ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያከናወነች ያለችው ጥረት ፍሬያማ መሆኑን ቀጥሏል፤ በአፍሪካ ኅብረት አወያይነት ከሕወሓት ጋር የተደረሰው ስምምነትም እንደ አንድ ትልቅ የስኬት ምዕራፍ የሚታይ ሲሆን፣ አገሪቱ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የወሰደቻቸውና እየወሰደቻቸው የሚገኙ ርምጃዎች ለሰላም ያላትን ጽኑ አቋም ከቃል ባለፈ በተጨባጭ ያሳየችባቸው ናቸው።
አገሪቱ በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት ጠግኖ ሥራ በማስጀመር፣ እንደ ስልክ፣ ባንክ ያሉትን አገልግሎቶች ወደ ሥራ በማስገባት ፈጣን ምላሽ ሰጥታለች። በትራንስፖርቱ ዘርፍም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ለመጀመር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ሌሎች ተቋማትም እንዲሁ አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛሉ።
እነዚህ ተግባሮች በተከናወኑበትና እየተከናወኑ ባለቡት ወቅት ነው የአገሪቱን የሰላም ቁርጠኝነት ይበልጥ የሚያረጋገጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በመቀሌ ጉብኝት ያደረገው። ይህ የመንግሥት ውሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴ አገሪቱ በሰላም ስምምነቱ እንዲፈጸሙ የተቀመጡትን በመተግበር ያሳየችውን ቁርጠኝነት ይበልጥ አጠናክሮታል። ይህ ርምጃ ስምምነቱ ከሚጠይቃቸውም በላይ ብዙ ርቀት መጓዝ የተቻለበት ነው ማለት ይቻላል። ቡድኑ በመቀሌ ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያደረገው ፍጹም ቤተሰባዊ መቀራረብ ለጠላትም ለወዳጅም ታላቅ መልዕክት አስተላልፏል። እርምጃው ለሰላም ስምምነቱ በሚገባ መተግበር የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው እነዚህ እርምጃዎች የሰላም ስምምነቱ በጥሩ ጉዞ ላይ መሆኑን የሚያመላክቱ ከመሆናቸውም በላይ በዲፕሎማሲው መስክም ሌላ ድል እያስገኙ ናቸው። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እየተጎበኘች የምትገኝበት ሁኔታም ይህንኑ ያረጋግጣል።
የቻይና፣ የጀርመንና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ጉብኝትም ከዚሁ አኳያ የሚታይ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተወያይተዋል።
ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ባደረጉት ውይይት የአገራቱን ዘመናትን የተሻገረ ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ጥልቅና ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፤ ይህም ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ፈረንሳይና ጀርመን ጋር ያላትን ጠንካራ እና የቆየ ግንኙነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ተናግረዋል፤ ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ ስለተካሄዱ የዘርፉ ብዙ ማሻሻያዎች ገለጻ ተደርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በበኩላቸው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና የመሳሰሉትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉና ለውጡን ለማስቀጠል አገራቱ ሲያደርጉ የነበረውን እገዛ እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።
ጉብኝታቸውና ያደረጉት ውይይት የአገሪቱን ገጽታ በሚገባ ለማሳየት ያስቻለ ዕድል ተደርጎም ሊወሰድ የሚገባው ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማስገንዘብም ያስቻለም ነው። ትልቅ የዲፕሎማሲ ሥራ የተከናወነበት ነው፤ ኢትዮጵያ ከሁለቱ አገሮች ጋር ያላትን የቆየ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ በኩልም ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
በመልሶ ግንባታው ድጋፍ ለማድረግ ማረጋገጣቸው እንዲሁም ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውም ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ይታመናል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በተለይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የውጭ ጫናዎች አርፎባት እንደነበር ይታወሳል፤ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለበርካታ ጊዜያት አሉታዊ በሆነ መልኩ አጀንዳ ተደርጋለች። ተጥሎባት ከነበረ ማዕቀብ ጋር በተያያዘ እርዳታና ድጋፍ አይደለም በገንዘቧ የሚያስፈልጋትን ለመግዛትም ተቸገራ ነበር። ለግብርና ሥራዋ ወሳኝ የነበረውን ማዳበሪያ ማግኘት ተቸግራ እንደነበርም ይታወቃል።
ይሁንና ከጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ጋር ተያይዞ አሁን ነገሮች እየተቀየሩ ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጉብኝትና ውይይትም ይህንኑ ያመላክታል፤ ይህ የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ የሰላም አማራጭ ጥረትና እሱን ተከትሎ በተገኘው ውጤት ነው።
እነዚህ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አላቸው። ግንኙነቱም የመንግሥት ለመንግሥት ብቻም ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብም ጭምር ነው። በእነዚህ አገሮች በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ። በንግድ በኩልም ምንም እንኳ ወደ እነሱ ያጋደለ ቢሆንም፣ ግንኙነቱ ዘመናትን ያስቆጠረና ሰፊም ነው።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር የምታደርገው እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ የሚያስፈልጓትን የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ፣ የባለሙያና የመሳሰሉትን ድጋፎች ለማግኘት በእጅጉ ወሳኝ ናቸው።
በአጠቃላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የኢትዮጵያ ጉብኝት ዘመናትን የተሻገረውን የአገራቱ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል። ይህ መልካም ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎልበትና ወደ ቀደመው ሁኔታው እንዲመለስ ለማድረግ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም