ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን በአደባባይ በድምቀት ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት ደግሞ ጥምቀት አንዱና ዋነኛው ነው። የክርስትና ሃይማኖት አባቶች እንደሚናገሩት፤ ጥምቀት ከሐጢያት የመንጻት ተምሳሌት ነው።ይህን ተምሳሌት ዛሬ ለምንኖርባት ኢትዮጵያ አስፈላጊ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉት።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በመተባበርና በመከባበር የኖሩና ይህ አኩሪ ባህላቸውም ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭው ዓለም ዘንድ እንደ አንድ ትልቅ መገለጫ ሆኖ የሚወሳ ነው። ሆኖም ይህ አኩሪ ባህል ከጊዜ ጋር እየተለወጠና በምትኩም እሾህና አሜኬላ እያበቀለ መምጣት ጀምሯል። በመከባበር ፋንታ፣መወቃቀስ፣በመተባበር ፋንታ መገፋፋት፣ከአብሮነት ይልቅ ልዩነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከዘላቂ ጥቅም ይልቅ በአቋራጭ መበልጸግ፣ ከመስራት ይልቅ ዳተኝነት፣ በራስ ላብ ከመኖር ይልቅ በሙስና ሀብት ማከማቸት አኩሪ ባህላችንን እየወረሩት ነው።
እነዚህ እኩይ ተግባራት ደግሞ የኢትዮጵያውያን መገለጫዎች ካለመሆናቸውም በላይ የትውልድ ድቀትን በመፍጠር የሀገር መፍረስን ያስከትላሉ። ስለዚህም ጥምቀትን ስናከበር በየቦታው የሚታዩትን የጥላቻ፣ የልዩነት፣ የመከፋፈልና የመገፋፋት እሳቤዎችን በፍቅር፣በሰላም፣በመከባበርና በመተሳሰብ በመተካት ሊሆን ይገባል። የበዓሉም መከበር ዋነኛው ፋይዳም ይህ ነውና።
ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር በርካታ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚስተዋሉበት በዓል ነው። በዓሉ በአደባባይ የሚከበር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህልና ወጉን ጠብቆና አሸብርቆ በአደባባይ ይታደማል። ብዝኃ ማንነትም አምሮና ደምቆ ይውላል። የኢትዮጵያ ውበትም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይስተጋባል። የሀገር አንድነትና ህዝባዊ ትስስርም ይጠብቃል።
የኢትዮጵያ አንድነት እና በሰላም ውሎ ማደር የማይመቻቸውና ከብጥብጥና ሁከት አትራፊ የሆኑ ነጋዴዎች ደግሞ ይህንን ውብ መስተጋብር ለማጠልሸት በየጊዜው ጉድጓድ ሲምሱ ይታያሉ። በሃይማኖቶች መካከል ጸንቶ የቆየውን መከባበርና መተሳሰብ ለማደፍረስ የበግ ለምድ የለበሱ ቀበሮዎች ኢትዮጵያውያን በጥምቀት እንዳይደምቁ እኩይ ሴራቸውን ይገምዳሉ። ሆኖም ሰላም ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእነዚህን ክፉ አሳቢዎች ሴራ ሲያከሽፍ እንደቆየ ሁሉ ዘንድሮም ከመቼውም በተሻለ መልኩ አንድነቱን ጠብቆ በዓሉን በሰላም ማሳለፉና የሰላም ጸሮችን ማሳፈሩ የሚቀር አይደለም።
የዘንድሮው ጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ፋይዳው ባሻገር የሀገር ገጽታ የሚታደስበት በዓል ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ደምአፋሳሽ ጦርነት ውስጥ በመቆየቷና በዚህም ምክንያት ውድቀቷን የሚሹ አካላት ስሟን በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር በአገኙት አጋጣሚ ሲያጠለሹ ከርመዋል። በዚህም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የኢትዮጵያን ገጽታ በተበላሸ መልኩ የሚስለው የዓለም ኅብረተሰብ ቁጥሩ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። በተፈጠረው የተዛባ ምስልም በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎታቸውም የተቀዛቀዘበት ወቅት ነበር።
ሆኖም አሁን ኢትዮጵያ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምራለች። የዘንድሮውን የጥምቀት በዓልንም ስታከብር በሰላም ውስጥ ሆና ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን የጥምቀትን በዓል ሲያከብሩ ለሁለት ዓመታት ያህል የቆየውን የጦርነት ገጽታ በሚክስና ሰላሟንና ገናናነቷን በሚያሳይ መልኩ ሊሆን ይገባል። የውጭ ሚዲያዎች ሲዘግቡት ከቆዩት በተጻራሪ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመቻቻል ሀገር መሆኗን ማሳየት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ነው።
በአጠቃላይ ጥምቀት በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ የሚመጣ በዓል ነው። ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያውያን አብሮነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና መተሳሰብ ጎልቶ የሚወጣበት በዓልም ነው። በመሆኑም ከበዓሉ ከሚገኙት ጸጋዎች እንደ ግለሰብም፤እንደሀገርም ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተሳሰብንና መከባበርን በማስቀደም የሀገሩን ሰላም ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም