ጥምቀት በሃይማኖታዊ ይዘቱ ካየነው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ በዓል ነው። በባህላዊ ይዘቱ ካየነው ግን የመላው ኢትዮጵያ ባህል የሚታይበት በዓል ነው። ምክንያቱም ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ብዙ ባህላዊ ሥርዓተ ክዋኔዎች የሚከናወኑበት ነው።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የባህል ትስስር ምን ይሆን? ስንቶቻችንስ ልብ ብለነው እናውቃለን? ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ብሄር ወይም የአንድ ሃይማኖት ብቻ ነው የሚባል ነገር አለ ወይ?
ከዓመታት በፊት ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም በማህበራዊ የትስስር ገጹ የጻፈውን፤ እንዲሁም ‹‹ከአሜን ባሻገር›› የተሰኘው የታሪክ መጽሐፉ ላይ የጠቃቀሳቸውን መነሻ በማድረግ የሚከተለውን ዕይታውን ላስቀድም።
በዕውቀቱ ሥዩም ጎጃም ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው። ጎጃም አማራ ነው። እናም ባደገበት አካባቢ እንዲህ ይባላል አለ። ‹‹በሆነ ነገር ሲደነግጡ ‹አቴቴዬን› ገፈፍከው!›› ይላሉ። አቴቴ ቃሉ ኦሮምኛ ነው፤ ባህሉም ኦሮሚያ ውስጥ የነበረ ነው። እነሆ በባህል ውርርስ የጎጃም እናቶች እያሉት ነው። የአጼዎቹ የፈረስ ስም ‹‹አባ›› የሚል ቅጽል አለው። አባ ማለት ኦሮምኛ ነው፤ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የሚባል ነው። እነሆ የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ምኒልክ፣ የአጼ ኃይለሥላሴ… የአጼዎች ሁሉ የፈረስ ስም መነሻው ‹‹አባ›› ነው። አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኛው፣ አባ ጠቅል… እየተባለ ይጠራል።
በዕውቀቱ እንደሚለው፤ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ቁማር የአብሮነት ባህሉን እየጣሉ የሚነጣጥል ዘዴ ነው የሚፈልጉት። ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላትን ድል ያደረጉት በጋራ እንደሆነ የጠላት አገር እማኞች ሳይቀር መስክረዋል። አጼ ዮሐንስ አራተኛ ኤርትራ ውስጥ የግብጽ ወራሪን ድል ሲያደርጉ ከግብጽ በኩል ሆኖ ይዋጋ የነበረው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ አጼ ዮሐንስን ለማገዝ የኢትዮጵያ ብሄሮች ከጫፍ እስከ ጫፍ ይጠራሩ እንደነበር መስክሯል።
እዚህ ጋ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ወግ የተወራረሰው። ‹‹ከተለያየ ማዕዘን የመጡ እኝህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም። በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ። በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል። ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹የአማራ ባህል ›ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም›› ይላል በዕውቀቱ ሥዩም።
ሐተታውን ሲቀጥልም፤ ‹‹ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ ስርዓታችን ነው። አንዲት ጠይም፣ ባለሹርባ ሴት፣ የሐበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው። ይህ ምስል በስነ ስዕል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቢዮንሴና ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰዓት የቡና ስነ ስርዓት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ስርዓታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው››
ይሄን የቡና ስነ ሥርዓት ዘርዝረን እንየው። የእያንዳንዱ ብሄር መዋጮ አለበት። የልጅቷ ሹሩባ የተምቤን ባህል ነው። የሐበሻ ቀሚሷን የሸመነው ሽሮሜዳ የሚሰራ የጋሞ ተወላጅ ነው። ጀበናውን የሰራው የጅማ ሙስሊም ነው። አቦል፣ ቶና እና በረካ የሚለው የአረብኛ ቃል ነው። ታዲያ ይሄንን ውህድ ባህል የአማራ ወይም የኦሮሞ ነው ማለት ፍትሐዊ ነው ጎበዝ?
ከመቶ ዓመታት በፊት ደግሞ ቡና የእስልምና እምነት ተከታዮች ልማድ ነበር ይባላል። ይሄ ኢትዮጵያን በዓለም እያስተዋወቀ ያለው የቡና ስነ ሥርዓት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያበረከተው መዋጮ ነው ማለት ነው። ታዲያ ይሄን መሳይ አኩሪ ባህል ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ላይ የጫኑብን ባህል እንበለው?
ድሮ የሰው ልጅ የኑሮ ሥርዓት ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አስገዳጅ ነበር። እንደዛሬው ከቤቱ ቁጭ ብሎ በበይነ መረብ የፈለገውን ማዘዝ አይችልም፤ በቴሌቭዥን መስኮት የፈለገውን ማየት አይችልም። ያዘዘውን ነገር በቀላሉ ማስመጣት አይችልም። ያለው አማራጭ መሄድና መገበያየት ነበር። ጎንደር ላይ የሚመረት ነገር ወለጋ ውስጥ አይኖርም፤ የወለጋው ጎንደር ውስጥ አይኖርም። የጅግጅጋው ነዋሪ መቀሌ ድረስ ይሄዳል፤ የመቀሌው ሰው አሶሳ ወይም ጋምቤላ ይሄዳል። በእነዚህ ሁሉ መስተጋብሮች የባህልና የታሪክ ውርርስ ነበር። እንዲህ ነው ኢትዮጵያን የገነቧት።
ለእነዚህ ሁሉ ነገሮች የዛሬው የጥምቀት በዓል ምስክራችን ነው። የበዓሉን ባህላዊ ይዘት ልብ በሉ!
ለዚህ በዓል ብዙ ነገሮች ይገዛሉ። የበዓሉ ቀን ልብ ብላችሁ ከሆነ ጎዳናው ሁሉ በሻጮች የተጥለቀለቀ ነው። ያ ሻጭ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ላይሆን ይችላል! እሱማ ልብሱን ለባብሶ ታቦት ያጅባል። የእስልምና ወይም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩ ግን የሥራ ልብሱን ለብሶ ለእሱ የጦፈ ገበያ ነው። አንድ ሙስሊም ባለሱቅ የጥምቀት በዓል መምጣት ከኦርቶዶክሱ በላይ ያስቸኩለዋል። ኦርቶዶክሱ ምን ልግዛ እያለ ሲጨነቅ ሙስሊሙ ምን ላስመጣ እያለ ይጨነቃል። ለጥምቀትና ለገና በዓል የሚገዛዙ ስጦታዎችን ያስመጣቸው የመርካቶ ሙስሊም ነጋዴ ነው። ከዚህም አለፍ ሲል፤ የሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ መለያ የሆነውን መስቀል የሚሰራው የሙስሊም አንጥረኛ / የእጅ ባለሞያ ሊሆን ይችላል ።
በአጠቃላይ የአንዱ በዓል ለሌላው ድምቀት ነው። ባለፈው ዓመት በዓይኔ ያየሁትን ገጠመኝ ልናገር። ከሲ ኤም ሲ ሚካኤል ወደ ወሰን በሚያስወጣው የአስፋልት መንገድ እየወጣሁ ነው። ዕለቱ ልክ የዛሬ ዓመት የጥምቀት ዕለት ነበር። ታቦት በሚሄድበት መንገድ ሁሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ተተክለዋል።
ሰዓቱ ታቦታት ወደየመንበራቸው ሄደው ቤተ ክርስቲያን በአቅራቢያው የሌለ መንገዶች ፀጥ ረጭ ያሉበት ነበር። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በዚህ ሰፊ አስፋልት እየወጣን ሳለ አንድ የተተከለ ሰንደቅ ዓላማ ነፋስ ጣለው። ስንደርስ እናነሳዋለን ብለን ወሬያችንን ይዘን ስንወጣ ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጡ ሙስሊም አባት ሲያነሱት አየን። አንስተው ከላዩ ላይ በነበረች ገመድ ነገር አስረውት ሄዱ።
እኝህ አባት ያ የጎዳና ድምቀት ድምቀታቸው ነበር ማለት ነው። ‹‹ምን አገባኝ ለሌላ ሃይማኖት ማድመቂያ የተሰቀለ ነው›› አላሉም። ያንን ያደረጉት ልቦናቸው አዝዟቸው እንጂ ለማንም ብለው አይደለም። እንዲያውም በአካባቢ ሰው ስለሌለ ለታየታ ብለው እንኳን አይደለም። ግን ያ ድምቀት ድምቀታቸው ነበር።
የጃንሜዳን ጥምቀት የሚያውቅ ያውቀዋል። በቦታው መድረስ ያልቻለ እንኳን በቀጥታ ሥርጭት እና ዘመኑ በፈጠራቸው የቴክኖሎጂ አማራጮች ማየት ይችላል። በባህላዊ ሥርዓተ ክዋኔው ውስጥ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ወግና ባህሎች ይታዩበታል። የወጣቶች ጨዋታዎች ይታያሉ። ይሞ ቃል ይደምቃል።
እንዲህ አይነት መልከ ብዙ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ክብር በመስጠታችን ከእኛ አልፈው የዓለም ሀብት ሆነዋል። እንዲህ አይነት ኢትዮጵያን በዓለም የሚያስተዋውቁ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ልንጠብቃቸው ይገባል!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም