልጻ፣ ለአብነትም ለሴቶች ቶፕ የሚባለው ከ1300 እስከ 1000 ድረስ ሲሆን፣ ቀሚስ የቅናሽ የሚባለው እስከ 3000 ብር እንደሆነና ከፍተኛው ከ30 ሺ ብር በላይ እንደሆነ ገልጻለች። እሷ እንዳለችው፤ የልጆችና የወንዶች አልባሳትም በተመሳሳይ እንደ ጥለቱ የሚለያይ ሲሆን፣ የልጆች ሱሪና አላባሽ እንዲሁም ቁምጣ እስከ 600 ብር ይሸጣል፤ የአዋቂዎች አላባሽ ብቻ እስከ 1000 ብር ይሸጣል።
ነጠላ እየቋጨች ያገኘናት ሌላኛዋ የአገር ባህል አልባሳት ነጋዴ መቅደስ አማረም ገበያ እንዳለፉት አመታት ሞቅ ያለ አለመሆኑን ትጋራለች። የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ገበያ ደብዘዝ ያለ መሆኑን ነው የገለጸችው። እንደ እሷ አገላለጽ፤ የዛሬ ዓመት በዚህ ወቅት ገበያው እጅግ ደማቅ ነበር። ዘንድሮ ግን በጣም ተቀዛቅዟል። ‹‹ለዚህም ነው ነጠላ እየቋጨሁ ያለሁት›› በማለት ገበያው እንዳለፉት ዓመታት ሞቅ ያለ አለመሆኑን አስረድታለች። እንደ ሌሎች ነጋዴዎች ሁሉ ታድያ መቅደስ፤ ለገበያው መቀዛቀዝ የኑሮ ውድነቱ ዋናው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የምትናገረው።
ከሚገዙ ሸማቾች ይበልጥ ጠይቀው የሚሄዱት በቁጥር የበዙ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ የዋጋው መወደድም ገበያው ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም ትላለች።
ለአልባሳቱ ዋጋ መወደድ ደግሞ የክር እና የሌሎች ግብዓቶች ዋጋ መጨመር አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሳለች። ሸማኔው፣ ጠላፊውና ሰፊው የግብአት ዋጋ ሲጨምር ባለቀለት ልብስ ዋጋ ላይ ጨምረው ለመሸጥ እንደሚገደዱ ነው የተናገረችው። የጥምቀት በዓል በዋናነት ሰዎች በአገር ባህል አልባሳት የሚደምቁበትና በዓሉን የሚያደምቁበት እንደመሆኑ በተለያየ ጥራትና ዲዛይን የተዘጋጀውን የአገር ባህል ልብስ በመጠኑም ቢሆን ሸማቹ እንደየአቅሙ እየሸመተ መሆኑን ተናግራለች።
እኛም በሽሮ ሜዳ ተገኝተን የአገር ባህል አልባሳት ገበያን እንደተመለከትነው ሸማኔው የተጠበበባቸው ውብና ድንቅ ቀልብን የሚስቡ አልባሳት በአይነት በአይነታቸው ተደርድረው ተመልክተናል። ይሁንና ነጋዴዎች እንደሚሉት፤ የአገር ባህል አልባሳቱ ዋጋ የሚቀመስ አይደለም፤በዚህ የተነሳም ሸማቹ እንደልቡ መሸመት እንዳልቻለ ታዝበናል። ይህም አብዛኞቹ የባህል አልባሳት አምራቾች የሚስማሙበት ሃሳብ ነው። በተለይም ለአልባሳቱ ግብዓት የሚሆኑ ድርና ማግን ጨምሮ የክርና የሌሎች ገብዓቶች ዋጋ መናር የባህል ልብሱን የመሸጫ ዋጋ ከሸማቹ አቅም በላይ አድርጎታል።
ላለፉት በርካታ ዓመታት ከበዓል መባቻነት የማይዘሉት ባህላዊ አልባሳት አሁን አሁን በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ሳይቀር ሲዘወተሩ ይስተዋላል። በተለይም በበዓላት ወቅት በአገር ጥበብ ልብስ አምሮና ደምቆ መታየት የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምርጫ እየሆነ መጥቷል። ከዚህም ባለፈ አልባሳቱ በውጭው ዓለም እየተለመዱ የመጡ በመሆናቸው አገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አበርክቶ ለመጠቀም መትጋት ያስፈልጋል፤ የግብአት አቅርቦትንም መፍታት የግድ ይላል ። አበቃን!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም