በሸማ ጥበብ ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ባህላዊ አልባሳት በአይነት፣ በጥራት፣ በዲዛይንና በቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል። የአልባሳቱ ተጠቃሚዎችም ኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን የውጭ ሀገራት ዜጎችም ሆነዋል። ታዲያ እነዚህ ባህላዊ አልባሳት በብዛት በሸማቹ ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውሉት የበዓል ወቅትን ተከትለው ነው። በተለይ በክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የባህል አልበሳቱ ገና፣ ጥምቀት፣ ፋሲካና አዲስ ዓመት በዓላት ሲመጡ ገበያቸው ይደራል። ተፈላጊነታቸውም ይጨምራል። ከበዓላት ውጭ አልባሳቱ ለሰርግ፣ ልደትና ለሌሎችም ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ከበዓላትና ከሌሎች ፕሮግራሞች በተጨማሪ ግን አልባሳቱ በስራ ቀናት ሰዎች ሲለብሷቸው አይታዩም። ልብሶቹ ነጭና ቆሻሻ የማይችሉ በመሆናቸውና ይህንንም ተከትሎ በስራ ቦታ ብዙም ምቾት የማይሰጡ ስለሆኑ በሰዎች ዘንድ ተመራጭ እንዳልሆኑም ይነገራል። አሁን አሁን ግን የባህል አላባሳቱ ከሌሎች ዘመናዊ አልባሳት ጋር ተዋህደው በስራ ቀናትም ጭምር ሰዎች እንዲለብሷቸው በተለየ ዲዛይን ልብሶቹን አዘጋጅተው ለገበያ የሚያቀርቡ አልጠፉም።
ከነዚህ ውስጥ አንዷ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛዋ ቤቴልሔም ጥጋቡ ናት። ቤቴልሔም ጥጋቡ ከጋዜጠኝነት ስራዋ ጎን ለጎን ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድና ከመደበኛ የስራ ልብሶች ጋር ተዋህደው እንዲለበሱ በተለየ ዲዛይን በቤቷ በማዘጋጀት ለገበያ ታቀርባለች።
ጋዜጠኛዋ የባህላዊ አልባሳቶቹን በተለየ ዲዛይን አዘጋጅታ ሰዎች ከበዓላት ወቅት ውጭ በአዘቦት ቀንም ጭምር ከሌሎች ልብሶች ጋር አቀላቅለው እንዲልብሱ የማድረጉን ስራ የጀመረችው በቤቷ ሲሆን በቅድሚያ ስራዎቿን እንካችሁ ያለችው ለስራ ባልደረቦቿ ነበር። የስራ ባልደረቦቿም አላሳፈሯትም። በስራዋ ተደንቀው በሚፈልጉት ትእዛዝ በልዩ ዲዛይን ያዘጋጀችላቸውን አልባሳት ገዝተው ለብሰዋል። ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም በእርሷ የተዘጋጁትን የባህል አልበሳት እንዲለብሱ አድርገውላታል።
በዚህ የተጀመረው የጋዜጠኛዋ የባህል አልባሳትን በተለየ ዲዛይን አዘጋጅቶ ለገበያ የማቅረብ ሥራ ዛሬ ላይ ተጨማሪ ገበያ እየሳበላት የመጣ ይመስላል። ምርቶቿም በተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ‹‹መቀነት የልብስ ንድፍ›› በሚል ስያሜም በህፃናት፣ በልጆችና በአዋቂዎች ከበዓላት ውጭ በሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየትኛውም ጊዜ ከሌሎች ዘመናዊ ልብሶች ጋር ተቀላቅለው ሊለበሱ የሚችሉ አልባሳትን ለተጠቃሚዎች እያቀረበች ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም በክር የህፃናት ጫማዎችንና የግድግዳ ጌጣጌጦችንም በእጇ ሰርታ ከስራ ባልደረቦቿ ባሻገር የሌሎችንም ቀልብ ስባለች።
በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ አልባሳትን በተለየ ዲዛይን በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡ ዲዛይነሮች ቁጥር ጥቂት የማይባል ባይሆንም ጋዜጠኛ ቤቴልሔም እነዚሁ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድና በተለየ ዲዛይን በማዘጋጀት ከበዓላት ውጭ በስራ ቀንም ጭምር በክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅና ተፈላጊ ሆነው እንዲለበሱ በማድረጓ ስራዎቿን ከሌሎቹ ለየት ያደርገዋል። ሲለበሱ ቀለል ያሉና ምቾት የሚሰጡ መሆናቸውም በተጠቃሚዎች ዘንድ ይበልጥ ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
በተጨማሪም የምታዘጋጃቸው አልባሳት በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች በፈለጉት ቦታ ሊለብሷቸው የሚችሉ ናቸው። የጋዜጠኛዋ ዋናው እሳቤም አልባሳቱ በተለየ ዲዛይን ተሰርተው ከክርስትና እምነት ተከታዮች በዘለለ የሌሎች እምነት ተከታዮችም ጭምር በስራም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ እንዲለብሷቸው ማድረግ ነው። በበዓላት ወቅት ብቻ የሚለበሱትን የባህል አልባሳት በተለየ ዲዛይን በማዘጋጀት በአዘቦት ቀንም እንዲለበሱ የማድረግ ትልምም ይዛ ነው የተነሳቸው።
እነዚህ የባህል አልባሳት በተለያየ መጠን ከህፃናት እስከ አዋቂዎች ድረስ በአብዛኛው በትእዛዝ የሚዘጋጁ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ጋዜጠኛዋ የተለየ የዲዛይን ሃሳብ ከመጣላት ልብሱን አዘጋጅታ ለገበያ ታቀርባለች። የልብሶቹም ዋጋ ብዙም ኪስ የማይጎዳ ሲሆን ልብሱ የሚሰራበት ቁሳቁስ ከግምት ውስጥ ገብቶ ለአዋቂዎች ከ700 እስከ 1200 ብር ይሸጣል። ለህፃናትና የልጆችም በዚሁ ዋጋ መካከል ሆኖ ለገበያ ይቀርባል።
ደምበኞቿ ጋር የምትደርሰው ‹‹መቀነት የልብስ ንድፍ›› በሚለው የቴሌግራም ገፅ ሲሆን ደምበኞች በዚሁ ገፅ ገብተው በተለጠፈው ስልክ ቁጥር በመደወል በሚፈልጉት ዲዛይን እንድታዘጋጅላቸው ያደርጋሉ። በተጨማሪም ደምበኞች በባህል ጨርቅ የተሰሩ ጋወን፤ ለቀሚስ ለሱሪ አላባሽ ፤ የክር የሳሎን ጫማዎችን፤ ስካርፎችን፤ ቦርሳዎችን እዚሁ ገጽ ላይ ማግኘት እና ማዘዝ ይችላሉ። ከዚህ ውጭ አብረዋት የሚሰሩ የስራ ባልደረቦቿም ምርቶቿን በመግዛት ያበረታቷታል፤ ሌሎችም እንዲገዙላት ያስተዋውቁላታል። በዚህም የምርቱ ፈላጊ ደምበኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ዜጎችም ጭምር ይፈለጋል። ነገር ግን አልበሳቱን በተለየ ዲዛይንና የሁሉንም ፍላጎት ባማከለ መልኩ መስራት ላይ ገና ብዙ ይቀራል። እንደ ጋዜጠኛ ቤቴልሔም ጥጋቡን የመሰሉና ባህላዊ አልበሳቱን በተለየ ዲዛይንና ለሁሉም በሚስማማ መልኩ በማዘጋጀት ለገበያ የማቅረቡ ጅምር ግን ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ጅምር ባህላዊ አልባሳቱ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገራት ያሉ ዜጎችንም ጭምር ቀልብ በመሳብ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ ነውና ጅምሩ በሌሎችም ዲዛይነሮች ሊጠናከር ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም