በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ተወካዮች መካከል ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባለ 12 ነጥብ የሰላም ስምምነት ከደረሱ ቀናት አልፈው ወራት እየተቆጠሩ ነው። በእርግጥም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በአፍሪቃ ኅብረት አስተባባሪነት በተደረሰው ስምምነት ተቋጭቷል።
በሂደት ይከወናሉ የተባሉ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው። ስምምነት ከተደረሰባቸው ነጥቦች መካከል ሕወሓት ትጥቅ_እንደሚፈታ የተደረገው ይጠቀሳል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥም ሌላው ነው።
ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ብቻ አላት በሚለው በሁለቱ መካከል ስምምነት መፈረሙም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። በመሬት ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሕወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ተዋጊዎችን ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ማድረግም አንዱ የስምምነቱ አካል ነው።
የጥይት ድምጽ በዘላቂነት እንዳይሰማ በመስማማት፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችል ዘላቂ ግጭት ማስወገድ የፕሪቶሪያው ስምምነት ይዞ ከመጣቸው አንኳር ውጤቶች አንዱ ነው። በትግራይ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ እና የሽግግር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈርሟል።
የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ለማቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ በስምምነቱ መሠረትም በትግራይ ክልል መሠረታዊ አገልግሎት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የማድረግም ሥራ እየተከናወነ ነው።
በመካከላቸው የነበረውን ጦርነት ለማቆም የተስማሙት የፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት የስምምነቱን ተግባራዊነት ጦርነቱን በማስቆም ጀምረዋል። ከስምምነቱ ዋናውና ቀዳሚ የሆነው አስቸኳይ ተኩስ ማቆም በሁለቱም አካላት ተተግብሯል።
በተለይ በትግራይ ጦርነት የጀመረውና ሁለት ዓመት ለዘለቀው ጦርነት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የነበረው ሕወሓት በይፋ ትጥቁን መፍታት ጀምሯል። ከሁለት ዓመታት በኋላ ስለሰላም መነገሩ ብዙ ተስፋዎችን ይዞ መጥቷል። ትጥቅ መፍታት መጀመር ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሰላም የመኖር ተስፋም እንዲኖራቸው አድርጓል። በትግራይ፤ በአማራና በአፋር ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው መከራ እንዲያከትም ረድቷል። የሰላም ስምምነት መደረጉና በትግራይ ሰላም መስፈኑ የተቋረጡ መሠረተ ልማቶች እንዲጀመሩና ሰብአዊ ድጋፍም በስፋት እንዲገባ በር ከፍቷል።
መንግሥት በጦርነት የተጎዱ በርካታ የጤና ተቋማት ዳግም መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሕክምና ግብዓቶችን በጤና ሚኒስቴር በኩል እያሟላ መገኘቱ ማሳያ ነው። እንደ ስቴትስኮፕ፤ ስትሬቸር፣ ያሉ የሕክምና ግብአቶችና መድኃኒቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል። በዚህም ኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር ችሏል።
ይሄም ብቻ ሳይሆን ጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ወቅት ብልሽት የደረሰባቸው የሕክምና መሣሪያዎች ከአዲስ አበባ ባለሙያ በመላክ ጥገና እንዲደረግላቸው ማድረግ ተችሏል። በዚህም በመታገዝ አብዛኞቹ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ተቋማት የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠት የቻሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅተዋል። እንዲያውም ከሰሞኑ ከወደ ጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚጠቅሰው እንደ ትግራይ ክልል ስምንት ሆስፒታሎችና 26 ጤና ጣቢያዎች መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ጤና ሚኒስቴር በዚሁ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማትን መሠረታዊ አገልግሎት ለማስጀመር ለመድኃኒት እና ለአነስተኛ መሣሪያዎች ግዢ ያስፈልጋል ያለውን ሰባት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ለመሸፈን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እርብርብም እንደሚያሻ ጥርጥር የለውም።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እጅግ በሚያስገርምና ተአምር በሚመስል ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በሚያስደስትም ሁኔታ የአየር ትራንስፖርት በትግራይ ክልል ክፍት ሆኗል። እንዲያውም ከሰሞኑ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የተመራ ልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ መጓዙ የሰላም ስምምነቱ እየጸና ስለመሄዱ ማሳያ ነው።
የጉዞው ዓላማም ለረጅም ጊዜ በጦርነት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የቆዩትና በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አገራችንን የወከሉትን የትግራይ ተወላጅ አትሌቶችንና አሰልጣኞችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት መሆኑም በሚዲያዎች ሲነገር ተደምጧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የትግራይ ተወላጅ አትሌቶችና አሰልጣኞች የጉዞው አካል መሆናቸው በግጭቱ ምክንያት ላልቶ የቆየውን የእርስ በእርስ ማህበራዊ መስተጋብር ለማጠናከር እንደሚበጅም ይገመታል።
በኢትዮጵያ ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት መጀመሩን ተከትሎ፣ በርካታ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሰየም ወደ ትግራይ ጎራ ያሉም ሆነ በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ መገናኛዎች ሲናገሩ ማድመጥ ተችሏል።
በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሠረት የሚጥል እና መንግሥትና ሕዝብም ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ ዕድል የሚሰጥ ነው የተባለለት የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ከአገር ውስጥ አልፎ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጭምር በመዘገብ ላይ ናቸው። እየተከናወነ ያለው ሰላምን የማስፈንና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሁኔታ ክልሉን መልሶ ለመገንባትና የኢትዮጵያንም መጻኢ ዕድል ያማረ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩም ከስምምነት መደረሱ ሁሉም ዜጎች በአገራቸው ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል፤ ለልማትም አነሳስቷል።
በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ እስከ አሁን ባለው አተገባበር ተስፋ ሰጪ ነው። በመሆኑም ሁሉም የስምምነቱ ነጥቦች መሬት ወርደው ሲተገበሩ ደግሞ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ፣ አርሶ አደሮችም ወደ እርሻቸው ፣ ሠራተኞችም ወደ ሥራቸው፣ ነጋዴዎችም ወደንግዳቸው እንዲመለሱ ሰፊ ዕድሎችን ይፈጥራል። ስለዚህም የተጀመረው የሰላም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሂደቱን መደገፍና ለውጤት ማብቃት የዜግነት ግዴታ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም