ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ቅሚያ፣ ማጭበርበር እና ሌሎችም በሰው ንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በተለይ በከተሞች አካባቢ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በቀንም ሆነ በሌሊት፤ በስውርም ይሁን በአደባባይ፤ በግልም ይሁን በተደራጀ መልኩ ከአነስተኛ ገንዘብ እስከ ከፍተኛ ንብረት ከግለሰቦችም ሆነ ከተቋማት ሲዘረፍ፣ ሲሰረቅ፣ ሲጭበረበርና በቀማኞች እጅ ሲገባ ማየትና መስማቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ተግባር ዛሬ ላይ በርካታ ዜጎችን ለችግር እየዳረገ ብቻ ሳይሆን፤ ወጥቶ በመግባት እንቅስቃሴያቸው ላይ ትልቅ ስጋትም ሆኗል፡፡
ከስርቆት፣ ዘረፋ እና በሌሎችም የማጭበርበር ስልቶች የሚፈጸሙ ወንጀሎች በተለይ በአዲስ አበባ እና ሌሎችም ትላልቅ ከተሞች አካባቢ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ ችግሩን ለመግታት እና ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ከመኪና ስርቆት ጀምሮ የግለሰቦችን ኪስና ቦርሳ እስከማውለቅ የሚደርሱ የሌብነት ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ አበረታች ሥራዎች ስለመኖራቸው ፖሊስ ከሚያወጣቸው ሪፖርት መገንዘብ ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ በፖሊስ እና በሌሎች የመንግሥት የፀጥታና ደህንነት አካላት የሚከናወኑ ተግባራት ብቻቸውን የሚፈለገውን ውጤት የሚያመጡ አለመሆናቸው እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወንጀሎች የሚፈጸሙት በተጠናና በታቀደ መልኩ ከመሆኑም በላይ፤ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ከኅብረተሰቡ እይታ ውጪ ያልሆኑ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ወንጀሉን ከመከላከል አኳያ ኅብረተሰቡ እነዚህን ሌቦችና ዘራፊዎች በሚመለከትበት ወቅት ለሕግ አካል መጠቆም ወይም እንዲያዙ መተባበር ይኖርበታል፡፡
በዚህ መልኩ የሕዝብ ተሳታፎ በጉልህ የሚገለጽባቸው አካባቢዎች የመኖራቸውን ያህል፣ ችግሩን እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሌቦቹ፣ ቀማኛዎቹና አጭበርባሪዎቹ ቦታና ሁኔታን እያዩ የወንጀል ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ የልብ ልብ የሚሰጣቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ሌብነት የቀነሰባቸው ሰፈርና አካባቢዎች የመኖራቸውን ያህል፤ ሌባ በስፋት የሚፈነጭባቸው ሰፈርና አካባቢዎች መበርከታቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዚህ የዘረፋ እና ስርቆት መገለጫ ተጨማሪ መስክ ሆኖ የመጣው ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባል ነን የሚል የማጭበርበሪያ አካሄድን የሚጠቀሙ ግለሰቦች መታየታቸው ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለሚፈጽሙት ወንጀል ማደናገሪያ እና እንደ ማስፈራሪያም ያገለግላቸው ዘንድ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው እንደ መከለያ መጠቀም ያስችላል ብለው ያሰቡትን አንድን የመንግሥት ተቋም መታወቂያ በማዘጋጀት ከተቋም የተላኩ በማስመሰል የሚፈጽሙት ውንብድና ነው፡፡
በዚህ መልኩ ለወንጀል የሚሰማሩ ግለሰቦች በአብዛኛው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መታወቂያ በሃሰተኛ መልኩ በማዘጋጀት የሚጠቀሙና የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሰሞኑን ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የደኅንነትና የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን የሚሉ ግለሰቦች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ይሄን አስመልክቶም አገልግሎቱ በተለያዩ መንገዶች ክትትል ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ በዚህ መልኩ ኅብረተሰቡን እያጭበረበሩ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡
ሰሞኑን በተደረገ ጥብቅ ክትትልም፣ ፈለቀ ዴብሳ ደማ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02፣ አስፋው አዳማ ሙታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ሳምሶን ገነነ መንገሻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ ተስፋ ሀተው ገምቴሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ሰበታ ክፍለ ከተማ፣ ዮሰን በቀለ ትክሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክፍለ ከተማ ሐሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መታወቂያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትንም ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ለሕገወጥ ድርጊት የሚያውሉ ግለሰቦችም በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ሥምሪት ተይዘዋል፡፡
እነዚህን አጭበርባሪዎች ተከታልሎ በመያዝ እና በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ በኩል በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት እና እየተወሰደ ያለው ርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጥረት ብቻውን ለውጤት የሚበቃ ባለመሆኑ እነዚህን አጭበርባሪዎች ተከታትሎ ለሕግ አካል የማሳወቅና የመንግሥት አጋዥ አቅም መሆን ከኅብረተሰቡ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ረገድ ኅብረተሰቡ የመንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን በማለት በሐሰተኛ መታወቂያ የማጭበርበር ድርጊት ለመፈጸም ከሚሞክሩ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ለጥቆማ በተዘጋጁ መስመሮች ጭምር ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ እንዲሁም በየደረጃው ላሉ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በማድረስ በተለይም በከተሞች አካባቢ እየተበራከቱ የመጡ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም