ሰላም ልጆች እንዴ ናችሁ! ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጎበዝ ልጆች ሁሌ ሳምንቱን የሚያሳልፉት በትምህርት ነው።እናንተም ጎበዝ ተማሪ ስለሆናችሁ ሳምንቱን ያሳለፋችሁት በትምህርት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።ጎበዝ ተማሪዎች የጊዜን ጥቅም በሚገባ ያውቃሉ ስለዚህ ያላቸዉን ጊዜ በአግባቡ በመከፋፈል ይጠቀማሉ፤ ማንበብ ባለበት ሰዓት ያነባሉ፤ መጫወት ባለባቸው ሰዓት ይጫወታሉ፤ መማር ባለባቸው ሰዓት ደግሞ ይማራሉ። እናንተም ሰዓታችሁን እንደዚህ በስርዓት ከፋፍላችሁ እንደምትጠቀሙበት አምናለሁ፡፡
ልጆች ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት በተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ እውቅናን ያተረፉትንና እናንተም በርግጠኝነት የምታውቋቸውን ሁለት መንታ እህታማቾች ነው፤ እስቲ እነማን እንደሆኑ ገምቱ።ሄራን ተሾመ እና ሶሊያና ተሾመ ካላችሁ ትክክል ናችሁ።ሄራንና ሶሊያና የአምስት ዓመት ህፃናት ሲሆኑ በቪዥን የአይነ ስውራን የኬጂ አንድ ተማሪዎች ናቸው።
ልጆች ሄራንና ሶሊያና እጅግ ፈጣኖች እና ነገሮችን በቀላሉ ማስታወስ የሚችሉ ድንቅ ልጆች ናቸው።አንዴ ብትተዋወቋቸው ሌላ ቀን ስታገኟቸው አይረሷችሁም ልክ ድምፃችሁን እንደሰሙ በስማችሁ ይጠሯቹኋል።ይሄ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ታውቃላችሁ፤ ነገሮችን የሚዳምጡት በትኩረት ነው።ስለሁሉም ነገር ማወቅ ስለሚፈልጉ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃሉ።ከዚያ ግን ለጥያቄያቸው የሚሰጣቸውን መልስ በፍፁም አይረሱም፤ ይህንን ማድረጋቸው በትምህርታቸው ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ በጣም አግዟቸዋል።ክፍል ውስጥ የተማሩትን እና አስተማሪዎቻቸው የሚነግሯቸውን በፍፁም አይረሱም፤ የተማረውን የማይረሳ ልጅ ደግሞ በፈተና ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ እናንተም ታውቃላችሁ አይደል? ስለዚህ የማታውቁትን መጠየቅ እና ለጥያቄዎቻችሁ የሚሰጣችሁን ምላሽ በደንብ ማዳመጥና ሌላ ጊዜ ለማስታወስ መሞከር አለባችሁ፤ ሄራንና ሶሊያናም የሚመክሯችሁ ይሄንኑ ነው፡፡
ልጆች ሌላውና አስገራሚው የሄራንና የሶሊያና ችሎታ ምን መሰላችሁ ነገሮችን በእጆቻቸው በመዳበስ ለይተው ማወቃቸው ነው።እናንተ እንደነሱ በአይናችሁ ሳታዩ በእጆቻችሁ ብቻ ነገሮችን ምን ምን እንደሆኑ መለየት ትችላላችሁ? እነሱ ግን ጓደኞቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ መምህራኖቻቸውን፣ የሚኖሩበትን ቤትና የሚማሩባቸውን ክፍሎች በእጆቻቸው በመዳበስ ይለያሉ። ይሄንን ችሎታ ቸውን ለማዳበር የረዳቸው የቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ነው፤ ቤተሰቦቻቸው ነገሮችን በእጆቻቸው ብቻ በመዳሰስ እንዲለዩ መጀመሪያ እነሱ እጃቸውን ይዘው በማስነካት ምን እንደሆነ ይነግሯቸዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን ራሳቸው በመንካታ መለየት ይጀምራሉ፡፡
ሁለቱ እህትማቾች መንታ ስለሆኑ ሁሌ የሚገኙት አንድ ቦታ ነው፤ ሶሊያና ለሄራን ያላት ፍቅር ልዩ ነው፤ ሄራንም ለሶሊያና ያላት ፍቅር የሚያስቀና ነው።ነገር ግን ይህ ፍቅራቸው እርስ በርሳቸው አንዳቸው ላንዳቸው ብቻ ያላቸው ፍቅር አይደለም፤ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ሁሉ ልክ እንደራሳቸው ይወዳሉ።ልጆች እናንተም ልክ እንደ ሄራንና ሶሊያና እህትና ወንድሞቻችሁን መውደድ አለባችሁ፤ ቤተሰቦቻችሁንና በዙሪያችሁ ያሉትን ሰዎች በሙሉ መውደድ አለባችሁ።ፈጣሪም ደስ የሚለው ሰዎች ሲዋደዱ ነው፤ እናንተ ደግሞ ፈጣሪ ደስ እንዲለው ትፈልጋላችሁ አይደል? ስለዚህ ሁሉንም ሰው መውደድ የሚያስቀይሟችሁንም ይቅር ማለት አለባችሁ።ሄራንና ሶሊያናም ይህንኑ እንድታደርጉ ነው የሚመክሯችሁ፡፡
ልጆችዬ ሄራንና ሶሊያና ሁል ጊዜ ምን ያደርጋሉ መሰላችሁ፤ ኦዲዮ ባይብል ያዳምጣሉ።ኦዲዮ ባይብል ማለት በድምፅ የተቀዳ የመፅኃፍ ቅዱስ ትምህርት ማለት ነው፤ መፅሃፍ ቅዱስን ሲለሚያደምጡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ያውቃሉ፤ ለሌሎችም ያዳመጡትን ይነግራሉ፤ መዝሙር ሲዘምሩም ጎበዞች ናቸው።ሌሎች ልጆችም ልክ እንደነሱ በየእምነታቸው መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቁራሃንን ማንበብ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ፡፡
መንትያዎቹ ልጆች ከመልካቸው መመሳሰል ባሻገር አብዛኛውን ጊዜ የሚፈልጉት ነገርም ይመሳሰላል ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለሁ።ሄራንና ሶሊያናም ወደፊት መሆን የሚፈልጉት እና የሚያደንቁት ሰው ተመሳሳይ ነው።የሚያደንቁትና ወደፊት ልክ እንደሱ መሆን እንፈልጋለን የሚሉት ማንን መሰላችሁ፤ ታዋቂው እና በስራዎቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈውን አርቲስት ዳዊት ፅጌን ነው።ለምን እሱን መሆን እንደሚፈልጉ ሲናገሩ “እሱ በጣም ጎበዝና ታታሪ ነው፤ በጣም ሰው ያከብራል ጥሩ ስነምግባር ያለው ሰው ነው” ይላሉ።ከዚህ ቀደም በአካል አግኝተውትም ይህንኑ ለራሱ ነግረውታል።
መንትዮቹ ወደፊት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ምን መሆን እንደሚፈልጉ እስቲ ገምቱ? ዶክተር፣ ሳይንቲስት፣ ወይም መምህር ካላችሁ ጎበዞች ናችሁ።ዶክተር ለታመሙ ተስፋ ነው፤ በህመም የሚሰቃዩ ሰዎችን በማከም ወደ ጤናቸው እንዲመለሱ ይረዳቸዋል የሚወስዱትንም መድሃኒት ይሰጣቸዋል፤ መምህራን ተማሪዎቻቸውን በእውቀት የበለፀጉ እንዲሆኑ በማድረግ የተለያዩ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ የእውቀት እናት እና አባት ናቸው። ሳይንቲስቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተመራምረው ለዓለም አዲስ እና ችግር ፈቺዎችን ሰዎች ያፈራሉ።ስለዚህ ሄራንና ሶሊያና እነዚህን ሙያዎችን ከልባቸው ስለሚወዷቸው ዶክተር፣ መምህር እና ሳይንቲስት መሆን ይፈልጋሉ፡፡
ያሰቡትንና የሚፈልጉትን ለመሆን ደግሞ ጠንክረው መማር እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ትምህርታቸውን በአግባቡ ይማራሉ። እናንተም የምትፈልጉትን ለመሆን ከፈለጋችሁ ትምህርታችሁን በአግባቡና በትኩረት መከታ ተል እንዳለባችሁ ነው የሚመክሯችሁ።
ልጆች ቤተሰቦቻቸውን ማስቸገር የለባቸውም፤ የእናትና አባታቸውን ምክር መስማት እና ተው አታድርጉ የተባሉትን ነገር መተው አለባቸው።ትምህርት ቤትም መምህራኖቻቸው የሚያስተምሯቸውን ትምህርት በደንብ ማዳመጥ እና ማጥናት አለባቸው፤ እርስ በርስም መዋደድ አለባቸው ሲሉ ምክራቸውን ለናንተ እንዳደርስ ነግረውኛል እኔም ይሄው ለናንተ አድርሻለሁ እንደምትተገብሩትም ደግሞ አምናለሁ።በሉ ለዛሬ እዚህ ላይ ላብቃ ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ፡፡
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም