ብቸኝነት ከኑሮ ውድነት ተዳምሮ ሆድ እያስባሳት ነው። ጠዋት ማታ ሀሳብ ትካዜ ልምዷ ሆኗል። ሁሌም ከአንድ ዓመት በፊት የነበረውን ሕይወት በትዝታ ታሰባለች። እንደዛሬው ‹‹ባዶ ነኝ›› ብላ አታውቅም ። ‹‹አይዞሽ፣ አለሁሽ›› የሚል አባወራ ጎኗ ነበር ።
የዛኔ ድካም ልፋቷ፣ ህመም ችግሯ ሳይሰማት አልፏል። ከባለቤቷ ስትኖር ህልም ውጥኗ ትርጉም ነበረው ። ስለ ትዳር፣ ኑሮዋ አሻግራ ታስባለች። አርቃ ታልማለች። ይህን በወጠነች ጊዜ ውስጧ እፎይታን ያቀብላታል። የወደፊቱን፣ የነገውን ዓለም በብርሃን ያሳያታል።
አሁን የትናንቱ ትዳርና አብሯት የኖረው አባወራ ከጎኗ የሉም። ሁሉም እንዳለፈው ክረምት ተሰናብተዋት ሄደዋል። ማህሌት ይህን ባሰበች ቁጥር ውስጧ አብዝቶ ይደነቃል። የነበረው እንዳልነበረ፣ መሆኑን እያሰበች ትተክዛለች፣ ታዝናለች። የዛሬን አያድርገውና ከባለቤቷ ጋር የወጠኑት ትዳር በአንድ ወንድ ልጅ ተባርኳል። ልጁ ሲወለድም ደስታቸው የጋራ እንደሚሆን አስባ ነበር። እሷ ባለቤቷ ልጅ ወልዶ የማሳደግ ውጥን እንዳልነበረው አሳምራ ታውቃለች። ልጁን ሲያይ ግን ውስጡ እንደሚቀየር ዕምነቷ ነበር። ማህሌት ያሰበችው አልሆነም። ባሏ ልጅ በማግኘቱ ሳይሞቀው፣ ሳይበርደው ከረመ። ቢገርማትም ቻለችው።
የዛኔ በእነሱ ቤት ‹‹አባት ደስ ይለዋል፣ ልጅ ሲወለድለት›› ይሉት ዜማ ትርጉም አልነበረውም። አባወራው በልጁ መምጣት አለመደሰቱን በተለያየ ድርጊቶች ገለጠ። አዲስ ልጅ እንዳገኘ አባት ጥርሱ አልታየም፣ ፈገግታው አልደመቀም። ጥቂት ቆይቶ የውስጡን ስሜት በገሀድ የሚያሳይበት ጊዜ ደረሰ። ‹‹እዚህ ነኝ›› ሳይል አራስ ሚስቱን ከነጨቅላ ልጇ ትቷት እብስ አለ።
እናትና ልጅ
አሁን ማህሌት የብቸኝነትን ሕይወት ጀምራለች። ብዙ ያቀደችበት ባለቤቷ ጥሏት ከሄደ ሰንብቷል። ቢከፋት፣ ቢቸግራትም የመጣውን መቻል እንዳለባት አውቃለች። ከእንግዲህ ህጻኑ ‹‹ልጄ›› የሚል አባት የለውም። እሷም ብትሆን ጎጆዋን ያለአባወራ ልትመራ ግድ ብሏታል። ከሁሉም ግን ትንሹ ልጇ ተስፋዋ ሆኗል። ጠዋት ማታ ለእሱ መኖር ትለፋለች፣ እንደ እናት ስለጤናው፣ ስለዕድገቱ ታስባለች። ባሏ ጥሏት በሄደ ማግስት ኑሮ አንገዳግዷታል፤ ቤት ኪራዩ፣ የእለት ወጪው፣ የህጻኑ ፍላጎትና ሌላም ብቻዋን የምትወጣው አልሆነም።
ማህሌት ኑሮን ለመግፋት የቀን ስራ ላይ ትውላለች። ልጇ ከፍ ሲል የሚያስፈልገው ብዙ ነው። አሁንም ቢሆን በዕድሜው የሚያሻውን ማግኘት አለበት፣ እናት ነችና ከእሷ ይልቅ ልጇን ታስቀድማለች፣ እየራባት የእጇን ለእሱ ታጎርሳለች።
አሁን የማህሌት ልጅ እያደገ ነው። ከጊዜያት በኋላ በሆዱ እየዳኸ በእግሩ መቆም ይሞክራል። እየቆመ፣ ሊራመድ ሊሮጥ ይፈጥናል። እናት ይህን ስታስብ ፊቷ ይፈካል፣ ውስጧን የተለየ ሀሴት ይሞላዋል። ልጁ ጥቂት ቆይቶ ትምህርት ቤት እንደሚገባ ታውቃለች። ቦርሳውን አዝሎ፣ ምሳ ዕቃውን ይዞ ስትሸኝ፣ ስትቀበለው ይታያታል። ይሄኔ ሁሉን ረስታ ሳቅ፣ ፈገግ ትላለች።
ኑሮ ከባድ ነው። ጎጆን ለብቻ ማቆም፣ ልጅን ያለአጋዥ ማሳደግ ይፈትናል። ማህሌት በዚህ እውነታ እያለፈች ነው። ለብቻ መኖሩን፣ ለብቻ ልጅ ማሳደጉን ከነችግሩ ይዛዋለች።
ልጁ ከፍ ማለት ሲይዝ፣ ምግብ መብላት ጀምሯል። ለህጻኑ ከእሷ የተሻለው ሁሉ ይገባዋል። የአቅሟን እየሰራች የፍላጎቱን ልትሞላ ትጥራለች። ለልጇ ካሏት ‹‹ለእኔ›› አትልም፣ አትሰስትም፣ በልቶ ጤና እንዲያድር በወጉ አድጎ ካሰበው እንዲደርስ ሁሉን ታደርጋለች።
ልጁ ስድስት ወራትን ተሻግሯል። ከዚህ ዕድሜ በኋላም ቀጣዩን ሂደት ይጀምራል። ከጥቂት ወራት አለፍ ብሎ ማህሌት የልጇን ቆሞ መሄድ ታያለች። እጁን በእጇ ይዛ፣ ወገቡን ደግፋ ‹‹ዳዴ… ዳዴ›› ትለዋለች። ህጻኑ ያልጠነከረ ወገቡን፣ ያልበረቱ እግሮቹን ያውተረትራል። እየወደቀ እየተነሳ፣ እየሳቀ፣ እያለቀሰ ይራመዳል።
እናት ማህሌት ይህ ምስል በአእምሮዋ ሲደርስ ደጋግማ ፈገግ ትላለች። ልጇ መራመድ ከጀመረላት ብዙ ሸክም ይቀላል። እንዳሻት እጁን ይዛው ትሄዳለች። በእርግጥ ከዚህ መድረስ ቀላል አይደለም። ውጣውረድ፣ ፈተና አለው። ለእሷ ግን ከያዘችው ችግር በላይ አይከብዳትም።ስለልጇ እጅ እግሯ አይሰንፍም። አቅም ጉልበቷ አይደክምም። ሁሌም ትከሻዋ ሰፊ፣ልቧ ጠንካራ ነው።
ወፌ ቆመች…
እነሆ! የህጻኑ የሩጫ፣ እርምጃ ጊዜ ደርሷል። እናት ማህሌት አሁን ያለበት ዕድሜ ልጇ የሚድህ፣ የሚቆምበት፣ የሚወድቅ የሚነሳበት ጊዜ መሆኑን አውቃለች። ህጻኑ ከታዘለበት ትከሻ ወርዶ በመሬቱ አንዲቧች፣ እንዲሳብ ትረዳዋለች፣ እንዳሰበችው እጁን በእጇ ይዛ ‹‹ ወፌ ቆመች፣ ወፌ ቆመች›› ትለዋለች። እሷን አይቶ ሲስቅ ደስ ይላታል፣ሲወድቅ ታቅፈዋለች። እያባበለች፣ እየዳሰሰች ትስመዋለች።
የወይዘሮዋ ትንሽ ልጅ ከመሬቱ ተቀምጦ ይውላል። እናት የመዳሁን ምልክት እየጠበቀች ነው። ዕቃ ይዞ እንዲቆም፣ ወድቆም እንዲነሳ የማታደርገው የለም። ልጁ የእናቱ ሀሳብ የእሱ ጭምር ሆኗል። ዕድሜውን የረሳ፣ የዘነጋ አይመስልም፣ አቻዎቹ እንደሚሆኑት ሊሆን የአቅሙን ይሞክራል፣ ይታገላል።
እናት የልጇን የመቆም ፍላጎት ታያለች። ደግማ ደጋግማ ልትረዳው፣ ልታነሳው እየሞከረች ነው። ህጻኑ የብቻው ሙከራ እየተሳካ አይደለም። ይህን ስታይ እናት ለምን? ስትል ሀሳብ ይውጣታል። በእሱ ዕድሜ ያሉትን እያስተዋለች ለጎረቤቶች ታማክራለች።
ጎረቤቶቿ ‹‹አንዳንድ ልጆች አንዳንዴ ቶሎ አይድሁም፣ አይቆሙም›› እያሉ ያስረዷታል። እነሱን እየሰማች የሌሎቹን ልጆች ታያለች ። በልጇ ዕድሜ ያሉ ሁሉ ዳዴና ‹‹ወፌ ቆመችን›› አልፈው መሮጥ ጀምረዋል። ስለህጻኑ ብታስብም ተስፋ አትቆርጥም። አሁንም ልጇን ከወለል ከሜዳው ለቃ እንዲሄድ፣ እንዲሮጥ ትናፍቃለች። ትንሹ ልጅ አንዳች ሳይሞክር ከእጇ አምልጦ ዝንጥፍጥፍ፣ ዝልፍልፍ፣ይላል ።
ማህሌት አሁን የልጇ ነገር እያሳሰባት ነው ። ብዙዎች ደጋግመው እንዳሏት የህጻኑ ችግር ቶሎ ያለመሄድ አልመስል ካላት ቆይቷል። ለመቆም ሲሞክር አቅም ያጣል፣ ይንቀጠቀጣል። ልጇ ያለአንዳች እርምጃ የአንድ ዓመት ልደቱን ማክበሩ ስጋቷን ለውሳኔ አጣድፎ ከሀኪም ቤት ደጃፍ አድርሷታል።
ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታሎች የዘለቀው ምርመራ ውጤቱ ተጠበቀ። ህጻኑን ያዩት፣ያከሙት ሁሉ መልሳቸው ተመሳሳይ ሆነ። በተነሳው ራጅ ላይ አንዳች የሚታይ ችግር እንደሌለበት ነግረዋታል። እናት ማህሌት በተሰጣት ውጤት ተስፋ አልጣለችም። አሁንም መቆምና መራመድ ለተሳነው ልጇ መፍትሄ ለማግኘት በሌላ አማራጭ ሮጠች።
ማህሌት ልጇን ይዛ ዘውዲቱ ሆስፒታል ደርሳለች። ሥራ መፍታትና እጅ ማጠር እየፈተናት ነው። ከምንም በላይ አንድዬ ልጇ ብቸኛው ጉዳይዋ ነው። ሁሌም ህመሙ ያማታል፣ ትኩሳቱ ያግላታል። በሆስፒታሉ ጥቂት ቆይታ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ተልካለች።
አሁን አንድ ችግር እንዳለ ውስጧ እየነገራት ነው። ጠዋት ማታ ልጇን አዝላ ትሄዳለች፣ ትመጣለች። ኑሮ ከብዷታል። ከአምስት ወራት ምልልስ በኋላ ውጤቱ ደርሷል ተባለች። ልቧ እየመታ፣ ውስጧ እየተጨነቀ ነው። ሀኪሞች ፊት ቀርባ የሚሏትን ጠበቀች።
የምርመራው ውጤት
በሀኪሞች እጅ የደረሰው የህጻኑ የምርመራ ውጤት በጭንቅላቱ ውስጥ የሞላ ውሃ መኖሩን ያስረዳል። አስቸኳይ ቀዶ ህክምና ያስፈልገዋል። እንዲህ ካልሆነ የልጁ ጉዳት ይጨምራል። እናት ማህሌት ከሀኪሞቹ የሰማችውን እውነት ለመቀበል ከብዷታል። ትንሹ ልጇ፣ እንዲሄድ፣ እንዲሮጥ የጓጓችለት ብቸኛ ስጦታዋ ችግር ላይ ነው። እሷ እንዳሰበችው ተነስቶ የሚቆም ሮጦ የሚሄድ አልሆነም።
የተባለውን ህክምና ለመጀመር አልጋ መያዝ ያስፈልጋል። ተኝቶ ለመታከም ወረፋ የያዙ በርካቶች ናቸው። ማህሌት ከሶስት ወር በፊት ተራ እንደማታገኝ ተነገራት። ብቸኝነቷን ያዩ ችግሯን ያስተዋሉ ልበ ደጎች ቅድሚያውን ሰጧት። በቅርብ ሆና የምትረዳት አንዲት ሴትም የሚያስፈልገውን ልታሟላ ጎና ቆመች። ልጇን ከህክምናው አድርሳ ለጭንቅላቱ ‹‹ሸንት›› የተባለው መሳሪያ እንዲገባለት ሆነ።
ደጋግሞ የገባለት የጭንቅላት ውስጥ ‹‹ሸንት›› ለህጻኑ አልተስማማም። ሙከራው ቀጠለ። ቀዶ ህክምናው ተደጋገመ። ሁለት ዓመት ያልሞላው ህጻን አስራአንድ ጊዜ ቀዶ ህክምና ተደረገለት።
ማህሌት የልጇ ህክምና ሲጠናቀቅ ቤቷ ተመለሰች። የምትኖረው በኪራይ ነው። ወጪ እንጂ ገቢ የላትም። ከጎኗ የሚያግዛት አይዞሽ ባይ የለምና ለኑሮዋ መሮጥ ያዘች። ልጇን አዝላ በየቤቱ ልብስ አጠባ ጀመረች። ያገኘችውን እየሰራች ለእሷና ለህጻኑ ፍላጎት ለመድረሰ ሁሌም አይሞላም። እጅ ያጥራታል። ኑሮ ይከብዳታል።
እንዳሻው የማይሄድ የማይራመድ ልጅ ይዞ ኑሮን መግፋት ይከብዳል። በቤት ኪራይ ሕይወት አይመችም። አንዳንዶች ልጁን ሲያዩ ቤቱን ለማከራየት አይፈቅዱም። ያከራዩ ደግሞ ‹‹ዋጋ ጨምሪ›› ላለማለት ምክንያታቸው ይበዛል። በየአጋጣሚው በልጁ ያሳብባሉ፣ ይጠየፋሉ። ማንነቱን ለመናገር አይጠነቀቁም፣ቃላት አይመርጡም።
ሲያሻቸው በግልጽ ይሰድቧታል፣ ያንቋሽሽዋታል። ምንም ብትባል ምንም አትልም። ምርጫ የላትም። ለልጇ እስትንፋስ ለእሷ መኖር ስትል ሁሉን ትችላለች። ተቀይማ ልውጣ ብትል የምታኮርፍበት የዘመድ ቤት የለም። ሁሉን ችላ ነገን ተስፋ ታደርጋለች።
አሁን ትንሹ ልጅ ዕድሜው ከፍ ብሏል። ስድስተኛ ዓመቱን ከያዘ ጀምሮ እናት ማህሌት ሌላ ጉዳይ ያሳስባት ይዟል። ልጁ በዚህ ዕድሜ እንደእኩዮቹ ትምህርት ቤት መሄድ፣ ዕውቀት መገብየት አለበት። የመናገር፣ የመስማት ችግር የለበትም። እንዳሻው መራመድ መሄድ አለመቻሉ ግን ከትምህርትና ከባልንጀራ አያውለውም።
ማህሌት እኩዮቹን እያየች ልጇን ታስባለች።ሀሳቧን ዕውን ለማድረግ የሚያራምድ አቅም ከእሷ የለም። ጠዋት ማታ የሚያብሰለስላት ጉዳይ ከሀሳብ ማለፍ አልቻለም። ልጁን ከነችግሩ ተቀብሎ የሚያስተምር አላገኘችም። ለማስተማር ደግሞ በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል። ገንዘብ፣ጤና ማጣትና የማስተማር ፍላጎት በአእምሮዋ ቦታ ይዘው አጨናነቋት።
ዛሬም ከትከሻዋ ያልወረደ ልጇን ይዛ ትምህርት ፍለጋ ተንከራተተች። ያዩዋት፣ ያገኘዋት ሁሉ ደግመው አላዋሯትም። ፊት አዞሩባት፣ በር ዘጉባት። ተስፋ አልቆረጠችም። የልጆች ድምጽ በሰማችባቸው ትምህት ቤቶች እየዞረች ‹‹እርዱኝ፣ ልጄን አስተምሩልኝ›› ብላ ተማጸነች። አንዳንዶች ጊዜ ወስደው አዳመጧት ሌሎች ደግሞ በይሆናል እግሯ እስኪቀጥን አመላለሷት።
ነገን ተስፋ አድርጋ የምትሄደው እናት ልፋት ተማጽኖዋ ፍሬ ያዘ። ከዕለታት በአንዱ ችግሯን ያዩ፣ እንክርቷን ያስተዋሉ ቅኖች በራቸውን ከፍተው አስገቧት። ለትምህርት ቤት ‹‹እንከፍላለን›› ያሉ ቃላቸውን ጠበቁ። ልጇ በእሷ ትከሻ ሆኖ የሚመላለስበት የትምህርት ዕድል ተገኘለት። የእናት ማህሌት ፊት ፈካ፣ የተራበ ሆዷ በተስፋ ጠገበ። ከእንግዲህ የእሷም ልጅ እንደእኩዮቹ ‹‹ተማሪ›› ሊባል ነው። አልዘገየችም። በትከሻዋ እንዳዘለች ከእኩዮቹ ቀላቀለቸው።
እናት ማህሌት አሁን ስለትምህርት ወጪ አታስብም። ልጇን በክፍያ የሚያስተምርላት አግኝታለች። ህጻኑ እንደሌሎች አይሮጥም፣ አይራመድምና ልዩ ድጋፍ ያሻዋል። ለዚህ ደግሞ የተዘጋጀ ባለሙያ የለም። ትምህርት ቤቱ ከእናቱ የቀረበ ሰው እንደማይኖር አምኗል። እሷም ብትሆን እስከግማሽ ቀን አብራው ልትቆይ ተስማምታለች።
እናት ልጇን ያስገባችበት ትምህርት ቤት ከመኖሪያዋ በብዙ ይርቃል። በሰዓቱ ለመድረሰ ትራንስፖርት መጠቀም አለባት። ይህን ማድረግ ያልቸለችው ማህሌት ልጇን አዝላ ረጅም መንገድ ትጓዛለች። በልፋት ድካም ያገኘችውን ትምህርት ቤት ማጣት አትሻም። ሰውነቷ ቢዝል፣ ቢንቀጠቀጥም ስለልጇ ዋጋ ትከፍላለች፣ ጠዋት ማታ አዝላው ትሮጣለች።
ባተሌዋ ሴት ልጇን አድርሳ ግማሽ ቀን ጠብቃ ለስራ ትጣደፋለች። የሚተርፋት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። አንዳች ሳይጠቅማት እንደባከነች ትውላለች። ይህን ደግሞ መተው ፈጽሞ አይቻላትም። ከልጇ ትምህርት፣ ከስራዋም እያለች የምትሮጥበት ውሎ የእስትንፋሷ ተስፋ ነው። የያዘችውን ይዛ የቤት ኪራይዋን ታሰላለች።
አንዳንዴ ከእጇ ያለው ገቢ ያስጨንቃታል። ለልጇ ምሳ የምትቋጥረው ታጣለች። ዛሬ ቢኖራት ነገ ጓዳዋ ይነጥፋል፣ ህጻኑን በርሀብ መቅጣት አትፈልግም። ራሷን ጎድታ አንጀቷን አስራ ምሳ ዕቃውን ትሞላለች።
ማህሌት ከአጠገቧ የእኔ የምትለው ዘመድ፣ ቤተሰብ የለም። እስከዛሬ ባለቤቷ የት እንዳለ አታውቅም። ርቀው ያሉት ወላጆቿ በክፉ ደግ የሚደርሱላት አይደሉም። የእሷ ተስፋ በትከሻዋ ያለው አንድ ልጇ ብቻ ነው። ወይዘሮዋ በጎጆዋ አውደ ዓመትና ደስታ ይሏቸው ትርጉም ካጡባት ቆይተዋል።
ስለህመሙ ግንዛቤ ካገኘችበት ሆፕ ኤስ ቢኤች /Hope SPH / ከተባለ ድርጅት በቀር ስለችግሯ የሚያዋይ፣ የሚያማክራት የለም። እሷም ብትሆን በወጣትነት ዕድሜዋ ሰርታ እንዳታድር እጅ እግሮቿ ተይዘዋል። የነገው ንጋት ግን ሀኪሞች ስለልጇ በሰጧት ታላቅ ተስፋ ደምቋል።
ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላ አንድ ቀን ልጇ ተነስቶ እንደሚሮጥ፣ እጇን በእጁ ይዞ እንደሚራመድ ታስባለች። መሽቶ ሲነጋ የሀኪሞቹ ቃል ዕውን እንዲሆን ትናፍቃለች። አዎ ! ትምህርት ናፋቂው ትንሽ ልጅ በእግሮቹ ላይ ተስፋ ታስሯል። ሁሌም ይህ እንደሚሆን ታምናለች። ዛሬን በዳዴ፣ ነገን በሩጫ ችግሩን ያመልጣል። ካሰበውም ግብ ይደርሳል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም