መቄዶንያ ሲባል ቀድሞ የሚመጣልን ‹‹ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል የማኅበሩ ቁልፍ ሐረግ ነው፡፡ ማዕከሉ ለረጅም ዓመታት ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ሕመምተኞችንና ሌሎች ወገኖችን ከያሉበት በማንሳት መጠለያና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህን በጎ ተግባር ለመደገፍ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት በምርኩዝ መሄድ መቄዶንያን ከመርዳት አይገታንም በማለት በማዕከሉ ተገኝተዋል፡፡
እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች የዕድሜ ባለፀግነታቸው እና ባሳለፉት ውጣ ውረድ ምክንያት ለራሳቸው እርዳታ የሚፈልጉ ቢሆንም መቄዶንያ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ያላቸውን ተካፍለው ለማሳለፍ በቂ ሞራል አላቸው፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በመቄዶንያ በመገኘት ለማኅበሩ አባላት የምሳ ግብዣ ያደረጉ ሲሆን፤ ግብዣውን ያደረጉት ለአዲስ ዓመት መዋያ ተብሎ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለአርበኞች ማኅበር ከተሰጠ የበዓል ስጦታ መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ይናገራሉ፡፡
‹‹እኛ አቅማችን ቢደክምም በምርኩዝ ብንራመድም ሞራላችን ግን መቄዶንያ የሚገኙት አቅመ ደካሞች ወገኖቻችን ለመርዳት በቂ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በውስጣችን ፍቅርና ሠላም ካለ ተካፍለን እንበላለን ብንታመምም የሚያሳክመን አናጣም ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለእምነታቸው እና ለባሕላቸው ቦታ የሚሰጡ በመሆናቸው ይህን የመሰለ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል እና ኃላፊነት ተሰምቶት በርህራሄ የሚያገለግል የክብር ዶክተር ቢኒያምን ማግኘት ትልቅ ስጦታ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በመሆኑም እርስ በርስ በተገኘው አቅም በመረዳዳት ለማኅበሩ አባላት አስተዋፅዖ ማድረግ የሞራል ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በዓመት ሦስት በዓላትን እንደሚያከብር የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ሚያዚያ 27 የድል በዓል፣ የካቲት 12 ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ከተማ የጨፈጨፋቸው ንፁሓንን ለመዘከር እና ዋነኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በወርቅ ቀለም ያስፃፈው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቀን ተጠቃሽ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም መቄዶንያ ከሚገኙት አቅመ ደካሞች መካከል በጦር ሜዳ ቆይታቸው ከውስጣቸው ጥይት ተለቅሞ ያላለቀ ጀግኖች መኖራቸውን መርሳት እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡
የማኅበሩ አባል እና የምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ትግስት ኃይሌ በበኩላቸው፤ ትውልድ እና ዕድገታቸው አዲስ አበባ ኮሪያ ሰፈር መሆኑን ጠቅሰው፤ ወላጅ አባታቸው የጀመሯቸውን የጀግንነት ሥራዎች ሳይፈፅሙ በማለፋቸው እሳቸውም የአባታቸው ፈለግ በመከተል እያገለገሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
የማኅበሩ አባላት በድጎማ የሚተዳደሩ ቢሆንም ለአዲስ ዓመት ከተሰጠን ላይ ተካፍለን ለማሳለፍ መቄዶንያ መገኘታቸውን ይገልፃሉ፡፡ መቄዶንያ የሚገኙት ወገኖች ከምንም በላይ የሰው ፍቅር የሚያስፈልጋቸው ስለሆኑ ባለን አቅም ሁላችንም እዚህ በመገኘት በገንዘብና በጉልበት መርዳት ቢቻል መልካም መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
በተመሳሳይ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ሻረው፤ ማህበሩ ከ86 ዓመት በፊት የጣሊያን ወራሪ ሀገራችንን በወረረበት ወቅት በመንዝ እና ተጉለት አንቀላፊ በተባለ ቦታ መመሥረቱን ጠቅሰው፤ በወቅቱ በተናጠል የነበረውን ውጊያና ትግል በአንድነት በመሆን ጠላትን ለማዳከም እንደተመሠረተና እስከ መጨረሻው ድረስ ሀገርን ነፃ ያወጣ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
መቄዶንያ በአሁኑ ሰዓት ትልቅ ዓላማ ያለው እና በተግባር ሥራውን እያስመሰከረ የሚገኝ ማኅበር በመሆኑ የአርበኞች ማኅበርም ከበፊት ጀምሮ ተካፍሎ መብላትን የሚያውቅ በመሆኑ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጠ የበዓል ስጦታ በማካፈል ከወገኖቻችን ጋር አብሮ ማሳለፍ መቻሉን ያብራራሉ፡፡
መቄዶንያን ቀደም ሲልም እየመጡ እንደሚጎበኙ ጠቅሰው፤ ማኅበሩ ሰፊ ወጪ እያወጣ ደካሞችን እያገዘ እና በሌሎች ክልሎችም ቅርንጫፎች እያስፋፋ በመሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ እና እገዛ ስለሚያስፈልገው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማገዝ አለበት ይላሉ፡፡
የመቄዶንያ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ የክብር ዶክተር የሆኑት ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤ መቄዶንያ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ተከብረው እንደሚኖሩ እና የጤና ችግር ሲገጥማቸውም የግል ሕክምና ድረስ እየተከፈለላቸው እንደሚታከሙ ገልፀው፤ መንፈሳዊ ሕይወታቸውም ቢሆን ግቢው ውስጥ ለሙስሊሞች፣ ለኦርቶዶክሶች እና ለፕሮቴስታንት ተከታዮች የፀሎት ቦታ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ማኅበሩ ላደረገው አስተዋፅዖ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም