የዕለት ጉርስ ቢቸግሯቸውም በቀላሉ እጅ አልሰጡም:: ፈተና ቢፈራረቅባቸውም አሜን ብለው አልተቀበሉም:: አባታቸው በ60 ብር የጥበቃ ደመወዝ ላኑራችሁ፤ እናንተ አርፋችሁ ትምህርታችሁን ተማሩ ቢሏቸውም አዕምሯቸው አልፈቀደም::
በአንድ የስራ መስክና ቦታ ብቻ ታጥረው መቀመጥንም አልመረጡም:: ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሥራ ሳይመርጡ ሰርተዋል፤ በዚህ ሁሉ ጥረታቸውም ሮጠው የድህነት ቀንበርን ከጫንቃቸው ላይ አውልቀው ጥለዋል:: የዛሬው የስኬት አምዳችን እንግዳ – ሃጂ ቶፊቅ ከድር::
ሐጂ ቶፊቅ ከድር የተወለዱት በምዕራብ ወለጋ ‹‹ሙጊ›› በሚባል ስፍራ ነው:: ትምህርቻውንም በልጅነታቸው በዚያው አካባቢ መከታተል ጀመሩ:: አባታቸው የቡና ገበያ ይባል የነበረ ድርጅት ጥበቃ ነበሩ:: ደመወዛቸው 60 ብር ሲሆን፣ በዚህ ሁሉንም የቤተሰባቸውን አባላት ያስተዳድሩ ነበር::
ይህን የአባታቸው ልፋትና የቤተሰብ ጫና የተመለከቱት ሃጂ ቶፊቅ ከስድስተኛ ክፍል በላይ መማር አልቻሉም:: ይልቁንም በሥራ ቤተሰባቸውን እያገዙ ወደ ተሻለ የሕይወት ምዕራፍ ለመሸጋገር ጥረት ማድረግ ጀመሩ::
የትውልድ አካባቢያቸው ቡና በብዛት የሚለማበት ነው:: እሳቸው የቡና ለቀማ ሲካሄድ የሚወዳድቀውን መሰብሰቡን ተያያዙት፤ ይህንንም በሙቀጫ በመውቀጥ ‹‹ቀሽር›› የሚባለውን ለገበያ ማቅረብና ሳንቲም መቋጠር ጀመሩ:: በዚህም ቤተሰባቸውን በአቅማቸው ማገዝ ጀመሩ::
ትምህርት ቤት ደግሞ ሌላ ሥራ መፍጠር አለብኝ ብለው አሰቡ:: የወዳደቁ ጨርቃጨርቅና ወረቀቶችን ይሰበስባሉ፤ ከዚያም ኳስ ይሰሩበታል፤ ኳሱን በአስር ሳንቲም ለልጆች መሸጥ ውስጥ ገቡ:: ለቤታቸው እንጨትም እየለቀሙ ቤተሰባቸውን አግዘዋል::
ድህነት ግን ሆድ አስባሳቸው፤ ትምህርታቸውንም አቋረጡ:: አባታቸው እንደ እኔ ጥበቃ ልትሆን ነው ወይ ትምህርትን ቀጥል ብለው ቢያሳስቧቸውም እሳቸው ግን አሻፈረኝ እንዳሉ ቀሩ:: ድህነትን ለማሸነፍ የትውልድ ቀያቸውን ለቀው ወደ ጋምቤላ አመሩ፤ በዚያም ጫማ ማስዋብ ጀመሩ::
መምህሩ አጎታቸው አቶ ያሲን ከድር ትተውት ወደ መጡበት አካባቢያቸው ወደ ቤተሰባቸው መለሷቸው፤ እሳቸው ግን ቤተሰብ ዘንድ ብዙም አልቆዩም:: ለሁለተኛ ጊዜ እዚያው ወደ ጋምቤላ ሄዱ:: በጋምቤላ ‹‹ኢታንግ›› አካባቢ ሄደው ንግድን አሀዱ ብለው ጀመሩ::
በዚህ አካባቢ በርካታ ስደተኞችና ተረጂዎች ነበሩ:: እነዚህ ስደተኞችና ተረጂዎች ከሚሰጣቸው የእርዳታ ዘይት የተረፋቸውን ሲሸጡ ሐጂ ቶፊቅ ይመለከታሉ:: ይህ አጋጣሚ የዘይት ንግድ እንዲጀምሩ ገፋፋቸው:: በዚህም ቤተሰባቸው ማገዛቸውን ቀጠሉ፤ እንዲያም ሆኖ ግን የከፋውን ችግር ማቃለል አልቻሉም:: በድጋሚ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰው አንድ ብለው ቡና ተከላ ጀመሩ::
ይህ ስራቸው ጥንካሬ ሰጣቸው፤ አባታቸውም ከጥበቃ ስራቸው ጎን ለጎን ቡናውን መንከባከቡን ተያያዙት:: ቡናው ሕይወታቸው እያሻሻለው መጣ::
ሃጂ ቶፊቅ በዚህም አላበቁም፤ በሂደት ወደ ቡናው ንግድ ገቡ:: እዚህም ሌላ ፈተና ገጠማቸው:: በ1983 ዓ.ም ቡና ጭነው ሲጓዙ ኮንትሮባንድ ነው ተባለና ተወረሰባቸው:: ይሄኔ ተስፋ ቆረጡ፤ በቃ ቤት አልገባም ሲሉ ወሰኑ፤ የውትድርናውን ዓለም ተቀላቀሉ፤ ስልጠና ወስደው በተወለዱበት አካባቢ ጉሊሶ በምትባል ቦታ ተመደቡ:: የአካባቢውን ቋንቋና ባህልም ስለሚያውቁ የፕሮፓጋንዳ ስራ እንዲሰሩ፤ ከሌሎች ሰዎች ኃላፊነት ተሰጣቸው:: በዚህም ህብረተሰቡን ስለአገር፤ ሰንደቅ ዓላማ፣ ዴሞክራሲ፣ የህዝቦች አንድነትና ስለሠላም ህዝቡን በማስገንዘብ ሰሩ::
በዚህ ስራ ላይ እያሉ አባታቸው ሊጠይቋቸው ይመጣሉ:: እኔ በ60 ብር ደመወዝ እያስተዳደርኳችሁ፣ አንተም በዚህ ሥራ ተወስነህ ቤተሰባችን አይቀየርም እባክህን ትምህርትን ቀጥል ሲሉ አሳሰቧቸው:: አገርህን ለመርዳት ከፈለግህ የምልህን ስማኝ ብለው ተማፀኗቸው:: በዚህን ጊዜ ሃጂ ቶፊቅ አንድ ነገር ወሰኑ:: ከስር መሰረቱ የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር የሥራ ዘርፍ መቀየር እንዳለባቸው ወሰኑ፤ ከተቋማቸው የእረፍት ፈቃድ ወሰዱ፤ በዚያው ራሳቸውን ከውትድርናው ዓለም አገለሉ::
ወደ ተከሉት ቡናም ተመልሰው መንከባከብ ጀመሩ:: በኋላም ቡና ለቅመው ከሸጡ በኋላ እንደ ገና ንግዱን ተያያዙት:: ቡና ወደ ጠረፍ በመውሰድ የቡና ንግድ ስራውን አጧጧፉት:: ወደ አሶሳም ቡና መላክ ጀመሩ፤ እያሉ እያሉም ወደ ሱዳን ጠረፍ አመሩ:: የቡና ንግዳቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰፊው ማስኬድ ውስጥ ገቡ::
በዚህ አካባቢ በንግድ ዓለም እየሰሩ ሳሉ ነው ከባለቤታቸው ጋር የተዋወቁትና በ1990 ዓ.ም በዚያው አሶሳ አካባቢ ጋብቻ የመሰረቱት:: ኑሮ ከሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት ተሸጋገረ:: ባለቤታቸውም የንግዱን ስራ ተቀላቀሉ፤ መተጋገዙ እየሰፋ መጣ፤ ቤተሰብም እየሰፋ ልጆችም እያደጉ መጡ::
በአሶሳ ከተማም በተለምዶ አረብ ሰፈር በሚባለው አካባቢ በ6ሺ500 ብር 1ሺ251 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤት ተገዛ:: በዚህ ቦታ እየኖሩ በሂደት ባለ አንድ ፎቅ ህንጻ ገንብተው ለክልሉ የመንግስት ተቋማት ቢሮ ይሆን ዘንድ አከራዩት:: የቡና ንግድ እና ተክሉንም እያሰፉ ሥራቸው ማቀላጠፉን ተያያዙት::
ሃጂ ንግዳቸውን ከአሶሳ እና ሱዳን ጠረፍ ወደ አዲስ አበባ አስፋፉት:: በ1996 ዓ.ም መንግስት የጠረፍ ንግድ ህግ ሲያወጣ ሃጂ ቶፊቅ ከድርም ፈቃድ አውጥተው በመላ አገሪቱ እየተንቀሳቀሱ መሥራት ጀመሩ:: ፈቃድ አውጥተው የቀድሞ የቡና ንግዳቸውን በሰፊው ተያያዙት፤ የንግዱ ስራ አደገ::
የቢዝነስ ሐሳቡም ተበራከተ፤ ከአንዱ ዘርፍ ወደ ሌላው ዘርፍ ማደግና መመልከት ሆነ:: ለአውሮፓ ገበያ የማይውል ቡና ለየመን፣ ሱዳንና፣ ጅቡቲ ማቅረብ አለብን ብለው ያቀረቡት የፈቃድ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የቡና ንግዱ ተጠናክሮ ቀጠለ ብዙ ትርፋማም አደረጋቸው:: የዕይታ አድማሳቸው ሌሎች የቢዝነስ ሸሪኮችን ከመፈለግ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ መግባት በሚል ራዕይ መንቀሳቀስ ጀመሩ::
የቡና ንግዳቸው እያደገ ሲመጣ 1996 ዓ.ም ‹‹አሙና ኮንስትራክሽን›› ብለው በአሶሳ ፈቃድ አወጡ:: ለኢንቨስትመንቱም ከቀረጥ ነፃ ሁለት ተሽከርካሪዎችን አገኙ:: በክልሉም በርካታ መሠረተ ልማቶች ይገነቡ ጀመር:: በዚህም ሥራ የማግኘት ዕድላቸው እየሰፋ መጣ:: በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋርም ተወዳጁ፤ በጨረታዎች እየተወዳደሩ ግንባታውን ተያያዙት:: በዚህም የ ጂ አይ ዜድ፣ አይ አር ሲ፣ ኦክስፋም፣ ወርልድ ቪዥን የሚያወጧቸውንና ጨረታዎች እና የክልሉ መንግስት በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት በርካታ ግንባታዎችን አከናውነዋል:: የፋይናንስ አቅማቸውም በትልቁ እያደገ መጣ:: አስር ሳንቲም ይቸግራቸው የነበሩት ሐጂ ቶፊቅ ሚሊዮን ብሮችን ይቆጥሩ ጀመር:: በአገር ውስጥና በውጭ አገር ልምድ ቀሰሙ:: የቢዝነስ ሥራቸው አደገ፤ ለበርካቶችም የሥራ ሰንሰለትና ዕድል ፈጠረ::
2000 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ገቡ:: ይህን ተከትሎ ሥራቸው እየሰፋ መጣ:: ይሄኔ ከባለቤታቸው ግን አንድ ጥያቄ ቀረበላቸው:: ‹‹በዘጠኝ ዓመትህ ከቤት ወጥተህ ብዙ ገንዘብ አግኝተሃል፤ ግን በሃይማኖት ይቀረናል፤ ስለዚህ ወደ ሳኡድ አረቢያ ሃጂ እናድርግ›› አሏቸው:: ሃጂ ቶፊቅም በትዳር አጋራቸው ሃሳብ ተስማምተው ሃጅ አደረጉ::
አዲስ አበባ እንደገቡም በ37 ሚሊዮን ብር አንፎ ዓደባባይ አካባቢ ሥራ በማከናወን ጥሩ ዕድል ከፈቱ:: ይህም በአዲስ አበባ ውስጥም በቀጣይ ብዙ ሥራ ለመሥራት ትልቅ አጋጣሚ ሆነላቸው:: በንግድም በግንባታም እያደጉ ሸሪኮችም እየተበራከቱ መጡ::
ሃጂ ነጋዴና ተቋራጭ ብቻ አይደሉም፤ የአገር ሽማግሌም ናቸው:: ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አልፎ አልፎ በአገሪቱ ይከሰቱ በነበሩ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና መሰል ግጭቶች በርካታ ወጣቶች ሲታሰሩ ቆመው አልተመለከቱም:: የአገር ሽማግሌ ሆነው ማሸማገሉንና መምከሩን ተያያዙት:: ሀጂ በወጣቶቹ ጉዳይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ፊት ለፊት እስከ መነጋገር ደርሰዋል:: ከአቶ አባ ዱላ ገመዳ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማምጣት ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፤ በዚህም ብዙዎች ከእስር እንዲፈቱ አድርገዋል::
ሃጂ ቶፊቅ ‹‹አቶ በላይህ ክንዴ የሚባሉት ባለሃብት የሚሰሩት ሥራ ያስቀናኛል›› ይላሉ:: ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቢሯቸው ሄጄ ስለቢዝነስ ተመካክርን፤ ተግባባን ሲሉ ይገልጻሉ:: በዚህ ጊዜም ለደቡብ ክልል ወልቂጤን ማዕከል በማድረግ ፊቤላ ዘይትን በማከፋፈል 290 ሚሊዮን ብር ለፊቤላ አስረከብን፤ እኛም ትርፋማ ሆንን የሚሉት ሀጂ ቶፊቅ፣ በአዲስ አበባም የፊቤላን ዘይት ማከፋፈል ጀመርን ይላሉ::
ከዚህም በተጨማሪ ከዳንጎቴ በዋናነት ሲሚንቶ በመረከብ ለጂማ እና አከባቢው ሲያከፋፍሉ መቆየታቸውንም ይናገራሉ:: ሃጂ ቶፊቅ ከቡና ንግድ ወደ ኮንስትራክሽን በሂደትም ወደ ሲሚንቶ ንግድ ገቡ:: በዚህም በርካታ የሥራ ዕድል ፈጠሩ፤ የገንዘብ አቅማቸውም አደገ:: ለአገር ውስጥ በሚያስገቡት የውጭ ምንዛሪም በተደጋጋሚ ከባንኮች ተሸልመዋል፤ ምስጋናም ቀርቦላቸዋል::
ሃጂ ቶፊቅ ግን ወደ ውጭ በሚጓዙበት ወቅት በተደጋጋሚ የሚመለከቱት አንድ ነገር አለ:: ያደጉ አገራት ንግድ ላይ በማተኮር ብቻ ሳይሆን ያደጉት በኢንዱስትሪ ላይ በመስራት መሆኑን ተረድተዋል:: በዚህም አንዲት ትንሽ የአውሮፓ አገር ምርት በመላ አፍሪካ ሲሸጥ ይመለከታሉ:: በዚህም ጊዜ እርሳቸው አንድ ሐሳብ መጣላቸው:: እኔ ለአገሬ የምከፍለው ውለታ አለብኝ፤ ከንግድ አለፍ ያለ ዕይታ ያስፈልገኛል ወደሚለው ምዕራፍ ተሸጋገሩ:: የቢዝነስ አማካሪዎቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸውን ስለዚሁ ጉዳይ አማከሩ:: ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት እፈልጋለሁ ምን ትላላችሁ ብለው ሃሳባቸውን አካፈሏቸው::
በርካታ ነጋዴ ጓደኞቻቸው ኢንዱስትሪ በአጭር ጊዜ አታተርፍበትም በንግዱ መቀጠል ይበጃል አሏቸው:: አማካሪዎቻቸው ግን ኢንዱስትሪ ማለት ለመጪው ትውልድ የሚቀመጥ ሃብትና አደራ ብሎም ጉልህ ታሪክ ነው ሲሉ መከሯቸው::
በዚህን ጊዜ ሃጂ ቶፊቅ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የኢንዱስትሪ ግንባታ ጀመሩ:: በአሁኑ ወቅትም ግንባታው እየተከናወነ ሲሆን፣ በ2016 በጀት ዓመት የጥቁር አዝሙድና የምግብ ዘይት በማምረት ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት እየተጉ ናቸው::
ከባንክም ስድስት ሚሊዮን ዶላር ጠይቀው ሁለት ሚሊዮን ዶላር ተፈቅዶላቸው ሥራቸውን እየቀላጠፉ ነው:: በቀጣይ በሚፈቀድላቸው ዶላርም የተሻለ ሥራ ለመስራትና የአገራቸውን ውለታ ለመመለስ እየተጉ ነው:: በተለይም የጥቁር አዝሙድ ዘይትን ወደ ሱዳን፣ ሳውድ አረቢያ፣ ዱባይና ሌሎች አገራት በመላክ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት በማለም እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል::
ሃጂ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አልፈው ከዕለት ጉርስ ችግር ተላቀው በአሁኑ ወቅት ‹‹ቶከ›› ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል ድርጅት መስርተው ለ1000 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ኢንዱስትሪ እየገነቡ ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅትም ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል:: ለዘመናት ያለሙትን ህልም በአሁኑ ወቅት እየኖሩት ነው::
ሃጂ ቶፊቅ ወላጅ አባታቸው በከፍተኛ ህመም ተሰቃይተው ቢሞቱም፣ በርካቶችን ከችግር ለመታደግ እየሰሩ ነው:: አባታቸው ጥበቃ ሆነው ይሰሩበት የነበረውን የቡና ገበያ የተባለውን ድርጅት ውስጥ የነበረውን ማሽን በጨረታ ገዝተው በአሁኑ ወቅት ቡና እየፈለፈሉበት ለገበያ ያቀርባሉ:: አባታቸው ለጥበቃ ይጠቀሙበት የነበረውን የጦር መሳሪያ ጭምር በአሁኑ ወቅት ለድርጅታቸው በህጋዊ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው:: ምንም እንኳን አባቴ በህይወት እያለ ባላንቀባርረውም ለበርካታ የተቸገሩ አባቶች መከታ እንድሆን አድርጎ ስለቀረፀኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው ይላሉ- የአባታቸውን ውለታ ሲያስታውሱ::
ሃጂ ቶፊቅ በንግድ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ኃላፊነትም በሰፊው ይሳተፋሉ:: ለዚህም የተበረከቱላቸው የምስክር ወረቀቶች ህያው ምስክር ናቸው:: ለአብነትም በአዳማ ከተማ ወላጅ አልባ ህጻናት ያስተምራሉ:: ለአገራቸው እያስገቡ በሚገኘው የውጭ ምንዛሪም በተደጋጋሚ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል::
መንግስት ለሚያቀርብላቸው ጥያቄም ቀዳሚ ተባባሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ:: የአገር ሽማግሌ ሆነው ኃላፊነታቸው ተወጥተዋል፤ እየተወጡም ነው:: በኢንቨስትመንቱም ቢሊዮኖችን እያንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ እየተጉ ነው:: ታዲያ ሀጂ አንድ ምክር አላቸው:: ‹‹ባለሃብት ማለት ለራስ ሳይሆን ለአገር መኖር ነው:: በመሆኑም ሃብትና ፀጋ ያለን ሰዎች ለአገራችን የምንሰጠው ለራሳችን መልሰን የምንሰጠው ነውና በሃቅ ለኢትዮጵያ እንሥራ›› ይላሉ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም