ኢትዮጵያውያን በአንድነት በዓደባባይ ከሚያከብሯቸው፤ ከፍ ያሉ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ካሏቸው አመታዊ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የአከባበር ሥርዓቱ የሚፈጥረው ድምቀት ደግሞ የሀገር ገጽታን በመገንባት ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ፤ ከሀገር አልፎም በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦም የዓለም ሀብት እስከመሆን የደረሰም ነው።
በክርስትና እምነት አስተምህሮ ቀኑ የዓለም መድሀኒት የሆነው እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሀንስ የተጠመቀበትን ዕለት ለማስታወስ የሚከናወን ቢሆንም፤ ከዚህ ያለፉ ባህላዊ እሴቶችንም ደርቦ የያዘ ነው። ምክንያቱም በዓሉ ከመንፈሳዊ በዓልነቱ በተጨማሪ፣ ባህላዊ እሴቶችን ባካተተ መንገድ በድምቀት መከበሩ፤ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ባለፈ ከእምነቱ ተከታዮች ውጪ ያሉ ሰዎችም ቀኑን በጉጉት እንዲጠብቁ አድርጓል። ይሄ ደግሞ ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀትና ውበት ሆኗል።
”ለጥምቀት ያልሆነ…” እንዲሉ፤ የእምነቱ ተከታዮች በዕለቱ ተውበውና አምረው አደባባዮችን ማድመቃቸው፤ ካህናቱ ልብሰ ክህነታቸውን ለብሰው፣ መዘምራኑ የተለያዩ ጌጠኛ ልብሶቻቸውን ለብሰው በመንፈሳዊ ኅብረ ዜማ ለበዓሉ ድምቀት ሆነው በየአደባባዩ ተውበው መታየታቸው ውበቱን የሚያጎላና ከመንፈሳዊነቱ ባሻገርም በብዙዎች እንዲጠበቅም የሚያደርጉ ናቸው፡፡
በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እውቅና ካገኙ ዓለም አቀፍ የአደባባይ በዓላት አንዱ የመሆኑ እውነታም በራሱ፣ በዓሉ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አስችሎታል። በዚህም በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ ከፍ አድርጎታል። ይሄ ደግሞ የበዓሉን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶችን ከማጎልበት ባለፈ፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ እንዲል አድርጎታል። በቀጣይም ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በዓሉ ከፈጠረው ዓለም አቀፍ ትኩረትም ጋር በተያያዘ በበዓሉ ላይ ለመታደምና ለማክበርም ጭምር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ ይህም ሀገሪቱ ድህነትን አሸንፋ ለመውጣት ለጀመረችው ትግል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል፡፡
በዚህ መልኩ የሚገለጸው የጥምቀት በዓል ታዲያ ከመንፈሳዊ ክዋኔው ባለፈ ባህላዊ እሴቶችን ባከበረ እና የቱሪዝም ሀብትነቱ በሚጎለብትበት መልኩ በሰላም አክብሮ መዋል ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በዓሉን በሰላም ማክበር እንደ ሀገር ያለውን መንፈሳዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን አስጠብቆ ለማስቀጠል ወሳኝ ነው ።ለዚህ ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው።
በተለይም የእምነቱ ተከታዮች የበዓሉን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በአግባቡ በመረዳት በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የሚሆን መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ዝግጁነትም ይጠበቅባቸዋል። መላው ሕዝብም የበዓሉን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በአግባቡ በመረዳት በዓሉ በሰላም ተከናውኖ እንዲያልቅ የተቻለውን ሁሉ ማበርከት ይኖርበታል። ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ ዘብ መቆም ይጠበቅበታል።
የጸጥታ ኃይሎችም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሕዝቡ ጋር በተሻለ ቅንጅት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፤ በተለይም በዓሉ የአደባባይ በዓል ከመሆኑ አንጻር ሊኖራቸው የሚገባው ዝግጁነት ከፍ ያለና አስተማማኝ ሊሆን ይገባል። በዓሉን የእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ከሚፈልጉ የውስጥ ሆነ የውጪ ኃይሎች ለመታደግ የጥፋት ኃይሎችን እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፈጣን እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል። ከሰሞኑ በጸጥታ ኃይሎች እየተወሰዱ ያሉ ሰላም የማስከበር ሥራዎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
በተለይም አሁን እንደ ሀገር ካለንበት የጦርነት ማግስት ሀገራዊ እውነታ አንጻር፣ በዓሉ በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ሰላም በተጨባጭ ለመላው ዓለም ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ስለሚሆን፤ ይህንን አጋጣሚ በአግባብ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል። በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ቱሪስቶች የሀገር ውስጥ ቆይታቸው ሰላማዊና አስደሳች እንዲሆንና ተመልሰው እንዲመጡ የተሻለ ዕድል ለመፍጠር በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማስተናገድ ይገባል!
ከዚህ ጎን ለጎንም እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ፣ የተጠመቀበት በኋላም የሞተበት ትልቁ አላማ እርቅ መሆኑን በማሰብ አሁን ያለንበትን የእርቅ መንገድ ወደ ላቀ ስኬት የሚሄድበትን መንገድ አይናችንን ከፍተን ማየት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም